ከሁሉ በኋላ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ታየኝ

ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን ስለ ጌታ ትንሣኤ ማስረጃ እያቀረበ ነው:: በዚያን ዘመን ለጌታ ትንሣኤ ማስረጃ ስትጠቅስ በማቴዎስ ወንጌል እንዲህ ይላል ብለህ እንዳትጠቅስ ገና ወንጌላት አልተጻፉም:: ቢጻፉም ማቴዎስ በሕይወት እያለ በቃሉ መመስከር ሲችል ጽሑፉን ማስረጃ ማድረግ አያስፈልግህም:: ስለዚህ ለመነሣቱ ማስረጃዎች ከተነሣ በኋላ ያዩት ሰዎች ነበሩ:: በሕይወት ያሉትን የዓይን ምስክሮችን መጥቀስ ይቻላል:: የዓይን እማኞች ምስክርነት ከጽሑፍ በላይ የታሪክ ማስረጃ ነው:: ስለዚህ ጳውሎስ ስለ ጌታ ትንሣኤ “እነ እገሌ አይተውታል” እያለ መዘርዘርን መረጠ::

ጌታ ከተነሣ በኋላ እንደ ቀድሞው ለሁሉ አልታየም:: እርሱን ለማየት የተገባቸው ጥቂት ወደ ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ነበሩ:: በማኅበር ያዩት አሉ:: በግል ያዩት አሉ::
ያዩት ነገር ወንጌል የሆነላቸው ብፁዓን ዓይኖች ያሏቸው እንዴት የታደሉ ናቸው? የተሰቀለውን ተነሥቶ ያዩት! ዳግም በሚመጣበት አካል የተገለጠላቸው ምንኛ የታደሉ ናቸው? ከመድኃኔ ዓለም አፍ ተቀብለው ኪዳን ያደረሱ! የጌታን ቅዳሴ ተቀብለው ያስቀደሱ! የትንሣኤው ማግስት ምስክሮች እንዴት ዕድለኞች ናቸው? ቢሞቱም እንኳን መነሣታቸውን በጌታ ትንሣኤ አይተው ደስ ብሎአቸው ያንቀላፉ እነርሱ ምንኛ የታደሉ ናቸው?

ቅዱስ ጳውሎስ በወንጌል ከተጠቀሱት ከነ ኬፋ በተጨማሪ ለይቶ ጌታ ለማን ለማን እንደታየ ገለጸ:: ለያዕቆብ ታየ ብሎ የእልፍዮስን ልጅ ለይቶ ጠቀሰው:: የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፍት እንደሚሉት ይህ ሐዋርያ ከሌሎች በተለየ የጌታን ትንሣኤ ሳላይ እህል አልቀምስም ብሎ የተሳለና አክፍሎትን የጀመረ ነበርና ጌታ ለይቶ ክብሩን አሳይቶታል:: ከዚያም ለዐሥራ ሁለቱ ታየ ብሎ የጌታን ድኅረ ትንሣኤ አስተርእዮ ዘረዘረ:: እኔ ማለትን የማይወደው ትሑት ቅዱስ ጳውሎስ “ከሁሉ በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ አለ::

ጭንጋፍ ምንድር ነው? ጭንጋፍ (ጸዕጻዕ/ ተውራድ) ለፅንስ የሚነገር ቃል ነው:: መወለድ ያለበትን ጊዜ ያልጠበቀ ያለ ጊዜው የተወለደ ፅንስ ነው:: በመጠኑ ከሌላው ጊዜውን ከጠበቀ ፅንስ የሚያንስ ሲሆን ዕድገቱን በተገቢው ጊዜ ከሚወለድ ልጅ ጋር ለማስተካከል ሲባል በሙቀት ማቆያ ክፍል እንዲቆይ ይደረጋል:: ይህ ፅንስ ሲወለድ በሕመም ውስጥ ሆኖ ተሰቃይቶ ተጨንቆ ነው::

ቅዱስ ጳውሎስ ራሱን ለመግለጽ የተጠቀመበት ይህ አንድ ቃል የሕይወት ታሪኩን ጠቅልሎ የያዘ ድንቅ ቃል ነበር::ቅዱስ ጳውሎስ ምንም እንኳን የቤተ ክርስቲያን ብርሃን የሆነ ሐዋርያ ቢሆንም እንደ ዓሥራ ሁለቱ ሐዋርያት በጊዜው የተጠራ አልነበረም:: እርሱ ከሐዋርያት ጋር አብሮ በዳግም ልደት የተወለደ ሳይሆን ያለ ጊዜው ክርስቶስ ባረገ በስምንተኛው ዓመት የተጠራ ነበረና ራሱን ካለ ጊዜው ከተወለደው ፅንስ ጋር አመሳስሎ እንደ ጭንጋፍ የምሆን ብሎ ጠራ::

ጭንጋፍ ሲወለድ በመጠኑ ከሌላው ፅንስ ያነሰ ይሆናል::
ቅዱስ ጳውሎስም ራሱን ጭንጋፍ ካለ በኋላ “እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ” ብሎ አብራርቶታል:: (1ቆሮ 15:9)

ልጅ ጭንጋፍ ሆኖ ሲወለድ በሥቃይ ነው:: ጤና ያጣል ይታመማል:: እናቲቱም ትታወካለች በድብታ በጭንቀት ትቸገራለች:: ባለሙያዎቹ እንደሚሉት እናት ያለ ጊዜው ከተወለደ ልጅዋ ጋር እናታዊ ትስስር ለመፍጠርና የእናትነት ፍቅርዋን ለመሥጠት ባልጠበቀችው ጊዜ የመጣ በመሆኑ ምክንያት ለጥቂት ጊዜ ትቸገራለች:: በአጭሩ ጭንጋፍ ሆኖ ሲወለድ እሱም ይሰቃያል እናቱንም ያስጨንቃል:: ወዲያው እንደሌላ ሕፃን በሰው እጅ አይታቀፍም:: ከተፈጥሮአዊ እስከ ሰው ሠራሽ እንደየጊዜው እየዘመነ በሔደው የልጅ ሙቀት መስጫ መንገድ እየታገዘ የሰውነት አካሎቹ በአግባቡ መሥራት እስከሚችሉና በሽታ መቋቋም እስከሚችል ይቆያል::

ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ጭንጋፍ ነበርኩ ያለው ለዚህ ነው:: በዳግም ልደት የተወለደው በደማስቆ መንገድ ወድቆ ሊቋቋመው ባልቻለው ብርሃን ተመትቶ ነበር:: “ሳውል ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምፅ ሲሰማ ፅንስ ነውና ዓይኑን እንኳን መግለጥ አልቻለም ነበር::
ከተወለደ በኋላም ወዲያው ወደ ቤተ ክርስቲያን እቅፍ ወደ ሐዋርያት ማኅበር አልገባም:: እንደ ጭንጋፍ የምሆን እንዳለ ሙቀት ያስፈልገው ነበርና የሰው እጅ ሳያቅፈው ሦስት ዓመት በሱባኤ ቆይቶ በመንፈስ ቅዱስ ተሟሟቀ::

“ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥ ከእኔም በፊት ሐዋርያት ወደ ነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፥ ነገር ግን ወደ ዓረብ አገር ሄድሁ እንደ ገናም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ። ከሦስት ዓመት በኁዋላ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ” ብሎ ስለ መንፈሳዊ ኃይል መልበሱ ይናገራል:: (ገላ 1:15-18)

ጭንጋፍ ሆኖ የተወለደ ልጅ የሚገጥመው ችግር ከወላጆቹ ጋር በሥነ ልቡና ለመተሳሰር መቸገሩ ነው::
ቅዱስ ጳውሎስን ለማመንና እንደ ልጅ ለመቀበል የቤተ ክርስቲያን ማኅበርም ተቸግራ ነበር::
“ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከደቀ መዛሙርት ጋር ይተባበር ዘንድ ሞከረ፤ ሁሉም ደቀ መዝሙር እንደ ሆነ ስላላመኑ ፈሩት” ሐዋ 9:26 ስለዚህ ሐዋርያው እንደ ጭንጋፍ ነኝ አለ::

ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጌታ መነሣት ምስክሮች ብሎ ሌሎችን ከዘረዘረ በኋላ “ከሁሉ በኋላ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ታየኝ” ብሎ ተናገረ:: ክርስቶስ ተነሥቶአል ወይ ብለው ሲጠይቁህ አዎ ተነሥቶአል እነ እገሌ አይተውታል ብለህ ዘርዝረህ “ከሁሉ በኁዋላ ለእኔም ታየኝ” ብለህ መናገር መቻል እንዴት መታደል ነው!?

ወዳጄ ክርስቶስ መነሣቱን ታምናለህ:: ልክ ነህ ለብዙዎች ታይቶአል:: አንተስ ከሁሉ በኁዋላ ለእኔም ታየኝ ማለት ትችል ይሆን? ጌታ ከተነሣ በኁዋላ ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ለብዙዎች ታይቶአል:: ብዙዎቹ ቅዱሳን አይተውታል:: ቅዱስ እስጢፋኖስ አይቶታል : ቅድስት አርሴማ አይታዋለች : አቡነ ተክለ ሃይማኖት አይተውታል : አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ተመልክተውታል:: አባ ጳኩሚስ በዕንባ ተመልክቶታል : ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ አይታዋለች::

ሁሉም ቅዱሳን ብዕር ቢሠጣቸው ከዕንባ ጋር
“ከሁሉ በኁዋላ ለእኔም ታየኝ” ብለው የትንሣኤውን ማስረጃ ዝርዝር ይቀጥላሉ:: ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በበረሃ ሲጸልይ አይቶት ነበርና ሰው ባገኘ ቁጥር
ወቅቱ የፋሲካ ሰሞን ባይሆንም እንኳን በፈገግታ ተሞልቶ
“ክርስቶስ ተነሥቶአል!” ብሎ ያበሥርና ሰላምታ ይሠጥ ነበር::

ጌታ ሆይ ለእኔ ለኃጢአተኛው የምትታየኝ መቼ ይሆን? ቸርነትህን አይቻለሁ! ፍቅርህን አይቻለሁ! ብሩሕ ገጽህን የማየው መቼ ይሆን? መች እደርሳለሁ የአምላኬንስ ፊት መቼ አየዋለሁ? እኔም እንደ ቅዱሳንህ “ከሁሉ በኁዋላ ለእኔ ታየኝ” ብዬ የተቀመጠውን ብዕር አንሥቼ የምጽፈው መቼ ይሆን? አቤቱ ፊትህን እሻለሁ! አቤቱ ፊትህን ከእኔ አትመልስ! አቤቱ ፊትህን እሻለሁ!

