📖የቤተክርስቲያን ፈተና

የቤተክርስቲያን ታሪክ የሚጀምረው ከዓለመ መላእክት ነው፡፡ ታዲያ ፈተና ሁሌ አብሯት የሚኖር ቤተክርስቲያን መፈተን የጀመረችው በዚሁ በዓለመ መላእክት ነበር፡፡ ዲያብሎስ ትዕቢትንና ሐሰት ከራሱ አንቅቶ መላእክትን «እኔ ፈጠርኋችሁ» በማለት ባሰማው የሐሰት አዋጅ ከሰው ልጅ ወደዚህ ምድር መምጣት ጀምሮ በብሉይ ኪዳንም በርካታ ፈተናዎች ተፈራርቀዋል፡፡

የቤተክርስቲያንን ታሪክ ስናጠና ለቤተክርስቲያን የመፈተን ምክንያት የሚሆኑ አካላትንና ድርጊቶችን ቆጥሮና ወስኖ ማስቀመጥ ወይም መገደብ ባይቻልም ጐልተው የሚታዩትን መዘርዘር ግን ይቻላል፡፡ ከእነዚህ የፈተና ምንጮች ዋነኞቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

«የቤተክርስቲያን የውስጥ ጠላቶች በጌታ አነጋገር «ጸራዊ» በሐዋርያት አነጋገር «ቢጽ ሐሳውያን» በሊቃውንት አነጋገር «መናፍቃን» ይባላሉ፡፡ የቤተክርስቲያን ልጆች ሳይሆኑ የቤተክርስቲያን ልጆች መስለው ወይም ከቤተክርስቲያን እምነትና ትምህርት የተወሰነውን የተማሩ ፤የተወሰነውንም ተምረው ያልያዙ ጐደሎዎች ናቸው፡፡ እነርሱም እንክርዳድ ስንዴ መስሎ እንደሚያድግ በክርስቶስ ዐጸደ ወይን በቤተክርስቲያን ውስጥ የበቀሉ አሳሳቾች ናቸው፡፡

ስልታቸውን በየስፍራውና በየዘመኑ እየለዋወጡ ሐመረ ኖኅ ቤተክርስቲያንን በምንፍቅና ማዕበላቸው እያንገላቷትና እያማቷት ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ወዳልተሰበኩት ሕዝብ ደርሳ ትምህርቷን እንዳታስተምር ልዩ ልዩ የክህደት ትምህርት በመፍጠር አባቶችን ሥራ ያስፈቱ ናቸው፡፡ይልቁንም በአሁኑ ዘመን በክህደት ትምህርታቸው ብቻ ሳይቆጠቡ ቤተክርስቲያን ላይ ሁሉን አቀፍ ዘመቻ የከፈቱበት ወቅት ነው፡፡ የተቸገሩ ምእመናንን የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ እንሰጣለን በማለት፣ የቤተክርስቲያኒቱን የመንፈሳዊ ትምህርት ተቋማት እንረዳለን በማለት፣ እንዲሁም ለሆዳቸው ያደሩ ሰዎችን በመጠቀም የቤተክርስቲያን ዋነኛ የፈተና ምንጭ ሆነው ቀጥለዋል፡፡

በቤተክርስቲያን ታሪክ ከጌታ ትንሣኤ እስከ 70 ዓ.ም ድረስ ያለው ዘመን ዘመነ ሐዋርያት ከ70 ዓ.ም እስከ 160 ዓ.ም ያለው ደግሞ ዘመነ ሐዋርያነ አበው እንዲሁም ከ16ዐ ዓ.ም እስከ 312 ዓ.ም ያለው ዘመነ ሰማዕታት በመባል ይታወቃል፡፡በመጀመሪያዎቹ ሁለት ክፍላተ ዘመናት የነበረው የቤተክርስቲያን አገልግሎት ከአይሁድ ጋር የተደረገ ተጋድሎ ነው፡፡ ይኸውም ምንም እንኳን የአይሁድ ማኅበረሰብ ቃል ኪዳን የተገባለት፣ ትንቢት የተነገረለት፣ በአንድ አምላክ አማኝ ቢሆንም የክርስቶስን አዳኝነትና አምላክነት ላለመቀበል በአመጽ በመግፋቱ፣ እነርሱን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመመለስና ለማቅረብ የተደረገ ጥረት ነበር፡፡

