ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ

ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ በጣና ሐይቅ እንደጸለየች።

በሸዋ ከፍለ ሀገር በቡልጋ አውራጃ ልዩ ስሟ ቅዱስ ጌዬ የተባለች ሀገር ነበረች ይህችም የእናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ የትውልድ ሀገሯ ናት። በዚህም ሀገር በወርቅና በብር በሐር እና በልዩ ልዩ ልብስ በወንድና በሴት አገልጋዮች በፈረስና በበቅሎ የከበረ አንድ ስሙ የታወቀ ሰው ነበር። የዚህ ሰው ስሙ ቅዱስ ደረሳኒ ሲሆን የሚስቱም ስም ቅድስት ዕሌኒ ይባላል ሁለቱም ባልና ሚስቱ እግዚአብሔር የሚፈሩ ደጋግ ሰዎች ስለነበሩ በጎ ሥራቸው በዓለም ሁሉ የታወቀ ነበር። እነዚህም ሰዎች በእግዚአብሔር ዘንድ የተመረጠችና የከበረችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራን ግንቦት 12 ቀን ወልደው በደም ግባቷና በጠባይዋ እየተደሰቱ አሳደጓት ከዚያም የእግዚአብሔርን ሕግጋትና ሥርዓቶችንም ሁሉ አስተማሯት። ባደገችና ለአቅመ ሔዋን በደረሰች ጊዜ የንጉሥ ባለሟል የሆነ ትውልዱ፤ ነገዱ ከአባ ፃሠርጓ ወገን የሆነ ለኢየሱስ ሞዓ ልጅ ለሠምረ ጊዮርጊስ በሕግ አጋቧት። እሱም በዚህ ዓለም ገንዘብ በጣም የከበረ ከመሆኑም በላይ በይበልጥ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው ነበረ። ከደም ግባቷ የተነሣ ሙሽራይቱ ማለት እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራን እጅግ አድርጎ ወደዳት። አሟቷ ኢየሱስ ሞዐም ይህች ብላቴና “በታላቅ ቁም ነገር የተመረጠች ነች” በማለት ትንቢት ይናገርላታል ስለዚህ እንደ እመቤቱ አድርጐ ያከብራት ነበር። ከዚህም በኋላም ለሕጋዊ ባሏ ለሠምረ ጊዮርጊስ ዓሥራ አንድ ልጆች ወለደችለት ከነዚህም መካከል ዘጠኙ ወንዶች ሁለቱ ሴቶች ነበሩ። ልጆችዋንም ሕገ እግዚአብሔርን እያስተማረች በክብር በሥርዓት አሳደገቻቸው።


በዚያን ዘመን የእግዚአብሔር ባለሟል የሚሆን አፄ ገብረ መስቀል የሚባል የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነበር። እርሱም ዝናዋን ሰምቶ ሥነ ምግባሯን ተመልክቶ ይልቁንም በሷ ላይ ያደረውን ኃይለ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ስለገለጸለት እጅግ አድርጐ ይወዳትና ያከብራት ነበር። ከዕለታት በአንድ ቀን በጸሎትሽ አስቢኝ በማለት በራሱ በንጉሡ ቤተ መንግሥት ከሚያገለግሉ አገልጋዮች ወይም ሠራተኞች መካከል እንዲያገለግሏት 174 አገልጋዮች ላካላት። ዳግመኛም ፈረስና በቅሎ ከነሥራታቸው እንደዚሁም ለነገሥታት ሚስቶች የሚገባ ከሐርና ከወርቅ የተሠራ ልብስና የወርቅ ጫማ ላከላት። ነገር ግን እሷ ይህን ሁሉ ክብር አልፈለገችም ይልቁንም ለዓላማዊ ዕንቅፋት ወይም ከንቱ ውዳሴ ይሆንብኛል በዚያውስ ወርቁ ጌጡ ልብሱ ተሸጦ ለነዳያን ይመጸወታል ለቤተ ክርስቲያን መባዕ ይሰጣል እኒህን አገልጋዮች ግን ምን አደርጋቸዋለሁ በማለት ወደ እግዚአብሔር እያመለከተች ቆየች።


ከአገልጋዮችዋ መካከል ምግባሯ የከፋ የምታናድዳትና የምታበሳጫት አገልጋይ ነበረች። ከዕለታት በአንድኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ በጣም ተበሳጨችና በዚያች አገልጋይ አፍ ውስጥ የእሳት ትንታግ ጨመረችባት። ያም እሳት ትንታግ በአገልጋይዋ ጉረሮ ድረስ ዘለቀና ገደላት። በዚህን ጊዜ ቤተሰቦችዋ መጥተው የአገልጋይቱን አስከሬን ወደሌላ ክፍል ወሰዱት። ብፅዕት ክርስቶስ ሠምራም ደንግጣ ካለችበት ቤት ውስጥ ወደ ሌላው ክፍል ገባችና ወደ ሰማይ አቅንታ “ወይኔ ወዮልኝ ወዮታ አለብኝ የካህን ሚስት ስሆን ነፍስ ገዳይ ሆኛለሁና። ሰውስ ምን ይለኛል ለነፍሴስ ምን እመልስላታለሁ ከእግዲህ ከክርስቲያን ወገን ልቆጠር አይገባኝም በደሌንስ እንደምን አድርጌ ልሸሸሽጋት እችላለሁ” እያለች አለቀሰች።