“ኢየሱስ ክርስቶስ በግዕ ዘቀራንዮ
ለላሕይከ ንትሜነይ ከመ ንርአዮ”
“የቀራንዮው በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ
ውበትህን ልናየው እንመኛለን”

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

ፍርሃትን የሚጥል ፍፁም ፍቅር

በሌሊት ማለፍና በፀሐይ መውጣት መካከል ገና ጨለማ ሳለ ሁለቱ ማርያሞች ማርያም መግደላዊትና የያዕቆብ እናት ማርያም ከሰሎሜ ጋር ሽቱ ሊቀቡት ወደ መቃብሩ ሄዱ። በዚህ ግርማ ሌሊቱ ባልተለየው ድምፀ አራዊቱ በሚሰማበት ሌሊት የአይሁዳውያን ዛቻና የኃያላኑን የሮማ ወታደሮች ቁጣ ተጋፍጠው የክርስቶስን ክቡር ሥጋ ሽቶ ይቀቡ ዘንድ ወደ መቃብሩ ገሰገሱ። እነኚህ ሴቶች የክርስቶስን ሞት ሰምተው መቃብሩን ሊያዩ ከሩቅ የመጡ እንግዶች አልነበሩም ይልቁንም በዕለተ አርብ እየተላጋ ሲወሰድ፣ በየመንገዱ ሲጎተትና መስቀል ተሸክሞ ሲሄድ እያለቀሱ በደም የተዋበ የመስቀሉን መንገድ በእንባ ያጠቡ ሴቶች ናቸው።

ሐዋርያቱ ሸሽተው በሄዱበት አሁን አድን ያሉት የኢየሩሳሌም ሰዎች አሁን አጥፋው ብለው ጲላጦስን በሚማፀኑበት ወቅት ከእግረ መስቀሉ ሥር የነበሩ ሴቶች ናቸው። ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በአዲስ መቃብር ሲቀብሩት ከሩቅ ሆነው ያዩት ሴቶች ናቸው። ጌታቸውን በመቃብር ትተው እንቅልፍ አልወስድ ቢላቸው በሌሊት ተነስተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ወንጌላዊው ማቴዎስ ሁለቱ ሴቶችን በስም ሲጠራ ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ በትንሳኤው ዘርዘር ያለ መገለጥን ያየችው ቅድስት ማርያም መግደላዊት ላይ ዋናውን ትኩረቱን ያደርጋል። ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ግን የሦስቱንም ስም ዘግቦ እናገኘዋለን። ይሄ አዘጋገብ የታሪክ ልዩነት ሳይሆን የወንጌላውያኑን የትኩረት ነጥብ የሚያሳይ ነው።

እነዚህ ሴቶች ማልደው ወደ መቃብሩ ሲደርሱ ድንጋዩን ማን እንደሚያንከባልልላቸው ተጨንቀው ነበር።
ራሔልና ሴቶቹ የውሐውን ምንጭ መዝጊያ ድንጊያ የሚያንከባልልላቸው አጥተው እስከ ቀትር እንጠብቃለን? ብለው እንደተጨነቁት ማየ ሕይወት ክርስቶስ ያለበትን በጲላጦስ ማህተም ታትሞ በሮማ ወታደሮች የሚጠበቀው የመቃብር ድንጋይን ሚያንከባልላቸው ሰው እያሳሰባቸው ነበር። ሲደርሱ ግን የገጠማቸው ፍፁም ተቃራኒ ነበር። እንደ ያዕቆብ ሆኖ የመቃብሩን ድንጋይ የሚያንከባልል መልአክን እግዚአብሔር ልኮላቸው ነበር። /ዘፍ 29:8-10/

የእስክንድርያው ቅዱስ ቄርሎስ በልደቱ ሌሊት መንጋቸውን ሲጠብቁ ለነበሩ እረኞች አትፍሩ ያሉ መላእክት (ሉቃ 2:10) ዛሬም እጅግ ጨለማ በነበረው ፀሐይ አልባ የማለዳ ጠዋት የመጡትን ሴቶች አትፍሩ አሏቸው እያለ በልደቱ የተሰበከውን የምስራች በትንሳኤው ሌሊት ስለመደገሙ ይደነቃል።

መላእክቱ የተናገሩት ቃል እጅግ የሚያረጋጋ ነበር። የሚፈልጉትን አስቀድመው ያውቁ ነበርና ከሕማማቱ በፊት የነገራቸውን አስታውሰው እንደ ተናገረው ተነስቷል ብለው አወጁላቸው። ይሄንን ዜና የሰሙት አንስት ለሐዋርያት ለመናገር ተፋጠኑ። ቅዱስ ቄርሎስ የቅዱስ ጳውሎስንና የኢሳያስን ቃል ተውሶ ትንሳኤውን ሊያውጁ የተነሱትን እግሮችን መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ሲል ያወድሳል። ሮሜ 10:15፣ ኢሳ 52:7

መነሳቱን ግን በመላእክት ብቻ ሰምተው እንዳይቀሩ እርሱ ራሱም በፊታቸው ታየላቸው። አስቀድመው መላእክት አትፍሩ የተባሉ ቅዱሳን አንስት ከክርስቶስም አንደበት የሚያረጋጋውን ቃል ሰሙ “እነሆም፥ ኢየሱስ አገኛቸውና፦ ደስ ይበላችሁ አላቸው። እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፦ አትፍሩ፤ ሄዳችሁ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ተናገሩ፥ በዚያም ያዩኛል አላቸው።” ማቴ 28:9-10

ወንጌላዊው ዮሐንስ ደግሞ ሌላም ቃል ይነግረናል። ሴቶቹ ለደቀመዛሙርቱ ከተናገሩ በኋላ ሐዋርያት ወደ ቦታው መጥተው መቃብሩ ባዶ መሆኑን አይተው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ማርያም መግደላዊት ግን ከመቃብሩ አጠገብ ቀረች። ዮሐንስ አፈወርቅ በዚህ ነገር ይደመማል። ቅዱስ ጴጥሮስ መቃብሩን አይቶ ተመለሰ ማርያም መግደላዊት ግን እዛው መቅረቷን ከሴትነት ልባዊ ፍቅርና ርህራሄ ጋር ያገናኘዋል። በእውነትም ሴት ያላትን የፍቅር ጥግ አስቀድሞ በመስቀል ኋላም በትንሳኤው ተገለጠልን። የዩሐንስ አፈወርቅን እይታ ገታ አድርገን የወንጌላዊውን ትረካ እንከተል። በጌታ መቃብር ቀኝና ግራ የተቀመጡ መላእክት ምን ትፈልጊያለሽ ብለው ጠየቋት። እርሷም ጌታን ወስደውታል የትም እንዳረጉት አላውቅም። ብላቸው ወደ ኋላ ዘወር ስትል ክርስቶስን አየችው። ታሪኩን ከወንጌላዊው አፍ እናዳምጥ:-

“ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም። ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ? አላት። እርስዋም የአትክልት ጠባቂ መስሏት፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ አለችው። ኢየሱስም፦ ማርያም አላት። እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ፦ ረቡኒ አለችው፤ ትርጓሜውም፦ መምህር ሆይ ማለት ነው። ኢየሱስም፦ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፦ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት። መግደላዊት ማርያም መጥታ ጌታን እንዳየች ይህንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች።” ዩሐ 20:14-18

ቅዱስ ቄርሎስ ይሄንን ተመልክቶ እንዲህ ይላል ሞት በሷ በኩል የመጣባት ሔዋን በገነት የአትክልት ስፍራ የሞትን ቃል እንደሰማች ሁሉ (ዘፍ 3:1) ማርያም መግደላዊትም በአትክልቱ ስፍራ ለሞት ሞት የሆነውን ትንሳኤውን ሰማች። ይለናል።

ምናልባት በዚህ ንግግር ውስጥ ክርስቶስ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ አላረግኩም የሚለው ቃል ጥያቄ ያስነሳ ይሆናል ። ሊቁ ጠርጡለስ ክርስቶስ ሌላ አምላክ እየጠራ አይመሰላችሁ ይለናል። ይልቁንም ፈጣሪ ያለውን የፍጡር ሥጋን ይዞ እንደተነሳ ሊያመላክት እንጂ እርሱ ፍጡር ሆኖ ሌላ ፈጣሪ ኖሮት አይደለም ይላል በዚህ ሀሳብ ቅዱስ ቄርሎስና አፈወርቅ ዮሐንስም ይስማማሉ ፍጡር ሥጋን ገንዘብ ስላደረገ ተናገረ እንጂ። እግዚአብሔር አብ የእርሱ አባትና አምላክ የሚሆንበት አገባብ ከኛ ይለያልና ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ አለ እንጂ ወደ አባታችንና አምላካችን አለማለቱን ቅድስት ቤተክርስቲያን ታስተምራለች።

ወደ ቅዱሳት እናቶቻችን እንመለስ ጌታ እስከመስቀል ላልተለየው ሐዋርያ ቅድስት ድንግል ማርያምን እንደሰጠው ሁሉ እስከመስቀል ለታመኑለት ቅዱሳት የከበረች ትንሳኤውን አስቀድሞ ገለጠላቸው። ባገለገሉት ልክ በወደዱትም መጠን አከበራቸው ቅዱስ ዮሐንስ አፈ በረከት እንዳለው የትንሳኤውን ወንጌል ለሐዋርያት ይሰብኩ ዘንድ የተገቡ አደረጋቸው።

ቤተክርስቲያንም ለዚህ መታሰቢያ የትንሳኤን ስድስተኛ ቀን ቅዱሳት አንስት ብላ ታከብረዋለች።

ክርስቶስ ተንስአ እም ሙታን – ክርስቶስ ከሙታን ተነሳ

⛪️ ዘበእንቲአሃ ለቤተክርስቲያን ⛪️

የክርስቶስን መከራና ሕመም ኬርኤላይሶን ብለን ያሰብንበት ዕለተ ስቀለት ካለፈ አንድ ሳምንት ሞላው። በስግደትና በሐዘን ያሰብነው ሕማሙ መዳረሻው ለእኛ ካጠላብን የሐዘን ቀንበር ነፃ መሆን ነውና የከፈለልንን ፍፁም ፍቅር ለማሰብ ቅድስት ቤተክርስቲያን የሰሙነ ትንሳዔውን የመጀመሪያ አርብ ቅድስት ቤተክርስቲያን ብላ ትሰይመዋለች።

ዕለተ አርብ ቤተክርስቲያን ተብሎ የመሰየሙ ምስጢር መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ አርብ የተቀበለውን መከራ ለማን ብሎ ነው የተቀበለው ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ነው። ምክንያቱም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም መፍሰስ የዘመናዊው ዓለም ምዕራባዊ ክርስትና እንደሚያስበው እያንዳንዱን በነጠላ በግል ለማዳን ሳይሆን እያንዳንዱን በቃሉና በደሙ በመሰረታት ሕብረት በኩል የራሱ አካል ለማድረግ ነውና።

የመጽሐፈ ሰዓታቱ ሊቅ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በመሐረነ አብ ጸሎቱ መግቢያ ሃሌ ሉያ ብሎ ይጀምርና ዘበእንቲአሃ ለቤተክርስቲያን ተጸፋእከ በውስተ ዓውድ ከመትቀድሳ በደምከ ክቡር ዘበእንቲአሃ ዝግሃታተ መዋቅሕት ጾረ ወተአገሰ ምራቀ ርኩሰ እንዘ አልቦ ዘአበሰ አምላክ ዲበ ዕፀ መስቀል ተሰቅለ /በክቡር ደምህ ትቀድሳት ዘንድ ስለቤተክርስቲያን በአደባባይ በጥፊ ተመታክ፤ ስለ እርሷ ሲል ታስሮ ተጎተተ፣ እርኩስ ምራቅን ታገሰ ያለበደል አምላክ በመስቀል ላይ ተሰቀለ ሲል የክርስቶስ ዋጋ መክፈል ለቤተክርስቲያን መሆኑን ይናገራል።

ለመሆኑ ይህች ቤተክርስቲያን ማናት? ብዙዎቻችን ስለቤተክርስቲያን ስናስብ አእምሯችን ላይ የሚመጣው ህንፃው ወይም ተቋም ነው። በእርግጥ ህንፃ ቤተክርስቲያን ከቤተክርስቲያን ሦስቱ ትርጉሞች አንዱ ቢሆንምና ለአስተዳደር እንዲመች ሲባል ቤተክርስቲያን በተቋማዊ መልክ ብትገለጽም ቤተክርስቲያንን እንደ አንድ ድርጅት መረዳት ከሌሎች የእምነት ድርጅቶችና ፈራሽ ተቋማት ጋር የምትነፃፀር አድርጎ መረዳትን ፈጥሮብናል።

ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል መነሻ አቅሌሲያ /ἐκκλησία/ ሲሆን ትርጉሙም ጉባዔ፣ አንድነት፣ ሕብረት ማለት ሲሆን የጉባዔው ባለቤት ራሱ እግዚአብሔር ስለሆነ ቤተክርስቲያን ጉባኤ እግዚአብሔር ተብላ ትጠራለች። (ማቴ 16:18)

ቤተክርስቲያን የተመሰረተችው በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነትን በሚገልፅ መሠረተ እምነት ላይ ነው። ለዚህም ነው ክርስቶስ ጴጥሮስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ ብሎ ሲመሰክር አንተ አለት (በግሪኩ Πέτρος – ጴጥሮስ) ትባላለህ ካለው በኋላ ምስክርነቱን በሴት አንቀጽ በዚህችም አለት (በግሪኩ πέτρα – ጴጥራ ) ላይ ቤተክርስቲያኔን እመሰርታለሁ የሲኦል ደጆችም አያናውጧትም በማለት የተመሠረተችው በሥጋና ደም ሳይሆን ከእግዚአብሔር በተገኘ ቃል መሠረት መሆኑን ይነግረናል (ማቴ 16: 15-18)።

ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር ቃል ተመስርታለች ስንል ምን ማለታችን ነው የሚል ካለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይለናል “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤” ኤፌሶን 2፥20 በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የሚናገሩ የነቢያትና የሐዋርያት የመጻሕፍትም ሆነ የትውፊት ትምህርቶች የቤተክርስቲያን መሰረት መሆናቸውን ይናገርና የማዕዘኑ ራስ እርሱ ጌታችን መሆኑን ይናገራል።

መምህረ ዓለም ጳውሎስ ከሌሎች ሐዋርያት አብልጦ ስለቤተክርስቲያን አምልቶ በመናገር የሚታወቅ ሐዋርያ ነው ይህ ሐዋርያ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ በምን ያህል መጠን እንደተወደደች ለባሎች በሚሰጠው ምክር ላይ ያነሳዋል።


“ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ። እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ።” ኤፌ 5:25-27

ቤተክርስቲያን ድካምና እድፈት እንዳይኖርባት አድርጎ ምን ያህል እንደ ወደዳት እናስተውል። እርሷ ከዳግማዊው አዳም በዐለተ አርብ ከጎኑ ተገኝታለችና ዳግማዊት ሔዋን ናት። ሔዋን የሚለው ቃል የሕያዋን እናት እንደ መሆኑ የስሙ ትርጓሜም ልክ የሚመጣው በክርስቶስ አባትነት ሕያዋንን ለምታፈራው ለቤተክርስቲያን ነው። በዚህች ቤተክርስቲያን በኩል ካልሆነ ማንም ሕይወት እኔ ነኝ ካለን ከክርስቶስ ጋር አይገናኝምና ከሷ ውጭ ያሉ ሁሉ ሙታን ናቸው።

የቤተክርስቲያን ክብር ይህን ያህል ነው ምክንያቱ ደግሞ ራሷ ክርስቶስ ስለሆነ ነው። ከዚህም ባሻገር ቤተክርስቲያን ወሰን አልባ ናት። ከቀደመው ሰው መፈጠር አስቀድሞ በዓለመ መላእክት የነበረች ጉባዔ ናት። ይህችው ጉባዔም በምድር በብሉይ ኪዳን አበው ዘንድ ነበረች። በነዳዊት አንደበትም ይህቺ ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት ብሎ ያናገረው እርሱ እግዚአብሔር ነው መዝ 132:14። ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ በነቢያትና በሐዋርያት መሰረት ላይ ብሎ የተናገረው።

እርሱ ክርስቶስ ይህቺኑ ቤተክርስቲያንን ያፀና ዘንድ በውስጧ ባሉ ሰውና መላእክት መሐል ያለውን የጥል ግድግዳ ያጠፋ ዘንድ ሰው ሆነ። በሐዲስ ኪዳን አዳምን ያከብረው ዘንድ መልዕልተ መስቀል እንቅልፍ በተባለ ሞት ውስጥ ሆኖ ከጎኑ በፈሰሰ ውሃና ደም የማትሞተዋን ሔዋንን ሰራልን። በዚህች ቤተክርስቲያን በኩል ብቻ ከክርስቶስ ጋር ህብረት መፍጠር እንድንችል ዘንድ የሚያዛምዱንን ምሥጢራት ሰራልን በጥምቀት ከአንድ ማህፀን በመወለዳችን ወንድምና እህት አደረገን። እራሱን የከበረ ማዕድ በማድረግ በቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ አፋቀረን። በሜሮን መንፈስ ቅዱስን አሳደረብን። ከክርስቶስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ ራስ በመሆን አካሉ እንሆን ዘንድ ፈቀደ።


አንድ የሰውነት አካል ብቻውን ሕያው እንደማይሆን አንድ ክርስቲያንም ያለ ቤተክርስቲያን ሕብረት በክርስቶስ ሕያው መሆን አይችልም በመሆኑም ከክርስቶስ ጋር ይጣበቅ ዘንድ ከቤተክርስቲያን ጋር አንድ መሆን ይኖርበታል።

ቤተክርስቲያን ራሷ በሆነው ክርስቶስ አማካኝነት ሕልውናዋም ዘላለማዊ ነው። በምድር የምትጋደል ቤተክርስቲያን እንዳለች ሁሉ በሰማይም አሸናፊት ቤተክርስቲያን አለችና የአማኞች ሞት ከተጋድሎዋ ቤተክርስቲያን ወደ አሸናፊቷ ቤተክርስቲያን መሸጋገሪያ ነው። በመሆኑም በአሸናፊዋ ቤተክርስቲያን የሚገኙ ምዕመናን ከተጋዳይዋ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ጋር ይነጋገራሉ፣ ይፀልያሉ በማይቋረጥ ሕብረት ይኖራሉ። ዕብ 12:1።

ይህንን ሁሉ ክብር ያለብሳት ዘንድ እናትም ትሆነን ዘንድ በመከራ መስቀል ቤተክርስቲያንን የዋጃት የአምላካችን ክርስቶስ ስሙ የተመሰገነ ይሁን።

ክርስቶስ ተንስአ እም ሙታን – ክርስቶስ ከሙታን ተነሳ።

የልደታ ለማርያም ቅዱስ ትውፊት

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት የተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በዓላት ጋር በተያያዘ ከተለያዩ አካላት በተደጋጋሚ የሚቀርቡ ትችቶችን መሰማት ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል

የዓለምአቀፋዊቷ ቤተክርስቲያንን ትውፊት ያጠና ግን በዓላቱ በዘመን የረዘመ በቦታም የሰፋ ነገር ግን እንደ ቦታው ታሪካዊ ሂደት ለውጥን የሚያስተናግድ ተመሳሳይነትን ማግኘቱ የማይቀር ነው። የዚህ ምንጩም ዜና ቅዱሳን ነው።

የቅዱሳንን ዜና ሕይወት መጻፍ በብሉይ ኪዳን የተጀመረ ሲሆን ሊቀ ነብያት ሙሴ በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፉ የቀደሙ ርዕሳነ አበውን የነአዳም፣ ኖህ፣ ሄኖክ፣ አብርሃምን ታሪክ ሰንዶልናል። የቅዱሳን መሳፍንትና ነገስታትም ዜና ሕይወት በመጽሐፈ መሳፍንት፣ ነገስትና ዜና መዋዕል በሌሎቹም ክፍላት የተፃፉ ናቸው።

በሐዋርያት ሥራ መጽሐፉም ሉቃስ የሐዋርያትን አገልግሎት ከትቧል። እኒህ ሁሉ ዜና ቅዱሳን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተቱ ሲሆን ሳይገኙ በመዘግየት ያልተካተቱ የሐዋርያት ጽሑፎችና የድኅረ ሐዋርያት ዜና ቅዱሳን በተናጥል (ገድላትና ተአምራት) እንዲሁም በስብስብ (ስንክሳር) መልኩ እየተዘገበ ከዚህ ዘመን ተደርሷል። የአንዳንድ የቅዱሳን ዜና በዓለም ሁሉ የሚታወቅ ሲሆን የሌሎች ዜና ገድል ግን በተወሰነ ቦታ ብቻ የሚታወቅ ሆኖ እናገኘዋለን።

እንደ ዓለም ገዝፎ በመታወቅ ደረጃ የቅድስት ድንግል ማርያምን መታወቅና መከበርን የሚያህል የለም። የድንግል ማርያም ነገረ ልደት በሁሉም ጥንታዊያን አብያተክርስቲያናት የሚታወቅና የሚከበር በዓል ነው። በነገረ ድህነታዊ ዋጋቸው በአለም ሁሉ ከሚከበሩት የሁለት ፍጡራን በዓላትም ዋነኛው የእመቤታችን ልደት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል ተብሎ በጌታችን የተነገረለት የመጥምቁ ዮሐንስ ልደት ነው።

የእመቤታችን ነገረ ልደት የተመዘገበበት ጥንታዊው መጽሐፍ የጌታ ወንድም ተብሎ የተጠራው ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ያዘጋጀው መጽሐፈ ልደት (the book of nativity) ወይም መጽሐፈ ያዕቆብ (book of James) በግሪኩ ደግሞ ፕሮቶቫንጌልዮን ነው።

መጽሐፉ በኦርቶዶክስና የካቶሊክ አብያተክርስቲያናት በቀኖናቸው ተቀባይነት የሰጡት መጽሐፍ ሲሆን 16 ምዕራፎች ያሉት መጽሐፍ ነው። እንደ ስያሜው አምላክን ስለወለደች ቅድስት ድንግል ማርያምና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የሚያወራ ሲሆን እመቤታችን ዘመዱ እንደመሆኗ ከእርሷና ከቅርብ ዘመዶቿ እየሰማ እንደፃፈው ይታመናል።

በ1ኛው ክ/ዘ እንደተጠናቀቀ የሚነገርለት ይህ መጽሐፍ እንደ ኦሪገን ያሉ የጥንቷ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት በትምህርታቸው ላይ የጠቀሱት ሲሆን በ1552 ወደ ላቲን ተተርጉሟል።

መጽሐፉ ሲጀምር “የኢየሱስ ክርስቶስና የዘለዓለማዊት ድንግል ማርያም የልደት ታሪክ፤ የክርስቶስ ዘመድና ወንድም በሚሆን ዋና ሐዋርያ እንዲሁም የመጀመሪያው የኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች ሊቀጳጳስ በሆነ ታናሹ ያዕቆብ” ብሎ ይዘቱንና ጸሐፊውን ይናገራል።

የመጽሐፉ ታሪክ በሁሉም አቢያተክርስቲያናት የሚታመን ሲሆን ታሪኩ ከመጽሐፉ መታተም ከ600 ዓመት በፊት በተጻፉ ሌሎች ጥራዞች ላይ ሳይቀር መጠቀሱ በእድሜ ቅድምናና መነሻ ታሪክ እንዳለው ማሳያ ይሆናል።

የቅድስት ድንግል ማርያም የትውልድ ስፍራን በተመለከተ ልዩነቶች ያሉ እንዲሁም ናዝሬትና የኢየሩሳሌም መግቢያ ከተሞች በኔ ነው በኔ ነው የተወለደችው እያሉ ሚፎካሩ ሲሆን ኦርቶዶክሳዊት የተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ግን “ሙሽራዬ ሆይ፥ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፤ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፤ ከአማና ራስ ከሳኔርና ከኤርሞን ራስ፥ ከአንበሶች መኖሪያ ከነብሮችም ተራራ ተመልከች።” መኃልየ. 4፥8 የሚለውን የሰለሞንን ቃል መነሻ አድርጋ መወለዷ ከሊባኖስ መሆኑን ታስተምራለች። በሊባኖስም እጅግ ጥንታዊ የሆነ በስሟ የሚጠራ ቤተመቅደስም ይገኛል።

በዓለማችን የሚገኙ የተለያዩ ክርስቲያኖች (ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ ምስራቅ ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ አንጋሊካን፣ ሉተራውያን) የእመቤታችን ልደት በተለያዩ ቀናት የሚያከብሩ ሲሆን የምዕራብ አብያተክርስቲያናት ጷግሜ 3 (September 8), የምስራቅ አብያተክርስቲያናት (ኦርየንታልና ምስራቅ ኦርቶዶክስ መስከረም 10 (September 21) እንዲሁም የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የግብፅ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ በግንቦት 1 ያከብሯታል።

የእመቤታችንን 33 በዓላቷን በሚዘረዝረው የተአምረ ማርያም መቅድም ላይም መስከረም 10 የሚያከብሩ እንዳሉ ይጠቅስና “እኛ ግን..” ብሎ “…በተረዳ ነገር  አባቶቻችን ሊቃውንት እንዳስተማሩን ልደቷ ግንቦት 1 ነው እንላለን” ሲል ይመልሳል።

የእመቤታችን የልደት በዓል እስከ ደርግ ውድቀት ድረስ በብሔራዊ በዓልነት ሲከበር የነበረ ሲሆን እንደ ፊሊፒንስ ባሉ ሀገራት ስራ የማያዘጋ ብሔራዊ በዓል ተደርጎ ይከበራል።

ሁሌም የጌታ ትንሳኤ በሚከበርበት በበዓለ 50ው በዓል የሚከበረው የልደታ ማርያም ዓመታዊ በዓል ዘንድሮ ይበልጥ ከትንሳኤው በዓል ጋር ተቀራርቦ በአዳም መታሰቢያ ሐሙስ ላይ ውሏል።

መልካም የአዳም ተስፋ ማርያም የልደት በዓል

ክርስቶስ ተንስአ እም ሙታን – ክርስቶስ ከሙታን ተነሳ

አዳምና ማርያም

አምላካችን እግዚአብሔር አዳምን ሊያድነው ፈቅዶ ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም) ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ›› ብሎ ቃል የገባለትን በማሰብ ከትንሳኤ በኋላ ያለው  ዕለተ ሐሙስ ‹የአዳም ሐሙስ› ወይም ‹አዳም› ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ታድያ ይህ የአዳም ሐሙስ ዘንድሮ በ2016 ዓ.ም ለአዳም ተስፋው፡ ለሔዋንም መድኃኒቷ ከሆነችዋ ኢሳይያስ ከእሴይ በትር ውስጥ እንደምትገኝ ከነገረላት ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ልደት ጋር በአንድ ቀን ውሏል።

ይሕ ሐሙስ አዳም ተስፋው ተፈጽሞ ከነልጅ ልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ ይሆን ዘንድም ዕለቱ ይከበራል፡፡ (ሉቃ. ፳፬ ፥፳፭-፵፱)

    አዳምና ሔዋን ከሲኦል የወጡት በዕለተ ዓርብ ቢሆንም የቤተ ክርስቲያን አበው ሊቃውንት  የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት በማሰብ ዝክረ አዳም ሐሙስ እንዲከበር በወሰኑት መሠረት የሚከበረው የአዳም ሐሙስ አባታችን አዳም በተሰጠው የተስፋ ቃል የሁላችን ድኅነት ስለመፈጸሙ፣ አዳም ከነልጆቹ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻ ስለ መውጣቱ ይዘመራል።

      ከገነት በኃጢአቱ ምክንያት የወጣው አዳም የተገባለትን የቃልኪዳን መፈጸም በጉጉት ይጠብቅና በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከሲዖል ነጻ እስኪወጣ ተጨንቆ ለነበረው አዳም እመቤታችን ምልክት ነበረች። አዳምም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በተባለው መሰረት አምላኩ የሚወለድባትን የልጁን ልጅ መወለድ ዛሬ አገኘ።

አዳምና ሔዋን በንስሐ ተመላልሰው የተቀበሏትም ይኅችም ተስፋ፡ በሲኦል ውስጥ ለደረቀው አዳም መረስረስ እንዲሆንለት ለሰው ልጆች ዝናምን የምታሰጥ ደመና ናት።

አዳም እመቤታችን እስኪያገኝ ምን ያህል ናፈቀ? ምን ያህልስ ጓጓ? ነቢያት አምላካቸው እንደሚወለድ ይተነብዪት የነበረ ትንቢት የሚፈጸምባትን እናቱን እስከሚያገኟት ጓጉ። ለዓለሙ ሁሉ ደስታ እንደሆነ ቅዱስ ሉቃስ የጻፈለት አምላክ በማህጸኗ እንደሚያድር በቅዱስ ገብርኤል ብስራት ሰማች።  አዳም በሔዋን ምክንያት ያጣውን ገነት በእመቤታችን በኩል አገኛት። ተረግማና ደርቃ የነበረችው ምድር በልጇ በረከትን ለበሰች።

  የእመቤታችን ለአዳም ተስፋ መሆን በጌታችን መወለድ ብቻ አላበቃምና ዛሬም፡ አዳም ተስፋ ሲያጣ ከእመቤታችን ይጠጋጋል። በእንተ ማርያም መሀረነ እያለ አምላኩን በእርሷ በኩል ይለምናል። የተሰጣትን ቃልኪዳን እያሰበ ምንም እንኳም ኃጥእ ብሆን ለእናትህ ስለገባህላት ቃልኪዳን ብለህ እያለ ይማጸናል። ከገነት ተራቁቶ በተሰደደ ጊዜ ልብስ ሆና እርቃኑን የሸፈነችለት እናቱን እያሰበም ዛሬም ድረስ በተስፋዋ ይኖራል።

የአልዓዛር ትንሳኤ

የትንሳኤውን ሳምንት ቀናት እንደ በዓል የምታከብረዋ ቅድስት ቤተክርስቲያን በእለተ ረቡዕ የአልዓዛርን መታሰቢያ ታደርጋለች። የአልዓዛርን መታሰቢያ ሌሎች የኦርቶዶክስ አብያተክርስቲያናት በታሪክ ቅደም ተከተል መሰረት ከሆሳዕና በፊት ባለው ቅዳሜ የሚያከብሩ ሲሆን ቤተክርስቲያናችን ግን የምስጢር ቅደም ተከተልን መሰረት አድርጋ ከትንሳኤው በኩር ከኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ቀጥሎ ባለው ረቡዕ ታስበዋለች።


በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የክርስቶስን ትንሳኤ ሳይጨምር 9 ከሞት የመነሳት ታሪኮች የተመዘገቡ ሲሆን ከ9ኙ ውስጥ 3ቱ በነብያት (የሰራፕታዋ ልጅ፣ የሱነማዊቷ ልጅ፣ በኤልሳዕ መቃብር ላይ የወደቀው ሬሳ ) የተፈፀሙ ሲሆን 4ቱ ደግሞ የተፈፀሙት በኢየሱስ ክርስቶስ ነበር (የኢያኢሮስ ልጅ፣የናይኗ እናት ልጅ፣ የቢታኒያው አልዓዛርና በተሰቀለ ወቅት መቃብሮች ተከፍተው የወጡ ሙታን ናቸው)። የተቀሩት ሁለት ተአምራት የተሰሩት ደግሞ በሐዋርያት ነው (ጣቢታና አውጤኬስ)።
ከነዚህ ሁሉ የተዘገቡ ከሞት የመነሳት ታሪኮች ውስጥ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 11 የተመዘገበው የአልዓዛር ከሞት መነሳት ከትንሳኤው ጋር የተገናዘበ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ለምን ተከበረ? ብለን እንጠይቅ።


አልዓዛር ክርስቶስን ከሚያገለግሉ ብርቱ ቤተሰቦች ውስጥ አንዱ ሲሆን በአገልግሎት የሚራዱና ጌታን አጥብቀው የሚወዱት የማርታና የማርያም ወንድም ነው። ክርስቶስም ቤተሰቡን አብዝቶ ይወድ የነበረ ሲሆን አልዓዛር ሲታመምም እኅቶቹ በነብሱ ይደርስ ዘንድ መታመሙን ፈጥነው የነገሩት ለጌታችን ነበር። ጌታችን መልዕክቱ በደረሰው ጊዜ አልዓዛር አርፎ ነበርና ይሄን ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸው በማግስቱ ወደ አልዓዛር ቤት ለመሄድ ተነሱ።

ወደ አልዓዛር ቤት ሲደርሱ አልዓዛር ከሞተ አራት ቀን ሆኖት ነበር ። እኅቶቹን ማርታንና ማርያምን አናግሮ ወደ የት እንደቀበሩት ጠየቃቸው። ወደ መቃብሩም ወርዶ መቃብሩን አንሱት ብሎ አላዓዛርን ተጣራ አልዓዛርም ከተቀበረበት መቃብር በሕይወት ወጣ (ዩሐ 11:1-44)።


የአልዓዛር ትንሳኤ ከብዙ ትንሳኤዎች የተለየበት ብዙ ምክንያት አለው። የተወሰኑትን ለመመልከት ያህል፡-


የአልዓዛር ከሞት መነሳት ለጌታችን ሞት ምክንያት ነበር


ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ የአልዓዛርን ታሪክ ባሰፈረበት ምዕራፍ ከታሪኩ ግርጌ ብዙዎች በእርሱ እንዳመኑ ጠቅሶ ከፊሎች ግን ለፈሪሳውያን በመናገራቸው አይሁድ ክርስቶስን ለመግደል እንዲሰባሰቡ አደረጋቸው። ዮሐ 11:45-47 በመሆኑም የአልዓዛር ሞት በተቀራራቢ ጊዜ ከተከናወኑት የሆሳዕና ክብር፣ ቤተመቅደሱን ከማፅዳት ጋር እንደ ክርስቶስ ስቅለት መንደርደሪያ ተደርጎ ይወሰዳል።


የአልዓዛር ሞት የክርስቶስ አምላክነቱ ማረጋገጫ ነው


ከአልዓዛር በስተቀር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱ የመነሳት ታሪኮች የተፈፀሙት በትኩስ ሬሳ ማለትም ሟቹ በሞተበት ወይም በሚቀበርበት ቀናት ነው። በመሆኑም እንዲህ አይነቱ ከሞት ማስነሳት በአይሁድ ዘንድ የክርስቶስን አምላክ ነው ብሎ ለመቀበል የሚያስችል አልነበረም። የመጀመሪያው ተመሳሳዩን ተግባር ነብያትም ፈጽመውት የነበረ መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የአይሁዳውያን ልማዳዊ አስተሳሰብ ነው። አይሁዳውያን ሰው ከሞተ በኋላ ነፍሱ ለሦስት ቀናት በአየር ላይ ሆና ሳትርቀው ትቆያለች ከዛ በኋላ ነው ጥላው የምትሄደው የሚል እምነት ነበራቸው በመሆኑም ክርስቶስ በኢያኢሮስና በናይኗ መበለት ልጅ የሰራው ተአምር በአይሁድ ዘንድ አምላክ የሚያስብል አይደለም። በአልዓዛር ትንሳኤ ግን አስቀድመው ነብያት በኋላም ሐዋርያቱ ያልሰሩትን ድንቅ ሰርቶ ኃይሉን ገለጠ።


ክርስቶስ ያስነሳው አልዓዛር ከሞተ አራት ቀን የሞላውና መቆየቱም የተነሳ ሽታ ያመጣ ሬሳ ነበር። ሌላው ደግሞ እንደው ተጠራጣሪዎች እንደሚሉት የውሸት ሞት እንኳን ቢሆን (ሞቶ መስሏቸው የቀበሩት እንኳን ቢሆን) /Staged death/ ለአራት ቀን ያለምግብ፣ ያለውሀና ያለ አየር መቆየቱ በራሱ የሚገድለው በመሆኑ መሞቱ በህዝብም በአህዛብም የተረጋገጠ ነው። በመሆኑም የአልዓዛር መነሳት የኢየሱስን የእግዚአብሔር ልጅነት ያረጋገጠ ነበር።


የአልዓዛር መነሳት የክርስቶስን ፍቅር የሚያሳይ ነው።


የክርስቶስ ተአምራት ሁሉ የመነጩት ለሰው ልጅ ካለው ፍቅር ቢሆንም ለኢያኢሮስ ልጅ ዘመዶች  “አታልቅሱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” ያለው ክርስቶስ ስለ አልዓዛር ሞት ከማርታ፣ ማርያምና አብረው ካሉ ዘመዶቿ ጋር አለቀሰ። በዚህም ፍቅሩንና የሰው ልጅ መሆኑን አረጋገጠ።


የአልዓዛር ትንሳኤ የእውነተኛው ትንሳኤ ውብ ምስል መሆኑ


የእስክንድርያው ሊቅ ቅዱስ ቄርሎስ የአልዓዛርን ትንሳኤ ባብራራበት ትምህርቱ የአልዓዛር ትንሳኤን የሚመጣው የዕለተ ምጽዐት የሰው ልጅ ትንሳኤ ቆንጆ ማሳያ አድርጎ ያነሳዋል። ቅዱስ ቄርሎስ አልዓዛር የተነሳበት የአይሁድ 7ኛ ወር የመለከት በዓል (የዳስ በዓል መቃረቢያ) የመሆኑን መነሻ ከእለተ ምጽዓት የመለከት መነፋት ጋር ያያይዘዋል። ሙሴ ለዳስ በዓል መቃረቢያ መለከት እንደሚያስነፋ ለዘላለማዊቷ ድንኳን (መንግስት) መቃረቢያ መላእክትን መለከት እንደሚያስነፋ ያለ ነው ይላል። ቅዱሱ ከአልዓዛር መነሳት በፊት የነበረውንም ለቅሶ ከክርስቶስ በክብር መገለጥ በፊት ከሚኖረው ለቅሶ ጋር በማስተባበር የአልዓዛርን ትንሳኤ የኋለኛው ትንሳኤ ምልክት ነው ይለዋል።


የአልዓዛር ትንሳኤ የክርስቶስ ትንሳኤና ሕይወት መሆኑንና በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ ሕያው መሆናቸው የተመሰከረበት ነው


ክርስቶስ ከማርታ ጋር የነበረው ንግግር  ወንጌላዊው እንዲህ ይተርክልናል።
ማርታም ኢየሱስን፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ አለችው።
ኢየሱስም፦ ወንድምሽ ይነሣል አላት።
ማርታም፦ በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ አለችው።
ኢየሱስም፦ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤
ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት።
እርስዋም፦ አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ አለችው።


እዚህ ላይ ክርስቶስ ለማርታ የተናገረው ወሳኝ ነገር እንይ ትንሳኤና ሕይወት እኔ ነኝ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳን ሕያው ነው በማለት ትንሳኤ ከሌሎች በፀጋ የሚያገኘው ሳይሆን የባህርይ ገንዘቡ መሆኑን በመናገር በርሱ ለሚያምኑ ሁሉ በእርሱ ሕያው በመሆን የዘላለም ሕይወት የፀጋ ተካፋዮች መሆናቸውን አውጆበታል።
በመሆኑም የአልዓዛር ትንሳኤ ከፍጥረታት የሞት መነሳት ታሪኮች ሁሉ የተለየና ጌታችን አምላክነቱን ያወጀበት ልዩ ትንሳኤ በመሆኑ ከክርስቶስ ትንሳኤ ጋር ተያይዞ ይከበራል።


ክርስቶስ ተንስአ እም ሙታን – ክርስቶስ ከሙታን ተነሳ።

የልደታ ለማርያም ክብረ በዓል የት የት ይከበራል?

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በእነዚህ አብያተ ክርስትያናት ውስጥ የልደታ ለማርያም ዓመታዊ የንግሥ በዓል ይከበራል።

1) ማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤ/ክ             
   
ልዩ ስም፦ልደታ /ክ/ከ ልደታ             
 

2)ደብረ መድኃኒት አቡነ ሃብተማርያም ወቅድስት ልደታ ወቅድስት አርሴማ ገዳም 
          
ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ አስኮ ካኦጄጄ ዱቄት ፋብሪካ ከፍ ብሎ ቃሌ ተራራ ላይ             
              
3) ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል             
   
ልዩ ስም፡- አዲስ ከተማ ክ/ከ መርካቶ             
                 
4)    ደብረ ስብሐት ቅድስት ልደታ እና ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤ/ክ             

ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ ቀራንዮ            
                 
5)     ቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን                     

ልዩ ስም፦ቦሌ ክ/ከ ቦሌ እግዚአብሔር አብ                   
                 
6)   ኤረር በር ምስራቀ ፀሐይ ቅዱስ ዑራኤል  ቤተክርስቲያን        

ልዩ ስም፦ቦሌ ክ/ከ ኤረር በር             
                 
7)     አያት መካነ ሕይወት መድኃኔዓለም እና ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ    
       
ልዩ ስም፦ቦሌ /ክ/ከ አያት ጠበል             
                 
8)    ኮተቤ  ደብረ ልዑል ዳግማዊ ቁልቢ ቅዱስ ገብርኤልና ኆኅተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ቤ/ክ             

ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ ኮተቤ መሳለሚያ             
                 
9) መካነ ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና ቤ/ክ             

ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ ኮተቤ            
                 
10) ሲኤምሲ መካነ ጻድቃን አቡነ ተክለሃይማኖትና ቅድስት ልደታ  ቤተክርስቲያን
          
ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ መሪ ሎቄ              
                 
11)  ቦሌ ሰሚት መካነ ሰላም መድኃኔዓለም ቤ/ክ             

ልዩ ስም፦ቦሌ ክ/ከ ሰሚት             
                 
12)     መሪ አያት ምስራቀ ፀሐይ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስቅዱስ             

ልዩ ስም፦ቦሌ ክ/ከ መሪ             
                 
13) ካራ አሎ ደብር ቅዱስ ደብረ ቀርሜሎስ መድኃኔዓለም እና ጻድቁ አቡነ ገሪማ            
   
ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ ኮተቤ ካራ             
                 
14)    ርእሰ አድባራት እንጦጦ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ወ ኤልያስ             
   
ልዩ ስም፦ጉለሌ /ክ/ከ  እንጦጦ             
                 
15)   መንበረ ስብሐት ቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ             
   
ልዩ ስም፦ጉለሌ ሽሮ ሜዳ            
                 
16)     ደብረ ዕንቁ ልደታ ለማርያም             
   
ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ 01 ራሽያ ኤምባሲ ጀርባ             
   
17)    እንጦጦ ሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም             
   
ልዩ ስም፦ጉለሌ /ክ/ከ ሽሮሜዳ             
   
18)   ፈረንሳይ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክ             
  
 ልዩ ስም፦የካ /ክ/ከ ፈረንሳይ ብረት ድልድይ
             
   
19)   ብሔረ ፅጌ መካነ ሰላም ቅድስት ማርያምና መድኃኔዓለም ቤ/ክ             
   
ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ብሔረ ፅጌ             
  
20)     ጽርሐ ንግስት ቅድስት ሐና ቤ/ክ             
   
ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ፉሪ ሐና ማርያም              
   
21)  ድልበር መካነ ጎልጎታ መድኃኔዓለም ቤ/ክ      
ልዩ ስም፦ጉለሌ ድልበር       


22)    ደብረ ቢታንያ አቡነ ተክለሃይማኖት እና ቅድስት ልደታ ለማርያም              
  
ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ቆሬ 5 ቁጥርና 2 ቁጥር ማዞርያ              
 
23)   አዲስ አምባ ደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት እና ደብረ ፍስሐ  ቅዱስ ገብርኤል              
 
 ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ሳሪስ አዲስ ሰፈር              
  
24) ፉሪ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል             
 
ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ጋራ ኦዳ              
 
25)    መካኒሳ ደብረ ገነት  ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ              
 
ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ መካኒሳ               
 
26)   ለቡ ደብረ ታቦር በዓለወልድና አበ ብዙሃን አብርሃም ገዳም              
  
ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ /ክ/ከ ለቡ              
 
27)     ጎፋ መብራት ኃይል ደብረ መዊዕ ቅዱስ መርቆሬዎስ እና መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ              
  
ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ጎፋ መብራት ኃይል              
 
  28)  ደብረ ይድራስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክ              
  
ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ ቤተል              
  
29)     ቦሌ ቡልቡላ ምስካበ ቅዱሳን አባ ሳሙኤልና ቅዱስ አማኑኤል              
  
ልዩ ስም፦ቦሌ ክ/ከ ቡልቡላ              
  
30) አለም ባንክ ጀሞ ደብረ ራማ ቅዱስ ገብርኤል             
  
ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ አለም ባንክ              
  
31)  አቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤ/ክ              
  
ልዩ ስም፦አቃቂ ቃሊቲ /ክ/ከ ጋራው መድኃኔዓለም

መልካም በዓል።

ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ

በሚያዚያ ወር ዜና እረፍታቸው ከሚከበርላቸው ቅዱሳን አንዱ የግብፅ የኢትዮጵያና የኤርትራ ኦርቶዶክስ አብያተክርስቲያናት የመንበር አባት የሆነው የመጀመሪያው የእስክንድርያ ፓትሪያርክ ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ነው።


ቅዱስ ማርቆስ አባቱ አርስጦቡሎስ እናቱ ደግሞ ማርያም ይባላሉ፤ በልጅነቱም በዘመኑ ይሰጥ የነበረውን የላቲን፣ ግሪክ፣ የዕብራይጥን ቋንቋዎችን ተምሯል፤ጌታችን በኢየሩሳሌም እየተዘዋወረ ሲያስተምር ቅዱስ ማርቆስ ገና ታዳጊ ወጣት ነበር፤ ወላጆቹን እየታዘዘና እያገለገለም አድጓል፡፡ ጌታችን በምሴተ (ጸሎተ) ሐሙስ የአይሁድን ፋሲካ ለማክበር ቤት እንዲያሰናዱለት ቅዱሳን ሐዋርያትን ሲልክ ቤቱን የሚያሳያቸው ልጅ እንደሚያገኙ ነግሯቸዋል። ይህም ልጅ ቅዱስ ማርቆስ ነበር ፤ ‹‹…ወደ ከተማ ሂዱ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰውም ያገናኛችኋል፤ ተከተሉት፤ የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ መምህሩ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው ይላል በሉት…›› (ማር.፲፬፥፲፫ ) ሊቃውንት አባቶች በትርጓሜ ይህ ልጅ ቅዱስ ማርቆስ እንደሆነ ተርጉመውልናል፡፡
ቅዱስ ማርቆስ ጌታችን በተያዘበት ምሴተ ሐሙስ ተከትሎትም ነበር ‹‹… ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጎበዝ ይከተለው ነበር…..›› (ማር. ፲፬፥፶፩ ) ይህ ጎበዝ የተባለውም ቅዱስ ማርቆስ ነው፤ ቅዱስ ማርቆስ የቀድሞ ስሙ ዮሐንስ ይባል ነበር፤ጌታችን የሐዲስ ኪዳን ቁርባን ለቅዱሳን ሐዋርያት የሰጠበት ቤት እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን ለአንድ መቶው ሃያ ቤተሰብ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በሃምሳኛው ቀን ሲልክ፤ ( ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት፣ሰባ ሁለቱ አርድእት፣ ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳን አንስት) በማርቆስ እናት በማርያም ባውፍልያ ቤት በነበሩ ጊዜ ነበር፡፡ በዚህም ቤታቸው የሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ተብላለች፡፡


ጌታችን ለቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹…ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው፤ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው›› በማለት አዘዛቸው፤(ማቴ.፳፰፥፳) ቅዱሳን ሐዋርያትም ዓለምን ዞረው እንዲያስተምሩ ባዘዛቸው መሠረት ለማስተማር ሲሄዱ ቅዱስ ማርቆስ መጀመሪያ ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ከዚያም ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር አብሮ ተጉዟል፤ ከእነርሱም የማስተማር ልምድን ከወሰደ በኋላ ወንጌልን ለመስበክ ለብቻው ወደ እስክንድርያ ተጓዘ፤ በዚያን ወቅት የእስክንድርያ ከተማ ነዋሪዎች የጣዖት አምላኪዎች ነበሩ፤ ወደ ከተማው ከገባ በኋላ እንዴት አድርጎ ሕዝቡን እንደሚያስተምር ሲዘዋወር ያደረገው የጠፍር ጫማው ተበጠሰ፤ ወደ ሰፊም ሄደ፤ ጫማ ሠሪውም እየሰፋ ሳለ እጁን ወስፌ ወጋው፤ ከዚያም ‹‹ኤስታኦስ›› አለ ! በዮናናውያን ቋንቋ ‹‹ኤስታኦስ›› አንድ አምላክ ማለት ነው፤ ቅዱስ ማርቆስም ከጫማ ሰፊው ይህንን በመስማቱ ጠጋ አለና‹‹ አንድ አምላክን ታውቀዋለህ?›› አለው ሰውየውም ሲሉ እንደሚሰማ እንጂ ምን እንደሆነ እንደማያውቅ ገለጸለት፤ በዚህን ጊዜ ቅዱስ ማርቆስ የታመመ እጁን በተአምራት ፈወሰለት፡፡
ከዚያም ወንጌልን አስተማረው፤ እውነትን አሳውቆ ከጣዖት አምልኮ መለሰው፤ ሰውየውም ደስ ብሎት ወደ ቤቱ ወሰደው፤ ቤተሰቦቹንም አስተምሮ አጠመቃቸው፤ብዙዎችም ከተሳሳተ መንገድና ከጣዖት አምልኮ ተመለሱ፤ የዚህ ሰው ቤትም በእስክንድርያ የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ሆነች፤ ብዙ ሰዎችም በክርስትና እምነት አመኑ፡፡ ቅዱስ ማርቆስም ወደ ሌላ ሀገርም ለማስተማር ተጓዘ፡፡


ከብዙ ጊዜ በኋላ ያመኑት ምእመናን (ክርስቲያኖች) የትንሣኤን በዓል የሚያከብሩበት ቀን በደረሰ ጊዜ አብሯቸው እንዲያከብር ቅዱስ ማርቆስን ጠሩት እርሱም በመጣ ጊዜ ጣዖት አምላኪዎች ያዙት፤ ከዚያም ጣዖት አምላኪዎቹ ቅዱስ ማርቆስን በአሰቃቂ ሁኔታ ከሠረገላ ጋር አሥረውት መሬት ለመሬት ይጎትቱት ጀመር፤ ብዙ ካንገላቱት በኋላ ሚያዚያ ፴ (ሠላሳ) በ፷፰ (ስድሳ ስምንት) ዓ.ም በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡ አላውያኑም የቅዱስ ማርቆስን ክብርት ሥጋ ሊያቃጥሉ ሲሉ ኃይለኛ ዝናብ ዘንቦ በተናቸው፤ክርስቲያኖቹም በክብር አንሥተው በቤተ ክርስቲያን ቀበሩት፡፡ ጌታችን በትምህርቱ ‹‹…ጻድቅን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል …›› ባለን መሠረት ምእመናን በረከቱን እናገኝ ዘንድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም የቅዱስ ማርቆስን የዕረፍት መታሰቢያ በዓል ሚያዚያ ፴ (ሠላሳ) ቀን ታከብረዋለች፡፡ (ማቴ.፲፥፵፪) በረከቱ ይደርብን፤

አምላከ ቅዱስ ማርቆስ በረከቱን ያድለን አሜን!!!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!

ጌታዬ ፡ አምላኬም

  በሙታን መነሳት ከማያምኑ ሰዱቃውያን ወገን የነበረው ዲዲሞስ የተባለ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የሚታወቀው የጌታችንን ከሞት መነሳት ከአሥሩ ሐዋርያት በሰማ ጊዜ ችንካሩን ካላየና ካልነካ እንደማያምን በተናገረው በኋላ ግን ዳግመኛ እርሱ በተገኘበት በዝግ ቤት ተገልጦ ጌታችን መሻቱን ሲፈፅምለት እጁ ተኮማትሮ ፣ ማመንን አምኖ ” ጌታዬ ፡ አምላኬም ” ብሎ በመመስከሩ ነው።

    በሮማና በፐርሺያ መካከል ይኖር የነበረ የዑር (ኤዴሳ) አብጋር ዑካማ (አብጋር-ጃንሆይ እንደማለት ነው) የተባለ ገዢ  በጠና ታሞ ነበርና የጌታችንን የማዳን ዝና ከግሪክ ነጋድያን በመስማቱ እርሱም ፈውስን ከእጆቹ ያገኝ ዘንድ ለጌታችን በሐዋርያው እንድርያስ አገናኝነት ጌታችንን ባገኙት ግሪኮች ለላከለት መልእክት ምላሽ ከትንሣኤው በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱን ይልክለት ዘንድ ቃል ገብቶለት ነበርና ከዕርገቱ በኋላ ቅዱስ ቶማስን ወደ ዑር ልኮታል።  ቅዱስ ቶማስ ወደ ሕንድ ተጉዞ ፣ ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ የሆነውን ታዴዎስ በላከው መሰረት ይህን ንጉሥ ፈውሶ ሀገሩን ባርኮ ፣ ብዙ ሰዎች ተጠምቀው ክርስቲያኖች ለመሆን በቅተዋል፡ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ተተክለውም በምሥራቅ እስያ የመጀመሪያይቱ የክርስቲያኖች ከተማ መሆንዋ በታሪክ ተጽፏል።

በሀገረ ሕንድ በታክሻሲላ ከተማ የነበረ ንጉሥ ጎንዶፓረስ በኢየሩሳሌም ስለነበረው የሰሎሞን ቤተ መንግሥት ዝና ይሰማ ነበረና የታወቁ ግንበኞችን እንዲያመጡለት ነጋድያንን ባዘዘው መሰረት ቅዱስ ቶማስን ወደ ሕንድ ሲጓዝ በመንገድ ያገኘው አንድ ነጋዴ በኢየሩሳሌም በግንበኝነት ሙያ ይተዳደር እንደነበር ነግሮት ነበርና ከንጉሡ ጋር ለቤተ መንግሥቱ ስራ እንዲዋዋል ያደርጋል። ንጉሡም ባሳየው ሰፊ ሜዳና ጫካ ምኞቱ ይፈጸምለት ዘንድ በየጊዜው የሚሆኑ ብርና ወርቅ ፣ ለሰራተኛ መቅጠሪያ እና እብነበረድ እንዲሁም ብረትና እንጨት መግዣ የሚሆን ገንዘብም ይልክለት ነበር። ቅዱስ ቶማስ ግን ወደ ድኾች መንደር በመዝለቅ ይመጸውተው የመንግሥተ ሰማያትንም ወንጌል ማስተማሩን ቀጠለበት።

የኋላ የኋላ ይህን የጓጓለትን ቤተ መንግሥት መጠናቀቅ ለማየት በሄደ ጊዜ ምንም ባለማግኘቱ የተበሳጨው ንጉሡ አስጠርቶ በጠየቀው ጊዜ ቅዱስ ቶማስ ” በምድር ላይ የድንጋይ ቤተ መንግሥትን ላያዩ ይችላሉ ፡ በሰማይ ላይ ግን ሰርቼልዎታለሁ” በማለት መልሷል። በዚህም መልሱ ንጉሡ ተበሳጭቶ ወደ ወኅኒ እንዲወርድና እንዲሰቃይ አዘዘ። ያን ዕለት ሌሊት ልዑል ጋድ የተባለ የንጉሡ ወንድም ታሞ ያርፋል ፡ ነፍሱንም መላእክት ማረፊያዋን ባስመረጧት ጊዜ የሚያምረውን ቤተ መንግሥት መረጠች ፡ ከመላእክቱም አንዱ “ይህ ያንቺ አይደለም ፡ ቶማስ ለንጉሥ ጎንዶፓረስ የሰራለት ሰማያዊ ቤተ መንግሥት ነው” አላት። በዚህ ቅስፈትም የልዑሉ ነፍስ ከሥጋው ተዋሐደች ። ያየውንም ሁሉ ሊቀብሩት ለተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉና ለንጉሡ መሰከረ። ንጉሡም በቅዱስ ቶማስ ላይ ስላደረሰው ግፍ አዝኖና ተጸጽቶ ከወኅኒ አወጣው ፣ ከነቤተሰቡም ተጠመቀ ። በሀገሩ የነበሩ ባለጸጋጎችም ይህንን ለድኾች በመመጽወት የሰማይ ቤተ መንግሥት የመስራት ምሳሌውን ተከተሉ።
  
   ቅዱስ ቶማስ ከሕንድ ማላባር እስከ ቻይና ሰብኳል ፡ በኋላም በሚላፒር አምላክያነ ጣዖት ቆዳውን ገፍፈው ስልቻ በመስራት በሰውነቱ ጨው ነስንሰው ባደረሱበት ግፍና መከራ ሰማዕትነትን ተቀብሏል ፡ አጽሙም በኤዴሳ በክብር አርፏል። መታሰቢያው በቤተክርስቲያናችን ግንቦት 26  ይደረጋል።

ምንጭ:- ኦርቶዶክሳዊ ወጣት

ማዕዶት- መሻገር

ማዕዶት “ዐደወ” ተሻገረ ከሚል የግዕዝ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጓሜውም መሻገር ነው። እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ትውፊት ከትንሳኤ ቀጥሎ ለሚገኘው ሰኞ ስያሜ የሆነው ማዕዶት የበዙ ምስጢራትን የያዘ ነው።

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና መከራ እኛ የሰው ልጆች ከሲኦል ወደ ገነት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻግረናልና ማዕዶትን እናከብራለን።

በዚህ ቀን በዋነኝነትም ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ከስጋው በሥልጣኑ ለይቶ ክብርት ነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዳ በሲኦል የምስራቹን ቃል እርሱም የተስፋ አበው ፍፃሜን መስበኩና ሙታንን ከሲኦል ማውጣቱ የሚታሰብበት እለት ነው።

በእርግጥ ይህ ሁነት የተከናወነው እጅግ የበዛ ምስጢራትና ተአምራት በተከናወነበት በእለተ አርብ ቢሆንም መሻገር ትፍስሕት ነውና ቤተክርስቲያን ከትንሳኤው በኋላ ባለው የመጀመሪያ ቀን በሲኦል የነበረው የእዳ ደብዳቤ መቀደዱን ታከብራለች።

ሊቀ ሐዋርያት ጴጥሮስ በሲኦል ቅድስት ነፍሱ ያደረገችውን ስብከት እንዲህ ይነግረናል:- ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥ በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው። 1ኛ ጴጥ 3:18-19

የቤተክርስቲያን መምህር የሆነው አፈ በረከት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የክርስቶስን በሲኦል መውረድና ነፍሳትን ማሻገር ከጨጓራ አለመስማማት ጋር (gastronomic analogy) አመሳስሎ እንዲህ ይለዋል:-

‹‹የክርስቶስን ሰውነት በመቀበሉ ሞት ታላቅ ስኅተት ሠራ፡፡ ይህ ሰውነት በእርሱ የገዥነት ሥልጣን ሥር ያለ ተራ ሰውነት ፣ ኃጢአተኛ የሆነና የሚሞት ሰውነት መስሎት ነበር፡፡ ከሰውነታቸው ጋር የማይስማማ ምግብን የበሉ ሰዎች ሲያስመልሳቸው የሚያወጡት አልስማማ ያላቸውን ምግብ ብቻ ሳይሆን የበሉትን ነገር ሁሉ ነው፡፡ በሞትም ላይ የሆነው ይኼው ነው፡፡ ሞት ፍጹም ንጹሕና የማይሞት የሆነውን የክርስቶስን ሥጋ ዋጠ ፤ የማይሞተው ሕያዉ ክርስቶስ ለአልጠግብ ባዩ ሞትና ሲኦል የሚመር እና የማይስማማ ምግብ ሆነበት፡፡ ሊስማማው ስላልቻለም ተፋው ፤ ከክርስቶስ ሥጋ ጋርም ሲኦል ሆድ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ ውጦ የያዘውን ሙት ሁሉ አብሮ ተፋ፡፡ ለሞት የሚስማማው ብቸኛ ምግብ ኃጢአት ብቻ ነው፡፡ ኃጢአት የሌለበት የጌታ ሰውነት ለሲኦል የማይስማማ ምግብ ነው፡፡


ሞት ሊላመጥ የማይችልን ትልቅ ድንጋይ ዋጠ ፤ ይህ ድንጋይ የማይላመጥ ብቻ ሳይሆን በሆድ ውስጥ ቆይቶ የሚያፈራርስና የሚሰባብር ነው፡፡ ስለዚህ ሞት ‹የማዕዘን ድንጋይ› የሆነውን የክርስቶስን ፍጹም ቅዱስ የሆነ ሥጋ በዋጠ ጊዜ በታላቅ ሥቃይና ድካም ውስጥ ሆኖ ጥንካሬዎቹን ሁሉ አጣ፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጴጥሮስ ‹ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለም› ያለው፡፡ (ሐዋ.፪፥፳፬) የትኛዋም ሴት ልጅ ለመውለድ ምጥን ባማጠች ጊዜ ሞት የክርስቶስን ሥጋ ይዞ የተጨነቀው ያህል ተጨንቃ አታውቅም” በእርግጥም መብላት የሌለበትን መብል የበላው አዳምን ካጋጠመው ደዌ ይፈውስ ዘንድ እግዚአብሔር ወልድ በሞት ተበላ። ዕፀ በለስ ለአዳም ባህርይ ባለመስማማት ሁሉንም እንዳሳጣችው ክርስቶስን የዋጠ ሲኦልም ለባህርዩ የሚስማማ አልነበረምና ሁሉንም አስተፋው።

ሌላኛው የቤተክርስቲያን ኮከብና ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ይሄንን በክርስቶስ ከተደረገ ታላቅ ምሥጢር በኋላ ሞት ያጣውን ክብርና ነፃነት በሰውኛ ዘይቤ እንዲህ ያናግረዋል:-

‹‹ሞት እንዲህ አለ ፡- ‹‹ይህ ማን ነው? የማንስ ልጅ ነው? እኔን ድል የነሣኝ ይህ [ኢየሱስ የተባለ] ሰው ከየትኛው ቤተሰብ የተገኘ ይሆን? የትውልዶች ሁሉ የዘር ሐረጋቸው የተዘረዘረበት መጽሐፍ በእጄ ላይ አለ፡፡ ከአዳም ጀምሮ የነበሩት ሰዎች ስም አንድ በአንድ ማንበብ ጀመርሁ፡፡ ከእኔ ያመለጠ [ያልሞተ] አንድም ሰው የለም፡፡ ነገድ በነገድ ሁሉም በክንዶቼ ላይ ተጽፈዋል…

…. በእርግጥ አልዋሽም ፤ የሁለት ሰዎች ስም ብቻ ከእኔ ዘንድ የለም ፤ ሄኖክና ኤልያስ ወደ እኔ አልመጡም … በመላው ምድር ሁሉ ዞሬ ፈለግኋቸው ፣ ዮናስ እስከ ወረደበት የዓሣ አንበሪው ሆድ ድረስ ወርጄ ፈለግኋቸው፡፡ በገነት ውስጥ ተሸሽገው ከሆነ እንዳልፈልጋቸው የሚያስፈራ ኪሩብ ጠባቂ ሆኖ ቆሟል፡፡ ያዕቆብ መሰላልን ተመልክቶ ነበር ፤ ምልባት ወደ ሰማይ የወጡት በዚያ መሰላል ይሆንን?››

በቅዱሱ ብዕር ሞት ስለሆነው ነገር እንዲህ እያለ መናገሩን ይቀጥላል።

“ሞት እንዲህ አለ ፡- ወደ ሙሴ ዘመን ብመለስ ሳይሻለኝ ይሆን? ሙሴ እኮ በዓልን ደግሶልኝ ነበር፡፡ በግብፅ ፋሲካ የታረደው በግም ከእያንዳንዱ ግብፃዊ ቤት የበኩር ልጅን ሠጥቶኝ ነበር፡፡ በሙት ላይ ሙት በሲኦል ደጃፍ ተከምረውልኝ ነበር፡፡ ይኼኛው የፋሲካ በግ [ክርስቶስ] ግን ሲኦልን በዘበዘው ፣ ሙታንንም ከእጄ ነጥቆአቸው ወጣ፡፡ ሙሴ ያሳረደው የቀደመው በግ መቃብሮችን ሞላልኝ ፤ ይኼኛው በግ ክርስቶስ ግን ሞልተው የነበሩትን መቃብሮች ባዶ አደረገብኝ››
​‹‹የኢየሱስ ሞት ለእኔ ሥቃይ ነው ፤ ከሞቱ ይልቅ ለእኔ በሕይወት እንዲቆይ በተውኩትና ወደ እርሱ ባልቀረብኩ ይሻለኝ ነበር፡፡ በሌሎች ሰዎች ሞት ደስ ይለኝ ነበር ፤ የእርሱን ሞት ግን ጠላሁት፡፡ በሕይወት ሳለ የሞቱ ሰዎችን አስነሥቶ ነበርና እርሱም ከሞት እንደሚነሣና ወደ ሕይወት እንደሚመጣ ገምቼ ነበር፡፡ እርሱ ግን በሞቱ ሙታንን ወደ ሕይወት ወሰዳቸው ፤ ይዤ ላስቀራቸው ስሞክርም በሲኦል ደጃፍ አሽቀንጥረው ጥለውኝ ሔዱ … ገና አሁን እኔም ስለ ወዳጆቻቸው ሞት የሚያለቅሱ ሰዎችን የኀዘናቸውን ጣዕም ቀመስሁት … ከሰዎች ላይ የሚወዷቸውን በመቀማት የማመጣባቸው ሥቃይ በተራው በእኔም ላይ ወደቀ”። ሶሪያዊው ኤፍሬም እንደተናገረው የክርስቶስ ሞት ምትን ያስደነገጠና ያሸበረ ነበር። አባቱ ቅዱስ ዳዊት ነፍሴን በሲኦል አትተዋትም እንዳለው ዳግመኛም ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ስጦታንም ለሰዎች ሰጠ እንዳለው (መዝ 16:10፣ መዝ 68:18) በሲኦል ነብሳችን እንዳይቀር የቀኝ ገዢያችንን ሞት ምርኮ ማረከ፣ ለኛም ክቡር የሆነውን ነፃነት ስጦታ አድርጎ ሰጠን። እንደ ሙሴ ከባህረ ኤርትራ ሳይሆን ከባህረ እሳት ያሻገረን እግዚአብሔር ይመስገን።

ክርስቶስ ተንስአ እም ሙታን – ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሳ።