የአቡነ ሀብተ ማርያም ጽንሰት፦

አቡነ ሀብተ ማርያም

የኢትዮጵያ ንጉሥ እስክንድር በነገሠ በሺህ አራት መቶ ሰማንያ ስድስት ዓመተ ምሕረት ቅዱስ ፍሬ ብሩክ የሚባል አንድ ሰው በዚያች ሀገር ውስጥ ነበር፤ ይኸውም ከከበሩም ሰዎች ተለይቶ ብዙ ገንዘብ ያለው ባለ ጸጋ ነበር። በሕጋዊው ጋብቻ ስሟ ቅድስት ዮስቴና የምትባል ሴት አገባ፤ ይኽችውም ሴት በደግ ሥራ ሁሉ የተሸለመች ያጌጠች ነበረች። ብዙ ደግቷንና ትሩፋቷን ኋላ እንነግራችኋለን፤ ነገር ግን አስቀድመን በዚህ ዓለም ከሕጋዊ ባሏ ጋር በንጹሕ ጋብቻ እግዚአብሔርን በመፍራት ምጽዋትን በመስጠት የውሃትንና ትሕትናን ገንዘብ አድርጋ በትዕግሥትና በበጎ ሥነ ምግባር ሁሉ ጸንታ እንደኖረች እነግራችኋለን። እንዲህ ባለ ሥራ ሳለች መንፈሳዊ ሐሳብ እንዲህ ሲል ተነሳባት፤ “ለአንቺ በዚህ ዓለም መኖር ምን ይረባሻል ፤ ዛሬ የሚያልፍ የሚጠፋ ነውና፤ ጌትነቱ የሚመሰገንበት ለዘለዓለም የሚኖር የማያልፍ ሌላ ዓለም ይገለጣልና”፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ቢነዳ በነፍሱ ከተጎዳ ምን ይጠቅመዋል ምን ይረባዋል” እንዳለ። ለአንቺ ግን በሰማይ ጸንቶ መኖርና ሁለተኛዋን ሀገር መያዝ ይሻላል” የሚል ሐሳብ መጣባት፤ ይህን ካሰበች በኋላ ፈጥና ተነሥታ በሌሊት ከቤቷ ወጥታ፤ በሀገሯ አንጻር ትይዩ ወደ ሆነው በረሃ ሄደች፣ በውስጡ ከሰው ወገን የማይኖርበት ቦታ መካከሉ ምድረ በዳ ወደሆነው በረሃ ደረሰች። ከጅቦች፣ ከነብሮች፣ ከዓሣማዎች፣ ከጦጣዎችና ከዝንጆሮዎች በስተቀር ምንም ምን የማይኖርበት በረሃ ነበር። በዚያችም ቦታ ደጃፏ ያልተዘጋች ትንሽ ዋሻ አገኘች ምንም ምንም ሳትናገር ከዋሻው ውስጥ ገባች። በዋሻው ውስጥ ቁሞ በትጋት መዝሙረ ዳዊትን በአንክሮ በተደሞ የሚደግም ክቡር ባሕታዊን አየች፤ ባየችውም ጊዜ ደነገጠች። እርሱም ሴቲቱን ባያት ጊዜ ፍርሃት መንቀጥቀጥ በላዩ ላይ ወረደበት፣ በመስቀል ምልክትን አማተበ። ይህም ቅዱስ ባሕታዊ ፊቱን በአማተበና ስመ እግዚአብሔርንም በጠራ ጊዜ እንዳልሸሸች ስላየ ይህች ሴት ክርስቲያን መሆኗን አወቀ። መጀመሪያ ስትገባ የጋኔን ምትሐት መስላው ነበርና፤ ሰው መሆኗን ባወቀና በተረዳ ጊዜ ተቆጣት። “አንቺ ዘማዊት ሴት ምንኵስናየን ታፈርሽ ዘንድ ከየት መጣሽ” አላት። “ወይም ደግሞ ሰይጣን በልብሽ ገብቷልን?። “ጌታዬ እኔስ የሕያው እግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ነኝ እንጅ አንተ እንደምትለኝ ዘማዊት አይደለሁም” አለችው። “ነገር ግን ቤቴን ንብረቴን ያለኝን ትቼ መጥቻለሁ፣ በዓለም ውስጥ ያለውን ሁሉ ንቄ እመንን ዘንድ እወዳለሁና ስለዚህም ወደዚህ ምድር በዳ መጣሁ። በዚህም ገዳም ወይም በረሃ ሰው እንዳለ አላውቅሁም ነበር፤ ሰውን የሚባሉ አራዊት ብቻ የሚኖሩበት ይመስለኝ ነበር” አለችው።

ይህም ባሕታዊ በትሕትና በፈሪሃ እግዚአብሔር ይህን የሚያስደንቅ መልካም መልስ በመለሰችለት ጊዜ። አንድ ሰዓት ያኽል ካሰበ በኋላ “በፍቅር አንድነት ወደ ቤትሽ ተመለሽ” ብሎ በሰላም ተናገራት። እርሷም “ወደዚህ ቦታ ዳግመኛ አልመጣም እንጅ ካንተ ዘንድ ተለይቼ እሄዳለሁ። ነገር ግን ወደ ቤቴ ተመልሼ አልሄድም። ከገዳማት በአንድ ቦታ መንኵሼ መኖር እወዳለሁ እንጅ” አለችው። ጌታ “በወንጌል እርፍን በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚያርስ የለም” እንዳለ ወደ ዓለም አልመለስም” አለችው።


ያም ባሕታዊ “ምንኵስናስ የለሽም አልታዘዘልሽም፤ ነገር ግን በሰላም ወደ ቤትሽ ወደ ሕጋዊ ባልሽ ተመለሽ። የተፈቀደልሽንስ እነግርሻለሁ ከሕጋዊ ባለቤትሽ ወንድ ልጅን ትወልጃለሽ እርሱም ለዓለም ሁሉ የሚጠቅም ይሆናል። የገድሉና የትሩፋቱ ዜና እስከ ዓለም ዳርቻ ይደርሳል፤ በሕይወተ ሥጋ ሳለ በፈጣሪው በእግዚአብሔር ፈቃድ የብዙዎቹን ሰዎች ነፍሳት ከሲኦል ያወጣል። እንደ መላእክትም ክንፈ ጸጋ ተሰጥቶታል። በሰው አካል በሥጋ ሁኖ ሳለ በተመሥጦ ወደ ሰማይ ወጥቶ የሥላሴን የአንድነትን የሦስትነት ምሥጢር ያያል”።


ቅድስት ዮስቴናም ከአረጋዊ ባሕታዊ ይህን ነገር ሰምታ አደነቀች፤ “የፈጣሪዬ ፈቃድ ከሆነ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ” አለች፤ ይህን ብላ ተመልሳ ወደ አገሯ ወደ ቤቷ ገባች፤ ቤተሰቦቿም መውጣቷንም መግባቷንም ምንም አላወቁባትም፤ ከዚያም በነሐሴ 26 ቀን ጸነሰች። ከዘጠኝ ወራትም ከቆየች በኋላ፤ መልኩ እንደ በረዶ ነጭ እንደ ጽጌ ረዳም ብሩህ ቀይ የሆነ መልከ መልካም ልጅ ወለደች ሁለንተናውም ጨረቃ የጉለቱ ምልዓት 15 ሌሊት ሆኖ በብሩህ ብርሃን በምልዓት በሚያድርበት ጊዜ እንደሚያበራው መልካም ብርሃን ገጹ ብሩህ የሆነ ልጅ ወለደች፤ ይህ ሕፃን በግንቦት ወር በ 26 በተወለደ ጊዜ በአባቱና በእናቱ ቤት ታላቅ ደስታን ሆነ፤ ዘመዶቻቸውን ጎረቤቶቻቸውን አማቾቻቸውን ምርዓቶቻቸውን ጠርተው ለበዓሉ እንደሚገባ መብሉንና መጠጡን ሰጥተው በሚገባ አጠገቡዋቸው፤ …ካህኑም ተቀብሎ አጠመቀው ከአጠመቀውም በኋላ ለነፍሱ ዋስ (ለክርስትና አባቱ) አሳልፎ ሰጠው ስሙንም ሀብተ ማርያም ብሎ ሰየመው።

ከአባታችን ከአቡነ ሀብተ ማርያም እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!።

ምንጭ፦ ገድለ አቡነ ሀብተ ማርያም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *