እንጦጦ መንበረ ንግሥት ቁስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያን

የእንጦጦ መንበረ ንግሥት ቁስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያን አተካከል ጥንተ ታሪክ እንደሚያስረዳው፤ ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ከእንጦጦ ቤተ መንግስታቸው ወደ ፍልውሃ እና ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሲንቀሳቀሱ የመንበረ ንግሥት ቊስቋም ቤተክርስቲያን በታነፀችበት ስፍራ ድንኳናቸውን ተክለው ዕረፍት ያደረጉበት ነበር። ከዕለታት በአንድ ቀን ዕረፍት አድርገው ሳለ እንቅልፍ ያሸልባቸውና በህልማቸው አንዲት እጅግ የተዋበች ሴት ልጅ አዝላ በእቴጌ ጣይቱ አምሳል “ይህንን ቦታ ልቀቁልኝ ቤቴን ልስራበት ” ስትላቸው ያያሉ። ንጉሡም ከእንቅልፋቸው ደንግጠው በመነሳት የሆነውን ሁሉ ለባለቤታቸው ለእቴጌ ጣይቱ ብጡል ይነግሯቸዋል። በመቀጠልም በእቴጌ ጣይቱ አምሳል ስለታየቻቸው “በስምሽ ሆስፒታል ትሰሪበት ዘንድ ፈቅጄልሻለሁ” ብለው ቦታውን ለባለቤታቸው ለእቴጌ ጣይቱ ይሰጧቸዋል።

ከጊዜ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ ስለታመሙ እቴጌ ጣይቱ ባለቤታቸውን ማስታመም ይጀምራሉ፡፡ የእንጀራ ልጃቸውም ወ/ሮ ዘውዲቱ አብረዋቸው ያስታመሙ ስለነበር እቴጌ ንጉሡ ያዩትን ራዕይ እና ሀኪም ቤት መስራት አለመቻላቸውን ጭምር በትካዜ ይነግሯቸዋል። ከጥቂት ዓመታት በኃላ ንጉሡም በሞት ጎዳና ይሸኛሉ። እቴጌም እንጦጦ ተቀምጠው ያለፈውን አዱኛ እያስታወሱና አዲስ አበባን እየተመለከቱ “ነበር እንዲህ ቅርብ ነው ወይ” አሉ ይባላል። ብዙ ዓመትም ሳይቆዩ እሳቸውም ባላቸውን ተከትለው አረፉ። ልጅ ኢያሱ መሪነቱን ይዘው በነበሩበት ጊዜ፤ ራስ ተፈሪ አልጋወራሽ ሲሆኑ፤ ዘውዲቱ ንግሥተ ነገሥታት ተብለው ነገሡ።

ዘውዲቱ ንግሥተ ነገሥታት ተብለው በትረ መንግሥትነቱን ከተረከቡ በኃላ፤ እቴጌ ጣይቱ የነገሯቸውን አስታውሰው፤ ሃሳባቸውን ለመፈጸም በመነሳት፤ ዛሬ መንበረ ንግሥት ቊስቋም ማርያም ከተተከለችበት ቦታ ላይ ሆስፒታል ይገነቡ ዘንድ ዝግጅቱ ይጠናቀቅና የመሰረት ቁፋሮ ይጀመራል። በቁፋሮ ወቅት አስደናቂ ነገር ይከሰታል፤ ይኸውም “ታቦት ቊስቋም ” የሚል ጽሑፍ ያለበት የንግሥት ዕሌኒ የመዳብ ወንበር እና የብረት መስቀል ይገኛል። ንግሥት እሌኒ ማለት የአጼ ዘርዓ ያዕቆብ እኅት ሲሆኑ በ፲፬ኛው (14ኛው) መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ንግሥናቸውም በ፲፱፻፳፮ እንደነበር የኢትዮጵያ የታሪክ መጻሕፍት ያስረዳል። ፬፻፺፪ (492) ዓመት እድሜ ያለው ንብረት በመሬት ተቀብሮ በጥበበ እግዚአብሔር ተጠብቆ ምንም ሳይበላሽ ይኖር ነበር ማለት ነው ። በዚህም ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ተደንቀው ንዋየ ቅድሳቱን ፣መስቀል እና ሌሎችም የተገኙትን በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም እንዲቀመጥ ያደርጋሉ።

በቁፋሮ ጊዜ በተገኘ ንዋየ ቅድሳት ምክንያት ሥራው ወደተቋረጠው የሆስፒታል ቦታ በመሄድ ቤተክርስቲያን ይሰራ ዘንድ ህዳር ፮ ቀን ፲፱፻፲፰ ዓ.ም (ህዳር 6 ቀን 1918 ዓ.ም) የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ። መቃኞውም አስቸኳይ ይሰራ ዘንድ ለራስ ደስታ ዳምጠው ትእዛዝ ተሰጠ። በበጎ ስራቸው እና ካህናትን በመውደዳቸው ምክንያት ዘመነ ካህናት ተብሎ በሚጠራበት ጊዜ፤ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒሊክ ዘመነ ንግሥና፤ በግብጻዊው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቴዎስ ፍጻሜ ዘመን፤ በሰሜን አዲስ አበባ ልዩ ስሙ እንጦጦ በተባለ ስፍራ፤ በራስጌ ርእሰ አድባራት እንጦጦ መንበረ ጸሐይ ቅድስት ማርያምና ደብረ ኀይል ቅዱስ ራጉኤል ወኤልያስ፤ በግርጌ ሀመረ ኖኅ ኪዳነ ምህረት እና ቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔዓለም ቤተክርስቲያንን አዋሳኝ አድርጋ፤ በመኀል ባለ ልዩ ጉብታ (መሶብ) በምትመስል፤ በግማሽ አዲስ አበባን ሊያሳይ በሚችል ቦታ ላይ፤ መቅደስና ቅኔ ማኅሌት ያለው መቃኞ ቤተክርስቲያን ሰርተው በትዕዛዙ መሰረት አሰርተው ታቦተ ቊስቋም ማርያምንና ታቦተ ኢየሱስ ሌሎችንም ንዋየ ቅድሳት በእጨጌ ተድላና በዐቃቤ ሰዓት መምሬ አበበ ትዕዛዝ፤ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እና ታላላቅ ሹማምንት ምዕመናን በተገኙበት፤ በግብጻዊው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቴዎስ ባራኪነት፤ ታቦቷ ህዳር ፮ ቀን ፲፱፻፲፱ ዓ.ም (ህዳር 6 ቀን 1919 ዓ.ም) ገባች። ንግሥቲቱም ፲፭ (15) ጋሻ መሬት ከአርሲ አገር ለአገልጋዮች ካህናት መተዳደሪያ ሰጥተዋል።

ስያሜዋንም መንበረ ንግሥት ቊስቋም ማርያም ብለዋታል። መኳንንቱም የተለያየ ስጦታ አበርክተውላታል። በዚህ ወቅት ታቦቷን ይዘው የመጡ በመቃኞዋ ጊዜ አስተዳዳሪ የነበሩት መምሬ ብስራት ሃብተማርያም ናቸው። መምሬ ብስራት ሃብተማርያም እኚህ ታላቅ አባት የመንበረ ንግሥት ቊስቋም ማርያም ቤተክርስቲያን ከመመረቋ አስቀድሞ፤ በስዕል ቤት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ያገለግሉ ነበር። ንግሥተ ንግሥታት ዘውዲቱም የቊስቋም ማርያም ቤተክርስቲያንን በ፲፱፻፲፱ ዓ.ም አሰርተው በመጠናቀቅ ላይ ስለነበር ታቦቷ ወደ መቃኞ ቤተ ክርስቲያን የምትገባበት ዕለት ህዳር ፮ ቀን ፲፱፻፲፱ ዓ.ም እንዲሆን በመወሰኑ ለአገልግሎት የሚያስፈልጉ በእጨጌ ተድላ እና በአቃቤ ሰዓት አበበ አማካኝነት አገልጋይ ካህናት ሲመርጡ መምሬ ብስራት ሃብተማርያም አስተዳዳሪነቱን ግብዝናውን ተሹመው ታቦተ ቊስቋም ከበዓታ ለማርያም ገዳም ይዘው እንዲሄዱ ታዘዙ። ፲፱፻፲፱ ዓ.ም ኅዳር ፮ ቀን ጀምሮ አዲሱ ቤተክርስቲያን በቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ተሰርቶ እስከ ተመረቀበት ግንቦት ፳፬ ቀን ፲፱፻፳፭ ዓ.ም ለሰባት ዓመታት ያኽል ግብዝናን ከእልቅና በመያዝ ቤተክርስቲያኒቱን ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል። በኋላም የደብሩን አስተዳዳሪነት ለአለቃ መርሻ ያስረከቡ ሲሆን የውስጥ ግብዝናን ይዘው ቆይተው በህመም ምክንያት ለመምሬ ዘውዴ ሰረጸ ድንግል አስረክበው ታህሣሥ ፴ ቀን ፲፱፶፭ ዓ.ም በ፹፬ ዓመታቸው አርፈዋል፡፡

 

ቤተ ክርስቲያኗ ስትመሠረት የነበሩት የመጀመሪያዎቹ አገልጋዮች አባ ወልደ ሰማያት፣ መምሬ መንግሥቱ፣ ዲያቆን ጥሩወርቅ ያብዛ፣ ዲያቆን ደግፌ፣ ዲያቆን ተስፋ፣ ደብተራ ሙሉነህ አየለ፣ ደብተራ ግዛው ተክለጊዮርጊስ፣ ደብተራ በላይነህ፣ አለቃ አልታዬ ወልደዮሐንስ፣ አለቃ ኃይለጊዮርጊስ ጀማነህ፣ መሪጌታ ተክለ ሃይማኖት በላይነህ፣ እና መምሬ አስፋው ወልደ ኢየሱስ ነበሩ። በዚህ ሁኔታ የተተከለችው መንበረ ንግሥት ቊስቋም ማርያም ስብሐተ እግዚአብሔር በሰፊው እየተከናወነ እና መንፈሳዊ አገልግሎት ተጠናክሮ በመቀጠሉና በታቦቷ ሰሚነት ብዙ ሰዎች ከከተማ እየመጡ ይፈወሱባታል። በ፲፱፻፳ ዓ.ም ግንባታው የተፈጸመው የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ቤትም ከቊስቋም ማርያም ጋር ተቀራራቢ ስለነበር የበዓታው መምህር ሊቀ ሊቃውንት የሚል ማዕረግ ሲሰጠው የቊስቋም ካህናትና ንዋየ ቅድሳት ባለ አደራም ስለነበር የቊስቋም ካህናት ጉዳይ በእርሱ ባልደረባነት ለመንግስት እንዲያቀርብ ንግሥቲቱ ፈቅደዋል። ከቤተክርስቲያን ወረድ ብሎ ባለው መሬት ላይም የቊስቋም መንፈሳዊ ት/ቤት በሚል መሰረት ጥለው መስከረም ፳፩ ቀን ፲፱፻፳ ዓ.ም ተመርቋል።

ይህ መቃኞ ቤተ መቅደስ ወደ ሕንጻ ቤተክርስቲያን እንደ ደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል እና የካ ደብረ ሳህል ቅዱስ ሚካኤል ይሰራ ዘንድ ንግሥቲቱ ትዕዛዝ ሰጥተው ሳለ ባደረባቸው ህመም ምክኒያት ሳይሰራ መጋቢት ፳፬ ቀን ፲፱፻፳፪ ዓ.ም አርፈዋል። ስለ ውለታቸው ቤተክርስቲያንም ዘወትር በጸሎት ታስባቸዋለች ስራቸውንም ለትውልድ ስትዘክር ትኖራለች። ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን፤ ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ተብለው መንግሥቱን ሲረከቡ፤ በራስ ደስታ ዳምጠው አማካይነት አሁን ያለውን ቤተክርስቲያን በንጉሠ ነገሥት አጼ ኃ/ሥላሴ ዘመን ተሰርቶ ግንቦት ፳፬ ቀን ፲፱፻፳፭ ዓ.ም የበዓተ ግብጽ ዕለት ታቦተ ሕጉ ከመቃኞ ወደ ህንጻ ቤተ ክርስቲያኑ፤ ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ በተገኙበት በመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ጳጳስ ተባርኮ ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል። ብጹዕነታቸውም የተለያዩ አልባሳትን አበርክተዋል ።