ሦስተኛው ክፍል ግን ቅዱሳን አበው ከአላውያን ነገሥታት ጋር ባደረጉት ተጋድሎ የሚዘከር ዘመነ ሰማዕታት ነው፡፡ በክርስትና ሃይማኖት ትምህርትና በመምህራኑ አማናዊ ምሳሌነት በመላው ሮም የክርስትና ሃይማኖት ተስፋፍቶ ነበር፡፡ በመሆኑም ለባሮች የነጻነት ትምህርት የተሰበከላቸው ሲሆን ባለጸጋዎችም ቢያምኑ የክርስቶስ አገልጋዮች ለመሆን እንደሚበቁ ተነገራቸው፡፡ /1ቆሮ 7፥22/ የአሕዛብን የቀደመ ትዕቢትና ኩራት የእግዚአብሔር ቃል ሲያፈራርሰው፤ የአሕዛብን የአመንዝራነት ሕይወት የክርስቲያኖች ቅድሰና አሸነፈው፡፡ በአሕዛብ ልማድ በወንዶች መካከል ሴቶች የክብር ቦታ ያልነበራቸው ሲሆን በክርስትና እኩልነትና መከባበር ታወጀ፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ክፉዎች በክርስቲያኖች ላይ የሰውን ሥጋ ይበላሉ፤ ለቄሳር አይታዘዙም፤ ግብር አይከፍሉም፤ የሚሉ ተራና ክፉ ወሬዎችን አወሩ ፡፡ በዚህ የተነሳ እንደነ ዲዮቅልጥያኖስ ያሉ ኢአማኒያን/ከሃድያን/ ነገሥታት ስልጣናቸውን መከታ አድርገው ብዙ ክርስቲያኖች በሰማዕትነት እንዲያልፉ ያደረጉበት እኩይ ተግባር ፈጸሙ፡፡ ይህም ደጉ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ መንበረ ሥልጣኑን ይዞ ለክርስቲያኖች ሠላም እስኪያወርድላቸው ድረስ የቀጠለ ጉዳይ ነበር፡፡

ቤተክርስቲያን ለምድራዊ ኑሮ ሲባል በተለያየ ሥርዓተ መንግሥት ሥር የሚኖሩ ሰዎችን ነው በሥርዓቷና እና በትውፊቷ እንዲኖሩ የምትጥረው፤ የእርሷ ድርጊት ሁሉ ከአመራራቸው ጋር የማይሄድ የሚመስላቸው ሁሉ እንደየዘመናቸው ሁኔታ መከራን አጽንተውባቸዋል፡፡ ይህም የሁል ጊዜ የቤተክርስቲያን የፈተና ምንጭ ሆኖ የቀጠለ ጉዳይ ነው፡፡

«የክርስቶስ ፍቅር ገብቷቸው ክርስትናንና ከዚያ የሚከተሉትን ኃላፊነቶችን፣ ክህነትን እስከ ጵጵስና ድረስ «አውቃለሁ፤ እበቃለሁ» ብለው ወይም « ይገባኛል» ብለው ሹመት ፈልገውና ተካሰው ሳይሆን «እኛ አንበቃም ተውን» እያሉ፣ ነገር ግን ለመንጋው የግድ መሪ ስለሚያስፈልገው «እናንተ ለዚህ ሓላፊነት ትበቃላችሁ መንጋውን ጠብቁ» እየተባሉ አደራ ሲጣልባቸው የተሰጣቸውን ከባድ ሓላፊነት የሚጠይቀውን ዋጋ ሁሉ በመክፈል የተወጡ ብዙ ቅዱሳን አባቶች ቤተክርስቲያናችን አሏት፡፡

በሦስቱ ጉባኤያት /ኒቅያ ቁስጥንጥንያና ኤፌሶን/ ዶግማዋን አጽንታ፣ ክፉዎችን ለይታ፣ ጥርት ያለውን እምነት ይዛ፣ አንድነቷን ጠብቃ የተጓዘችው አንዲት ዓለም አቀፋዊት ኦርቶዶክሳዊ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ የሕንድ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንን የአሳዛኝ ታሪክ ምሳሌ ያደረጋት የመናፍቃን ደባ ነው፡፡ የሮም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከኦርቶዶክሳውያኑ ጐራ ተለይታ የኖረችው እዚህ ግባ በማይባል ፖለቲካዊ / ምድራዊ ሥልጣን/ ምክንያት በተጀመረ ጠብ ነው፡፡

«ሰውን ብትታገል ብትዋጋ ታሸንፈዋለህ ወይም ያሸንፍሃል ቤተክርስቲያንን ግን ለማሸነፍ አይቻልም ቤተክርስቲያን ሁል ጊዜ ትዋጋለች ተሸንፋ ግን አታውቅም ዲያብሎስ ዝናሩን አራገፈ ቀስቱን ጨረሰ፡፡ ቤተክርስቲያንን ግን አልጎዳትም» ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን በመጥቀስ የጻፉት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የቤተክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ነው / የቤ.ተ. ገጽ 48/።

ፈተና የቤተክርስቲያን የመኖሯ መገለጫ ነው፡፡ነገር ግን ቤተክርስቲያን ፈተና በሚገጥማት ወቅት በሚነሳው ማዕበል ተከፍተን ከመርከቧ ወደ ባሕር እንዳንወርድ ምን ማድረግ ይገባናል❓

ጥቂት ነጥቦችን እናነሳለን፡፡የ አበው አባቶቻችን የተጋድሎ ገድል ስናነብ የምንረዳው ምንም እንኳን ወጥ የሆነ መንፈሳዊ ሕይወት ቢኖራቸውም ከባድ ፈተና በገጠማቸው ጊዜያት ግን የበለጠ ይበረታሉ። በርካታ ቃል ኪዳናትን የተቀበሉት በርካታ መንፈሳዊ መጻሕፍትን የጻፉት የብዙ ጸጋ ባለቤት የሆኑት በፈተና ውስጥ ነው፡፡

የምንማረው ከአባቶቻችን ነውና ቤተክርስቲያን ፈተና ላይ በምትሆን ጊዜ በጋዜጣ በሚጻፈው፣ በድረገጽ በሚለቀቀው «እንዲህ ሆነ እንዲህ ተደረገ» ወሬ ተገፍቶ እርሱን ብቻ በማውራት የራስ ሕይወትን መዘንጋት አይገባም፡፡ የሚሰሙት ዜናዎች፤ የሚፈጸሙት ድርጊቶች የግል መንፈሳዊ ሕይወትን የመሸርሸር አቅማቸው በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው የቀደመ መንፈሳዊ ሕይወታችን መጠበቅ ማጽናት እግዚአብሔር አምላክ በፈተና ውስጥ ለቤተክርስቲያን በጐ የሆነውን ሁሉ እንዲያደርግ ጉዳዩን በጸሎት መያዝ መሆን አለበት፡፡

ቤተክርስቲያናችን መሠረተ እምነታዊ /ዶግማዊ/ በሆነ ችግር የተፈተነች እንደሆነ የቤተክርስቲያን ቋሚ ምስክር የሆኑ መጻሕፍትን፣ ትውፊተ አበውን፣ የቀድሞ የቤተክርስቲያን ድንጋጌዎችን መጠየቅ፣ ማንበብ በእርሱም መመራት ተገቢ ነው፡፡