ከዚህ በኋላ እንዲህ ስትል ለእግዚአብሔር ብፅዓት አደረገች “አቤቱ ይህችን በእኔ እጅ የሞተችውን አገልጋይ ነፍስዋን ከሥጋዋ አዋህደህ ብታሥነሣልኝ ልጆቼን ቤቴን ንብረቴን ትቼ ባለ ዘመኔ ሁሉ አንተን እከተላለሁ። አንተን ከመከተል ከቶ ወደኋላ አልልም። ለሰውነቴ ጌጥ ወይም ግርማ ሞገስ የሚሆናት ወይም የሚሞቃት ልብስ ከቶ አልለብስም ሥጋዬን የሚያረካ ምግብም አልመገብም። አቤቱ ጌታዬ ሆይ ጸሎቴን ስማኝ ልመናዬም በፊትህ ፈጥኖ ይድረስ አቤቱ ፊትህን ከኔ ከባሪያህ አትመልስ”። እንዲህ እንዲህ እያለች በልቅሶና በሐዘን ለብዙ ሰዓት ከጸለየች በኋላ ድካም ተሰማትና ዕረፍት አደረገች። ከዚህ በኋላ ቤተሰቦችዋ እሷ ወዳለችበት ክፍል መጥተው “እመቤታችን ሆይ ሙታ የነበረችው አገልጋይሽ በእግዚአብሔር ኃይልና በአንቺ ጸሎት ተነሥታለችና ደስ ይበልሽ” አሏት። በዚህ ጊዜ ፈጥና ተነሥታ ደስ እያላት ሙታ የነበረችው አገልጋይ ካለችበት ቦታ ደረሰችና ሕይወት አገኘቻት ከዚያም ቃሏን ከፍ አድርጋ “ልመናዬን ቸል ያላለ ቸርነቱንም ከኔ ከባሪያው ያላራቀ ፈጣሪ ይክበር ይመስገን” ብላ በታላቅ ምስጋና እግዚአብሔር አመሰገነች።


ከዚህ በኋላ አስቀድሞ ከአፏ የወጣውን ከአንደበቷ የተነገረውን ቃል አስባ ልብሰ ምንኵስናዋን ማለት ቆቧን ቀሚሷን አጽፏን መታጠቂያዋን አዘጋጀች። ቤተሰቦቿና አገልጋዮቿም “እመቤታችን ሆይ ይህ የምታዘጋጂው የምናኔ ልብስ ለምንሽ ነው ወይስ ለማን ነው የምታዘጋጂው” አሏት። እርሷም “ሃይማኖት ያስተማሩኝ አባቴ ልብስ አልቆባቸዋል ሲሉ ሰምቼ ለሳቸው ነው የማዘጋጀው” አለቻቸው።

ከዚህም በኋላ ከዕለታት በአንደኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ አገልጋዮቿን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሄድ ዘንድ ተዘጋጁ አለቻቸውና እነሱም አሺ በጎ ብለው አጅበዋት ወደ ቤተክርስቲያን ሄዱ። ከዚያም እንደደረሱ “በሉ እንዲህ እኔ ከዚህ ጥቂት እቆያለሁና እናንተ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ ለኔ ይህች አንዲት አገልጋይና ይህ ሕፃን ልጅ ብቻ ይበቁኛል አለቻቸው። በዚያኑ ጊዜ አገልጋዮቿ እጅ እየነሱ ወይም እየተሰናበቱ ወደቤታቸው ተመለሱ። ከዚያም ከዳዊት መዝሙር “ልቤ ጽኑ ነው አቤቱ ልቤ ጽኑ ነው እግዚአብሔርን ፈጽሜ አመሰግነዋለሁ እግዚአብሔር የደህንነቴ መብራት ስለሆነ ምን ያስደነግጠኛል እግዚአብሔር የሕይወቴ መተማመኛ ነው ምንስ ያስፈራኛል የሚለውን እየጸለየች የሚያልፈውን ዓለም በማያልፈው ዓለም ለመተካት ወይም ለመለወጥ አውጭኝ እግሬ ብላ ገሠገሠች። ያ በልስላሴና በእንክብካቤ የኖረ እግር ከመንገዱ ብዛት እንደዚሁም ከቅርቅፍቱና ከእንቅፋቱ የተነሣ ፈለግ ሲያወጣ ሥጋውን እየቆረጠች ስትጥለው ደሙ እንደጒርፍ ውሃ ይወርድ ነበር። ያች የተከተለቻት አገልጋይ ግን ከእመቤቷ እግር እየተቆረጠ የሚወድቀውን የአካል ቊራጭ እያነሳች በልብሷ ትቋጥረው ነበር። በዚህ ዓይነት ችግርና ፀሐይ ሐሩር የብዙ ጐዳና ጉዞ ተጉዛ ከአሰበችበት አገር ደረሰች። በደብረ ሊባኖስ አቅራቢያ ወይም አካባቢ ስትደርስ የራስ ፀጒራን ይዛው በነበረ ምላጭ ላጨች ልብሷንም አውልቃ ለነዳያን አከፋፈለች የያዘችውንም ገንዘብ በመንገድ ላይ ላገኘችው ሁሉ መጽውታ ጨረሰች። ከዚያም አስቀድማ ያዘጋጀችውን ልብስ ምንኵስና ማለት ቀሚስዋን አጥልቃ አጽፋን ተጐናጽፋ ቆቧን ደፍታ ደብረ ሊባኖስ ከሴቶች ገዳም ደረሰች። የገዳሙ መነኰሳትም በታላቅ ክብር ተቀብለው ወደበዓታቸው አስገቧት።


እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ለሳጥናኤል ምሕረት እንደለመነች፦

ከዕለታት በአንድኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ጓንጉት በምትባል ደሴት ውስጥ ዓርብ ዕለት ከቀኑ በስድስት ሰዓት ላይ ስለሰው ልጆች ስትጸልይ ሣለ፡ ዓለሙ ሁሉ ከንቱ እንደሆነና የሰውም ልጅ ሕይወት እንደጥላ ኃላፊ ጠፊ መሆኑን ፈጽማ ተመለከተች። ነቢዩ ዳዊት “ሰው ከንቱ ነገርን ይመስላል ዘመኑ ወይም ሕይወቱ እንደጥላ ያልፋል” ሲል ተናግሯልና። ዳግመኛም “ሰው ክብር እንኳ ቢሆን ሊኖር አይችልም እንደሚጠፋ ወይም ማስተዋል እንደሌለው እንስሶች መሰለ… ” አለ ክቡር ዳዊት። ስለዚህም ሁሉ ነገር አቤቱ ማራቸው ይቅርም በላቸው መጻተኛዋ ባሪያህንም ኃጢአቷን አታስብባት እያለች ወደፈጣሪዋ መሪር ዕንባን አለቀሰች። ያን ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ግርማ ወደ እርስዋ መጣ። በታላቅ ግርማ ሆኖ ባየችውም ጊዜ ደነገጠች ከእግሩ ሥርም ወደቀች።

ከዚህ በኋላ ነውር በሌለባቸው ንዑዳት ክቡራንና ንጹሐን በሆኑ እጆቹ አነሣት። ቀጥሎም “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ አትደንግጭ ነገር ግን የልብሽን ሃሳብ ንገሪኝ” አላት። እርስዋም “አቤቱ ባሪያህንስ በባለሟልነት ካሠለጠንካት አባታችን አዳምን በአርአያህና በአምሣልህ ስለምን ፈጠርከው። በእንጨት መስቀልስ ላይ ለምን ተሰቀልክ ስለአዳምና ስለልጆቹ አይደለምን?” አለችው። “አዎን ስለነሱ ስል ተሰቅያለሁ” አላት። “እግዲያውስ መሰቀልህ ወይም የተሰቀልከው ስለነሱ ከሆነ ከአቤል ጀምሮ እስከ ዛሬ የሞቱን ከዛሬም በኋላ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የሚሞቱትን አቤቱ ማራቸው ይቅርም በላቸው” አለችው። “አንተ ቸር ይቅር ባይ መዓትህ የራቀ ምሕረትህ የበዛ ነህና ከአንተ ሌላ አምላክ የሌለ እውነተኛ አምላክ ነህ ሁሉ ይቻልሃልና ። የሚሣንህ ነገር ከቶ የለምና ዓለም በጠቅላላዋ በእፍኝህ አትሞላም” በማለት እያለቀሰች ለመነችው። በዚያ ጊዜ ጌታ መልሶ “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እስኪ አንቺ ራስሽ ፍረጅ አዳም ከነልጆቹ ከሠራው ኃጢአት እና እኔ በጰንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን በቀያፋና በሐና በአደባባይ በዕለተ ዓርብ ከተቀበልኩት ሕማማተ መስቀል ቢመዘን የትኛው ይመዝን ይመስልሻል?” አላት። ይህንም ባላት ጊዜ ደነገጠችና ከመሬት ላይ ወደቀች። በዚህ ጊዜ ቅዱሳት በሆኑ እጆቹ ከወደቀችበት አነሣትና “እንግዲህ ይህን ሁሉ መከራ የተቀበልኩ ለማን ወይም በማን ምክንያት ይመስልሻል” አላት።


