ትሑትና ትዕግስተኛው አባት፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር


አባ ዮሐንስ ሐፂር፦ የዚህ ቅዱስ ወላጆቹ ከላይኛው ግብጽ ናቸው እነርሱም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ናቸው ግን ከእርሱ በቀር ልጅ የላቸውም የዚህ ዓለምም ብልጽግና ቢሆን የላቸውም ነገር ግን በበጎ ሥራ ባለጸጎች ናቸው። ይህንንም ቅዱስ እያስተማሩ በበጎ አስተዳደግ አሳደጉት።


የዚህም ቅዱስ ዕድሜው ዐሥራ ስምንት ዓመት ሲሆነው የእግዚአብሔር ቸርነት አነሣሥታው የመላእክት የሆነ አስኬማን ይለብስ ዘንድ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ ይኸውም የምንኵስና ልብስ ነው። ከዚያም በደረሰ ጊዜ አባ ባይሞይ የሚባለውን አንዱን አረጋዊ አባት ተገናኘው ዮሐንስም ሰገደለትና ወደ እርሱ እንዲቀበለው ለመነው ሽማግሌውም አባት “ልጄ ሆይ ያንተ በዚህ መኖር ልክ አይደለም በዚች ገዳም የሚኖሩ በእጆቻቸው ይሠራሉ በቀንና በሌሊት ይጾማሉ ይጸልያሉ በሚተኙም ጊዜ ያለ ምንጣፍ በምድር ላይ ይተኛሉ አንተ ወጣት ጎልማሳ ስለሆንክ ይህን ሁሉ ችግር አትችልም። ነገር ግን ወደ ዓለም ተመልሰህ እንደ ሰው ሁሉ በጎ አኗኗርን ትኖር ዘንድ ይሻልሃል የዚች ገዳም ኑሮ ጭንቅ ነውና” አለው።
አባ ዮሐንስም እንዲህ አለው እኔ በጥላህ ሥር ልኖር መጥቼአለሁና ስለ እግዚአብሔር ብለህ ተቀበለኝ እንጂ አትመልሰኝ ይህም አባ ባይሞይ እግዚአብሔርን ሳይጠይቅ ምንም ሥራ አይሠራምና በዚያን ጊዜ ሥራውን ይገልጥለት ዘንድ ስለ ዮሐንስ ሐፂር እግዚአብሔርን ለመነው የእግዚአብሔርም መልአክ ተገልጦለት “እርሱ የተመረጠ መሳሪያ ይሆናልና ተቀበለው ብሎሃል” አለው።


ከዚህም በኋላ ዮሐንስ ሐፂርን ወስዶ ወደ ቤተ ክርስቲያን አስገባው የምንኵስና ልብሶችንም አምጥቶ በላያቸው ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ጸለየ ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጾ በመስቀል ምልክት በልብሶቹ ላይ አማተበ ሽማግሌውም እነዚያን ልብሶች ለአባ ዮሐንስ አለበሰው።


ከዚያችም ቀን ጀምሮ አባ ዮሐንስ ተጋድሎንና አገልግሎትን ጀመረ አባ ባይሞይም ሊፈትነው ወደደ በአንዲትም ቀን ደብድቦ “ከአንተ ጋር መኖር አልሻም” ብሎ ከበዓቱ አስወጥቶ አባረረው የከበረ አባ ዮሐንስም ከሜዳ መካከል በውጭ ቆመ በየቀኑም በጥዋት እየወጣ “ከእዚህ ላይህ አልሻም” እያለ ይመታዋል እርሱ ግን “አባቴ ሆይ ይቅር በለኝ” ብሎ ከእግሩ በታች ይሰግዳል። በሰባተኛዪቱም ቀን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊሔድ ሽማግሌው አባ ባይሞይ ወጣ አባ ዮሐንስንም ሰባት መላእክት ከበው አክሊላትን ሲያቀዳጁት አያቸው ከዚያንም ጊዜ ወዲህ መፈተኑን ተወው ወደ መኖሪያውም አስገባው።


ከዚህም በኋላ በአንዲት ቀን አባ ባይሞይ የደረቀ ዕንጨት አግኝቶ ወስዶ ለአባ ዮሐንስ ሰጠውና “ይህን ዕንጨት ትከለው እስከሚበቅልና እስከሚያፈራ ድረስ ውኃን አጠጣው” አለው። አባ ዮሐንስም ለአባቱ ታዛዥ በመሆን ተቀብሎ ወስዶ ተከለው በየቀኑም ሁለት ሁለት ጊዜ ያጠጣዋል ውኃውም ዐሥራ ሁለት ምዕራፍ ያህል የራቀ ነው። ከሦስት ዓመትም በኋላ ያ ዕንጨት አቈጥቊጦ በቀለ ታላቅም ዛፍ ሁኖ አብቦ ጣፋጭ ፍሬን አፈራ። አባ ባይሞይም ከፍሬው ለቅዱሳን አረጋውያን ወሰደላቸውና “የታዛዡንና የትሑቱን ፍሬ እነሆ ብሉ” አላቸው እነርሱም ይህን ድንቅ ተአምር አይተው አደነቁ ለመምህሮቻቸው ለሚታዘዙ እንዲህ ያለ ጸጋ የሚሰጥ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።


አባ ባይሞይም ዐሥራ ሁለት ዓመት ያህል በጽኑዕ ደዌ ውስጥ ተይዞ ኖረ አባ ዮሐንስም ያገለግለው ነበር አባ ዮሐንስን እንደፈተነው የተመረጠ መሥዋዕትን ይሆን ዘንድ በዚህ ደዌ እንዲፈተን እግዚአብሔር ፈቅዷልና። በሚሞትበትም ጊዜ አባ ባይሞይ ቅዱሳን አረጋውያን መነኰሳትን ሰበሰባቸውና አባ ዮሐንስንም እጁን ይዞ “እርሱ ሰው ያይደለ መልአክ ነውና ተቀብላችሁ ጠብቁት” ብሎ ሰጣቸው። እርሱንም ደግሞ እንዲህ አለው “ከዕረፍቴ በኋላ ያን ዕንጨት ወደ ተከልክበት ቦታ ሂድና በዚያ ኑር እግዚአብሔር ላንተ ያዘጋጀልህ ነውና ብዙዎችም በአንተ እጅ ይድናሉ መታሰቢያህም በዚያ ጸንቶ ይኖራል ዜናህም በዓለም ሁሉ ይወጣል” ይህንንም ተናግሮ ዐረፈ አክብረውም ቀበሩት።


ከዚህም በኋላ ቅዱስ አባ ዮሐንስ አረጋዊ አባቱ አባ ባይሞይ እንደነገረው ወደዚያ ቦታ ሔዶ ኖረ ዜናውም በዓለም ሁሉ እጅግ እስከ ተሰማ ድረስ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ። በራሱ ቤተ ክርስቲያንም አበ ምኔት ሁኖ ተሾመ በሹመቱም ጊዜ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ እጆቹን በራሱ ላይ ሲጭን “አክዮስ አክዮስ አክዮስ” የሚል ቃል ከሰማይ ተሰማ ይህም “ይገባዋል ይገባዋል ይገባዋል” ማለት ነው። የቊርባን ቅዳሴን በሚቀድስ ጊዜ ቅዱስ ቊርባንን መቀበል የማይገባቸውን ይለያቸዋል “ዛሬስ ሔዳችሁ ንስሓ ግቡ ከዚያም በኋላ ተመልሳችሁ ሥጋውን ደሙን ተቀበሉ” ይላቸዋል።


ይህን አባ ዮሐንስንም ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ የቅዱሳን የሠለስቱ ደቂቅን ሥጋቸውን እንዲያመጣለት ወደ ባቢሎን ልኮታል ይህም በግንቦት ወር በዐሥረኛው ቀን ተጽፎአል።


በአንዲትም ዕለት አንድ መነኰስ ሊጎበኘው ወደ በዓቱ ቢመጣ አባ ዮሐንስን ተኝቶ አገኘው የእግዚአብሔርም መላእክት በላዩ ይጋፉ ክንፎቻቸውንም ያርገበግቡ ነበር አንዱም ሌላውን “ተወኝ ክንፌን በላዩ ላኑር ይለዋል” ይህንንም አይቶ እግዚአብሔርን አመሰገነው ።
ከዚህም በኋላ የመነኰሳቱን መንደር ሊበረብሩ የበርበር አረማውያን ወደ አስቄጥስ ገዳም በመጡ ጊዜ አባ ዮሐንስም ወደ አባ እንጦንስ ገዳም ወደ ቁልዝም ሔደ በዚያም በአባ እንጦንስ ገዳም በጎኑ ባለ ቦታ ተቀመጠ እስከ ሚያርፍባትም ቀን ድረስ የሚያገለግለው አንድ የታመነ ሰውን እግዚአብሔር አመጣለት።


ከዚህም በኋላ ከዚህ ዓለም ድካም ሊያሳርፈው በወደደ ጊዜ እግዚአብሔር ቅዱሳን ጻድቃኖቹን አባ እንጦንስን፣ አባ መቃርስን፣ አባ ጳኵሚስን ከእርሳቸውም ጋር መንፈሳዊ አባቱ አባ ባይሞይን ያረጋጉትና ከዚህ ከኃላፊው ዓለም መለየቱን ይነግሩት ዘንድ ወደርሱ ላካቸው። እነርሱም እንዲህ ብለው አረጋጉት “ደስ ይበልህ እግዚአብሔር የማያልቅ ተድላ ደስታን አዘጋጅቶልሃልና” ክብር ይግባውና ጌታችንም እንዳዘዘ “በእሑድ ቀን ሁለተኛ ወዳንተ መጥተን ወደ ዘላለም ሕይወት እንወስድሀለን” አሉት። ባርከውትም ከእርሱ ዘንድ ተመለሱ።


በዐርብ ቀንም አገልጋዩን ወደ አንድ ቦታ ላከው ከዚህም በኋላ ጥቂት ታመመ በእሑድም ቀን ሌሊት ዶሮ ሲጮህ እነዚያ ቅዱሳን ከሁሉም ቅዱሳን ማኅበር ጋር መጡ የመላእክትም ሠራዊት ሁሉ ወደርሱ መጡ ባያቸውም ጊዜ ደስ ብሎት በእግዚአብሔር እጅ ነፍሱን ሰጠ መላእክትም እያመሰገኑና እየዘመሩ በታላቅ ክብር ነፍሱን አሳረጓት በዚያንም ጊዜ ረድኡ መጣ ነፍሱንም ከበው እያመሰገኑ ሲያሳርጓት የጻድቃንና የመላእክትን ማኅበር አይቶ እያደነቀ አንድ ሰዓት ያህል ቆመ። ከመላእክትም አንዱ ወደርሱ መጥቶ የቅዱሳንን ስማቸውን በመጥራት በጣቱ እያመለከተ ይህ አባ ዕገሌ ነው ብሎ አስረዳው ረድኡም መልአኩን እንዲህ ብሎ ጠየቀው “ይህ በፊታቸው ያለ ፊቱ እንደ ፀሐይ የሚበራ ማን?” ነው መልአኩም “የመነኰሳቱ ሁሉ አባት አባ እንጦንስ ነው” ብሎ መለሰለት።


ወደ በዓቱም ያ ረድእ በገባ ጊዜ በምድር ላይ ሰግዶ እንዳረፈ አባ ዮሐንስን አገኘውና ታላቅ ልቅሶን በላዩ አለቀሰ ከዚያም በኋላ ወደ መነኰሳቱ መንደር ፈጥኖ በመሔድ ቅዱስ አባ ዮሐንስ ሐፂር እንደ ዐረፈ ነገራቸው። እነዚያም መነኰሳት አክብረው ገንዘው ሥጋውን ተሸክመው ወስደው በቦታቸው አኖሩት። የደረቀ ዕንጨት ተክሎ በአበቀለበት ላይ በሠራት የራሱ በሆነች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ልጆቹ ከዚህ አፍልሰው ወስደው እስከ አኖሩት ድረስ በዚያ ኖረ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ዮሐንስት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


“ሰላም ለዮሐንስ ሐጺር ትሩፈ ምግባር፤ ዘአጥረየ ትሕትና ወወረሰ ልዕልና”። ትርጉም፦ ትሕትናን ገንዘብ አድርጎ ልዕልናን የወረሰ መልካም ሥራው የበዛ ለኾነ ለዮሐንስ ሐጺር ሰላምታ ይገባል።

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ።