
ጣና ቂርቆስ በጣና ሀይቅ ውስጥ ከሚገኙት ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳማት አንዱና ቀዳማዊዉ ሲሆን የተመሠረተው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ982 ዓ.ዓ ነው።
የንጉስ ሰለሞን ልጅ ቀዳማዊ ምኒልክ ከእሥራኤል ታቦተ ጽዮንን አጅበው በታቦተ ጽዮን መሪነት በፈቃደ እግዚአብሔር የመኳንንት ልጆችና ታቦተ ጽዮንን የሚያገለግሉ ካህናት እንዲሁም ከሌዋዉያን በጠቅላላ ብዙ ሺህ ህዝብ አስከትሎ ወደ ደሴቱ በመምጣት ይህንን ታላቅ ገዳም መሠረተው፡፡ የቦታውንም ስም ሳፍ ጽዮን መካነ ሣህል በማለት ሠይመውታል፡፡
እስራኤላውያን ካህናት ታቦተ ጽዮንን ከዚህ ገዳም ሲያስቀምጡ አብሮ የመጣውን ህዝብ ከባህር ውጭ ባለው ሥፍራ ሥላሰፈሩት እስከ ዛሬ ድረስ አካባቢው ነገደ እስራኤል በመባል ይታወቃል፡፡ ከመጡት እስራኤላውያን ካህናት መካከል የሊቀ ካህኑ የሣዶቅ ልጅ አዛርያስ ይገኝበታል፡፡ ካህኑ አዛርያስ አምልኮተ እግዚአብሔርንና መስዋዕተ ኦሪትን ካስፋፋ በኋላ ከዚህ አለም በሞት ሲለይ በጣና ቂርቆስ ደሴት ነበር መካነ መቃብሩ ያረፈው፡፡ መካነ መቃብሩ የቃል ኪዳኑ ታቦት ድንኳን ካረፈበት ምስራቅ አቅጣጫ በሁለት የድንጋይ ቋጥኞች መካከል ይገኛል፡፡
የጣና ቂርቆስ ቤተ-ክርስቲያን ከገዳሙ ከፍተኛ ቦታ ላይ የተሰራ ሆኖ የቃል ኪዳኑ ታቦት (ጽላተ ሙሴ) ካረፈችበት ቦታ ምዕራብ አቅጣጫ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የቤተ-ክርስቲያኑ ቅርጽ አራት ማዕዘን የሆነበት ምክንያት የቃል ኪዳኑ ታቦት ድንኳን አምሳያ እንደሆነ መነኮሳት ይገልፃሉ፡፡
ህገ ኦሪትና አዲስ ኪዳን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰበከበትና የጽላተ ሙሴ ማደሪያ የሆነው ሣፋ ጽዮን ደብረ ሣህል ወይም የዛሬዋ ጣና ቂርቆስ አንድነት ገዳም እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በስደት ዘመኗ አረጋዊ ዮሴፍንና ቅድስት ሶሎሜን አስከትላ በመልአኩ ዑራኤል መሪነት ከዚህ ታላቅ ገዳም 3ወር ከ10 ቀን ከልጇ ጋር ተቀምጣበታለች፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ታላቅ ገዳም ሳለች ይመራ የነበረዉ መልዓክ ለዮሴፍ በህልሙ “ሄሮድስ ስለሞተ ህፃኑንና እናቱን ይዘህ ተመለስ” በማለት ሲነግረው ዮሴፍም ወደ ህፃኑ በመቅረብ /ፀአና በደመና/ በደመና ጫናት በማለቱ የገዳሙና የሀይቁ መጠሪያ ስም ጣና በመባል እደቀረ ይነገራል፡፡
የኢትዮጵያ ብርሀን ተብለው የሚጠሩት አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሀን ከነገሥታቱ ጋር ወደ እዚህ ቦታ በመምጣት የመጀመሪያውን የክርስትና እምነት ግዝረትን ሽረው ጥምቀትን፡ መሥዋዕተ ኦሪትን ሽረዉ አማናዊዉን የክርስቶስ ስጋና ደም በመሠዋት የክርስትና እምነትን አጽንተውበታል፡፡
አቡነ ሰላማ ጥምቀትን ብቻ ሳይሆን አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈፀምበትን ታቦተ ህግ በቦታው አራት ጽላት በመቅረፅ በዛን ጊዜ እምነቱ ይስፋፋባቸው ወደ ነበሩት ሀገራት በትግራይ አክሱም ፅዮን፡ በጎጃም መርጦ ለማርያም እና ጣና ቂርቆስ፡ በወሎ ተድባበ ማርያምን በማስተከል ሁሉንም ታቦታት ታቦተ ፅዮን በማለት እንደሰየሟቸው በቦታው ያለው ታሪክ ያትታል፡፡
አቡነ አረጋዊና አፄ ገብረ መስቀል ወደዚህ ታላቅ ገዳም በመምጣት በረከትን አግኝተዎል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በገዳሙ ለአምስት አመታት በመቀመጥ ምልክት የሌለውን ድጓ ጽፎ ለገዳሙ አበርክቷል፡፡
ብዙ ቅዱሳን አባቶቻችንና ቅዱሳት አንስት እናቶቻችን በምነና እና በጸሎት ጸጋ እግዚአብሔር አግኝተውበታል።
የተለያዩ ነገሥታት አፄ የተባሉባቸውን ዘውዶች፡ አክሊሎች፡ የማዕረግ ልብሶች ጌጣጌጦች እንዲሁም ሌሎች የከበሩ ዕቃዎች እስከ ዛሬ ተጠብቀው የሚኖሩበት የሀይማኖት ማዕከልና የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ ማሕደርና መሠረት ነው፡፡
ጣና በአጠቃላይ በውስጡ ከ37 በላይ ደሴቶች ሲኖሩት 27 ገዳማትን አቅፎ ይዟል።ገዳማቶች በ14ኛ ምእት ዓመት አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ባመነኮሷቸው ‹‹ሰባቱ ከዋክብት›› ተብለው በሚጠሩት ቅዱሳን አባቶች የተመሠረቱ ናቸው።
ከገዳማቶች መካከል፦
ደብረ ማርያም
ክብራን ገብርኤል
ዑራ ኪዳነምሕረት
መሀል ዘጌ ጊዮርጊስ
አቡነ በትረ ማርያም
አዝዋ ማርያም
ዳጋ ኢስጢፋኖስ
ይጋንዳ ተክለሃይማኖት
ናርጋ ሥላሴ
ደብረ ሲና ማርያም
ማንድባ መድኃኔዓለም
ጣና ቂርቆስ
ክርስቶስ ሠምራ ገዳም
ራማ መድኃኔዓለም
ኮታ ማርያም…እና ሌሎችም ገዳማቶች ይገኙበታል።

