
ወንጌላዊው ቅዱስ_ሉቃስ፦ ይህም ቅዱስ የከበረ ወንጌል ከመዘገባቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ የተቆጠረ ነው። እርሱም ወንጌልን ስለማስተማር በሥራው ሀሉ ሐዋርያት ጴጥሮስንና ጳውሎስን የሚያገለግላቸው ሆነ ለታኦፊላም ወንጌልንና የሐዋርያትን ዜና የጻፈ ሉቃስ ነው።
ቅዱሳን ጴጥሮስና ጳውሎስም ከተገደሉ በኋላ በሮሜ ሀገር የሚያስተምር ሆነ በቀናች ሃይማኖትም ይጸኑ ዘንድ ለምእመናን መልእክትን ይጽፍ ነበር። ስለዚህም ጣዖት አምላኪዎች ከአይሁድ ጋር በመስማማት አንድ ግምባር ፈጠሩ። በንጉሥ ኔሮን ፊት ቁመው ስለ ሐዋርያው ሉቃስ እንዲህ ብለው ጮኹ “ይህ ሉቃስ ብዙዎች ሰዎችን በሥራው ወደ ትምህርቱ አስገባቸው”። ንጉሥ ኔሮንም ወደ ፍርድ አደባባይ ሉቃስን እንዲይቀርቡት አዘዘ።
ሐዋርያ ቅዱስ ሉቃስም ከዚህ ዓለም መውጫው እንደ ደረሰ በመንፈስ ቅዱስ አውቆ ወደ ባሕር ዳርቻ ሔደ። በዚያም ዓሣ የሚያጠምድ አንድ ሽማግሌ ሰው አገኘ። መጻሕፍቱንና ደብዳቤዎቹን ሰጠው “ወደ እግዚአብሔር መንገድ መርተው ያደርሱሃልና” እነዚህን መጻሕፍት ጠብቃቸው አለው።
በንጉሥ ኔሮንም ፊት ቀርቦ በቆመ ጊዜ ንጉሡ “በሥራህ ሕዝቡን የምታስት እስከመቼ ነው” አለው ቅዱስ ሉቃስም ” እኔ ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያው ነኝ እንጂ ሥራየኛ አይደለሁም” ብሎ መለሰለት።
ንጉሥ ኔሮንም ሁለተኛ እንዲህ አለው “እየጻፈች ሰዎችን የምታስት ይቺን እጅህን እኔ እቆርጣታለሁ” ይህንንም ብሎ የቀኝ እጁን እንዲቆርጡ አዘዘ በቆረጡትም ጊዜ “ንጉሥ ሆይ እኛ የዚህን ዓለም ሞት እንደማንፈራ እወቅ ነገር ግን የጌታዬንና የፈጣሪዬን ኃይሉን ታውቅ ዘንድ አሳይሃለሁ”። ይህንንም ብሎ የተቆረጠች የቀኝ እጁን በግራ እጁ አንሥቶ ከተቆረጠችበት ቦታዋ ላይ አገናኝቶ እንደ ቀድሞዋ ደኅነኛ አደረጋት። ከዚህም በኋላ ለያት በዚያም የነበሩ አደነቁ የሠራዊት አለቃውና ሚስቱ ብዙዎችም ሰዎች ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ቁጥራቸውም አራት መቶ ሰባ ሰባት ነፍስ ሆነ ንጉሡም ከቅዱስ ሉቃስ ጋር ራሶቻቸውን እንዲቆርጡ አዘዘና ቆረጡአቸው የምስክርነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።
ከዚህም በኋላ የቅዱስ ሉቃስን ሥጋ በማቅ አይበት አድርገው ወደ ባሕር ጣሉት በእግዚአብሔርም ፈቃድ ወደ አንድ ደሴት ደረሰ። ምእመናንም አግኝተው ወስደው ገነዙት በአማረ ቦታም አኖሩት።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያ ቅዱስ ሉቃስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፦ የጥቅምት 22 ስንክሳር
የዕለቱ የማኅሌት ምስባክ፦ “ይኩን ሰላም በኃይልከ። ወትፍሥሕት ውስተ ማኅደረ ክበዲከ። በእንተ አኀውየ ወቢጽየ። መዝ 121፥7-8። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 10፥1-።
የዕለቱ የቅዳሴ ምስባክ፦ “አልቦ ነገር ወአልቦ ነቢብ ዘኢተሰምዐ ቃሎሙ። ውስተ ኵሉ ምድር ወፅአ ነገሮሙ። ወእስከ አፅናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ”። መዝ 18፥3-4።
የሚነበቡት መልዕክታት የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥1-5። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቈላ 4፥12-ፍ.ም፣ 1ኛ ዮሐ 1፥4-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 1፥1-6። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥1-5። የሚቀደሰውም የቅዱሳን ሐዋርያት ቅዳሴ ነው።
መልካም የወንጌላዊው የቅዱስ ሉቃስ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።

