ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ (14261460ዓ ም) በዘመናቸው አምልኮ ጣዖትን አስቆማለሁ ብለው ቆርጠው ተነሥተው ነበር፡፡ ይህንን ነገር ለማስቆምም ሦስት ዓይነት መንገድ ለመጠቀም አሰቡ፡፡ መምህራንን እየላኩ ሕዝቡን ለማስተማር፣ ለማስተማርያ የሚሆኑ ድርሰቶችን እንዲዘጋጁ ለማድረግና ራሳቸውም ለማዘጋጀት፣ በመጨረሻ ደግሞ ከዚህ ሁሉ የተሻገረውን ለመቅጣት፡፡ በተለይም በአምልኮ ጣዖት የተያዙትን፣ ይህንንም አምልኮ ከሕዝቡ ገንዘብ ለመሰብሰብና ሕዝቡን ለማታለል ሲሉ የሚያካሂዱትን ሰዎች የሚከታተሉ፤ ባለሥልጣናቱ በድብቅ ይህንን ተግባር ሲያከናውኑ፣ አንዳንድ ካህናትም ከሁለቱም ወገን ሆነው ሲያጭበረብሩ፣ ታዋቂ የሆኑ ሰዎችም በዚህ ባዕድ አምልኮ ውስጥ ሲነከሩ እየተከታተሉ ለንጉሡ መረጃ የሚሰጡ ሦስት ሰዎችን መድበው ነበር፡፡ ዘርዐ ክርስቶስ፣ ተዐውቀ ብርሃንና ገብረ ክርስቶስ የሚባሉት እነዚህ ሦስት ሰዎች ወደ ባዕድ አምልኮ የሚሄዱትን፣ በድብቅ ይህንን ተግባር የሚያከናውኑትን፣ በተለይም የቤተ መንግሥት ሰዎች ሆነው ለሕዝቡ የባዕድ አምልኮ ክፉ አርአያ የሚሆኑትን እንዲጠቁሙ፣ ተከታትለውም እንዲያሲዙ፣ አስይዘውም እንዲያስቀጡ ንጉሡ ሥልጣን ሰጥተዋቸው ነበር፡፡