ጌታም “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እስኪ የልብሽን ሃሳብ ወይም ፍላጐትሽን ንገሪኝ” አላት። በዚህን ጊዜ “አቤቱ ፈጣሪዬ ፈቃድህስ ቢሆን የአዳም ልጆች ከሥቃይ ከኵነኔ ይድኑ ዘንድ ዲያብሎስን ይቅር ትለው ወይም ትምረው ዘንድ እለምንሃለሁ። የኃጥእን መመለሱን እንጂ ጥፋቱን አትወድምና” አለችው። “የምለምንህ ወይም ማረው የምልህ ዲያብሎስን ወድጄው አይደለም ነገር ግን እርሱ ከተማረ በአዳም ልጆች ላይ ሥቃይና ኵነኔ ሊኖር አይችልም ብዬ በመገመት እንጂ። የነሱ ሥጋ ሥጋዬ እንደመሆኑ መጠን የኔም ሥጋ ሥጋህ ነውና” አለችው። ይህንም ባለችው ጊዜ ጌታ ፍግግ ብሎ “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ሌሎች ካንቺ በፊት የነበሩ ካንቺም በኋላ የሚነሱ የማያስቡትን እጅግ የሚያስደንቅ ልመና አቀረብሽ” አላት። ይህንም ካለ በኋላ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ጠርቶ “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ዲያብሎስን ማርልኝ ስትል ልመና አቅርባለችና እሺ ካላት ታወጣው በንድ ወደሲዖል ይዘሃት ሂድ” ብሎ አዘዘው። በዚህ ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እሺ ብሎ ሰግዶ እጅ ነሥቶ ወደሲዖል ይዟት ሄደ። አብረው በሚጓዙበትም ጊዜ “እንግዲህ ዲያብሎስ ከታረቀ ወይም ከተማረ የሰው ልጆች ሁሉ ያርፋሉ” እያለች ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ሚካኤል ታሳስበው ነበር። ይህ አምላክነትን ሲሻ ከክብሩ የተዋረደ ዲያብሎስ ምሕረት ለማግኘት ይሻ መስሏት ነበርና።


ከሲዖል አፋፍ በደረሱም ጊዜ የተመለከተችው ሥቃይ ተነግሮ የማያልቅ ነው ሰዎች ከሰዎች ጋር እንደውሻ ይናከሱ ነበር። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል “ምሕረት የሚፈልግ ከሆነ እስኪ በይ ዲያብሎስ ብለሽ ጥሪው” አላት። በዚህ ጊዜ በመላእክት ቋንቋ ሦስት ጊዜ “ሣጥናኤል ሣጥናኤል ሣጥናኤል” በማለት ጠራችው። ዲያብሎስም “ከዚህ በብዙ ሠራዊት ላይ ነግሼ ከምኖርበት አገር ማን ነው እሱ የሚጠራኝ” እያለ በታላቅ ቃል አሰምቶ ተናገረ። ከዚህም በኋላ “ለብዙ ዘመን ስፈልግሽ ወይም ሳድንሽ ቆይቼ ነበር ዛሬ ግን ከምኖርበት ቤቴ ድረስ መጣሽን” አላት። እርሷም “ጌታ ይቅርታ አድርጓልሃልና ከዚህ ከሥቃይና ከመከራ ቦታ ከወገኖችህ ጋራ ና ፈጥነህ ውጣ” አለችው። ይህንም በለችው ጊዜ ልቡ እንደ እሳት ነደደ አፈፍ ብሎ ተረማምዶ በግራ እጁዋን ይዞ ከሲዖል ረግረግ ውስጥ ወረወራት። በዚያን ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል የእሳት ሰይፍ ይዞ ከኋላ ከኋላዋ ይከተላት ነበርና ይህን ምሕረት የሌለው ዕቡይ ዲያብሎስ በያዘው ሰይፍ ቢቀጣው የሲዖል ደጃፍ ተከፈተች። በዚህ ሰዓት ታላቅ ጨኸትና ሁካታ ወይም መደበላለቅ ሆነ በሲዖል ያሉ የሰዎች ነፍሳት እንደንብ ከበቧት ወይም ሠፈሩባት። በዚያን ጊዜ በቅዱስ ሚካኤል ክንፍና በስዋም በተሰጣት ክንፈ ረድኤት ከሲዖል የወጡት ነፍሳት ቁጥር ዓሥር ሺህ ያህል ነበር። እነዚህ ከመከራ ያመለጡ ከሥቃይ የወጡ ነፍሳትን ባየች ጊዜ እጅግ አድርጋ ተደሰተች ከደስታዋም ብዛት የተነሣ የእናቱን ጡት እየጠባ እንደሚዘል እምቦሳ ጥጃ በመካከላቸው ትዘል ነበር።
ከዚህም በኋላ ወደ ፈጣሪዋ ሄዳ “አቤቱ ፍርድህ ከቶ እንደዚህ ነውን?” እያለች አደነቀች። ጌታም “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ዲያብሎስን ድል አድርገሽ ጥቂት ምርኮን አገኘሽን” አላት። እስዋም “አዎ ጌታዬ በኃይልህና በቸርነትህ አገኘሁ” አለችው። ከዚህ በኋላ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሚካኤል ጠርቶ “እነዚህን ነፍሳት ዓለም ሳይፈጠር ወደ አዘጋጀሁላት ወደ ክርስቶስ ሠምራ መኖሪያ ቦታ ውሰዳቸው” አለው። በዚህ ጊዜ “አቤቱ ፈጣሪዬ የእኔ መኖሪያዬ ወዴት ነው?” አለችው። ጌታም “መኖሪያሽ ከእናቴ ከድንግል ማርያም ጋራ ነው እነሆ በትረ ማርያም ብየ ሰየምኩሽ መቀመጫሽን ወይም ደረጃሽን ከእርስዋ ቀጥሎ ሁለተኛ አደረግሁልሽ የባለሟልነት ግርማ አጐናጸፍኩሽ አንቺን የሚወዱ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው” አላት። ይህንም ባላት ጊዜ ፈጽማ ደስ ተሰኘች ወደ ኋላዋም መለስ ብላ ብትመለከት ለዓይን የሚያንፀባርቁ ዓሥር አክሊላት አየች።

በየአንዳንዳቸው አክሊል ላይ ዐራት ከዋክብት አሉባቸው የእነዚህ ከዋክብት ቊጥራቸው ሲደመር አርባ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ከርስዋ ጋራ የነበረውን መልአክ “እነዚህ በላያቸው ብርሃናውያን ከዋክብት ያሉባቸው አክሊላት ለማን የተዘጋጁ ናቸው ሰውነቴ እጅግ አድርጋ ወዳቸዋለችና” አለችው። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም “ላንቺ ቢሆን ደስ አይልሽምን?” አላት። እርስዋም “አዎን ጌታዬ ለኔ ቢሆን እወዳለሁ” አለችው። “እንግዲያስ ላንቺ የተዘጋጁ ናቸው” አላት። “በምን ሥራዬ ለኔ ተሰጡኝ” አለችው። “ዐሠርቱ ቃላት ኦሪትን ስድስቱን ቃላተ ወንጌል ጠብቀሽ ቤትሽን ጥለሽ ይህን ዓለም ንቀሽ አጥቅተሽ የክርስቶስን ቀምበር ተሸክመሽ ፈጣሪሽን ስለተከተልሽው ነው” አላት። ይህንንም በአላት ጊዜ እጅግ አድርጋ ተደሰተች ሁሉን ማድረግ የሚችል እግዚአብሔርንም ፈጽማ አመሰገነች።

ስለ እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ዕረፍት፦

ከዚህ በኋላ በአዲስ ተጋድሎ ጀመረች። ደናግሉን ልጆቿን ሰበሰበችና “ከእግዲህ እርስ በራሳችሁ በመፈቃቀር ኑሩ እግዚአብሔርም በመፍራት ተቀመጡ” አለቻቸው። ይህንንም ከአለች በኋላ ለ1079 ደናግል ወይም መነኰሳት አስተዳዳሪ እመ ምኔት ሾመችላቸው። “ከወሰንኩላችሁ ሕግ ወይም ከሰራሁላችሁ ሥርዓት አትተላለፉ ከእግዲህ ከዛሬ በስተቀር በመንፈስ እንጂ በሥጋ አንገናኝም እና” አለቻቸው። ይህንንም ተናግራ ከእነርሱ ስትለይ አንዲት መነኵሲት ወይም መበለት ጠርታ ሹል የሆኑ ብረቶች አምጭልኝ” ብላ አዘዘቻትና አመጣችላት።


ከዚያም በእናታችን ክርስቶስ ሠምራ በቁመቷ ልክ ጉድጓድ አስቆፈረችና በውስጡ ዕፀ ከርካዕ ወይም የሎሚ እንጨት አስተከለችበት። ዳግመኛ “ከእግዲህ እግዚአብሔር ይቅር እስኪለኝ ድረስ ከዚህ አልወጣም” ብላ ከጉድጓዱ ውስጥ ገባች። ሦስት የተሳሉ ጦርች በፊቷ ሦስት ጦር በኋላዋ፣ ሦስት ጦር በቀኝ ጎኗ፣ ሦስት ጦር በግራዋ ጎን ተከለች። መበለቲቱም የፊጢኝ ወይም የኋሊት በገመድ አሰረቻት። ከዚህም በኋላ ስለ ዓለሙ ሁሉ ሕዝብ ይልቁንም ለኢትዮጵያ ሰዎች አጥብቃ ትጸልይና ታዝን ጀመር።


በዚህ አይነት ተጋድሎ ሰውነቷን ወይም ሥጋዋን በልዩ ልዩ ፀዋትወ መከራ ስትፈትን ኖረች። ፈጥና በክንፈ ረድኤት ወደ በዓቷ የምትመለስበት ጊዜ አለ። በዚህ አይነት ግብር ለብዙ ዘመን ኖረች። በምትሰግድበት ጊዜ ወደፊት ስትል ደረቷን ወደኋላ ስትል ጀርባዋን ወደቀኝ ስትል ቀን ጎኗን ወደግራ ስተል ግራ ጎኗን ጦሩ እየወጋት ከቊስሉ የተነሣ ጦሩ የወጋት ገመዱ የከረከራት መላ ሰውነቷ ሸቶ ተልቶ ለዐሥራ ሁለት ዓመት ተጋድሎ አደረገች።


እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ግን እግዚአብሔር ኃይል ጸንታለችና ከጉድጓድ ወጥታ በጣና ባሕር ውስጥ ገብታ እንድትጸልይ የእግዚአብሔር መልአክ አዘዛት ከዚያም በባሕሩ ውስጥ እየጸለየች ሦስት ዓመት ተቀመጠች።


ከሦስት ዓመት በኋላ እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ በጣና ባሕር ውስጥ ሳለች ለጌትነቱ ክብር መሰገድ የሚገባው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደእስዋ መጣ። እርሱም ጋር ቅዱሳን ሚካኤል፣ ገብርኤልና ሩፋኤል እናቱ ማርያም መጡ። ዐሥራ አምስቱ ነቢያት ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሰባ ሁለቱ አርድእት ጻድቃን ሰማዕታት ደናግልና መነኰሳት ሌሎች ሁሉም በየሥርዓታቸውና በየማዕረጋቸው በየነገዳቸው መጡ። ኄሮድስ ያስፈጃቸው ሕፃናት አለቃቸውን ሕፃኑ ቂርቆስን ተከትለው እደዚሁም ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት በየነገዳቸውና በየወገናቸው መጡ።


ከነዚህ ሁሉ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ ዳዊት መጥቶ “ልጄ ሆይ ስሚ ጆሮሽን አዘንብይ ወገንሽንና ያባትሽንም ቤት እርሺ ንጉሥ ውበትሽን ይወዳል እርሱ ጌታሽ ነውና” እያለ በገናውን ይደረድር ነበር። እንዲህም እያለ በሚዘምርበት ጊዜ በዚያ ያሉ ቅዱሳኖች በሙሉ “የእግዚአብሔር ባለሟል ወይም ወዳጅ ይህች ክርስቶስ ሠምራ በእውነት ብፅዕት ነች” እያሉ ዘመሩ።


በዚያን ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ዛሬ ከዚህ ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም ላስተላልፍሽ መጥቻለሁ” አላት። “ድካምሽ ወደዕረፍት ኃዘንሽ ወደ ደስታ ችግርሽ ወደ ብልጽግና ተለውጦልሻል። እውነት በእውነት እልሻለሁ ወይም እነግርሻለሁ በፍጹም ደስታ መታሰቢያሽን ያደረገ በመንግሥተ ሰማያት አስደስተዋለሁ። በችግሩ ወይም በጭንቁ ጊዜ በመታመን ስምሽን ቢጠራ እኔ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ አድነዋለሁ።


የገድልሽን ዜና የሚናገረውን መጽሐፍ የጻፈ ወይም ያጻፈ እኔ ስሙን በሕይወት መጽሐፍ እጽፍላቸዋለሁ። ቤተ ክርስቲያንሽን የሠራ ወይም ያሠራ ያሣነፀ ወይም ያነፀ እኔ በመንግሥተ ሰማያት ንጹሕ አዳራሽ አዘጋጅለታለሁ። በስምሽ ለተራበ ያበላ እኔ በዕለተ አርብ ከተቆረሰው ሥጋዬ አበላዋለሁ። በስምሽ ለተጠማው እፍኝ ውሃ ያጠጣ እኔ በዕለተ አርብ ከጎኔ በፈሰሰው ደሜ አረካዋለሁ። በዓልሽ በሚከበርበት ዕለት ጧፍ፣ ዕጣን፣ ወይም ዘይት ንጹሕ ስንዴ የመሰለውንም ሁሉ መባ ያገባ መሥዋዕቱን እንደ አብርሃምና እንደ መልከ ጼዴቅ መሥዋዕት አድርጌ እቀበልለታለሁ” አላት።


በዚህ ጊዜ “አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ባርያህ ባለሟልነትን በፊትህ ካገኘሁስ አንድ ጊዜ እናገር ዘንድ ፍቀድልኝ” አለችው። እርሱም “ትናገሪ ዘንድ ፈቅጄልሻለሁ” አላት። ” አቤቱ ሥጋዬ የሚቀበርበትን ወይም የሚያርፍበት ቦታ ወዴት ታዝዛለህ” አለችው። መቃብርሽ በዚች ጓንጒት በምትባል ደሴት ውስጥ ነው” አላት። “ነገር ግን ሥጋሽ በመሬት ውስጥ ይቀበራል ስላልኩሽ ኀዘን አይግባሽ በኋለኛው ዕለት እኔ አስነሣዋለሁና” አላት።


“አቤቱ እንዲህ ከሆነ መታሰቢያዬን እያደረገ ስሜን እየጠራ በስሜ በታነጸው ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ የሚቀበረውን እስከ ስንት ትውልድ ድረስ ትምርልኛለህ” አለችው። “እስከ ዐሥር ትውልድ ድረስ እምርልሻለሁ” አላት። ይህንም ቃል ኪዳን በሰጣት ጊዜ ፈጽማ ተደሰተች።
ዳግመኛም “ይህች ደሴት እንደ ደብረ ታቦርና ደብረ ዘይት ስሟ የተጠራ ይሁን” አላት። “እንደዚሁ ይህችን ሥጋሽ የምታርፍበትን ቦታ ቀደስኳት አከበርኳት። መጽሐፍ የተናገረውን አልሰማሽምን ቦታ ሰውን የሚያከብረው አይደለም ሰው ቦታን ያስከብረዋል እንጂ። ስለዚህ ነገር ስላንቺ ይቺን መካነ መቃብርሽን ቀደስኳት አከበርኳት። ስሟም ደብረ ፍቅር ደብረ ምሕረት ተብሎ ይሰየም ወይም ይጠራል። እውነት እውነት እልሻለሁ ሥጋሽ ከተቀበረበት ሄዶ መካነ መቃብርሽን የተሳለመ የእናቴን የማርያምን መካነ መቃብር እንደተሣለመ ይቆጠርልታል። እውነት እውነት እልሻለሁ አንቺን ያከበረ ሁሉ እኔ በሰማያዊ መንግሥቴ አከብረዋለሁ። አንቺን የወደደ ወይም ያፈቀረሽን እኔ አፈቅረዋለሉ።


ዳግመኛም “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ይህ የዛሬው በዓልሽ የደስታና የተድላ ቀን ነው” አላት። ይህንንም ብሎ በብዙ ወገን ወይም ሠራዊት ላይ ሾማት። “ክብርሽ ከአሮንና ከሙሴ፣ ከጴጥሮስና ከጳውሎስ፣ ሰይጣንን ድል ከአደረገው ከሕፃኑ ቂርቆስ፣ ከእንጦንስና ከመቃርስ፣ ከፀሐየ ልዳ እየተባለ ከሚጠራ ከጊዮርጊስ ጋር ክብር ጋር ትክክል ነው” አላት።


በደብረ ጽዮን ከሊቀ ዲያቆናት እስጢፋኖስ ጋር ትዘምሪ ዘንድ በክብር ተካከልሽ። በእውነት አንቺን የሚያፈቅሩ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው” አላት። ነቢዩ ዳዊት “አቤቱ እግዚአብሔርን ከሚያከብሩ ወይም ከሚፈሩ በስተቀር በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል በተቀደሰውስ ተራራ ላይ ማን ይኖራል” ብሎ ተናግሯልና። ስለዚህም አንቺን የሚያከብሩ ሁሉ አንቺን ከአለሽበት ቦታ ገብተው ከአንቺ ጋር ይደሰታሉ”።
ከዚህም አምላካዊ ቃል ጋራ በነሐሴ 24 ቀን የአባታችን ተክለ ሃይማኖት በዓል የሚከበርበት ዕለት ነፍሷ ከሥጋዋ ተለየች። በዚህ ጊዜ የነጎድጓድ ብልጭልጭታ ሆነ ነቢዩ ዳዊት “በመፍራትና በመንቀጥቀጥ ለእግዚአብሔር እልል በሉ” ብሎ እንደተናገረ የመላእክት ሠራዊትና ጻድቃን ሰማዕታትም ሁሉ እልል እያሉ አመሰገኑ። እርሷም ከነርሱ ጋር እየተደሰተች አመሰገነች። ከዚያም መላእክት ኢየሩሳሌም ሰማያዊት አድርሰዋት ወይም አሳርገዋት በአሸናፊው በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ሰገደች።


ከዚህ በኋላ ጌታ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራን እናቴ ማርያምን ወደ ምትኖርበት ውሰዳት” አለው። ቅዱስ ሚካኤልም “ጌታ ወደ አዘዘልሽ ቦታ እንሒድ” አላት። ቅዱስ ሚካኤልም ይዟት ሲሔድ እጅግ የሚያስደነግጥና ከፀሐይ ከጨረቃ ከዋክብት ብርሃን ይልቅ ብርሃኑ የሚያበራ መንበር አየች። ይህን መንበር በአየችውም ጊዜ በጣም አድርጋ ወደደችው።


የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም “ክርስቶስ ሠምራ ምን ትመለከቻለሽ” አላት። “ያን ቡሩህ የሆነ መንበር እመለከታለሁ” አለችው። “ይህ መንበር ለአንቺ ቢሆን ትወጃለሽን” አላት። “አዎን ጌታዬ ለእኔ ቢሆን እወዳለሁ” አለችው። “እንግዲያውስ ለአንቺ የተዘጋጀ ነው” አላት። በዚያ ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል “ጌታዬ መኖርያሽ እናቴ ከማርያም ጋር ነው ብሎኝ አልነበረምን”። ታዲያ እንዴት ይህ መንበር ለአንቺ የተዘጋጀ ነው ትለኛለህ” አለችው። መላአኩም “ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ለምን ቸኮልሽ” አላት። ይህን ካለ በኋላ ወደ እመቤታችን ወደ ድንግል ማርያም መኖርያ ወስዶ አደረሳትና። “ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እግዲህ ተመልከች” አላት። በተመለከተቻት ወይም ባየቻት ጊዜም ማርያም ወይም ሰው አልነበረችም ነገር ግን ከፍታዋ ወይም ቁመቷ የላቀ ተራራ ነበረች እንጂ።


ቅዱስ ሚካኤልም “ማርያም ነች ብኸኝ አልበረምን ታዲያ እንዴት ተራራ ልትሆን ቻለች” አለችው። ያን ጊዜ ምሥጢሯ እስኪገለጽልሽ ድረስ ትንሽ ታገሽ” አላት። ከዚያም ቀና ብላ ብትመለከት እመቤታችን ድንግል ማርያምን አየቻትና እንደአሞራ በራ አንገቷን አቅፋ ሳመቻት። እመቤታችንም “ክርስቶስ ሠምራ ሆይ አንቺ የተባረክሽ ነሽ አንቺንም የሚያፈቅር የገድልሽን ዜና የሚሰሙ ሁሉ የተባርኩ የተመሰገኑ ናቸው” በማለት ሳመቻት። ይህንም ከአለቻት በኋላ በቀኟ አስቀመጠቻት…።


ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ አባ ይስሐቅ የሚባል መነኵሴ ከእናታችን ከክርስቶስ ሠምራ ዘንድ ቢሄድ ሥጋዋ ብቻ ወይም አስከሬኗ በጉድጓድ ውስጥ እንደተተከለ ምሰሶ ወይም ዓምድ ቆሞ አገኘው። ነፍስዋ ከሥጋዋ ያልተለየች ወይም በሕይወት ያለች መስሎት ነበርና “እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ባርኪኝ” አላት። የሚመልስለት ቢያጣ ወደ እርስዋ ቀረበና ሥጋዋን ዳሰሰው። እንዳረፈችም ባወቀ ጊዜ ፈጽሞ ደነገጠ ከመሬት ላይ እየወደቀ እየተነሣ መራራ ልቅሶ አለቀሰ።


መነኰሳቱን ሁሉ ያለቅሱላት ዘንድ ጠራቸው። መነኰሳቱም እየተሽቀዳደሙና እየተሯሯጡ መጥተው አርፋ አገኟት። በዚህ ጊዜ “አንቺን የተሸከመች ማኅፀን የተባረከች ነች አንቺንም ያጠቡ ጡቶች የተመሰገኑ ናቸው” እያሉ ጽዕኑና መራራ ልቅሶን አለቀሱ።
ከዚህ በኋላ አባ ይስሐቅ ሥጋዋን ወይም አስከሬኗን በንጹሕ በፍታ ገንዞ በሳጥን አድርጎ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ቀበራት። መነኰስ ይስሐቅም ወደ በዓቱ መመለሱ ቀርቶ በዚያው ቤተ ክርስቲያን በስተ ምሥራቅ በኩል በቁመቱ ልክ ጎድጓድ አስቆፍሮ በውስጧ ገባ።
ከዚያም ከጎድጓዱ ውስጥ ገብቶ “ከእንግዲህ እስክሞት ድረስ እንደ እናቴ ክርስቶስ ሠምራ ከዚህ ጎድጓድ አልወጣም” በማለት ወሰነ። ይህንንም ካለ በኋላ መሪር እንባ እያለቀሰ እህል ሳይቀምስ እስከ 40 ቀን ተቀመጠ። ከ 40 ቀን በኋላ ነፍሱ ከሥጋው ተለየችና በእናታችን በክርስቶስ ሠምራ አማላጅነትና ልመና ፍጹም መንግሥተ ሰማያትን ወረሰ።


እናታችን ክርስቶስ ሠምራ በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ የኖረችው ሦስት መቶ ሰባ አምስት (375) ዓመታትን ነው። ከእናታችን ከቅድስት ክርስቶስ ሠምራ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎቷም ይማረን!።

ምንጭ፦ ገድለ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *