ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ

እስጢፋኖስ ማለት “መደብ” ማለት ሲሆን በግሪክ ቋንቋ “አክሊል” ማለት ነው፡፡ በግብሩ የቀን ሃሩር የሌሊት ቁር የማይለውጠው፣ መብራት ማለት ነው፡፡ ትውልዱ ከነገደ ብንያም ሲሆን አባቱ ስምዖን እናቱ ሐና ይባላሉ፡፡ እነርሱም እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ከነቢያትና ከጻድቃን ወገን ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ሁለት ወንድ ልጆችን ወለዱ፡፡ አንዱ ይሁዳ ሲባል ሁለተኛውም ቅዱስ እስጢፋኖስ (አስተፓኖስ) ነው፡፡


ቅዱስ እስጢፋኖስ የተወለደው ጥር 1 ቀን በእስራኤል ሃገር ውስጥ ልዩ ስሟ ሐኖስ በተባለች ቦታ ነው፡፡ የተወለደውም በስዕለት ነው፡፡ እርሱም ከመጥምቁ ዮሐንስ እግር ሥር በመሆን ተምሯል፡፡ በኋላም ወደ ቅዱሳን ሐዋርያት በመሄድ ይላላካቸውና ያገለግላቸው ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ከተሾሙት ከ7ቱ ዲያቆናት አንዱ ሲሆን የዲያቆናት አለቃ እርሱ ነው፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ወንጌልን በማስተማሩና ብዙዎችን ክርስቶስን ወደማመን ስለመለሳቸው ክፉዎች አይሁድ በጠላትነት ተነስተውበት ጥር 1 ቀን በ34 ዓ.ም ከጌታችን ቀጥሎ ከምእመናን ወገን የመከራውን ገፈት ስለተቀበለ (በድንጋይ ተወግሮ በሰማዕትነት ስላረፈ) “ቀዳሜ ሰማዕት” ተሰኘ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ “ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ” እየተባለ ይጠራል፡፡ ይኸውም የከበሩ ቅዱሳን ሐዋርያት በሰባቱ ዲያቆናት ላይ አለቃ አድርገው በሾሙት ጊዜ የተሰጠው ስያሜ ነው።


የመጀመሪያ ክርስቲያኖች የአማኞች ቊጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በሄደ ጊዜ የማኅበራዊው ኑሮ አስተዳደር ማለትም የምግብንና የመሳሰሉትን ቁሳቁሶች (ገንዘብም ጭምሮ) በትክክልና በእኩልነት የማከፋፈሉ ሥራ በሐዋርያት ዘንድ አስቸጋሪ ሆኖ ተገኘ፡፡ እነርሱም ደግሞ ዋና ተግባር አድርገው በትጋት ለመያዝ የፈለጉት ማስተማርን ነበር፡፡ ስለዚህም አማኞችን ሁሉ ሰብስበው ከመካከላቸው በመልካም ጠባያቸው የተመሰገኑ በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ ሰባት ሰዎችን እንዲመርጡ አሳስቧቸው፡፡ አማኞችንም ነገሩ አስደስቷቸው ሰባት ሰዎችን መረጡ፡፡ እነርሱም፡- ቅዱስ እስጢፋኖስ (ዕረፍቱ ጥር 1)፣ ቅዱስ ጵሮኮሮስ (ሰኔ 8)፣ ቅዱስ ጢሞና (ሚያዝያ 16)፣ ቅዱስ ፊልጶስ (ጥቅምት 14)፣ ቅዱስ ጰርሜና (መስከረም 1)፣ ቅዱስ ኒቃሮና (3 ጊዜ ሞቶ የተነሣ)፣ ቅዱስ ኒቆላዎስ (ሚያዝያ 15) ናቸው፡፡ ሐዋ 6፡5፡፡


እነዚህንም ቅዱሳን በከበሩ ሐዋርያት ፊት ባቆሟቸው ጊዜ ጸልየው እጃቸውን በራሳቸው ላይ ጭነው ሾሟቸው፡፡ በከበሩ ሐዋርያት ጫንቃ ላይ ተጭኖ የነበረው ከባድ ሸክም ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶችና ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ደሀ አደጎች በመርዳት ችግሮቻቸውን አቃለሉላቸው፡፡በከበሩ ሐዋርያት ከተመረጡት ሰባቱ ዲያቆናት መካከል ሊቀ ዲያቆናት ተደረጎ የተመረጠው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲሆን ሌሎቹም ዲያቆናት እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ወንጌልን በማስተማርና የመጀመሪያ ክርስቲያኖች በማስተዳደር በጽናት ተጋድለዋል፡፡ እነዚህም ሰባቱ ዲያቆናት ከአባቶቻቸው ከከበሩ ሐዋርያት አይተው የእነርሱንም መንፈስ ተቀብለው ያልተማሩ አህዛብን ልቡናቸውን ለመስበርና የእግዚአብሔርን ኃይልነት ተረድተው እንዲገነዘቡ በማሰብ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ያደርጉ ነበር፡፡

ከእነርሱም ውስጥ በዋነኛነት ቅዱስ እስጢፋኖስ በአህዛብ ፊት ያደረጋቸው ተአምራት እጅግ ድንቅ ናቸው፡፡

ቅዱስ እስጢፋኖስ በአህዛብ መካከል ቆሞ ሲያስተምር ከቆየ በኋላ አንድ አንደበቱ ዲዳ የሆነ ሰው አጠገቡ ቢመጣ በጆሮው የሕይወት እስትንፋስ እፍ ቢልበት መስማት የማይችለው መስማት ቻለ፡፡ በዚህም ጣኦት አምላኪው ናኦስ እና ተከታዮቹ ሁሉ ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ተመለሱ፡፡ ጣኦት አምላኪው ናኦስ በድርጊቱ በጣም ከመናደዱ የተነሣ በአጠገቡ የቆመውን በሬ ጠንቋዩ ናኦስ በጆሮው እፍ ብሎ ቢተነፍስበት በሬው በምትሃት ለሁለት ተሰንጥቆ በመሞቱ ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ የተመለሱት በናኦስ ምትሃታዊ ድርጊት በመሳባቸው እንደገና ወደ ናኦስ ተመለሱ፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስም በዚህ ጊዜ የአህዛብ ልቡና ወላዋይ እንዳይሆንና እንዳይጠፉም በማሰብ ናኦስ እፍ ብሎ ለሁለት ሰንጥቆ የገደለውን በሬ መልሶ በሕይወት እንዲያስነሣው ናኦስን ጠየቀው፡፡ ነገር ግን ናኦስ ያንን ማድረግ አልቻለም፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱስ እስጢፋኖስ “ናኦስ ዳግመኛ ሕይወት ዘርቶ ማስነሣት ካልቻለ ነገሩ ሐሰተኛ ነው ማለት ነው፣ እኔ ግን በእግዚአብሔር ኃይልና ድንቅ ሥራ ይህን ለሁለት ተሰንጥቆ የሞተውን በሬ ዳግመኛ ሕይወት ዘርቶ እንዲነሣ አደርገዋለሁ” በማለት ወደ እግዚአብሔር ከጸለየ በኋላ በሬውን አስነሣው፡፡ ይህንንም ተአምር አድርጎ በማስተማር ልቦናቸው ወላውሎ ወደ ናኦስ የተመለሱትን አህዛብ ገንዘቡ እንዲሆኑ በእግዚአብሔር ኃይልነት እንዲያምኑ አድርጓል፡፡

ናኦስ በአልሸነፍ ባይነትና በአጋንንት ረዳትነት ራሱን ወደ ላይ እንዲንሣፈፍ አድርጎ በአየር ላይ ቢወጣ ቅዱስ እስጢፋኖስ የእግዚአብሔርን ተአምር በማሳየት በትዕግስት ጠብቆ በአጋንንት ረዳትነት ወደ ላይ የተነሳውን ናኦስ በትእምርተ መስቀል ቢያማትብበት ይዘውት የነበሩት አጋንንት ሁሉ ለቀውት ሲበተኑ ናኦስም ምድር ደርሶ ተንኮታኩቶ በመውደቁ በጣኦት አምላኪነት የነበሩ ሁሉ ዳግም ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ተመልሰዋል፡፡


የሰማዕታት መጀመሪያ የሆነው ቅዱስ እስጢፋኖስ በትምህርቱና በተአምራቱ ብዙዎችን ወደቀናች ሃይማኖት ስለመለሰ ክፉዎች አይሁድ ቀኑበትና የሐሰት ምስክር አዘጋጁበት፡፡ “በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ የስድብን ቃል ሲናገር ሰምተነዋል” ብለው በሐሰት ከሰሱትና በሸንጎአቸው አቆሙት፡፡ ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስም ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ጌታችን ያለውን ሁሉንም እየጠቀሰ የሃይማኖትን ነገር አስተማራቸው፡፡ ነቢያትን ስለማሳደዳቸውና ስለመግደላቸው እየወቀሰ ሲናገራቸው በትምህርቱ ተናደው ጆሮአቸውን ይዘው በመጮህ በድንጋይ ወግረው ይገድሉት ዘንድ እየጎተቱ ከከተማው ውጭ አወጡት፡፡


ቅዱሱም በድንጋይ ወግረው ሲገድሉት ከጌታችን የተማረውን “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” እያለ ስለ ገዳዮቹ ምሕረትን ይለምን ነበር፡፡ ሰማይም ተከፍቶ የእግዚአብሔርን ክብር ተመለከተ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይኸውም የቀድሞው ሳውል ቅዱስ እስጢፋኖስን በድንጋይ ሲወግሩት የገዳዮቹን ልብስ ይጠብቅና ድንጋይ ያቀብል ነበር፡፡ “የሰማዕትህንም የእስጢፋኖስን ደም ባፈሰሱ ጊዜ፥ ራሴ ደግሞ በአጠገባቸው ስቆም ተስማምቼ የገዳዮችን ልብስ እጠብቅ ነበር አልሁ” ብሎ ራሱ ቅዱስ ጳውሎስ መስክሯል፡፡ ሐዋ 22፥20፡፡


የቅዱስ እስጢፋኖስ መምህር የነበረው ምሑረ ኦሪቱ ገማልያልና ልጁ አቢብ በእስጢፋኖስ ትምህርትና የሞቱ ሰዎች የሰጡትን ምስክርነት አይተው ከይሁዲነት ተመልሰው በክርስቶስ አምነው ተጠምቀዋል፡፡ ስለ ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲህ ተብሎ ነው የተጻፈው፡- “እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር፡፡ የነፃ አውጪዎች ከተባለችው ምኵራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያም ሰዎች ከኪልቅያና ከእስያም ከነበሩት አንዳንዶቹ ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር፤ ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም፡፡ በዚያን ጊዜ በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሡ፡፡ ቀርበውም ያዙት ወደ ሸንጎም አመጡትና “ይህ ሰው በዚህ በተቀደሰው ስፍራ በሕግም ላይ የስድብን ነገር ለመናገር አይተውም፤ ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ ያፈርሰዋል ሙሴም ያስተላለፈልንን ሥርዓት ይለውጣል ሲል ሰምተነዋልና” የሚሉ የሐሰት ምስክሮችን አቆሙ፡፡ በሸንጎም የተቀመጡት ሁሉ ትኵር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት”፡፡ የሐዋ ሥራ 6፥8-15፡፡

የአይሁድ በቅዱስ እስጢፋኖስ ላይ ያቀረቡት የክሳቸው ምክንያት ጌታችንን ከከሰሱት ክስ ጋር በሁለት ነጥቦች ይመሳሰላል፡፡ የመጀመሪያው ክሳቸው “የሙሴን ሕግ ሽሯል” የሚል ነው፡፡ “የሙሴን ሕግ በመሻር ኦሪት አትጠቅምም አትመግብም አታድንም፤ ሐዲስ ኪዳን (ወንጌል) ግን ትመግባለች ታድናለች” ብሏል ብለው ከሰሱት፡፡ የሐዋ ሥራ 6፥13፡፡ ሁለተኛው ክሳቸው “እግዚአብሔርንም ይሰድባል” የሚል ነው፡፡ የሐዋ ሥራ 7፥50፡፡ አይሁድም የቅዱስ እስጢፋኖስን የወንጌል ቃል ንግግሮች በእግዚአብሔር ላይ እንደተሰነዘሩ ስድቦች በመቁጠር ነበር የወነጀሉት፡፡ የኦሪት የካህናት አለቃውም ቅዱስ እስጢፋኖስ ለተከሰሰበት መልስ ይሰጥ ዘንድ ሲጠይቀው እርሱ ግን ለተከሰሰበት መልስ ከመስጠት ይልቅ ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ በዝርዝር በሚገባ ተረከላቸው።
ቅዱስ እስጢፋኖስም እንዲህ አላቸው፡- “ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ገደላችሁትም፡፡ ይህንም በሰሙ ጊዜ በልባቸው በጣም ተቈጡ ጥርሳቸውንም አፏጩበት፡፡መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፡፡ እነሆ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ፡፡ በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፈኑ፣ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ ሮጡ፤ ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት፡፡ ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ፡፡ እስጢፋኖስም “ጌታ ኢየሱስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል” ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር፡፡ ተንበርክኮም “ጌታ ሆይ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፡፡ ይህንም ብሎ አንቀላፋ፡፡ ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር፡፡ የሐዋ ሥራ 7፥52-60፡፡


ቅዱስ እስጢፋኖስ ስለንጽሕናው ስለድንግልናው፣ ስለሰማዕትነቱ ስለተጋድሎው እና ስለስብከቱ ስለተአምራቱ ሦስቱ አክሊላት ተቀዳጅቷል፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ አምላኩን ክርስቶስን በብዙ ነገር መስሏል፡፡ በመጨረሻዋ የመሞቻው ሰዓት ላይ እንኳን ሆኖ አምላኩን አብነት አድርጎ ተገኝቷል፡፡ ጌታችን “ነፍሴን ተቀበላት” እንዳለ ሁሉ ቅዱስ እስጢፋኖስም “አቤቱ ጌታ ሆይ ነፍሴን ተቀበላት” ብሏል፡፡ ጌታችን “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” እንዳለ እስጢፋኖስም “ጌታ ሆይ ይህን ኃጥአት አትቁጠርባቸው የሚያደርጉትን አያውቁምና” በማለት ለገዳዩቹ ምሕረትን ለምኗል፡፡ በጌታችን ጸሎት እነ ፊያታዊ ዘየማንን ጨምሮ እልፍ ነፍሳት ወደ ንስሐ ተመልሰው ገነት መንግስተ ሰማያትን እንደወረሱ ሁሉ በቅዱስ እስጢፋኖስም ጸሎት ብዙ ነፍሳት ድነው ገነት መንግስተ ሰማያትን ወርሰዋል፡፡
የጌታችን ቅዱስ መስቀል እልፍ ሙታንን ያስነሣ ድውያንን ይፈውስ እንደነበር ሁሉ የቅዱስ እስጢፋኖስም ዐፅም ሙታንን ያስነሣ ድውያንን ይፈውስ ነበር፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ የተወገረበት ድንጋይ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ታንጸውበታል፡፡

የቅዱስ እስጢፋኖስ ልደቱና ዕረፍቱ ጥር 1 ቀን ነው፡፡ ምእመናንም ሥጋውን ወስደው በክብር ቀበሩት፡፡ ጥቅምት 17 የተሾመበት ነው፡፡ መስከረም 15 ቀን ፍልሰተ ሥጋው ነው፡፡ የቅዱስ እስጢፋኖስ ቅዱስ ዐፅሙ ሙትን ያስነሣ ድውይን ይፈውስ ነበርና አይሁድ በቅናት ተነሥተው እንደ ጌታችን ቅዱስ መስቀል የቅዱስ እስጢፋኖስን ዐፅም አርቀው በመቆፈር ቀብረው በላዩም ቆሻሻ በመጣል ለ300 ዓመታት ያህል ተቀብሮ ኖሮ በመጨረሻ በፈቃደ እግዚአብሔር እንደ ቅዱስ መስቀሉ ተቆፍሮ በመውጣት መስከረም 15 ቀን ቅዱስ ዐፅሙ ወጥቶ በክብር በስሙ በታነጸው ቤተ ክርስቲያን በክብር ተቀምጧል፡፡

ከቅዱስ እስጢፋኖስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤት በረከቱ ያሳትፈን በጸሎቱ ይማረን!።

ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱስ ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደና ከገድላት አንደበት።


“ሰላም ለእስጢፋኖስ እንተ ነጸረ በዐይኑ። እንዘ ወልድ ይነብር ለአብ ውስተ የማኑ። ከመ ኖትያዊ ጠቢብ ኃዳፌ ሐመር በኪኑ። ባሕረ መጻሕፍት አመ ጸበተት ልሳኑ። ተቃውሞቶ መዋግድ ስእኑ”። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የጥቅምት 17።