ሀገሩ ሶርያ ሲሆን አባቱ ሊቀ ካህናት ነበር። በኤጲስ ቆጶስነት የተሾመባት አገር በጤግሮስና በኤፍራጥስ መካከል በምትገኝ ሥሩግ በምትባል አገር ስለሆነ ያዕቆብ ዘሥሩግ ተባለ። በ 3 ዓመቱ እናቱ ቤተ መቅደስ ስትወስደው መልአክ እጁን ይዞ በሊቀ ጳጳሱ እጅ እንዲቆርብ አድርጎታል። በዚህም ጊዜ ምሥጢራት ሁሉ ተገልጠውለታል።ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ገና በ ህጻንነቱ ሦስት ነገሮችን እንደሚፈራ ተናግሯል። “ነፍሴ ከሥጋዬ ተለይታ ስትወጣ ፡ከጌታችን ጋር ስትገናኝና መጨረሻውን ፍርድ ስሰማ እነዚህን ሦስት ነገሮች በእጅጉ እፈራለሁ” ብሏል።
በ 12 ዓመቱ ብሉይንና ሐዲስን አጠናቆ ተምሮ ጨርሷል። ጸጋውን ዐውቀው 5ቱ ታዋቂ ሊቃነ ጳጳሳት መጥተው እጅ ነስተውት አዲስ ድርሰት ድረስልን ቢሉት እርሱም በፍጹም ትሕትና “በእናንተ ፊት እንኳን አዲስ ድርሰት ልደርስ ቀርቶ የተደረሰውንም መናገር አልችልም” ብሏቸዋል።
ቅዱስ ያዕቆብ ከዚህ በኋላ ወደ ገዳም ገብቶ ትሕርምተ አበውን : ዕጸበ ገዳምን : ሕይወተ ቅዱሳንን በተግባር ተምሯል:: በድንግልናው ጸንቶ : ጾምና ጸሎትን እያዘወተረ ኑሯል:: በፈቃደ እግዚአብሔር የሥሩግ (በኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች መካከል የምትገኝ የሶርያ ግዛት ናት) ኤዺስ ቆዾስ ሆኖ ተሹሟል::
በዘመኑም:-
1.የ451ን የኬልቄዶን ጉባኤ አውግዟል::
2.ብዙ መናፍቃንን ተከራክሮ ምላሽ አሳጥቷል::
3.በወንጌል አገልግሎት መልካም እረኝነቱን አሳይቷል::
4.ዛሬ የምንገለገልበትን መጽሐፈ ቅዳሴውን ጨምሮ በርካታ መንፈሳዊ ድርሰቶችን ደርሷል::
ንጽሕናውና ቅድስናው እንደ መላእክት ነው የተባለለት ያዕቆብ ዘሥሩግ ጻድቅም ሐዋርያም ደራሲም ተከራካሪ መምህርም ነው።
በሦርያ ቋንቋ በመቶዎች የሚቆጠሩ በግጥም መልክ የተዘጋጁ ድርሳናትን ፣በመጻፍ “ዕንዝራ መንፈስ ቅዱስ “ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።በስሙ የሚታወቅ ቅዳሴም ደርሷል። በሀገራችን በቅዱሳን መላእክት በዓላትና በነገረ ምጽአት መታሰቢያ ዕለት ቅዳሴው ይቀደሳል።ስለ ነገረ ድኅነት በስፋት አስተምሯል።ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በግጥም መልክ የተዘጋጀ ድርሰት ደርሷል።
ቅዲስ ያዕቆብ ዘሥሩግ የመለኮትና ትስብእትናን ፍጹም ተዋሕዶ በማስተማሩ “የተዋሕዶ ጠበቃ “ተብሏል።የንስጥሮስንና የኬልቄዶናውንን የምንታዌ ትምህርት ይቃወማል።
ዕረፍቱም ሰኔ 7 ቀን ነው። ከአባታችን ከአቡነ ያዕቆብ ዘሥሩግ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎቱም ይማረን!።
ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን

