
እንኳን ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ለአንዱ ለወንጌላዊ ለቅዱስ ማቴዎስ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓል በሰላም አደረሰን።
“ሰአሉ ለነ አርባዕቱ ወንጌላውያን መምህራን ሥዩማን አዕማዲሃ ለቤተ ክርስቲያን ሰአሉ ለነ አስተምሕሩ ለነ”። ትርጉም፦ የቤተ ክርስቲያን ምሶሶዎች የምትኾኑ ሹማምንት መምህራን የምትኾኑ አራቱ ወንጌላውያን ለምኑልን ማልዱልን። ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በሰዓታቱ ላይ።
ሐዋርያው ወንጌላዊ ቅዱስ ማቴዎስ፦ ይህም እንዲህ ነው በብዙ አገሮች ውስጥ አስተምሮ ብዙዎች ሰዎችን እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ ከመለሰ በኋላ ክብር ይግባውና ጌታችን ወደ ካህናት አገር እንዲሔድ አዘዘው። ተጒዞም ወደ ከተማው መግቢያ ደጅ በደረሰ ጊዜ አንድ ወጣት ብላቴና አገኘ ወደ ከተማው ለመግባት እንዴት እንደሚችል ጠየቀው ወጣቱ ብላቴናም እንዲህ ብሎ መለሰለት “አንተ ግን ራስህንና ጽሕምህን ካልተላጨህ በእጅህም ዘንባባ ካልያዝክ መግባት አትችልም”። ይህም ነገር ለሐዋርያ ማቴዎስ አስጨንቆት ሲያዝን አስቀድሞ ያነጋገረው ያ ወጣት ብላቴና ዳግመኛ በስሙ ጠራው። ሐዋርያውም “ወዴት ታውቀኛለህ” አለው እርሱም “እኔ ጌታህ ኢየሱስ ነኝ አሁንም እንደ ነገርኩህ አድርግ እኔም ከአንተ ጋር አለሁ ከአንተም አልርቅም” አለው።
ከዚህም በኋላ ጌታችን እንዳዘዘው አድርጎ ወደ ካህናት አገር ገባ ለአማልክት ካህናት አለቃቸው ከሆነ ከአርሚስ ጋር ተገናኘ ከእርሱም ጋር ስለ አማልክቶቻቸው ተነጋገረና ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ጣዖቶቻቸውን አቃጠላቸው እንዲህም አላቸው። “ራሳቸውን ማዳን ያልቻሉ ሌላውን እንዴት ያድናሉ” በዚያንም ጊዜ ከአርሚስ ጋር ብዙዎች ሰዎች አምነው አጠመቃቸው ከሰማይም ማዕድ አውርዶ መገባቸው።
የሀገሩም ንጉሥ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ ከአርሚስ ጋር ሐዋርያውን ወደ እሳት ጨመረው ጌታችንም አዳናቸው።
ከዚህም በኋላ በሚያሠቃያቸው ነገር ሲያስብ እነሆ ልጁ እንደ ሞተ ነገሩት እጅግም አዘነ። ሐዋርያ ማቴዎስም “ልጅህን እንዲያስነሡት ወደ አማልክትህ ለምን አትለምንም” አለው ንጉሡም “የሞተ ማንሣት እንዴት አማልክት ይችላሉ” ብሎ መለሰ። ቅዱስ ማቴዎስም “ብታምንስ የእኛ አምላክ ልጅህን ማሥነሣት ይችላል” አለው። ንጉሡም “ልጄ ከተነሣ እኔ አምናለሁ” አለ በዚያን ጊዜ ሐዋርያው ክብር ይገባውና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸለየና የንጉሡን ልጅ ከሞት አስነሣው። ንጉሡም ክብር ይግባውና በጌታችን አመነ የአገር ሰዎች ሁሉም አመኑ የቀናች ሃይማኖትንም አስተምሮ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው ካህናትንም ሾመላቸው ከዚህም በኋላ ወደ ሌሎች አገሮች ሒዶ ወንጌልን አስተማረ።
ከዚህም አስቀድሞ በደመና ተነጥቆ ብሔረ ብፁዓን ገብቷል ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስን ሁል ጊዜ በየበዓላቸው ወደ እነርሱ ሲመጣ አየው ከእርሱም ጋር መቶ አርባ ሽህ ሕፃናት አሉ መላእክትም ሁሉ በዙሪያው ቁመው ያመሰግኑታል። በብሔረ ብፁዓን ስለ ሚኖሩ ወገኖችም ድንቅ ስለሆነ ሥራቸው ሁሉ ከሐዋርያው በኋላ ወደርሳቸው የገባ ዘሲማስ ቀሲስ ምስክር ሆነ።
ከዚህም በኋላ የሐዋርያው የተጋድሎውና የምስክርነቱ ፍጻሜ ሲቀርብ ወደ አንዲት ከተማ ገብቶ አስተማረ ብዙዎችንም አሳመነ አገረ ገዢውም ይዞ ከወህኒ ቤት ጨመረው። በዚያም አንድ እጅግ የሚያዝን እሥረኛ አይቶ ስለኀዘኑ ጠየቀው እርሱም ብዙ የሆነ የጌታው ገንዘብ ከባሕር እንደ ሠጠመበት ነገረው ሐዋርያ ማቴዎስም “ወደ ዕገሌ ባሕር ዳርቻ ሒድ ወርቅን የተመላ ከረጢትንም ታገኛለህ ያንንም ወርቅ ወስደህ ለጌታህ ስጥ” አለው።
ስለዚህም ድንቅ ተአምር ብዙዎች ክብር ይግባወና በጌታችን አመኑ። መኰንኑም በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ ቅዱስ ማቴዎስንም ራሱን እንዲቆርጡ ሥጋውንም ለሰማይ ወፎች እንዲጥሉ አዘዘ። ከከተማውም አውጥተው ቈረጡት ምእመናንም በሥውር መጥተው ወስደው በመልካም ቦታ አኖሩት።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያው በቅዱስ ማቴዎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፦ የጥቅምት 12 ስንክሳር።

