በሰሙነ ሕማማት የምንሰማቸው እንግዳ ቃላትና ትርጉማቸው

ሕማማት ከአለም አቀፋዊ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትውፊቶች መሐል አንዱ ነው። አብዛኞቹ የምሥራቅም ሆነ የኦርየንታል አብያተክርስቲያናት ከኢትዮጵያና ከግብፅ አብያተክርስቲያናት የዘመን አቆጣጠር ጋር የሚመሳሰለውን የጁልያን የዘመን አቆጣጠር ስለሚከተሉ ሕማማቱን በተመሳሳይ ቀን በተቀራራቢ ሥርዓት ያከብሩታል። የሕማማት ሰሙን ስርዓት ዓለማቀፋዊነት ማሳያዎች መካከል በሰሙነ ህማማት ወቅት በምልጃ የሚጠሩ ዓለምአቀፋዊ ቅዱሳንና ወደ ግዕዝም ሆነ አማርኛ ያልተተረጎሙ ቃላት መገኘታቸው ነው።


እኒህ እንግዳ ቃላት የሦስት ጥንታዊ ቋንቋዎች ማለትም ቅብጥ፣ ግሪክና ዕብራይስጥ ቃላት ሲሆኑ በግብረ ሕማማት መጽሐፍ ትዕዛዝ በሚባለው ክፍል ውስጥ የሚገኙና በስግደት ወቅት ካህናትና ምዕመናን በምልልስና በቅብብል የሚሏቸው ውብ ቃላት ናቸው።

1. በአምስቱም ቀናት የምንጠቀምባቸው ቃላት

ከቅብጥ (ከግብፅ ቤተክርስቲያን ጥንታዊ ቋንቋ) የመጡ


ናይናን፡-
የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «መሐረነ ፣ማረን» ማለት ነው፡፡ ቃሉ ከኢየሱስ፣ ክርስቶስ፣ አማኑኤል፣ እብኖዲ፣ ማስያስ፣ታኦስ፣ ትስቡጣ ተከትሎ የሚገባ ቃል ነው

እብኖዲ፡-
የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «አምላክ» ማለት ነው፡፡ «እብኖዲናይናን» ሲልም «አምላክ ሆይ ማረን» ማለቱ ነው፡፡

ከጽርዕ (ከጥንታዊ የግሪክ ቋንቋ) የመጡ

ኪርያላይሶን/ኪርዬኤሌይሶን:- «ኪርዬ» ማለት «እግዚነ»ማለት ሲሆን«ኤሌይሶን» ማለት ደግሞ «እግዚኦ-ማረን» ማለት ነው፡፡ ትርጉሙም «አቤቱ ማረን» ማለት ነው፡፡ «ኪርያላይሶን» የምንለው በተለምዶ ነው፡፡ ኪርያ ማለት እግዝእትነ/እመቤታችን ማለት ስለሆነ ሲጠራ «ኪርዬኤሌይሶን» መባል አለበት፡፡


ታኦስ፡-  «ጌታ ፣አምላክ» ማለት ነው፡፡ «ታኦስ ናይናን» ማለትም «ጌታ ሆይ ማረን» ማለት ነው


ትስቡጣ/ዴስፓታ:- ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም ደግ ገዥ ማለት ነው፡

ከዕብራይስጥ (ከአይሁድ ጥንታዊ ቋንቋ) የመጡ


ማስያስ፡-  «መሲሕ» ማለት ነው፡፡ «ማስያስ ናይናን» ሲልም «መሲሕ ሆይ ማረን» ማለት ነው፡፡

2. በዕለተ አርብ ብቻ የምንሰማቸው ቃላት

በዕለተ አርብ በስድስት ሰዓት ከወንጌልና የድህረ ወንጌል ንባባት በኋላ በቤተክርስቲያን ያሉ ሁሉ ቁጭ ብለው ሦስት ካህናት ጥቁር ለብሰው በዕዝል ዜማ የሚያዜሙት ዜማ አለ።  ዐርፍተ ነገሮቹ የቅብጥ ሲሆን ትርጉማቸውም:-

አምነስቲ ቲ ሙኪርያቱ አንቲ ፋሲልያሱ
  ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ – አቤቱ በመንግሥትህ አስበኝ ማለት ነው፡፡

አምንስቲ ቲ ሙአግያ አንቲ ፋሲልያሱ
ተዘከረነ ኦ ቅዱስ በውስተ መንግሥትከ – አቤቱ ቅዱሱ ሆይ በመንግስትህ አስበኝ፡ ማለት ነው።

አምንስቲ ቲ ሙዳሱጣ አንቲ ፋሲልያሱ
ተዘከረነ እግዚአ ኩሉ በውስተ መንግሥትከ- የሁሉ የበላይ የሆንክ ወይ በመንግሥትህ አስበን ማለት ነው፡

ድንግል ማርያም ስለ ልጇ ስላለቀሰችው ለቅሶ


ወዳጆቼ ሆይ የአባቶቼ አለቃ የያዕቆብ ለቅሶ ዛሬ ታደሰ አለ። በድንግልና ጸንሳ በድንግልና ለወለደችው ተወዳጅ ልጇ ድንግል ማርያም ለምን አታለቅስም? መከራ ስለተቀበለችበት ድንግል ማርያም ለምን አታለቅስም? የድንግልና ጡቷን ላጠባችው ድንግል ማርያም ለምን አታለቅስም? በቤተልሔም በበረት ለወለደችው ልጇ ድንግል ማርያም ለምን አታለቅስም? በማሕጸኗ ዘጠኝ ወር ለተሸከመችው ተወዳጅ ልጇ ድንግል ማርያም ለምን አታለቅስም? ከሃገር ሃገር አዝላው ለተሰደደችበት ልጇ ድንግል ማርያም ስለምን አታለቅስ? ከቶ መቃብራቸውን ስላላየችው ልጆቿ ራሄል የምታለቅስ ከሆነ በአንድ ልጇ መቃብር ደጃፍ ላይ ድንግል ማርያም ለምን አታለቅስ?


የባለ መልካም ስም ሽማግሌ የያዕቆብ ልቅሶ በብላቴናይቱ ድንግል ዛሬ ታደሰ። ወንድሞቹ ባሰሩት ጊዜ ያዕቆብ ወደ ዮሴፍ አልተመለከተም። ድንግል ግን ልጇ በእንጨት መስቀል ላይ ተቸንክሮ አየችው። ዮሴፍ በሰዲ ጉድጓድ ውስጥ ሳለ ያዕቆብ በላዩ እንዲያለቅስ ወደ ዮሴፍ አላየም። ድንግል ግን በአይሁድ ጉባኤ መካከል ተሰቅሎ ልጇን አየችው። ዮሴፍን ወንድሞቹ ልብሱን ሲያራቁቱት ያዕቆብ አላየም። ድንግል ግን በጎ ምክር በሌላቸው በአይሁድ መካከል ልብሱን ተገፎ ራቁቱን ሆኖ አየችው። ወንድሞቹ ዮሴፍን በሃያ ብር ሲሸጡት ያዕቆብ አላየም። ድንግል ግን ይሁዳ ልጇን በሰላሳ ብር ሲሸጠው አየች።አራዊት ባልቀደዱት ልብስና በሌላ ደም ላይ ያዕቆብ አለቀሰ። አምላካዊ ደም ግን ድንግል ማርያም ስለእርሱ በላዩ የምታለቅስበት በቀራንዮ አለት ላይ የፈሰሰው ነው። ድንግል ግን ዛሬ ያየችው ለልጇ ያለበሱትን ሌላ ልብስ ነበር የራሱን ልብስ ግን እርስ፡በእርሳቸው ተካፈሉት። የዮሴፍ ወንድሞች ወንድማቸው ዮሴፍን በሸሩት ጊዜ አለቀሱ ተጸጸቱ። የእስራኤል ልጆች ግን ጌታቸውን በሰቀሉት ጊዜ አላለቀሱም አልተጸጸቱም። የያዕቆብ ልጆች ወንድማቸው በነገሠ ጊዜ ተደሰቱ። አይሁድ ግን ጌታቸው ከሙታን ተለይቶ በተነሳ ጊዜ ደስ አላላቸውም።


ድንግል ሆይ በእውነት በልጅሽ መቃብር ላይ ልቅሶሽ ጣዕም ያለው አሳዛኝ ነበር።ማርያም ሆይ ለምን ተቀምጠሻል? ምን ታደርጊያለሽ ብለው የልጅሽን መሰቀሉን በነገሩሽ ጊዜ በመላእክት መካከል ቃልሽ ያማረ ነበር። እነሆ ልጅሽን በመኮንኑ ፊት አቁመውታል። የአይሑድ ሊቃነ ካህናትም ያሰቃዩታል። ያቃልሉታል። ማርያም ሆይ ምን ታደርጊያለሽ? እነሆ ልጅሽን በፍርድ አደባባይ መካከል ልብሱን ገፍፈው እያራቆቱት ነው።የኢያቄም ልጅ ማርያም ሆይ ለምን ተቀምጠሻል ምንስ ታደርጊያለሽ?እነሆ በኢየሩሳሌም ሜዳ የሚሰቀልበትን ግንድ ብቻውን ተሸክሟል። አንድስ እንኳን ወደ እርሱ የሚቀርብ የለም። የሃና ርግብ ሆይ ለምን ተቀመጥሽ? የምትሰሪውስ ምንድን ነው? እነሆ ልጅሽን ሰቅለውት በቀራንዮ ቦታ ቆሟል።የዳዊት ዘር ሆይ ልጅሽን በመስቀል ላይ ለምን ከፍ ከፍ አደረጉት?እመቤቴ ድንግል ሆይ በዮሐንስ ቤት ዛሬ ልቅሶሽ በእውነት ጣዕም ያለው ነበረ። እንዲህ ስትዪ ወዮ ለዚህ መራራ ወሬ ነጋሪ ለኢዮብና እስራኤል ለተባለ ያእቆብ ካረዷቸው መርዶ የመረረ ነው።ዛሬ ወደ እኔ ለሚመጣ ለዚህ ለክፉ ወሬ ወዮ ልጄ ሆይ ሃገሩን ባቃጠሉት ጊዜ ለሎጥ ካረዱት መርዶ ያስጨንቃል። በእኔ ላይ ለደረስው ለዚህ አስጨናቂ ነገር ወዮ ። ልጄ ሆይ ስለ ኃያላን እስራኤል ሞት ለዳዊት ካረዱት መርዶ ይበልጣል። በዚህ በክፉ ወሬ ወደ እኔ በመጣው ለዚህ ወሬ ነጋሪ ወዮ። ልጄ ሆይ እነሆ ስታረጋጋኝ ሠላሳ ዓመት ይሆናል።ልገስጽሕም አልተቻለኝም ዛሬ ወደእኔ ወሬህ እስከመጣ ድረስ ወጥተህ እስክትገባ አንዲትስ ሰዓት እንኳን አላመንኩም ።


ልጄ ሆይ ለሐዘኔ ሁሉ ምስክሬ ሰሎሜ ናት እኔ ዳኛውን አየው ዘንድ ከቤቴ አልወጣም፡ በፈራጁም ፊት አልቆምም ሌባውን ሲቆርጡት ሽፍታውንም ይገድሉት ዘንድ ሲፈርዱበት አላየሁም። ከቶ ቀራንዮን አላየሁትም። የጎልጎታን ቦታ አላውቀውም ሁልጊዜ በሚጣሉበት ቦታ አልቆምኩም። ልጄ ሆይ ክፉ የሆነ ፍርድ አላየሁም። በፍርድ አደባባይም ከቶ ለዘለዓለም አልቆምኩም ልጄ ሆይ ያደረግኩብህን ግፍ አላውቅም።

እኔም በዮሐንስ ቤት ነበርኩ። ወዳጄ ሆይ በሊቀ ካህናቱ በሃና ጊቢ የተቀበልከው ግፍ ወሬው መራራ ነው።ልጄ ወዳጄ ሆይ ዛሬ ከእኔ ላይ ነጻነቴን አስወገድኩ። ስለልደትህ በናዝሬት መልካም የምስራች ነገሩኝ ፡ ዛሬ ግን በኢየሩሳሌም ይህችን ክፉ መርዶ አረዱኝ ። በዮሴፍ ቤት መልካም ዜና ደረሰኝ፡ በዮሐንስ ቤት ግን የሞት ዜና መጣብኝ። ልጄ ወዳጄ ግን እኔ በልቤ ደስ እያለኝ ተቀምጬ ነበር ። በየዕለቱ ፋሲካ ደርሷል። በዓሉን እናከብር ዘንድ ወደ ቤታችን እንመለሳለን እያልኩ ነበር ። የዚህ አይነቱ አሽካም ደረሰኝ ። ልጄ ወዳጄ ሆይ በእንባና በሐዘን በዓሌ ወደ ለቅሶ ተመለስ። ፋሲካዬም ወደ ልብ ሐዘን።

ድንግልንም ልጇን ስላላየችው ፍጹም ሐዘንና ለቅሶ አገኛት። በዮሐንስ ቤትም ሳለች እንደገና ወደ ለቅሶዋ ተመልሳ ዮሐንስ ሆይ ወደ ቀራንዮ ትመራኝ ዘንድ እማጸንሃለሁ አለችው። ዮሐንስ ሆይ ከእኔ ጋር ወደ ጎልጎታ ትትሄድ እማጽንሐለሁ።ሌባውን ሲሰቅሉት ወንበዴን ቸብቸቦውን ሲቆርጡ አላየሁም እንደ ወንበዴ ልጄን ወዳጄን በውስጡ የሰቀሉበትን ቦታ አይ ዘንድ ሃገሬን ክብሬን ትቼ በእግሬ እሄዳለሁ።

ልጄ ሆይ ከወንድሞችህ አንድስ እንኳን አብሮ የቆመ የለም። ወይም ስላንተ አንድም ቃል የሚናገር የለም። ልጄ ሆይ በልጇ ላይ የእናት ሐዘን ሌላ ነው። ወዳጅም ስለ ወዳጁ የሚያዝነው ሌላ ነው። እናትም በተወዳጅ ልጇ ላይ ከልብ የምታዝነው ሐዘን ልዩ ነው። ወዳጅም በወዳጁ ልዩ ሐዘን አዝኖ ያለቅሳል ሐዘኔም በኢየሩሳሌም ካሉ ሰዎች ሁሉ ይጸናል።
ልጄ ወዳጄ ሆይ ልቅሶዬ በእኔ ዘንድ ከተሰበሰቡ ሰዎች ሁሉ ልቅሶ ይበልጣል። ዮሐንስም ከልቅሶና ከሐዘን መጽናናትን እንደማትችል፡ እርሱም ሊያረጋጋት እንደማይችል ባየ ጊዜ እርሷም ካላየሁት መጽናናት አልችልም እያለች ስለሆነ ዮሐንስም እኔ ካንቺ ጋር ወደ ቀራንዮ እሔዳለሁ ታዪው ዘንድ ተነሺ እንሒድ አላት። ድንግልም ከዮሐንስ ቤት ወጥታ በኢየሩሳሌም ሜዳዎች ውስጥ በእግሯ ተጓዘች። ድንግልንም ፈጥና ስትራመድ የሚያዩዋት ሰዎች እንዲህ የምታለቅስ ይህች ማናት አሉ። እርስ በእርሳቸውም ይነጋገሩ ነበር። ሌሎችም ከገበያ የምትሻውን ስትገዛ ከቶ ይህችን አላየናትም ይሉ ነበር። ሌሎችም እርስ በእርሳቸው ይህች እንግዳ ናት በሃገር ውስጥ ያለማስተዋል ትሄዳለችና ይሉ ነበር። የጌታ ኢየሱስ ደቀመዝሙር እንደሆነ ዮሐንስን የሚያውቁት እንጃ ይህችስ እናቱ ትሆናለች ። በመስቀል ተሰቅሎ ታየው ዘንድ ትሮጣለች ይሉ ነበር፡ ሌሎችም ይህች የዮሴፍ ሚስት ትሆናለች ስለልጇ ወሬ ነግረዋት ይሆናል ይሉ ነበር። ሌሎችም መልኳ ደም ግባቷ እንዴት ያምራል እዩ ይሉ ነበር።ሌሎችም በዚህ ሃገር ከቶ እንደዚህች አላየንም መልኳ የልጇን መልክ ይሉ ነበር። በገበያ ውስጥ ያሉ ሰዎች ስለእርሷ ይነጋገሩ ነበር። ነገሩም በገበያ ሁሉ ተሰማ። ሰሎሜም በኋላዋ ትከተላት ነበር፡ ሌሎችም ሴቶች ራሳቸውን ተከናንበው ይከተሏት ነበር፡ በልብ ከማዘንም ምንም ወደቀኝም ወደግራ መለስ ቀለስ አትልም ነበርና።

ልመናዋ በረከቷ በሀገራችን በኢትዮጵያ በሕዝበ ክርስቲያኑም ላይ ለዘለዓለሙ አድሮ ይኑር። አሜን።

ሥርዓተ ሰሙነ ሕማማት

‹‹ወአንትሙሰ ተዐቀቡ፤ ወግበሩ ተዝከረ ሕማማቲሁ፤ እናንተስ ተጠበቁ፤ የሕማሙን መታሰቢያ አድርጉ››፤/ትእዛዝ ፴፩/

ሰሙነ ሕማማት የሚባለው ከዐቢይ ጾም መጨረሻ ከሆሣዕና ማግስት ጀምሮ ባሉት ቀናት ውስጥ ያለው ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ የጌታችን የምሥጢረ ሕማማቱን ነገር መንፈስ ቅዱስ ሲገልጽለት ‹‹ውእቱ ነሥአ ደዌነ ወጾረ ሕማመነ፤ እርሱ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማታችንንም ተሸከመ››ማቴ. ፰፥፲፯/ኢሳ ፶፫፥፬/ ሲል ተናገረ፤ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ስለኛ ድኅነት በፍቃዱ ሕማማተ መስቀልን በትዕግስት በመሸከም መከራ መስቀሉ ስለተፈጸመበት፤ እኛም መከራ መስቀሉን የምናስብበት በመሆኑ ሰሙነ ሕማማት ተባለ፤ ኢሳ. ፶፫፥፬፡፡

ከ፻፹፰-፪፻፴ ዓ.ም የነበረው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ድሜጥሮስ እግዚአብሔር አምላክ በገለጠለት የጊዜ ቀመር (ባሕረ ሐሳብ) ሰሙነ ሕማማት ከዐቢይ ጾም ቀጥሎ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በቀመረ ድሜጥሮስ ዓመታትን በንዑስ፤ በማዕከላዊና በዐቢይ ቀመር እየቀመረች አጽዋማት የሚገቡበትንና በዓላት የሚውሉበትን ጊዜ ለምእመናን ታሳውቃለች፡፡ ታዲያ ሰሙነ ሕማማትን ጌታችን ለሰው ዘር በሙሉ ያደረገው ትድግናን ቅዱሳን መጻሕፍት በየበኩላቸው ቢዘረዝሩትም ቸርነቱ፤ ርህራሄውና በጠቅላላው በአምላካዊ ጥበቡ የሰራቸው ዕፁብ ድንቅ የሆኑ ሥራዎች ጸሐፊ፣ አንባቢና ሰሚ ሊደርስባቸውና ዝርዝራቸውን ሊከተላቸው ሲፈልግ፤ ገና በሀሳቡ ውጥን ላይ ድካም እንዲሰማውና ፍጡርነቱ ፈጣሪን እንዳይመረምር ያስገድደዋል፡፡

መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር በቃሉ ብቻ ዳን በማለት ሊያድነው ሲቻለው የሰውን ባሕርይ ባሕርዩ አድርጎ በፈቃዱ ሰው የሆነበትን፤ ሰውም ከሆነ በኋላ የተቀበላቸው ልዩ ልዩ መከራ የተቀበለበት ሳምንት ነው፡፡ ሰሙነ ሕማማትን የምናከብረው አባቶች ሐዋርያት የጌታን ጾም ለብቻው እንድናስበው እንዳደረጉን ሁሉ የጌታ ሕማማትም እንዲሁ በተለየ ለብቻው እንድናስበው የሰሩልን ሥርዓት ነው፡፡ ታዲያ ይህን ሳምንት ሊቃወንተ ቤተ ክርስቲያን ዓመተ ፍዳ፤ ዓመተ ኩነኔ (፶፻፭፻ ዘመን) እና የጌታችን ሕማም መከራ እንግልት የሚታሰቡበት ነው ብለው ያስቡታል፡፡ ስለዚህም እነዚህን ሁለት ነገሮች ምክንያት በማድረግ በሰሙነ ሕማማት የሚተገበሩ ሥርዓቶች አሉ፤ እነርሱም፡-

ጥቁር ልብስ መልበስ

በሰሙነ ሕማማት ወቅት በተለይ በዕለተ ዐርብ ካህናቱ ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፤ የኃዘንና የመከራ መገለጫ በመሆኑ በዚህ ወቅትም የጌታን ኃዘን መከራ ለማሰብና ለማስታወስ በማሰብ ነው፡፡ ጥቁር ልብስ ባይገኝ ደግሞ የተገኘውን ልብስ ገልብጠው ይለብሱታል፡፡

በጸሎተ ሐሙስ ቃጭሉ ተቀይሮ ጸናጽል ይሆናል

በጸሎተ ሐሙስ በቅዳሴው ወቅት ቃጭሉ ተለውጦ ጸናጽል ይሆናል፤ ምክንያቱም በዘመነ ኦሪት የነበሩ አበው ጸሎታቸው ፍጽም ሥርዓት እንዳላሰጣቸው ለማጠይቅ ነው፡፡ ከቃጭል የጸናጽሉ ድምጽ ከርቀት እንደማይሰማ ሁሉ የአበው ጩኸት አናሳ መሆኑን ለማጠየቅ፤ የይሁዳን ግብር ለመግለጥና ይሁዳ ጌታን ለማስያዝ በድብቅ ያደባ እንደነበር ለማስታወስ ነው፡፡

እርስ በእርሳችን አንሳሳምም፤ መስቀል አንሳለምም

እርስ በእርሳችን አለመሳሳማችን ይሁዳ በመሳም አሳልፎ መስጠቱን ለማሰብና ለማስረዳት ሲሆን መስቀልን ያለመሳለማችን ምክንያቱ ደግሞ፤ መስቀል በዘመነ ኦሪት የኃጥአን መቅጫ እንጂ የሰላም ምልክት እንዳልነበረ ለማጠየቅ ነው፡፡ መጻሕፍትም በመስቀሉ ሰላምን አደረገ እንዲሉ መስቀል አዳኝ የሆነ ጌታ ከተሰቀለ በኋላ መሆኑን እንድናስብ ነው፡፡

አብዝተን መጾም አለብን

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ወቅት አብዝተን እንድንጾምና እንድንጸልይ ያዙናል፤ ለምሳሌ በሰሙነ ሕማማት የሚችል በሁለት ቀን ውኃና ጨው ያለበት ምግብ እየተመገበ እንዲጾም ሲያዙን ያልቻለ ግን ፲፫ ሰዓት እየጾመ እየጸለየ ውኃንና ጨው የበዛበት ምግብ እንዲመገብ አዘዋል፡፡

ለሙታን ፍትሐት አይደረግም

በሰሙነ ሕማማት ወቅት ለሞቱ ሰዎች ፍትሐት አይደረግላቸውም፤ ዓመተ ፍዳና ዓመተ ኩነኔን የምናስብበት ወቅት በመሆኑ በዚህ ዘመን ደግሞ የነበሩ ሰዎች ፍትሐት እንደማይደረግላቸው ለማጠየቅ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን ተስፋ ላለውና ለአማኝ እንጂ ለማያምን ትንሣኤ ዘለክብር፤ ለማይነሣ ቢሆን ፍትሐት አይደረግለትም፡፡

በወይራ ቅጠል ጥብጠባ ይደረጋል

በዕለተ ዐርብ ሥርዓቱን ከፈጸምን በኋላ ወደ ካህናት አባቶቻችን እየሔድን በወይራ ዝንጣፊ ጥብጠባ ተደርጎልን ቀኖና እንቀበላለን፤ በዚህ ወቅት የምንቀበለው ቀኖና የሰሙነ ሕማማትን በተመለከተ ብቻ ነው፡፡ ወይራ ጽኑ በመሆኑ የጌታ መከራ ጽኑ መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡

ሕጽበተ እግር ይደረጋል

ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ዲያቆኑ ሁለት ኵስኵስቶችን ውኃ ሞልቶ ያቀርባል፤ አንዱ ለእግር፣ አንዱ ለእጅ መታጠቢያ፡፡ ‹ጸሎተ አኰቴት› በመባል የሚታወቀው የጸሎት ዓይነት ይጸለያል፡፡ ወንጌል ተነቦ ውኃው በካህኑ (በሊቀ ጳጳሱ) ይባረክና የሕጽበተ እግር ሥርዓት ይከናወናል፡፡ ይኸውም ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ያሳየውን የተግባር ትምህርት ለማሳየት ነው (ዮሐ. ፲፫፥፲፬)፡፡ ከውኃው በተጨማሪ የወይራና የወይን ቅጠልንም ለሥርዓተ ሕጽበቱ ማስፈጸሚያነት እንጠቀምባቸዋለን፡፡ ምሥጢሩም የሚከተለው ነው፤ወይራ ጸኑዕ ነው፡፡ ወይራ ክርስቶስም ጽኑዕ መከራ መቀበሉን ከማስረዳቱ በተጨማሪ እኛም (እግራችንን የሚያጥቡን አባቶች እና የምንታጠበው ምእመናን) መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ሥርዓተ ሕጽበቱን በወይራ እንፈጽማለን፡፡ የወይኑ ቅጠልም መድኃኒታችን ክርስቶስ በወይን የተመሰለ ደሙን አፍስሶ ለምእመናን የሕይወት መጠጥ አድርጎ መስጠቱን ለማዘከር በወይን ሥርዓተ ሕጽበትን እናከናውናለን (ማቴ. ፳፮፥፳፮)፡፡ በቀኝና በግራ የቆሙ ሊቃውንትም ‹‹ሐዋርያቲሁ ከበበ እግረ አርዳኢሁ ሐጸበ›› እያሉ ይዘምራሉ፡፡ ይህ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴው ተከናውኖ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ምእመናን ይቀበላሉ፡፡

ቅዳሴ

የጸሎተ ሐሙስ ቅዳሴ የሚከናወነው በተመጠነ ድምፅ ሲኾን፣ እንደ ደወል (ቃጭል) የምንጠቀመውም ጸናጽልን ነው፡፡ ልኡካኑ የድምፅ ማጉያ ሳይጠቀሙ በለኆሣሥ (በቀስታ) ይቀድሳሉ፡፡ ምክንያቱም ይሁዳ በምሥጢር ጌታችንን ማስያዙን ለመጠቆም ሲኾን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዘመነ ብሉይ ጸሎት ዋጋው ምድራዊ እንደ ነበር ለማስታወስ ነው፡፡ በመቀጠል ክብር ይእቲ፣ ዕጣነ ሞገር፣ ዝማሬ የተባሉ የድጓ ክፍሎች ተዘምረው አገልግሎቱ ይጠናቀቃል፡፡ ሕዝቡም ያለ ኑዛዜና ቡራኬ ይሰናበታሉ፡፡

በዚህ ወቅት በዋነኝነት ግብረ ሕማማት የተሰኘው መጽሐፍ ይነበባል

የሰሙነ ሕማማት ሥርዓተ ጸሎትና አገልግሎት ሁኔታ ከቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓተ አምልኮት ጋር የተያያዘ ቢሆንም አሁን ያለውን ሥርዓት የያዘ ግብረ ሕማማት የተሰኘው መጻሕፍ ተዘጋጅቶ በሥራ ላይ የዋለው ከጌታ ልደት በኋላ በ፲፬ተኛው ምእት ዓመት ነው፡፡ ከ፲፫፻፵ እስከ ፲፬፻፹ ዓ.ም የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሰላማ ብርሃነ ዐዜብ ከዐረብኛ ወደ ግዕዝ እንደተረጎሙት፤ ቀደም ሲል በግዕዝ ብቻ ታትሞ በነበረው የግብረ ሕማማት መጽሐፍ ውስጥ ተገልጧል፡፡

የመጽሐፉ ስያሜም ከጥንት ስሙ ጀምሮ ግብረ ሕማማት እንደሚባል በመጽሐፍ ውስጥ በብዙ ክፍል ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ ይህም ቀዳማዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ከጥንት ፍጥረት ከባሕርይ አባቱ አብ፤ ከባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ሕልው ሆኖ በረቂቅ ጥበቡ ዓለማትንና ፍጥረታትን ሁሉ በየወገኑ ፈጥሮ እንደ ባሕርያቸው በቸርነቱ እየመገበና እየጠበቀ ሲገዛ ይኖራል፡፡ አካላዊ ቃል ወልድ በተለየ አካሉ ዓለምን ከፈጠረበት በሚበልጥ ጥበብ ሰው ሆኖ፤ ሥጋን ለብሶ፤ ከድንግል ማርያም ተወልዶ፤ አዳምን ከነዘሩ እንደገና በአዲስ ተፈጥሮ ወደ ቀደመ ክብሩና ቦታው እንደመለሰው ያመለክታል፤ ፪ኛ ቆሮ. ፭፥፲፯/ ዕራ.፳፩፥፭/ ኢሳ. ፵፫፥፲፱/፡፡

ሆሳዕና፡ አሁን አድን

በቤተክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት 8ኛው ሳምንት ሆሣዕና ይባላል። ሆሣዕና ከሁለት የእብራይስጥ ቃላት יָשַׁע (ዮሻህ) እና נָא (ና) የመጣ ሲሆን ትርጒሙም “አቤቱ አኹን አድን” ማለት ነው፤ ታሪኩም በ4ቱ ወንጌላት ላይ የተመዘገበ ኪሩቤል ሱራፌል በፍርሀት በረዐድ ኹነው ዘፋኑን የሚሸሙት ጌታ በአህያና በውርንጫይቱ በትሕትና ተቀምጦ እየተመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት፣ የዘካርያስ ትንቢት የተፈጸመበት፣ ሕዝቡ ዘንባባ ይዘው የዘመሩበት፣ ሕጻናት በንጹሕ አንደበታቸው ሆሣዕና ብለው ያመሰገኑበት ታላቅ በዓል ነው፡፡ (ማቴ 21፡1-17፣ ማር 11፡1-10 ሉቃ 19፡29-38 ዮሐ 12፡12-16)


ጌታችንና ደቀመዛሙርቱ ወደ ኢየሩሳሌም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ። ቤተ ፋጌ ማለት የበለስ ቤት ማለት ሲኾን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ በሚወስደው መንገድ አቅራቢያ ያለች ትንሽ መንደር ናት። ኹሉን ዐዋቂ የኾነው ጌታ ጴጥሮስንና ዮሐንስን “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ” ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል” በማለት የኹሉ ፈጣሪ የኹሉ ጌታ መኾኑን አመለከታቸው።

ፈታችሁ አምጡ የሚለው ትዕዛዝ ዓለም ሁሉ ከኃጢአት የሚፈታበት ዘመን እንደደረሰና ከእርሱም ባሻገር ካህናት በተሰጣቸው ሥልጣነ ክህነት የሕዝቡንም የአሕዛቡን ኀጢአት የማሰር የመፍታት ሰማያዊ ሥልጣን የተሰጣቸው መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡

ሊቁ ቅዱስ አምብሮስ፡- “አህያየቱን ለመፍታት ማንም አይከለክላችኁም ብሎ መላኩ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ሥልጣን ሰማያዊ መኾኑ ያመለክታል፡፡” በማለት ልዩ ምስጢርን አስተላፎበታል፡፡


ኮርቻ ይቈረቊራል ልብስ ግን አይቈረቊርምና የማትቈረቊር ሕግ ሠራኽልን ሲሉ በአህያዋና በውርንጫዋ ላይ ኮርቻ ሳይኾን ልብስ አደረጉበት፡፡ ልብስ በአካል ያለውን ኀፍረት እንዲሰውር አንተም በደላችንን ትሰውርልናለህ የሚል ምስጢርን የያዘ ነው፡፡ ክብር ይግባውና ጌታ ንጉሠ ነገሥት ሲኾን፤ ኪሩቤል ዙፋኑን በፍርሀት በረዐድ የሚሸከሙት 24ቱ ካህናተ ሰማይ ዙፋኑን በፍርሀት የሚያጥኑለት እርሱ በትሕትና የዋህ ኾኖ በተናቁት በአህያና በውርንጫይቱ ላይ ተቀመጠ፤ ከኢየሩሳሌም እስከ ቤተ መቅደስ 16 ምዕራፍ ተጓዘ ይኽም የተናቁትን ሊያከብር እንደመጣና፤ በየዋሀን ምእመናን ልቡና እንደሚያድር ለማሳወቅ በእነርሱ ተቀመጠ፤ በአህያ የተቀመጠ አባሮ እንደማይዝ ሸሽቶ እንደማያመልጥ ርሱም ካልፈለጉት እንደማይገኝ ከፈለጉት እንደማይታጣ በምስጢር አመለከታቸው፡፡


ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ፡- ስለዚህ ነገር በትርጓሜ ወንጌሉ ላይ “እነዚኽ እንስሳት መላውን የሰው ልጅ ይወክላሉ፡፡ ኹለቱም አህያ መኾናቸውም የሰው ልጅ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት የነበረውን አኳኋን የሚያስረዳ ነው፡፡ ምክንያቱም አህያ በኦሪቱ ዘንድ ንጹሕ እንስሳ አይደለችም፤ ብዙ ክብደት ያላት የማትወደድ እንስሳ ናት፤ ዲዳ ናት፤ ደካማ ናት፡፡ ሰውም እንደተናገርን ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት እንዲኽ ነበረ፡፡” በማለት ሲያመሰጥር ሊቁ ቅ. ቄርሎስ ዘእስክንድርያም፡- “ፈጣሬ ኵሉ እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ጠቢብ አድርጐ ፈጥሮት ነበር፡፡ ማሰብና ማሰላሰል የሚችል ፍጥረት አድርጐ ፈጥሮት ነበር፡፡ ሰይጣን ግን አታለለው፡፡ ምንም እንኳን ሰው በሥላሴ አምሳል ቢፈጠርም መልኩን አበላሸው፡፡ ፈጣሬ ኵሉ እግዚአብሔርን ማወቅ ተሳነው፡፡ ክፉው ሰይጣን ሰውን እንስሳ እስኪመስል ድረስ ክብሩን አዋረደው፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት፡- “ሰውስ ክብሩን አላወቀም፤ የሚጠፉ እስሳትን መሰለ” ያለውም ስለዚኹ ነው /መዝ.49፡12/፡፡

በመኾኑም አህያይቱ ክብራቸውን አጥተው ተዋርደው የነበሩትን እስራኤል ዘሥጋን ትመስላለች፡፡ እስራኤል ከሕጉ ጥቂት ነገርን ያውቃሉ፡፡ ከነቢያትና ከቅዱሳንም ትንሽ ያውቃሉ፡፡ ከኹሉም በላይ ደግሞ ወደ አሚን የሚጠራቸውን ክርስቶስን አልታዘዙትም፡፡ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ሲላቸውም እንደምን እንደ አህያይቱ በድንቁርና ተይዘው እንደነበረ ሲገልጥላቸው ነው፡፡ ውርንጫይቱ ደግሞ አሕዛብን ትወክላለች፡፡ ውርንጫ እኽልን ለመጫን እንደማታገለግል ኹሉ አሕዛብም ማኅደረ እግዚአብሔር ከመኾን ርቀው ነበርና፡፡” በማለት ገልጽዋል፡፡ ሊቁ ጀሮምም፡- “ደቀ መዛሙርቱ አህያይቱንና ውርንጫይቱን ለመፍታት ኹለት ኾነው መላካቸው ለሕዝብም ለአሕዛብም መላካቸው ያመለክታል፡፡”
ያን ጊዜ ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ ይኽንም ማድረጋቸው እንኳን አንተ የተቀመጥኽባት አህያ መሬት መርገጥ አይገባኽም ሲሉ ነበር፤ ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቈረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር “የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር” በእጅጉ የሚደንቀው የ40 ቀን የ80 ቀን ሕጻናት የፈጠራቸው ጌታ በንጹሕ አንደበታቸው አንደበታቸው ተፈቶላቸው ጌታን ዘንባባ በመያዝ ማመስገናቸው ነው፡፡ ነገር ግን ጸሐፍት ፈሪሳውያን ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት፤ ኢየሱስም፦ እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? በማለት በሕጻናት እንደሚመሰገን የነርሱም ጌታ መኾኑን ከዳዊት መዝሙር በመጥቀስ ነገራቸው፡፡


ሊቁ ያዕቆብ ዘሥሩግ ሰለዚኽ ምስጢር ሲገልጸው ፡- “ፍቅርኅ ከዘባነ ኪሩብ አውርዶ በአህያ ጀርባ ላይ እንድትቀመጥ አስገደደህ፡፡ ብዙ ዓይንና ብዙ ገጽ ካላቸው ከሠራዊተ መላክእት ይልቅ በዲዳዋ አህያ ትመሰገን ዘንድ ወደደክ፡፡ በሰማይ ሠራዊት ሠረገላ ተቀምጠኅ ክብርኅን ማሳየት አልወደድክም፤ በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጠኅ ወደ ሰማይ ሠራዊት መኼድን መረጥክ እንጂ፡፡ በአርያም እሳታውያን የሚኾኑ ኪሩቤል ያመሰግኑኻል፤ በምድርም ሕፃናት ይዘምሩልኻል፡፡ በአርያም ብርሃናውያን መላእክት በብርሃን ክንፋቸው መንገድኽን ያነጥፉልኻል፤ በምድርም ደቀ መዛሙትኽ ልብሳቸውን አንጥፈው መንገድኽን አስተካከሉ፡፡ ወዮ! አርያማዊ ሲኾን ምንም ሳይንቀን ይጐበኘን ዘንድ ከአባቱ መጣ፡፡ እርሱም በገዛ ፈቃዱ ሰው እስከ መኾን ደርሶ መጣ፡፡ በአህያ ላይ ተጭኖም ይጐበኘን ዘንድ መጣ፡፡ ነቢዩ ዘካርያስ የመንፈስ ቅዱስን እንዚራ ይዞ በደስታ ትንቢትን ለመናገር ይቻኰላል፡፡ እየደረደረም የጽዮንን ልጅ ይጠራታል፡፡” በማለት አስተምሯል፡፡


ሆሳዕና የድህነት ጥሪ ስለሆነ ቅድስት ቤተክርስቲያንም ሁሌም እንደ ህጻናቱ አሁን አድን ብለን ዘወትር እንጠራው ዘንድ ከ9ኙ ዓበይት በዓላት አንዱ አድርጋ በልዩ ክብር ታከብረዋለች፡፡

ከበዓለ ሆሣዕና ረድኤት በረከት ያሳትፈን፡፡

ሳማ ብሔረ ሕያዋን እግዚአ ለሰንበት ገዳም( ሳማ ሰንበት)

ሳማ ብሔረ ሕያዋን እግዚአ ለሰንበት ገዳም
ሰንበትን የሰራት፣ በሰንበተ ክርስቲያን (እሑድ) መፍጠርን አሐዱ ብሎ የጀመረ፣ በሰንበተ ክርስቲያን ከሙታን ተለይቶ የተነሳ፣ በሰንበተ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት ልኮ ቤተክርስቲያንን የመሠረታት የሰንበት ጌታዋ (እግዚእ ለሰንበት) ኢየሱስ ክርስቶስ በሰንበተ ክርስቲያን ይህችን ዓለም ለማሳለፍ እንደሚመጣ አምናና ተዘጋጅታ የምትጠብቀው ቅድስት ቤተክርስቲያን ይህንን ለክርስቲያኖች ሁሉ የዘወትር ጉጉት የሆነውን የምጽአቱን ነገር ለማዘከር ከየዕለት አዋጇ ባሻገር በዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት በምልዐት በዓል አድርጋ ታነሳዋለች።


ይህ በዓል ከሚከበርባቸው አብያተክርስቲያናት አንዱ በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ቤተክህነት የሚገኘው የሳማ ብሔረ ሕያዋን እግዚአ ለሰንበት ገዳም ነው።


ገዳሙ ከግራኝ አህመድ በፊት በ1026ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን በወቅቱ ደብረ ዘይት ይሰኝ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን በግራኝ አህመድ ወረራ ወቅት ጠፍ ደብር ሆኖ ከቆየ በኋላ በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ አያት በንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ዘመን በድጋሚ ሲቀና ሳማ ተሰኘ።
የገዳሙን ታሪክ የሚያትቱ መዛግብት እንደሚናገሩት ገዳሙ በግራኝ አህመድ ዘመን ከጠፋ በኋላ የገዳሙ መሥራች የሆኑት አባ ገብረ ሕይወትና ሌሎች መነኮሳት ታቦተ ተክለሃይማኖትና ታቦተ ጊዮርጊስን ይዘው ከጎንደር ወደ ሸዋ መጡ።


ገዳማውያኑ ገለልተኛ በዐት ሲፈልጉ አሁን ሳማ ሰንበት በሚገኝበት የምንጃር ሸንኮራ አካባቢ ከሚገኝ ጠቦ ከሚሰኝ ወንዝ ሸንተረሩ ላይ በዐት ፈልፍለው ጽሙና ያዙ።


በዚህ ወቅት ሙገሬ ዛላ በተሰኘው ጫካ አንድ ተዓምር ተከሰተ። ዛፍ ሊቆርጥ ወደ ጫካው የገባ አንድ ገበሬ ዛፍ ለመቁረጥ ሲሞክር እሳት እየነደደ አላስጠጋ ይለዋል በዚህ ወቅት ካህናት ተጠርተው የምሕላ ጸሎት ሲደረግ በሥፍራው ላይ ታቦተ እግዚአ ሰንበት ተገኘና አውጥተው ሁኔታውን ለንጉሥ ሣህለ ሥላሴ አሳወቁ። ንጉሱም በጠቦ ወንዝ ሸንተረር ላይ ስለነበሩት መናንያን ሰምተው ስለነበረ ጽላቱ ለአባ ገብረ ሕይወት እንዲሰጥ በማዘዛቸው አባ ገብረሕይወት ተቀብለው ለረጅም ዘመን በዋሻቸው ዓመት እየቀደሱበት ቆዩ። በኋላ ላይም የአካባቢውን ነዋሪዎች በማስተባበር አሑን ገዳሙ በሚገኝበት ደልዳላ መሬት ላይ ገዳሙን ገደሙ።

ገዳሙ ከዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ጋር ግንኙነት እንዳለውም ይነገራል። ገዳሙ ከሰንበተ ክርስቲያን ስም ጋር በተያያዘ የተመሠረተ ብቸኛው ቤተክርስቲያን ሲሆን በውስጡ በርካታ የብራና መጻሕፍት የሚገኙበት ነው። በየዓመቱም በእኩለ ጾም በበዓለ ደብረ ዘይት የሚከብር ሲሆን በአንድ ወቅት ገዳሙ ተቃጥሎ ነበር። ከቃጠሎው በኋላ በክብና በሰቀላ መልክ ሁለት ሆኖ ተሠርቶ በክብ መልክ በተሠራው ታቦተ ተክለሃይማኖት፡ በሠቀላው ደግሞ ታቦተ እግዚአ ለ ሰንበት ገባበት ። በምርቃቱ እለት የተገኙት የወቅቱ ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ገዳሟን “ብሔረ ሕያዋን” ሲሉ ሰይመዋታል።

የመጋቢት 27 በዓለ ንግሥ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የት የት ይከበራል?

1 ደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍና ቅዱስ ሚካኤል

ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ክ/ከተማ

2)     ድልበር መካነ ጎልጎታ መድኃኔዓለም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ጉለሌ ድልበር

3)    ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም እና ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ ቀራንዮ

4)     ፍኖተ ሎዛ ቅድስት ማርያም ቤ/ክ
ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ ብርጭቆ ኮንዶሚንየም

5)     ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል

ልዩ ስም፦አዲስ ከተማ/ክ/ከ አውቶብስ ተራ

6)    አስኮ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክ
ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ አስኮ አዲስ ሰፈር
7)     ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም እና ቅድስት ኪዳነምሕረት ቤ/ክ

ልዩ ስም፦የካ አባዶ

8)     አያት መካነ ሕይወት መድኃኔዓለም እና ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ቦሌ /ክ/ከ አያት ጠበል
9)    ምስራቀ ፀሐይ መድኃኔዓለም ቀበና ካቴድራል(ቅዳሴ ቤት)

ልዩ ስም፦አራዳ ክ/ከ ቀበና

10)     ቦሌ ሰሚት መካነ ሰላም መድኃኔዓለም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ቦሌ ክ/ከ ሰሚት ወጂ

11)    ደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያምና ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ካቴድራል

ልዩ ስም፦ቦሌ ክ/ከ ጉርድ ሾላ

12) ካራ አሎ ደብር ቅዱስ ደብረ ቀርሜሎስ መድኃኔዓለም እና ጻድቁ አቡነ ገሪማ

ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ ኮተቤ ካራ

13)    ደብረ ጽጌ ቅዱስ ኡራኤል
ልዩ ስም፦ቦሌ ክ/ከ ካዛንቺስ

14)     ቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ወደብረ ትጉኃን ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ጉለሌ ክ/ከ ቀጨኔ መድሃኔዓለም

15) እንጦጦ መንበረ ንግስት ቁስቋም ማርያም ቤ/ክ
ልዩ ስም፦ጉለሌ ክ/ከ እንጦጦ ቁስቋም
16)   ፈረንሳይ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክ

ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ ፈረንሳይ ብረት ድልድይ

17)     ቦሌ ቡልቡላ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ቦሌ ክ/ከ ቦሌ ቡልቡላ
18)   ብሔረ ጽጌ መካነ ሰላም ቅድስት ማርያምና መድኃኔዓለም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ብሔረ ጽጌ

19)     ጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል

ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ጎፋ
18)     ጽርሐ ንግስት ቅድስት ሐና ቤ/ክ
ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ፉሪ ሐና ማርያም

19)     ረቢ መካነ ጎልጎታ መድኃኔዓለም
ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ ወረዳ 2 ካራ ቆሬ
20)     ጎፋ ቤዛ ብዙሃን ቅድስት ኪዳነምሕረት ካቴድራል

ልዩ ስም፦ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ጎፋ ካምፕ
21)     ቶታል ፈለገ ሕይወት ቅድስት ኪዳነምሕረትና መድኃኔዓለምቤ/ክ
ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ ቶታል 3 ቁጥር ማዞሪያ

22)  ማሕደተ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ልደታ /ክ/ከ ልደታ

23)   ደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤ/ክ
ልዩ ስም፦ቂርቆስ ክ/ከ መስቀል ፍላወር

24)     ደብረ ፍስሐ መካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ቂርቆስ /ክ/ከ ቂርቆስ

25)    ላፍቶ ደብረ ኢያሪኮ መድኃኔዓለም እና መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አብያተክርስትያናት

ልዩ ስም፦ ንፋስ ስልክ ላፍቶ(ላፍቶ)
26)     ፉሪ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ጀሞ 1 ኮንዶሚንየም

27)     ደብረ ሰሊሆም መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እና መድኃኔዓለም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦አቃቂ ቃሊቲ /ክ/ከ በርታ ሰፈረ ሰላም

28)  አቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ ጋራው መድኃኔአለም

29)  ፈጬ ደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ አቃቂ ቃሊቲ /ክ/ከ ፈጬ


30)  ቃሊቲ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል እና ደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ ሰፈረ ገነት

31)   ቃሊቲ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም እና አቡነ አረጋዊ ቤ/ክ
ልዩ ስም፦አቃቂ ቃሊቲ ወረዳ 12 ሰሪቲ

ንጋት (ትረካ)

መፈገግ ከንጋት በኋላ ላለች ቀን ባህሪዋ ነው ምን ብትዳምን የምትረጨው ብርሃን የምታጋባው ሙቀት ባይኖራት እንኳን ጨርሶ አትጨልምም ያ ነው ማታ ከሚለው ስያሜ የሚለያት በእርግጥ ውስጧ የተሸከመቻቸው የሐሳብ ክምሮች በኗሪው ልቦና ውስጥ ወይ ብርሃን ወይ ጨለማ ያደርጋት ይሆን እንጂ ለንጋት ብርሃን የማጣት ባህሪ ማን ሰጥቷል ? ልብ ግን የፀሐይ መውጣት ሳያሞቃት የዝናቡ ውሽንፍር ቁብም ሳይሰጣት እንዳች ነገር እንደደፈነው ጆሮ ጥቂት ብቻ ኦያደመጠች እንዲሁ ሳታገናዝብ መኖር ትችል እንደሆን የሚጠይቅ ካለ የሰማ የሰፈር ሰው ሁሉ ምሳሌ ስጥ ቢባል እጁን ወደ እኔ ይቀስራል በእርግጥ እውነት ነው። እኔጋር ቀን አዘቅዝቃች የማሰላሰል እና ነገርን የማጤን ለዛ ካጣሁ ጊዜያት ከመቆጠር ዘለዋል “እንግዲ በተዋት ጊዜ ይተዋት” እያሉ የሚያዝኑልኝ ሰዎች ሁሉ የትላንት እኔነቴን እያስታወሱ አይናቸውን አይኔ ላይ ቀስረው ምራቅ ይመ’ጣሉ ።


አዎ ብቻ መሆንን ወድጄ እራሴን ከአብሮነት ገትቼ እራሴ ላይ ቆልፌያለሁ ስላጣኋቸው ነገሮች ሳስብ አለኝ የምለው መስመር እንኳን ሳስቶ ሊበጠስ የደረሰ ክር ይመስለኛል በቃ ለእኔ መቋጨት ያልቻለኩት የማቆም ጫፍ ቆሜ ለመፈጥፈጥ የፊሽካ ድምጽ የምጠብቅ አይነት ሰው ነኝ ለምን አትበሉኝ ምክንያቹን ልክ አይደለሽም ለሚለኝ ውስጠቴ እንኳን በቂ አይደሉም ለራሴ በቂ ያሆንኩና ያለኝ የተነጠቀብኝ ሰው እንደሆንኩ ብቻ ነው ሚሰማኝ በማለዳ ክፍሌ የምትገባዋ ፀሐይ ለመንጋቱ ምልክት ናት ከዚያ በዘለለ ሙቀቷ ሰርጾኝ አያውቅም እንደውም ታደክመኛለች ሌላ የማይገፋ ቀን ይዛብኝ ትመጣለች ሰውነቴ በግድ ወዲህ ወዲያ ይበል እንጂ በትርጉም የሚሰራው ስራ አልነበረውም ክፍሌ ራሴ ለራሴ እያለቀስኩ የቀበርኩባት መቃብሬ ሆናለች። ለነብሳቸው ያደሩ ቤተሰቦቼ ቢሰለቹም እንዳልሞት በግድ ይመግቡኛል። ሌላ በኑሮዬ የማስታውሳቸው ነገሮች ደሞ የጠያቂ ድምጾች ናቸው ” ያቺ ልጅ እንዴት ናት እንደው ምንም ለውጥ የላት” የሁሉም ሰው ወሬ መጀመሪያ ናት። ” አለች ምንም ለውጥ የላት እንደተለጎመች ይንን ሆንኩ እንዲህም ተደረኩ አትል ግራ የገባው ነገር ነው እኛም እኮ ተጨነቅን ” ይላሉ ለመጣ ሁሉ ።ለምጄዋለሁ አልጋዬ ላይ ያስቀረኝን ድባቴ ወድጄ ተገዛሁለት እሱም ወደሽ ከተደፋሽ እያለ ይረግጠኛል ።


ሌሊቱ ከድቅድቅ ጨለማ ጋር ቢሆንም ምን እንዳስፈነጠረኝ የማላውቀው ስሜት ከዘመናት አልጋዬ አስነስቶ መስኮት ላይ ገተረኝ ከአንዳድ የሰማይ ከዋክብት በቀር የሚታይ ነገር የለም ጸጥ ረጭ ያለ ጨለማ የቆምኳቸው ሰዓታት ቢበዙም የድካም ስሜት ግን የለኝም ጨለማ ወስጥ የዛለ ስጋዬን መቆሜ ውስጥ ደሞ የድሮ ትጋት እና ጽኑ ስሜቴ ውልብ አለኝ እንዲህ ስለትላንቱ ማሰቤ በራሱ ለራሴ አስገረመኝ ።የቆምኳቸው ቀናት እና ቦታዎች በአእምዬ ውስጥ በተርታ ተስሎ እንደቀረበ አውደ ርዕይ ይታወሱኝ ጀመር ሰዓታቱ ፣ ማኅሌቱ …..ሁሉ ልቤ ላይ ቀረ ግን ከጨለማ ጋር ነው ። ወዴትም ከማይወስድ ድቅድቅ ጋር የውስጤን ሀሳብ ገታውት ጨለማው እንዳሸነፈኝ አይነት ማስተባበል ነግሬ ጸጥ አደረግኩት ዝምታ። ጨለማ ብቻ። …ከውስጤ ዝምታ ግን የምታባንነኝ በክፍሌ ግርግዳ ተሰቅላ ሰኮንድ የምትቆጥር መስመር ነች ጥቂትነቷ ሳያግዳት ጊዜ የምትለካ ሁኔታ የምትለውጥ ጥቂት ባለ ሙሉ መስመር።


ሳብሰለስል ከቆየሁት ሀሳብ ያነቃኝ ደግሞ ግርማው የሚያስፈራው ጨለማ በወጋገን ላለመሸነፍ የሚያደርገው ትግል ነበር ለካ ከጥቂት ሰኮንድ ቆጣሪ የምትወጣ ድምጽ ብቻ ሳይሆን እይታም ምልከታም ጊዜን ይለውጣል የማይገፋ የሚመስል ጨለማን በብርሃን ይተካል አሁን ነጋ ብርሃን ብቻ ነው ያለው፤ ሙሉ ብርሃን ያልጠቆረ ያልዳመነ ሙሉ ንጋት።


ውጪ ውጪ አለኝ በቃ ይህንን ብርሃን ከተከለለ ክፍል ውጪ ሆኜ ላጣጥመው ፈለኩ ግን ፈራሁ ደሞ አንድ ልቤ አይኔን በሰዓቱ እየላከ እያለፈኝ ያለውን ዘመን ያስታውሰኛል እየገፋ ያበረታኛል። እየፈራሁ ከመታጠቢያው ክፍል ገባሁ ልብሴን አላወለኩም ቧንቧው ማውረድ የሚችለውን ያህል ራሴ ላይ ከፈትኩት አንዳች ነገር ከላዬ ተንዶ የወረደ መሰለኝ ቁምሳጥኑ ፊት ካለው ሙሉ መስታወት ፊት ቆሜ ራሴን ቃኘሁት እንዲህ ራሴን ከተመለከትኩ ረጅም ጊዜ ….ጊዜው በዛች በቀስቃሽ ሰኮንድ ቆጣሪ ከተለካ ደሞ ዘመን በሉት። በረዥም ቁመቴ ላይ ነጭ ረዥም ቀሚስ ለቀቅኩበት ረዥም ነጭ ነጠላ አጣፍቼ በአዘቦቱ ማክሰኞ ትንሳኤ እደሆነለት ሰው ከመቃብር ክፍሌ ወጣሁ ተሰብስቦ ቡና ሲጠጣ የነበረው ቤተሰብ ሁሉ በድንጋጤ ይሁን በመረበሽ ስሜት ከውጭ እንደመጣ እንግዳ ቆመው ተቀበሉኝ ” ወዴት ነው ማለቴ የትነሽ እንዴት ተነሳሽ ” የጥያቄ መአት መልስ አልሰጠሁም መውጣት ብቻ ነበር የፈለኩት ” ልከተልሽ ” አለች እህቴ ስስት በለበሰ ድምጿ ” አይ እመለሳለሁ ብቻዬን ይሻላል ” ማለቴ ብቻ ትዝ ይለኛል እንኳን ለቤተሰቤ ለራሴም ከአንደበቴ ቃል መውጣቱ አስደንቆኛል።

የቤቱንም የጊቢውን በር ተራ በተራ ከፍቼ ወጣሁ ልክ የመጀመሪያውን ልቦናዬ ክርችም በብርሃን ተሸንፎ እንደተከፈተ። ከቤታችን ሩቅ ወዳልሆነው የእመቤታችን ቤተክርስቲያን ያላዘዝኩት እግሬ እየመራ ወሰደኝ አጸዷ እንደድሮው አይደለም ዛፎቿ የሉም ግን ሰላሙ አለ ያ የሚያረጋጋ መንፈስ አለ ከሁሉ በላይ በዓይኔ የፈልኩት ያ የሚያየኝ ያህል የሚሰማኝን ምስለ ፍቁር ወልዳ ሥዕልን ነበር አለ ከነመቀጫ ድንጋዩ። ተቀመጥኩ ዓይኔን ከዓይኗ ተክዬ አወራኋት ግን እያፈርኩ ግን እየፈራው ያስቀየምኳት ባዳ የሆንኩባት እናቴን ከዘመናት በኋላ ፊቷ ቁጭ ብዬ አየኋት ለካስ ናፍቃኝ ነበር መንፈሴ ተዋሃዳት።


ከዚህ ሁሉ መመሰጥ ውስጥ ግን ያነቃኝ የአንዲት እናት እልልታ ነበር ሁለት እጃቸውን ካለልክ ዘርግተው በታላቅ ድምጽ እልልልልሰ እያሉ ወደ ሥዕሏ ይመጣሉ ስለሚያያቸው ሰው ስለሚሰማቸው አካል ግድ የላቸው በመንታ የሚወርደው እንባቸውን ሳያብሱ እናቴ ክብር ይግባሽ ይላሉ ይህችን ብቻ እየደጋገሙ ከአጠገቤ ከሥዕሏ ፊት ተደፉ “ምን ተደርጎላቸው ነው ይለኛል ውስጠቴ ፊታቸው ላይ ያለ ደስታ ያፈለቀው እንባ ከተደፉበት መሬት ላይ ይንጠባጠባል ቀናሁ ማልቀስ አማረኝ እንደ እሳቸው ሞልቶልኝ እንዲህ እንባና ውዳሴን ማቅረብ አሰኘኝ እጃቸው አሁንም እንደተዘረጋ ነው። ከእኔ በስተቀኝ እጃቸውን በነጠላ ሸፍነው ፊታቸው ላይ ያገለደሙ ሁለት ሴቶች ይሾካሸካሉ አይናቸውን ሴትዬይቱ ላይ ተክለው ያወራሉ ” እኚህ ባለፈው ቤታቸው የተቃጠለባቸው ሴትዮ አይደሉ እንዴ ” አንዷ ትጠይቃለች ” እኮ ገርመውኝ እኮ ነው ብታይ እንዴት እንደሚያሳዝኑ ምንም እኮ አልተረፈላቸውም አመድ ነው የሆነው ደሞ ልጃቸው ቢቃጠልም ይተርፋል ብለን ነበር ሆስፒታል ገብቶ ተስፋ ሰጥቷቸው በሁለተኛው ቀን ሞተ በስተእርጅና የወለዱት አንድ ልጃቸው ነበር” ያብራራችው ነገር እና የሴትዮዋ ሁኔታ አልገጥም አለኝ የምሰማው ድራማ እንጂ እውነት የተፈጸመ ታሪክ ነው ብሎ ማመን ከበደኝ የእሳቸው ጸሎት ሌላ የእነሱ ወቀሳ ሌላ። ” ታዲያ ይሄ ሁሉ ጉድ ወርዶባቸው የምን እልልታ ነው ?” ” እንጃላቸው የሰፈሩ ሰው ግን አእምሮአቸው ሳይነካ አይቀርም ይላል አንቺዬ ነገሩ የሆነ ለት አለቀሱ ከእዛ በኋላ ብቻቸውን ቢቀሩም ተመስገን ብቻ ነው የሚሉት ታድያ ይሄ በጤና ነው ” ግራ አጋቡኝ የማየው ከምሰማው አልዋሃድ አለኝ ጆሮዬን ወደሳቸው መለስኩ አሁንም በጉልበታቸው ወድቀው እጃቸውን እንደዘረጉ ናቸው ” እናቴ ሆይ ሁሉን ሞላሽልኝ የወሰድሽውም ቢሆን እኮ ያንቺ ነው እዚሁ ሥዕልሽ ፊት ተደፍቼ አልቅሼብሽ አይደል ልጄን የሰጠሽኝ ይህንን ያህል እኔ ጋር ከኖረ ይበቃል እንደፍቃድሽ በራሴ ያገኘሁት ምን አለ ሁሉ ባንቺ ነው የእኔ እናት ክበሪልኝ የአምላክ እናት ተመስገኚልኝ ምን እልሻለሁ” ይላሉ እየፈገጉ ።

እንዳሉት ጤናቸው አልታወከም እንዳሟቸውም አይደሉም ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ እንደተባለ እንጂ አሁን ያጣዋቸው ነገሮች ትርጉም አልሰጥ አሉኝ ለዘመናት ቤት ዘግቼ የደበትኩባቸው ኩነቶች አሁን እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም አፈርኩም ደግሞም ይህንን ለእኔ ስላዘጋጀ ሐሴት አደረኩኝ። አሁን የለበስኩት ያምርብኛል ትርጉም ይሰጣል ቆምኩ ዓይኔን ወደ ሰማይ ከፍ አድርጌ ለዘመናት ከራቀኝ ፈገግታ ጋር ተመስገን አልኩ…..ሁሉን ውብ ማድረግ ታውቃለህና በምክንያት ትሰራለህና ሁሉ ካንተ ነውና ልዩ አድርገህ ፈጥረኸናልና አሁንም ተመስገን ።


ጸሐፊ – ሜላት ክብረት

ቅዱስ ጊዮርጊስና የአድዋ ድል

‹‹ሃያ ሺህ ያህል ወታደሮች ያሉበት የኤሮፓ ጦር በአፍሪካ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸነፈ። በእኔ እምነት መሠረት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደ አድዋው ያለ ጦርነት የለም።… በአፍሪካ በኩል ታላቅ የተወላጆች ኃይል መነሣቱ ታወቀ። የአፍሪካ ተወላጆች ታሪክ ተለወጠ። ጥቁሩ ዓለም በኤሮፓውያን ላይ ሲያምጽና ሲያሸንፍ የመጀመሪያው መሆኑ ነው። ሐበሾች አደገኛ ሕዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተጽፎላቸዋል። የኛ ዓለም ገና ቶርና ኦዲዮን በሚባሉ አማልክት ሲያመልክ በነበረበት ጊዜ ሐበሾች የክርስትናን ሃይማኖት የተቀበሉ ናቸው። አሁን የኹሉንም ፍላጎት አድዋ ዘጋው…››። (ጳውሎስ ኞኞ፣ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ፣ ገጽ ፻፶፱)። ይህንን የተናገረው ቤርክሊይ የተባለ ጸሐፊ ነው። (Berkeley, George; The Campaign of Adowa and the Rise of Menilik)።

ከአድዋ ጦርነት በኋላ ይህና እንዲህ ዓይነቱ የአድናቆት ምስክርነት ከዓለም ዙሪያ ለኢትዮጵያውያን መበርከቱን የተለያዩ የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ። የአድዋ ድል የዓለም ፖለቲካዊ አካሔድ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ነበረው። እንዲያውም የዚያን ዘመኑን የቅኝ ግዛት ዘመን ከአድዋ በፊትና ከአድዋ በኋላ ብሎ መክፈልና ማጥናት ይቻላል። በዓለም ላይ ከታዩ እጅግ አስገራሚና ወሳኝ ክስተቶች እንደ አንዱም መመደብ የሚችል ነው። ይህ የሆነው ደግሞ በጊዜው አሉ የተባሉትን ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን የታጠቀችና ከጊዜው ኃያላን አንዷ የሆነች አንዲት አውሮፓዊት ሥልጡን ሀገር፣ እዚህ ግባ የሚባል ሥልጣኔ በሌላትና እንደ አውሮፓውያኑ የምታመርተው ቀርቶ የምትገዛውና በእርዳታ የምታገኘው የጦር መሣሪያ እንኳን በቁጥር ውሱንና እጅግ ኋላ ቀር በሆነ፣ ዘመናዊ የጦርነት ስልትን እንደ ሌሎቹ ያልተራቀቀችበት፣ ጦርና ጋሻን በያዙ ዜጎቿ የምትዋጋ እንጂ የወታደሮቿ ቍጥር ጥቂት በሆነባት፣ በአንዲት አፍሪካዊት ሀገር መሸነፏ ነበር። ጦርነቱ በሁለት አውሮፓውያን ወይም በሁለት አፍሪካውያን ሀገራት መካከል የተደረገ ቢሆን ኖሮ፡ ጥቂትም ቢሆን የኃይል መመጣጠን ስለሚኖር ይህን ያክል አያስደንቅም ነበር። ነገር ግን በጉልበተኞች ጽንፍ ባለች በአንዲት ሀገርና በምስኪኖች ጽንፍ ባለች በሌላ ሀገር ምክንያት የተደረገ በመሆኑና ውጤቱም ሥጋ ለባሽ ከሚጠብቀው አመክንዮአዊ ውጤት እጅግ የተለየ መሆኑ አስገራሚ ያደርገዋል።

ከጦርነቱ መጀመር አስቀድሞ ጳውሎስ ኞኞና አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ እንደ ገለጹት ‹‹ሁሉም ኢጣሊያ ኢትዮጵያን እንደምታሸንፋት›› ያስቡ የነበረው ይህን አለመመጣጠን በሰውኛ መነጽር በማየት ነበር። ታዲያ ድሉ እንዴት ተገኘ? የድሉ ዋና መሠረት የሥነ ልቡናና አስተሳሰብ ሚዛን ነበር። የኢጣሊያ ወታደሮች በዘመናዊ መሣሪያዎቻቸውና በውጊያ አቅማቸው ክፉኛ ተማምነውና መተማመናቸውም ወደ ትዕቢት ከፍ ብሎ ነበር። ‹‹…በቅርብ ቀን ምኒልክን በቀፎ ውስጥ አሥሬ ሮማ ውስጥ አመጣዋለሁ…›› ይል የነበረው የኢጣሊያ የጦር መሪ፡ የጄኔራል ባራቲዬሪ ንግግርም ይህንን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነበር። ሕዝቡም ገና ጦርነቱ ሳይጀመር ‹‹ድል አድራጊው›› እያሉ እርሱን መጥራታቸው የዚህ ሌላው ማሳያ ነበር። (ጳውሎስ ኞኞ፣ ፻፷፫)።

በኢትዮጵያውያን በኩል ምንም እንኳን የኢጣሊያ ዐቅም እጅግ እንደሚልቅ ቢረዱትም፡ ከንጉሡ አዋጅ ጀምሮ ካላቸው የጦር ቁስ ይልቅ በእግዚአብሔር ላይ መተማመናቸው ጎልቶ ይታይ ነበር፡- ‹‹እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ። እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም። ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደ ፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም። ‹‹አሁንም ሀገር የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቶአል። እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ፣ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር። አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። ያገሬ ሰው፤ ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበትም የሌለህ ለልጅህ ለሚሽትህ ለሃይማኖትህ ስትል በኀዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፤ አልተውህም፤ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረኢሉ ከተህ ላግኝህ።›› (ጳውሎስ ኞኞ፣ ፻፶፮-፻፶፱)። በዚህ አዋጅ ላይ ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ የሚያኖረው እግዚአብሔር እንደ ሆነ፣ ርትዕንና ፍትሕን እስከ ያዙ ድረስ በእግዚአብሔር እርዳታ አለመጠራጠር፣ ጠላትን በጠላትነት የመፈረጁ ነገር የመጣው ሀገር የሚያጠፋና ሃይማኖት የሚለውጥ በመሆኑ እንደ ሆነ፣ በእግዚአብሔር ረዳትነት እንደሚዋጉት፣ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በውጊያና በጉልበት ብቻ ሳይሆን ለሃይማኖት ሲባል በማዘንም ማገዝ እንደሚቻል ማመን እንደሚገባ ተገልጾአል። ጦርነትን በውጊያ ብቻ ሳይሆን ‹‹የሚያዝኑ ብፁዐን ናቸው›› እንደ ተባለ በማዘንና ወደ እግዚአብሔር በማልቀስ ድል መንሣት ይቻላል ብሎ ማሰብ ምን ዓይነት መንፈሳዊ የሥነ ልቡና ልዕልና ነው? (ማቴ. ፭፡፬)። ኢጣሊያኖች የጎደላቸው ይህ ዓይነቱ ‹‹መሣሪያ›› ነበር።


የኢጣሊያ መልእክተኞች ሁሉ ለጦርነት መቋመጣቸውንና በጉልበታቸው ክፉኛ መመካታቸውን ያዩት እቴጌ ጣይቱም ‹‹የእስራኤል አምላክ ሆይ፣ ይህን ግፍ ተመልከት። በመድፋቸውና በጠብ መንጃቸው ተመክተው የፈቀዳቸውን ተናገሩ፤ ኃይል የእግዚአብሔር መሆኑን አላወቁም። እኛም በክርስቶስ ኃይል አንፈራቸውም›› ማለታቸው ያነሣነውን ጉዳይ በግልጽ የሚያሳይ ነው። የአድዋ ጦርነት እጅግ የተለያየ የኑሮና የፍልስፍና ሐሳብ (Paradigm) ባላቸው ሁለት ተቃራኒ ሀገራት መካከል የተደረገ ጦርነት ነው። አንደኛዋ ሀገር ቅኝ ገዢና ወራሪ፣ ብዙ ሀገራትን አስቀድማም የወረረች፣ አሉ ከተባሉ ሥልጡን ሀገራት አንዷ፣ ባለኝ የጦር መሣሪያና የሠለጠነ የወታደር ኃይል አሸንፋለሁ ብላ የምታስብና የምትወጋትን ሀገር እጅግ የናቀች፣ ጥቁር የነጭ ባሪያ መሆንና በነጭ ሥር መተዳደር አለበት ብላ የምታምን፣ የሌላ ሀገርን ሀብትና ንብረት ለመዝረፍ የመጣች፣ የወታደሮቿ የመጨረሻ ግብ ቅኝ ገዝተው ጀግና ተብለው መሞገስና የተሻለ ሀብትንና ዝናን እንደ ሀገርም እንደ ግልም ማካበት የሆነባት… ወዘተ ነበረች።

ሁለተኛዋ ደግሞ በተቃራኒው ቅኝ ገዝታም ተገዝታም የማታውቅ፣ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብንም ‹አግባብ አይደለም› ብላ የምትጠየፍ፣ ከሥልጣኔ አንጻር እጅግ ኋላ ቀር የምትባል፣ ከጉልበት ይልቅ በእግዚአብሔር የሚያምኑ ዜጎች የሞሉባትና የቱንም ሀገር ስለ ድህነቱ የማትንቅ፡ ስለ ብልጽግናውም ክባ የማትፈራ፣ የሰው ልጅ ሁሉ በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረና እኩል እንጂ ማንም የማንም ባሪያ እንዳልሆነ የምታምን፣ የሌላን የማትነካ የራሷንም የማታስነካ፣ የዜጎቿ (የወታደሮቿ) የመጨረሻ ግብ ሀገርንና ሃይማኖትን ማዳንና ለዚህም ሲባል በመሠዋት ሰማያዊ ክብርን ማግኘት … ወዘተ ነበር።


በዚህ የእሳቤ መሠረት የተነሣ ኢትዮጵያውያን ወኔያቸው ልዩ ነበር። ይህ ወኔ ‹‹የቆምኩትና የምዋጋው ለእውነት ነው፤ ምድራውያን ብቻ ሳይሆኑ እግዚአብሔርና በሰማይ ያሉ አገልጋዮቹ ሁሉ አብረውኝ አሉ፤ ብሞት እንኳን ሞቴ የከበረ ነው›› የሚል ግዙፍ አስተሳሰብ የፈጠረው ፍርሃትን የሚያርቅ ወኔ ነው። በዘመነ ሰማዕታት ክርስቲያኖች ወደሚሞቱበት ቦታ ሲወሰዱ እንደ ሌሎች ከመፍራትና ከመለማመጥ ይልቅ በፈገግታና ወደ ሰርጉ እንደሚሔድ ሙሽራ በደስታ እንደ ነበረው ሁሉ፡ ኢትዮጵያውያንም ይህ ዓይነቱ አሳብ በልባቸው የተሰነቀ ነበር። ስለዚህ ምንም መሣሪያን ያልያዙት፣ እንኳን መሣሪያን ሊይዙ ይቅርና ለእግራቸው ጫማ ያላደረጉትም ቢሆኑ ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ጸጉሩ የታጠቀ የኢጣልያ ወታደር ፊት ሲቆሙ በጥብዐትና በጀግንነት ነበር። በአንጻሩ ደግሞ የኢጣልያ ተዋጊዎች የኃይል ሚዛኑ በጥቂቱም ቢሆን ወደ ኢትዮጵያውያን ባደላበት ጊዜ ሁሉ ፍርሃት የሚወራቸው ዓይነት ነበሩ። የአምባላጌን በመሰሉት ውጊያዎች ላይ የኢትዮጵያውያኑን ድል ካዩ በኋላ አስጨናቂ የፍርሃት ዝግጅትን ያደርጉ የነበረው ለዚሁ ነበር። የመቀሌው ምሽግ እዚህ ላይ ሁነኛ ማስረጃ ይሆነናል፤ ጳውሎስ ኞኞ (፻፸፪-፻፸፭) እንደ ተረከው በመቀሌው ምሽግ የኢጣሊያ ወታደሮች በቅድሚያ ፫ ሜትር ስፋት ያለው ግንብ ገነቡ።
ይህ አልበቃ ብሏቸው በ፴ ሜትር ውስጥ በጣም የሾሉ ከፍታቸው ፴ ሳ.ሜ. የሆኑና አንዱ ካንዱ በ፳ ሳ.ሜ. የሚርቁ እንጨቶችን በብዛት ቸከሉ። ኢትዮጵያውያኑ ግር ብለው ሲመጡ እግረኞቹም ፈረሰኞቹም በነዚህ እንጨቶችላይ እየወደቁ ተሰክተውባቸው እንዲሞቱ ነበር። ይህም አልበቃቸውም፤ ከዚያ ቀጥሎ እሾኻማ ሽቦ እያድበለበሉ አስቀመጡ። ይህም ‹‹እንኳን ሰው ወፍ አያሾልክም›› የተባለለት ነበር። አሁንም ፍርሃቱ ስላልለቀቃቸው ጠርሙስ ሰብረው ነሰነሱ። ይህም በባዶ እግራቸው የሚመጡ የኢትዮጵያውያንን እግር ሸረካክቶ ለማስቀረት ነበር። ለመሞት አስቀድመው የተዘጋጁት አባቶቻችን ግን ታንክና ተዋጊ ቆራርጦ ባይኖራቸውም፡ ይህን ሁሉ ያልፉ ዘንድ በሃይማኖት ጥብዐት የተቃኘው ወኔያቸው በቂ ነበር። በባዶ እግራቸው በጠርሙስ ላይ ለመራመድ፣ ስስ ልብስ በሸፈነው ገላቸውም የተጠቀለለ ሽቦን ለመሻገር አላመነቱም። ግዙፉን ምሽግ እግዚአብሔርን ይዘው ሰበሩት። ይህ የኢትዮጵያውያኑ ወኔ ያስገረመው የኢጣሊያው የጦር መሪ የነበረው ጄኔራል ባራቲዬሪ እንዲህ ብሎ ነበር፡- ‹‹እኛ የሠለጠነው ዓለም ሥልጡን ወታደሮች ምንም አያውቁም ከሚባሉት ኢትዮጵያውያን የምንማረው ትምህርት አለ።
አበሾች ለባሩድና ጥይት ይሳሳሉ። የሚገድሉ ካልሆነ በስተቀር አይተኩሱም። ለዚያውም ቢሆን ፲ እና ፲፭ እርምጃ ያህል ቀርበው ባንድ ጥይት ደራርበው መግደል ይፈልጋሉ። ያለዚያ ተደበላልቀው በጎራዴ መምታት ይመርጣሉ እንጂ ጥይት ማበላሸት አይወዱም። ይህም በማስጮህ ብቻ ጥይት ለሚያባክነው ለሠለጠነው አገር ወታደር ጥሩ ትምህርት ነው። ለምሳሌ ደጀን የነበረው የመድፈኛው አዛዥ ካፒቴን ፍራንዚኒ መድፎቹን ይዞ ከጦር ሜዳ እንዲገባ ታዘዘ። ፴ ኪ.ሜ. ያህል ተጉዞ ከጦሩ ሜዳ ገባ። ቦታውን አመቻችቶ አንድ የመድፍ ጥይት ገና እንዳስተኮሰ ተገደለ። ይህም ሊሆን የቻለው ያቺን የመድፍ ጥይት ድምጽ የሰሙ ኢትዮጵያውያን በንዴት ተሞልተው በብዛት ሆነው ስለ ወረሩት ነው። የተመካንባቸው ደጀን የነበሩት መድፎቻችንም ካንድ ጥይት ተኩስ በኋላ ተማረኩ…››። ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረሥላሴ ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ በሚል መጽሐፋቸው እንደ ገለጹትም ‹‹…ሠራዊቱ ቀለብ ሊያመጣ የሔደው፣ አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ሊስም የሔደው ኹለት እጁ ነው እንጂ አንድ እጁ ለጦር አልደረሰም። የተኩሱን መድመቅ በሰማ ጊዜ ሠራዊቱ ተሰልፎ ተነሣ። አጤ ምኒልክም ከበቅሎ ወጥተው ወደሱ መንገድ ጀመሩ። ሰልፉ ግን አልተገናኘም። በየፊቱ ክምር እንዳየ ዝንጀሮ ወደ ጦሩ ወደ መድፉ ይሮጥ ነበር።… መድፉ ይመታኛል፣
ነፍጡም ይጥለኛል እሞታለሁ ብሎ ልቡ አልፈራበትም። …የቈሰለውም ሰው ‹አልጋው ይቁም እንጂ ኋላ ስትመለስ ታነሣኛለህ፣ በመሀይም ቃሌ ገዝቼሃለሁ› ይለው ነበር። ጥይትም ያለቀበት እንደ ሆነ የቈሰለውን ሰው ከወገቡ ዝናሩን እየፈታ እያባረረ ወደ ፊት ይተኩስ ነበር። ሰውም ከመንገድ ርዝመት ከተኩሱ ብዛት የተነሣ ደክሞት የተቀመጠ እንደ ሆነ ‹የምኒልክ ወሮታ፣ የጮማው የጠጁ ይህ ነውን?› እየተባባለ እንደ ገና እየተነሣ ይዋጋ ነበር››። በኢጣሊያና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ልዩነትን ጠንቅቀው ያውቁ የነበሩት ኢትዮጵያውያኑ ከጦርነቱ በፊት ጦርነቱ እንዳይካሔድ ያደረጉት ጥረትና ከጦርነቱ በኋላም ያሳዩት ጠባይ ከፍርሐትም ከተዐብዮም የራቀና ክርስቲያናዊነትን የተሞላ ነበር።

የዐፄ ዮሐንስ ልጅ የሆኑት ራስ መንገሻ ዮሐንስ ከአዲ አምባይ የጦር ሰፈር ለጣልያኑ ንጉሥ አስቀድመው ‹‹ለታላቁና ለተከበሩ ንጉሥ ኡምቤርቶ፤ በአሁኑ ጊዜ ሰይጣን በመካከላችን በመግባቱ ክርስቲያን የሆንን ሕዝቦች እርስ በርሳችን እንድንፋጅ ሆነ፤ ባለፈው ጊዜ የደረሰው ሁሉ የሰይጣን ሥራ ነው። ሰላምን ስለምንፈልግ እውነተኛና ትክክለኛ የሆነ ሰው ይላኩ።›› በማለት መልእክትን መላካቸው ለዚህ ማሳያ ነው። ጦርነቱ በድል ከተጠናቀቀ በኋላም ታዲያ ይህ ትሕትና በትዕቢትና በትምክህት ሳይቀየር ንጉሡ ‹‹በጥጋባቸው አድዋ ላይ ተዋግተው ድል ሆኑ። እኔ ግን በድንቁርናቸው ብዛት የእነዚያን ሁሉ ክርስቲያኖች ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አረግሁአቸው ብዬ ደስ አይለኝም…›› ማለታቸው ይህንን የመንፈሳዊ ልዕልና ያሳያል። (ጳውሎስ ኞኞ፣ ፻፶፱)። ‹‹እኔ ሴት ነኝ። ጦርነት አልወድም። ግን እንዲህ መሳዩን ውል ከመቀበል ጦርነት እመርጣለሁ…›› (ጳውሎስ ኞኞ፣ ፻፵፰) ብለው የተናገሩት የእቴጌ ጣይቱ ታዋቂ ንግግርም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ›› የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስን ቃል ሲተረጉም ‹‹እግዚአብሔር ከሌለበት ሰላም እግዚአብሔር ያለበት ጦርነት ይሻላል›› ብሎ ከተናገረው ጋር እጅግ ተመሳሳይ ነው። (ሮሜ.፲፪፥፲፰)።

በእውነትም ሀገርና ሃይማኖትን ከሚያሳጣ ‹ሰላም›ስ ጦርነት ይሻላል። በርግጥ በአድዋ ድል ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዋጽዖ በብዙ መልኩ የሚነገር ነው።


በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸውንና ሕዝቡን የሚመሩ አባቶችን ሁሉ አዝምታለች፤ ማዝመቷም በጸሎት እንዲያበረቱ ነው። ይህም ለዘማቹ ሁሉ እጅግ የሚያበረታታ ተግባር ነበር። ከዘመቱት መካከል ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ፣ እጨጌ ወልደ ጊዮርጊስ፣ የደብረ ሊባኖስ ፀባቴ፣ ከእንጦጦ ማርያም የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ ኪዳነ ወልድ፣ ንቡረ ዕድ ተክለ ጊዮርጊስ፣ መምሬ ገብረ ሥላሴ፣ መምህር ተክለ ማርያም፣ አፈ ንቡረ ዕድ ገብረ ማርያም፣ መምህር አርአያ፣ መምህር ገብረ መድኅን፣ ቀኝ ጌታ ቢሆን…ወዘተ ካህናት፣ ሊቃውንት (ከቀራንዮ መድኃኔዓለም፣ ከሆለታ ኪዳነ ምሕረት….) ይገኙበታል። ሕዝቡ እግዚአብሔር አብሮት እንዳለ እንዲያስብና በዘመቻ መንገዱ ሁሉ የሥነ ልቡናው ብርታት እንዳይሸረሸርም የንዋያተ ቅድሳት አብሮ መዝመት አስፈላጊ ነበር። ከታቦታት– የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም፣ ከሸዋ የግንባርዎ ማርያም፣ የበር ግቢ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የአክሱም ማርያምና መድኃኔዓለም…ወዘተ የዘመቱ ሲሆን መስቀሎች፣ ሌሎች ንዋያተ ቅድሳት፣ ቃጭል፣ ጥላዎች፣ ድባቦች፣ ሥዕላት – በተለይም የግንባርዎ ማርያም ‹አምለሱ› ሥዕለ ማርያም …ወዘተ ዘምተዋል። (በአድዋ ጦርነትና ድል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ድርሻ፣ ገጽ ፳፮-፳፰)::


በርግጥ ታቦትና ንዋያተ ቅዱሳትን ይዞ መዝመት ብቻ ለድል አያበቃም፤ እግዚአብሔርን በማያስቆጣ መንገድ መጓዝና ከእውነትና ከፍትሕ ጎን መሰለፍ እንጂ። ቤተ ክርስቲያንም ንዋያተ ቅድሳትንና የሃይማኖት አባቶችን ከማዝመትም በላይ የምእመናንን ሥነ ልቡና የገነባችበት መንገድ ለጦርነቱ እጅግ አስፈላጊ ነበር። ምናልባትም ያ ባይኖር ድሉም አይኖርም ነበር። ብዙ ጸሐፊዎችም ድሉን ከቤተ ክርስቲያን ጋር የሚያያይዙት ለዚሁ ነው። አፈ ሊቅ አክሊሉ ገብረ ኪሮስ የተባሉ ሊቅ ‹‹ለኢትዮጵያ ታሪኳ-ነው መልኳ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው የአድዋውን ድል መሠረት እንደሚከተለው ገልጠዋል። ‹‹… ምኒልክን ለአድዋው ድል ያበቃቸው አንዱም ፣ ኦርቶዶክሳዊ እምነታቸውና የልብ ጸሎታቸው ነው።›› (ገጽ፣፷፭) ዳንኤል ሮኘስ የተባለ ታዋቂ የፈረንሳይ ጋዜጠኛ ‹‹የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ታውቋታላችሁን?›› በሚል ርእስ ባዘጋጀው መጣጥፍ ላይ የሚከተለውን አስፍሯል። “ወራሪዎች ምድርዋን የያዙባት መሆኑን ታሪክ ያወሳል፤ ነገር ግን ሃይማኖት የእንቅስቃሴ መሣሪያዋ ሆኖ በመገኘቱ በነፃነት ተመልሳ ተገኝታለች›› የአድዋን ድል በቀጥታ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ጋር ያያያዙት ሌሎችም ኢትዮጵያን በአፍሪካ እንደምትገኝ ኢየሩሳሌም አድርገው መቍጠር ጀምረው ነበር። ፕሮፌሰር ሬይሞንድ ጆናስ ‹‹ THE BATTLE OF ADWA:-African victory in the age of Empire›› በተሰኘው ታሪካዊ መጽሐፋችው ‹‹የዓድዋን ድል ተከትሎ በመላው ዓለም ተበትነው ያሉ ዝርዋን አፍሪካውያን የዓድዋን፣ የምኒልክንና የነጻይቱን አገር ኢትዮጵያን ስም በልዩ ሁኔታ ማንሣት ጀመሩ፤ ጥቁር ሕዝቦች እንደ ታላቂቷ ጽዮናዊት ኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ ጉዞ ማድረግ ጀመሩ።›› ሲሉ መግለጻቸው ለዚህ ምስክር ነው። አንድ ጣልያናዊ ተዋጊም ‹‹በነጭ ፈረስ ተቀምጦ ወደ ቀኝና ወደ ግራ እየተመላለሰ ወደ ጦርነቱ ግቡ ኢጣሊያኖችን ማርኩ እያለ ትእዛዝ ሲሰጥና ሲዋጋን የዋለ ማነው?›› ብሎ መጠየቁ እየተገለጸ የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ አጋዥነት መገለጹም እዚህ ላይ መነሣት የሚገባው ነው። (በአድዋጦርነትና ድል…፣፶፫)። ይህንንም በአንድ ባለ ቅኔ፡- ‹‹ኃይል ውእቱ ዘጊዮርጊስ፣ አኮኑ ኵዕናት በላዔ ሮማዊት ነፍስ፣ ዘጌዴዎን ምኒልክ ዘአውረደ በዐውደ ሮምያ ጠለ ደም እምርእስ። (በአድዋ ጦርነትና ድል…፣ ፶፪)። (የሮማዊትን ነፍስ (ሰውነት) የበላ (ድል ያደረገ) የጊዮርጊስ ኃይል እንጂ ጦር አይደለም፣የጌዴዎን ምሳሌ ምኒልክ በሮምያ አደባባይ ከራስ ላይ እስካወረደ ጠብታ ደም።) ተብሎ የተነገረ ነው። የአድዋ ድል ብሔራዊና ዓለም ዐቀፋዊ ትሩፋቱ ባሻገር ሃይማኖታዊ ትሩፋቱም መነገር የሚገባው ነው።

‹ኢትዮጵያውያንን እንደ እስራኤል ዘነፍስ መቍጠርና ሀገሪቱንም ጸጋ እግዚአብሔርን የታደለችና ሀገረ እግዚአብሔር እንደ ሆነች አድርጎ ማየት፣ ሀገረ እግዚአብሔር ከሆነች ዘንድም መደፈር የለባትም በሚል እሳቤ ድንበሯን መጠበቅና በዚህም ሂደት መሠዋት የዜግነት ክብር ብቻ ሳይሆን ጽድቅም ነው ብሎ ማመን› ለኢትዮጵያውያን አዲስ እሳቤ ባይሆንም በአድዋ ድል ግን ይበልጥ ጠንክሯል፤ ከዓለም ሕዝብ መካከልም ይህንን ያመኑ እጅግ ብዙ ነበሩ። ከነጮች ተፅዕኖ ነፃ የሆነ የጥቁሮች የሃይማኖት እንቅስቃሴ በተለይ በአሜሪካና በደቡብ አፍሪካ ‹ኢትዮጵያኒዝም› በሚል ስያሜ እንዲጀመር መሆኑ ለዚህ ምስክር ነው። ለማጠቃለል ያህል የአድዋ ድል ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በገነባችው የመንፈሳዊ ሥነ ልቡና ብርታትና ለሀገርና ለሃይማኖት እስከ ሞት የመጋደል ወኔ የተገኘ መሆኑ ከድሉ እኩል መነገር ያለበት ነው።

ኢትዮጵያውያን የኢጣሊያን ወረራ በሀገረ እግዚአብሔር ላይ እንደ ተደረገ ሰይጣናዊ ጥቃት ነበር የቈጠሩት። ለዚህም ነው ድሉን እንኳን ሰይጣን ድል ከተነሣበት ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጋር በማመሳሰል ‹‹ሞዖ ለሞት ሠዐሮ ለጣዖት ገብረ ትንሣኤ በሰንበት›› እያሉ ዳግመኛም‹‹ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐፂባ በደመ ሰማዕታት›› ብለው እየዘመሩ ያከበሩት። (በአድዋ ጦረነትና ድል…፣ ፷)።


የአድዋ ጦርነት ሊጀመር ሰዓታት በቀሩበት ጊዜ እንደ ተዋጊ ሳይጨነቁ፣ ሁሉን ትቶ በተጠንቀቅ ከመቆምና የነደፉትን የውጊያ ስልት ከማሰላሰል ይልቅ ‹እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ይበልጣል› በሚል ታላቅ የሥነ ልቡና ዐቅም ዐፄ ምኒልክ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ ራስ መኮንን፣ ራስ መንገሻ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ ገቦ …ወዘተ በአድዋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እያስቀደሱ ነበር። በርግጥ ከዚህም በኋላም ንጉሡ በእርጋታቸው ጸንተው ዕለቱ ጊዮርጊስ በመሆኑ አሁንም ወደማይጕዓጕዓ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሄደው ልባዊ ጸሎትን አቅርበው ነበር። በጦርነት መጀመሪያ የመጨረሻው ሰዓት ለዚያውም ዐቅሙ እጅግ የሚገዝፍ ጠላት ከፊት ተደግኖ እንዲህ ዓይነት መረጋጋትን ያሳዩ ሌሎች ተዋጊዎች መኖራቸው እጅጉን አስገራሚ ነው። ይህ በርግጥም መንፈሳዊ ጥብዐት እንጂ ምን ይባላል? በአድዋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን፡ ተሰብስበው ሲያስቀድሱ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ ቀዳሽ ነበሩ። እርሳቸውም ከቅዳሴ በኋላ ሲያስተምሩ እንዲህ አሉ፡- ‹‹ልጆቼ ሆይ… ዛሬ የእግዚአብሔር ፍርድ የሚፈጸምበት ቀን ነው። ኺዱ ለሃይማኖታችሁ፣ ለሀገራችሁ ሙቱ፤ እግዚአብሔር ይፍታህ››። (ጳውሎስ ኞኞ፣ ፪፻፫)። በእውነት የእግዚአብሔር ፍርድ በዕለቱ ተፈጸመ፤ ለሀገርና ለሃይማኖት የተሠዉትን ሁሉ ነፍሳቸውን ይማርልን።(ሐመር መጽሔት)

የተከዜ ምዕራፈ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት እና መድኃኔዓለም ዘአቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ አንድነት ገዳም


በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ውስጥ ብዙ ገዳማት የሚገኙ ሲሆን ተከዜ ኪዳነ ምሕረት ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ገዳም አንዱ ነው። ገዳሙ የሚገኘው በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በላስታ ወረዳ  በዜሮ ሰባት ቀበሌ እና በመቄት ወረዳ ነው።  የአባቶች ገዳም ተከዜን ተሻግሮ ከወንዝ ማዶ የሚገኝ ሲሆን የእናቶች ገዳም ላስታ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ነው።  ገዳሙ የተከዜን ወንዝ በሥሩ እየጠጣ የቅዱሳን መነሀሪያ የሆነ በቆላማው የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የተከዜን ወንዝ መሠረት አድርጎ የተሠራ ነው። በስተ ሰሜን የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በደቡብ የአቡነ አሮን ገዳም በቅርብ ርቀት የሚያዋስኑት ገዳም ነው። ወደ ገዳሙ ለመድረስ በወልዲያ ወይ በባሕር ዳር በጋሸና አድርጎ ወደ ላሊበላ በሚወስደው መንገድ ላይ በተለምዶ ግራኝ አምባ (አዲስ አምባ) በመባል የምትታወቀው ከተማ ሲደርሱ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ታጥፎ እስከ ገዳሙ ክልል ድረስ በተጠረገው መንገድ በእግር ወይም በመኪና መጓዝ ይቻላል።

በገዳሙ ውስጥ ሦስት አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን እነሱም የቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በእናቶች ገዳም፣ የመድኃኔ ዓለም በአባቶች ገዳምና የቀጭን አበባ ሥላሴ ናቸው። አመሠራረትና እስካሁን ያለው ታሪክ የገዳሙ መሥራች በጽኑዕ ተጋድሏቸው የሚታወቁት አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ሲሆኑ የተመሠረተውም በቅዱስ ገብረ ማርያም (ሐርቤ) ዘመነ መንግሥት በ፲፪ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው።

የአባታችን አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ትውልዳቸው ሸዋ ቡልጋ ሲሆን አባታቸው ንዋየ ጽዮን እናታቸው ፍቅርተ ክርስቶስ የሚባሉ ደጋግ  በተለይም ለምጽዋት እና እንግዳ ለመቀበል የተጉ ክርስቲያኖች ነበሩ። በዘመናቸውም እመቤታችን በእንግድነት ተገልጻላቸው ይህን ቅዱስ አባት እንደሚወልዱ አብሥራቸዋለች።  የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ተምረው ዲቁና እንደ ተቀበሉ ወደ ታላቁ የአየለነ (እየላ) ሚካኤል መጥተው በዲቁና እያገለገሉ በጽኑ ተጋድሎ እየተጋደሉ ቆይተው ምንኵስናን ለመቀበል ወደ ደብረ በንኰል አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ገዳም ሄዱ። በዛም በብዙ ተጋድሎ ከቆዩ በኋላ በአቡነ መድኃኒነ እግዚእ እጅ ምንኵስናን ተቀብለው በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ከእመቤታችን እጅ የተቀበሏትን የቃል ኪዳን መታሰቢያዋ የሆነችውን ታቦተ ኪዳነ ምሕረት ይዘው መሃል ተከዜ ወደሚገኘው ወደዚህ ገዳም መጥተዋል። ወደ ገዳሙ ሲደርሱም በአናምርትና በአናብስት ተከቦ በረድኤተ እግዚአብሔር ሲጠበቅ አግኝተውታል። ለታቦተ ኪዳነ ምሕረት ማደሪያ የሚሆን ቤተ ክርስቲያን ከሠሩ በኋላ ሌሊት ተከዜ ወንዝ ውስጥ ሲጸልዩ እያደሩ ቀን ቀን አሜከላ አንጥፈው ሲሰግዱ በመዋል አብዝተው እየተጋደሉ መኖራቸውን ቀጠሉ። ገዳሙም የብዙ መናንያን መሰባሰቢያና ትልቅ ገዳም ሆነ። 

የተከዜ ኪዳነ ምሕረት ገዳም በቅዱስ ገብረ ማርያም (ሐርቤ) ዘመነ መንግሥት የተመሠረተ ሲሆን ገዳሙን ከምሥረታ ጀምሮ ወደ ተሻለ ደረጃ እስከ ማሳደግ ድረስ የደረሱት ታላቁ አባት ሐዋርያ ክርስቶስ ናቸው። እኒህ አባት በእግዚአብሔር ጥሪ የኦሪት መሥዋዕት ይሠዋበት በነበረው ከእየላ ሚካኤል ተነሥተው ወደዚህ ገዳም የተከዜን ወንዝ ተከትለው በመምጣት ዙሪያዋን አንበሶች እና ነብሮች አጥሯን ፤ ቅጥሯን እየጠበቁ አገኟት። ወደ ገዳሙ ሲገቡ ሰማይ ተከፍቶ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ ታያቸው። ጌታችን “ወዳጄ ሐዋርያ ክርስቶስ እንኳን ደኅና መጣህ፤ ሁል ጊዜ ከእኔ ጋር ትኖራለህ” አላቸው። ከዚህ ጋር አያይዞም “ይህ ቦታ ምዕራፈ ቅዱሳን ተብሎ ይጠራል” አላቸው። እርሳቸውም ከእመቤታችን በተቀበሉት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የቃል ኪዳኗ መታሰቢያ በሆነው በቅድስት ኪዳነ ምሕረት ታቦት ስም የመሠረቱትን ገዳም ምዕራፈ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረትና መድኃኔ ዓለም አንድነት ገዳም ብለው ከጌታችን በተነገራቸው ቃል ኪዳን መሠረት መጥራት ጀመሩ። ሐዋርያ ክርስቶስም  በዚህ ገዳም እየጸለዩ እና እየሰገዱ ለዓለም ምሕረትን እየለመኑ ለሕሙማን ፈውስን እያሰጡ የምንኵስና ሕይወት በገዳሙ እንዲሰፋ እና እንዲጠናከር አድርገዋል። 

በመጨረሻም እግዚአብሔር አምላክ እስከ ዳግም ምጽአት ‘‘ሞት የለብህም’’ ብሎ  ስለ ፍቅራቸውና ስለ ጽኑ ተጋድሏቸው ዐሥራ ሁለት ክንፍ ተሰጥቷቸዋል። ሐዋርያ ክርስቶስም ቃል ኪዳን ተቀብለው በ፲፩፻፲፭ ዓ.ም. ግንቦት ፲፮ ቀን ተሠውረዋል።  አፄ ምኒልክ ለገዳሙ መገልገያ የሚሆኑ የተለያዩ ንዋየ ቅዱሳትን አበርክተዋል። ልጃቸው ንግሥት ዘውዲቱ ከባላምባራስ ጉግሳ ወሌ ጋር በየገዳማቱ እየሄዱ ይረዱና ለሕይወታቸው ይማፀኑ ነበር። ብዙ ተኣምራትንም አድርጋላቸዋለች።

ገዳሙ ከተመሠረተበት ዘመን ጀምሮ  በሳቸው እግር በተተኩ አባቶች ፈተናዎችን እያለፈ በጽኑ ገዳማዊ ሕይወትና ሥርዓት ቢቆይም በ፲፱፻፸፯ ዓ.ም. በነበረው ድርቅ ምክንያት ተፈቷል። ከሦስት በማይበልጡ መነኰሳት እየተጠበቀ ያለ ምንም የውስጥ አገልግሎት እስከ ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. ቆይቷል። በ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. በአባ ኪዳነ ማርያም አማካኝነት በርካታ መናንያን ተሰባስበው ድጋሚ ተጠናክሮ በአሁኑ ሰዓት ፮፻፲፮ መናንያንና ከ፴ የሚበልጡ የአብነት ተማሪዎች የሚገኙበት ገዳም ሆኗል። (ምንጭ በገዳሙ ከሚገኙ አባቶች)

ሥርዓተ ገዳም አንድነት ገዳሙ የአንድነት ገዳም በመሆኑ ጥብቅ የአንድነት ሥርዓት ያለው ነው።

በዚህ ገዳም ቁሪት፣ ዘረኝነት፣ ነገረ ሠሪነት ክልክል ከመሆኑም አልፎ ውጉዝ ነው። ማንም በገዳሙ በምናኔ የሚኖርም ሆነ በእንግድነት የመጣ ሰው የገዳሙን የአንድነት  ሥርዓት የማክበር ግዴታ አለበት ። ምግብንም የገዳሙ መጋቢ ከቆነነው ውጭ መጠቀም ፈጽሞ ክልክል ነው። እንግዳ ወደ ገዳሙ  ለሥራ፣ ለጠበል፣ ለጸሎትና ለሱባኤ ሲመጣ ከመናንያን  በዓት ማረፍ ከተመደበለት ሊቀ አበው ውጭ ያለ ሥራና ያለ መጋቢው ፈቃድ ከሌሎች ጋር መገናኘት ክልክል ነው። ይህ እና ይህን የመሳሰሉት ሥርዓቶች በመናንያኑ ዘንድ የአንድነት ገዳማዊ መንፈሳዊ ሕይወት ቃል ኪዳን ውስጥ ተካትተው የሚታወቁ ናቸው።

ሥርዓተ ምንኵስና በገዳሙ ለምናኔ የሚመጣ ሰው ስለ መጣበት ምክንያት ተጠይቆ ያስረዳል። ቤተሰቡን ትዳሩን ልጆቹን በትኖ አለመምጣቱን፣ ወንጀል ሠርቶ ለመደበቅ አለመምጣቱን፣ ገዳሙን በማንኛውም መንገድ ሊጎዳ አለመምጣቱን፣ ማንነቱን የሚገልጽ መታወቂያ  እና መሰል ሁኔታዎችን ተጠይቆ ለ፺ ቀናት (ለሦስት ወራት) ደጅ እንዲጠና ይደረጋል። ከዚያም በሰላም ለኪ ወደ ገዳመ ማኅበሩ ገብቶ ለሦስት ዓመት የአመክሮ ጊዜ ይሰጠዋል። 

ከሌላ ገዳም ፈልሶ የመጣ እንደ ሆነ በምን ምክንያት ከነበረበት ገዳም እንደ ወጣ፣ በምግባር ችግርም ተባሮ እንደ ሆነ ይጠየቃል። ‹ነበርኩበት› ወዳለው ገዳም ተደውሎ ስለ እርሱ ይጠየቃል። ፈተና ጸንቶበት የመጣ እንደ ሆነ ይቀበሉታል። በምግባር ብልሹነትና ሁከት በማስነሣት የተባረረም ከሆነ ተለይቶ እንዲመከርና በጥንቃቄ ገዳመ ማኅበሩን በማይበጠብጥበት ሁኔታ እንዲታረም ይደረጋል። ምክንያቱም ሁከት ይፈጥራል በሚል ሥጋት ብቻ እንደ መጣ ቢባረር ወደ ዓለም ተመልሶ ይወድቃልና የመታረሚያና የጽሞና ጊዜ ይሰጠዋል። የማይመለስ ከሆነና ለገዳማዊ ሕይወት እንቅፋት የሚሆን ሆኖ የተገኘ እንደ ሆነ  ገዳሙን ለቆ እንዲወጣ ይደረጋል።

ምንፍቅናንና ሁከትን ሊዘራ የመጣ ከሆነ ግን ሳይውል ሳያድር ገዳሙን ለቆ እንዲወጣ ይደረጋል። በገዳሙ ውስጥ የአመክሮ ጊዜያቸውን በጥሩ ገዳማዊ ሕይወት ላሳለፉ አባቶችና እናቶች አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ የልደታቸው መታሰቢያ በሚከበርበት ሐምሌ ፲፮ እና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከስደት ተመልሳ ደብረ ቍስቋም በገባችበት በኅዳር ፮ የምንኵስና ሥርዓታቸው ይፈጸማል።

ሐምሌ ፲፮ የጻድቁ አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ በዓለ ንግሥ ሲሆን በኅዳር ፮ ደግሞ እመቤታችን ከስደት ተመልሳ ደብረ ቍስቋም የገባችበት ዓመታዊ በዓል ነው። ስለዚህ ወደ መርንኵስና ሕይወት ለሚቀላቀሉ አባቶችና እናቶች ከቅድስት ድንግል ማርያም እና ከአቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ቃል ኪዳን ለመቀበል ነው።  በገዳሙ ሥርዓት መሠረት ከወላጅ አልባዎች ውጭ ለምናኔ የሚመጡ ዕድሜያቸው ከ፲፰ ዓመት በታች የሆኑትን አይቀበልም። ይልቁንም ውስጣቸው ያለው መንፈሳዊነት ልምላሜው የማይቋረጥበትን መንገድ አመላክቶና ምክር ሰጥቶ ወደ ቤተሰቦቻቸው ይመልሳል። ፩.፫.የአመጋገብ ሥርዓት አመጋገብን በተመለከተም ገዳሙ ሥርዓት አለው።

በበዓለ ሃምሳ በቅዳሜና እሑድ ከጧቱ  ሦስት ከሃያ እና ዘጠኝ ሰዓት ከሃያ ላይ፣ ሥራ በማይሠራባቸው በዓላትና በፍልሰታ በቀን አንድ ጊዜ ዘጠኝ ሰዓት ፣ በሰሙነ ሕማማት ከዋክብት ሲታዩ፤ በሌሎች ቀናት ለአረጋውያንና ለካህናት ዘጠኝ ሰዓት በቀን አንድ ጊዜ ሲሆን ለሚወጡት ለሚወርዱት (ሥራ ለሚሠሩ) አርድእት በሰባት ሰዓት የመቁንን ሥርዓት ተሠርቷል። በገዳሙ አንድነት በ፳፻፰ ዓ.ም. በተወሰነው ውሳኔ መሠረት ዐበይት በዓላትንና ዓመታዊ የቅዱሳን መታሰቢያ በዓላትን ጨምሮ በየትኛውም ጊዜ በገዳሙ ውስጥ አስካሪ መጠጥ አይዘጋጅም፤ ሥጋ አይበላም፤ ከውጭም ይዞ መግባት ፈጽሞ ክልክል ነው።

በገዳሙ ሕመምተኞች የሚረዱበት በአባቶችም በእናቶችም ቤተ ሕሙማን ያለ ሲሆን እነሱን የሚንከባከቡ ትራስ ቀና የሚያደርጉ የሚያጎርሱ ልብሳቸውን የሚያጥቡ አረጋውያንንም የሚጦሩ ሊቀ አበው አሉ። በገዳሙ ውስጥ አእምሮውን ላጣ፣ ሂድ ሂድ ለሚለው ሰው ለ፫ ቀን፣ ለ፯ ቀን ጸሎተ ማርያም ይደረግለታል በሁሉም ጸሎቶች ያታሰባል፤ የንስሓ አባቱ እንዲጎበኙትና እንዲመክሩት ይደረጋል። የማይተወው ከሆነና የሚጸናበት ከሆነ እግረ ሙቅ ይደረግለታል። ከዚህም በተጨማሪ የምክርና የሕክምና እርዳታ የሚያገኝበት በገዳሙ አባቶችና እናቶች የሚገለገል መለስተኛ ክሊኒክም አለ። የቤተሰብ ጉብኝት ሥርዓት ዘመድ ጥየቃንም በተመለከተ ገዳሙ ሥርዓት አለው። ማንኛውም የመናኝ ቤተሰብ ዘመድ ‹በዚህ ገዳም ይገኛልና ልጠይቀው መጥቻለሁ› ካለ የገዳሙን ህልውና የሚፈታተን ሰው አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሚጠቅሙ መሠረታዊ ጥያቄዎችን እንዲሁም ስለ መናኙ ማንነትና ስም ይጠየቅና “የተባለው ሰው በገዳሙ ስለ መኖሩ እናጣራለን” ተብሎ በእንግዶች ማረፊያ እንዲያርፍ ይደረጋል። ከዚያም የተባለው ሰው በገዳሙ ያለ ከሆነ እከሌ የሚባል ሰው ያውቅ እንደ ሆነ ተጠይቆ “አውቀዋለሁ” ካለ “ሊጠይቅህ መጥቷልና ልታገኘው ትፈልጋለህ ወይ” ተብሎ ይጠየቃል። “አዎ አግኝቸው ስለ ደኅንነቴ እንዲያውቅና ስለ ሁሉም ነገር ልነግረው እፈልጋለሁ” ካለ እንዲገናኙ ይደረጋል። “አይ ላገኘው አልፈልግም ደኅና መሆኔን ነግራችሁ ሸኙት” ካለ ወይም “አይ ለምናኔ ሕይወቴ ፈተና ስለሚሆንብኝ ላገኘውም አልፈልግም እዚህ መኖሬንም አትንገሩት በጥሩ የእንግዳ አሸኛኘት አስተናግዳችሁ ሸኙት” ካለ በጥሩ ሁኔታ ተስተናግዶ ይሸኛል።

የገዳሙ አስተዳደር የአገልግሎት መዋቅር ገዳሙን የተመለከተ ማንኛውም ሕግና ሥርዓት ሲወጣና ሲወሰን ሁሉም የገዳሙ አንድነት በተገኙበት ነው። ከዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ቀጥሎ የገዳሙን የትኛውንም እንቅስቃሴ የሚቆጣጠርና የገዳሙ ሥርዓተ ገዳም በትክክል እየተተገበረ መሆኑን የሚከታተል ውይይት አድርጎ ለችግሮች የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ የአበው መማክርት አስተዳደር ጉባኤ የሚባል ፲፫ አባላት ያሉት አበ ምኔቱ፣ እመ ምኔቷ፣ አፈ መምህሩ፣ ጸሓፊው፣ መጋቢው፣ ሊቀ አርድእቱ እና የሰባቱ ዘርፎች ተጠሪዎች ያሉበት ነው።


የሥራ ዘርፎች
የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዘርፍ፦ ይህ ዘርፍ የቤተ ክርስቲያን የውስጥ አገልግሎት፣ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እና የአብነት ትምህርት ክፍሎችን በውስጡ የያዘ ነው።


የቤተ እግዚአብሔር አገልግሎት ዘርፍ፦  በዚህ ዘርፍ ውስጥ የማኅበር መቁነን ዝግጅት ክፍል እና የቁሳቁስ አቅርቦት አገልግሎት ክፍል ይገኛሉ። በውስጡ እንጨት ፈላጮች፣ አህያ ጫኞች ፣ ሊቀ አበው ፣ ባለ ተስፋዎች፣ እጓል መጋቢዎች እና አረጋውያንን ያካተተ ነው።

የአገልግሎት ዘርፉ ሥያሜ (የቤተ እግዚአብሔር አገልግሎት) የሚለው በገዳሙ ውስጥ ያለውን ሁሉ የሚያካትት ቢሆንም  ሥያሜው ግን በዚህ ክፍል ለተጠቀሱት የአገልግሎት ዘርፎች ብቻ ስተለተሰጠ እኛም ሥያሜውን እንዳለ ወስደነዋል። 


የእጅ ሥራ ዘርፍ፦  በውስጡም የጥሬ ዕቃና ምርት ማደራጃ፣ የሽመና፣ የሹራብ ሥራ፣ የጥልፍ ሥራና የኅትመት ሥራ ክፍሎችን በሥሩ የያዘ ነው። በእደ ጥበብ ሥራ ያለውን ከምርት እስከ ጥራት ፍተሻና ቁጥጥር ያለው በዚሁ ዘርፍ ሥር ነው። 


የግብርና ልማት ዘርፍ፦ በውስጡም የእርሻ፣ የደንና የአትክልት ልማት እና የርባታ ክፍሎችን የያዘ ነው።


የግንባታ ልማት ዘርፍ፦  የቤቶች ግንባታ፣ የመንገድ ሥራና የውኃ ሥራ ክፍሎችን በውስጡ የያዘ ዘርፍ ነው።
የቴክኒክና የኢንዱስትሪ ዘርፍ፦ የተሽከርካሪ አገልግሎት፣ የወፍጮና ሌሎች የሞተር ነክ አገልግሎቶች እና የብረታ ብረትና የእንጨት ሥራ ክፍሎችን የያዘ ዘርፍ ነው።

የሥነ ጽሑፍና ቅንብር ሥራዎች ዘርፍ፦ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች፣ የድምፅና የምስል ቅንብር ሥራዎች እና የድምፅና ምስል ቀረጻ ክፍሎችን የያዘ ዘርፍ ነው። ሁሉም የገዳሙ ማኅበረሰብ ከላይ ከተጠቀሱት የሥራና የአገልግሎት ዘርፎች ውስጥ የተካተተ ነው። የዘርፎቹም ተጠሪዎች የአበው መማክርት ጉባኤ አባላት ናቸው።

ምንጭ – ሐመር 2012

ነፍሴን የት ልውሰዳት?


“አጥብቄ ፈለግሁ . . . ደከምሁ፤ እጅግም ባዘንሁ፤ ዙሪያ ገባውን ሁሉ እየቃኘሁ የዓለምን ዳርቻዎች ሁሉ አማተርሁ፤ . . . ነገር ግን ነፍሴን እፎይ ብዬ አሳርፋት ዘንድ እሸሸግበት ጥግ አጣሁ የደከመ መንፈሴን ሰላም አሰፍንበት ዘንድ ማረፊያ ወደብ አጣሁ . . አዎ እጅግ ባተትሁ ነፍሴን ከደካማው ሥጋየ እሥር አላቅቄ ነጻነትን አጎናጽፋት ዘንድ ማረፊያው የሥጋ ሸክም ማራገፊያው ከቶ ወዴት ነው? “ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል” (ማር. ፰፥፴፮) እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ በዚህ ምድራዊ ዓለም የሚዳሰስ፣ የሚላስ፣ የሚቀመስ ይጣፍጥ ዘንድ ግን ከቶ በማይቻለው የዓለም ግሳንግስ የተወረረችና ዝላ የደከመች ነፍሴን ምኞት፣ ዝሙትና ፍቅረ ንዋይ የተሰኙ ወንበዴዎች ደብድበው ያቆሰሏትን ድኩም ነፍሴን ዘይቱን አፍስሶ ቁስሌን ወደሚያክምልኝ ያ ደግና ርኅሩኅ ሳምራዊ አደርሳት ዘንድ ከቶ የት ልሂድ፡፡” (ሉቃ. ፲፥፴፫) እያሉ አባ ሞገሴ ረዘም ባለ ንግግራቸው ድምፃቸውን ጎላ አድርገው ያወራሉ፡፡

አባ ሞገሴ ከሰው ጋር ያሉ መስሎኝ ትቻቸው ልሄድ ስል ብቻቸውን ናቸው። አመማቸው እንዴ ብዬ ልጠይቃቸው ስል ዐይናቸውን ወደሰማይ ቀና አድርገው ከነበሩበት ስሜት ማንም የሚያናውጻቸው ያለ አይመስልም። አባ ሞገሴ በአንድ ታዋቂና ታላቅ ደብር ጸሎት አሳራጊ አባት ናቸው። በዚህ ታላቅ ደብር ቄሰ ገበዝ ሆነው ለረጅም ጊዜ ካገለገሉ በኋላ የጸሎት አሳራጊ አባት እንዲሆኑ በካህናቱ ፈቃድ ከሰሞነኛነት ተለይተው የሚኖሩ አባት ናቸው። ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ቅዱስ አባት ለአርባ ዓመት ቆመው የጸለዩበት ቦታ ነው ከሚባል ጫካ ቆመው እየጸለዩ ነው። እኔም ስሜታቸውን ከምረብሽ በጽሞና ማዳመጡና ከጸሎታቸው በረከት መቀበሉ የተሻለ ነው ብዬ ማዳመጥ ጀመርሁ። አባ ከብሉያት ከሐዲሳት እየጠቃቀሱ ልመናቸውን ቀጠሉ።

ሰው መሆንን እና የሰውነትን ልክ በሚበላና በሚጠጣ በሚግብሰበስ ከንቱና ሕይወት የለሽ በድን በሆነ መስፈሪያ የሚመዝን ዓለም የታከተች ብኩን ነፍሴን አሳርፋት፤ ሰላም እሰጣት ዘንድ የት ልሂድ የት ልድረስ ፡፡ ታላቁን ቅዱስ መጽሐፍ ባገላበጥሁ ጊዜ እናንተ “ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ . . . . ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” (ማቴ፲፩፥፳፰-፳፱) ያለውን መንፈስን የሚያድስ ልብን የሚያበረታ ቅዱስ ቃል ዓይኖቼ ተመለከቱ ትንሽ አለፍ ብየ ቅዱሱን መጽሐፍ በትኩረት ሳገላብጥ ሌላ ለጥያቄዬ ምላሽ ፍንጭ የሚሆነኝን አጽናኝ ቅዱስ ቃል አስተዋልኩ “ሰላምን እተዉላችኋለሁ፡ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ። እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም” (ዮሐ.፲፬፥፳፯)፡፡ እያሉ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን የቅርብ ግንኙነት ስሰማ እኔም ወደ ኅሊናዬ ተመለስሁ።


በዚህ ጊዜ ልቤ ሐሤት አደረገች መንፈሴም ደስታን ተመላ . . . ያች ከዐሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም ይፈሳት የነበረች ሴት (ማቴ.፮፥፲፪) የጌታችንን የልብሱን ዘርፍ ስትዳስስ የተሰማት ዓይነት የፈወስ ተስፋ በውስጤ ለመለመ ደግሞም እንደ ሳምራዊቷ ሴት (የሐ. ፬፥፱) የማውቀውን ታሪኬን ነግሮኝ ለዘለዓለም እንዳልጠማ የሚያደርገኝን የነፍሴን እረፍት እንዳገኘሁት ተሰማኝ እናማ የእርሱን የአምላኬን የጌታዬንና መድኃኒቴን ጥሪ ተቀብዬ የከበደ ሸክሜን አራግፌ ዓለም እንደሚሰጠኝ ያልሆነውን የዘለዓለም ጥማቴን የሚያስወግድልኝን እረፍት አገኝ ዘንድ “ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ” (መዝ. ፻፳፩፥፩) እንዲል መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት ማለዳ በትጋት ተነሥቼ የክርስቶስ ሙሽራ፤ የክርስቶስ አካል (ፊል. ፬፥፲፭) ክርስቶስ በገዛ ደሙ የዋጃት (ሐዋ. ፳፥፳፰) የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የድሆች መጠጊያ ወደ ሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በፍቅር ገሰገስሁ፡፡


እናም በዚህ ልዩ ቀን እግሮቸ በተስፋ ከቤቴ ደጅ ተነሥተው የማለዳውን ፀጥታና ሰላም እያጣጣሙ “ቅረቡ ኀቤሁ ወያበርህ ለክሙ ወኢይትኃፈር ገጽክሙ ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል ፊታችሁም አያፍርም ይህ ችግረኛ ጮኸ እግዚአብሔርም ሰማው፤ ከመከራውም ሁሉ አዳነው” (መዝ. ፴፫፥ ፭) የሚለውን የቅዱስ ዳዊት ድንቅ መዝሙር በውስጤ እያዜምኩ ነፍሴን አሳርፋት ዘንድ በፍቅር እየተራመድኩ ወደ ቅዱስ ደጁ አመራሁ፡፡ እውነት እላችኋለሁ በማለዳ ከእንቅልፍ ድካም ተገላግለው በፀጥታው ጎዳና ወደ ደጀ ሰላሙ ሲያመሩ ያለው ጣዕም ያለው መንፈሳዊ እርካታ ከኅሊና በላይ ነው ፡፡


ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር አቅራቢያ በደረስኩ ጊዜ ኃጢአቴን እያሰብኩ ለመጸጸት . . . ልቤን አሰናዳሁ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልዩ ሰማያዊ መዓዛ ለመመሰጥ ደካማ ሥጋዬን ጎስሜ እንግዲህ እግዚአብሔርን እሺ በሉት፤ ሰይጣንን ግን እንቢ በሉት፤ ከእናንተም ይሸሻል እግዚአብሔርን ቅረቡት ይቀርባችሁማል ተብሎ እንደተጻፈ ጥንተ ጠላቴን እንቢ ብዬ በተመስጦ ገሰገስኩ . . . ያን ዕለት ደስታ ውስጤን እያረሰረሰኝ ነበር . . . ሄደኩ ተራመድኩ ፡፡


ነገር ግን ምን ዋጋ አለው የካራን ኑሮዬን ትቼ የሲናን በርሃ አቋርጨ ጉዞየን ፈጽሜ የተስፋይቱን ምድረ ከነዓንን ሳልረግጥ . . . አንድ አስደንጋጭ ጆሮን በመውጋት የሚያሳቅቅና ልብን የሚያሰበረግግ ድምፅ ወደ ጆሮዬ ገባ “ጧፍ ጧፍ . . . ሻማ፣ ነጠላ፣ ድስት፣ ብረት ድስት በርካሽ ዋጋ ይዉሰዱ … ቄጤማ ቄጤማ፣ ከኢየሩሳሌም የመጣች ልዩ መስቀል በአባቶች የተባረከ. . . ወ ዘ ተ::”
በዚችው ቅጽበት ከነፍሴ ተፋትቼ ከከንቱ ሥጋዬ ጋር በድጋሜ ጋብቻ ፈጸምኩ፤ እናማ በልቡናዬ ሐሳብ ማውጠንጠን ጀመርሁ “አወ ስመለስ ቄጤማ እገዛና በጠዋት ቤቴን አጫጭሸ ሞቅ ሞቅ አድርጌ ቡናየን አፍልቼ ከጎረቤቶቼ ጋር ፈታ እላለሁ . . .” ብቻ ምን አለፋቹህ በዚያች ቅጽበት ከሰማያዊው ከፍታ ማማ እራሴን አውርጄ ስለ ማኅበራዊና ሥጋዊ ሕይወቴ ማሰላሰል እየጀመርሁ ዐውድ እየቀያየርሁ ከነፍሴ ተፋታሁ ዴማስን ሆነኩና የተሰሎንቄ ውበት ሳበኝ። ወደ ኋላ ዞሬ መንፈሳዊ የሕይወት ጉዞዬ ተሰናክሎ የጨዉ ሐውልት ሆኜ ቀረሁ።


ትንሽ ከደካማው የሐሳብ ጉዞዬ መለስ ስል ለካንስ ምእመናን “ለእግዚአብሔር በፍርሃት ስገዱ” ያለውን የሠራዒ ዲየቆኑን አዋጅ ሰምተው በፍርሃት ሰግደዋል . . . እግሮቼም እኔ ልብ ሳልላቸው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር ዘልቀው ገብተዋል . . . በድርጊቴ በጣም ተሳቀቅኩ አፈርኩ ተሸማቀቅሁ . . . እናም ከምእመናን ጋር ለመመሳሰል በአምልኮ እሰግድ ዘንድ ጉልበቴን ሸብረክ ሳደርግ ምእመናን ሁሉ ከሰገዱበት “ተንሥኡ” ተብለው እየተነሡ ነበር፡፡ ከትንሽ የአስተውሎትና የተመስጦ ጊዜ በኋላ ይህ ከንቱ መርጦ አድማጭ ጆሮዬ ተምዘግዝጎ ከደጀ ሰላሙ ቅጽር ግቢ አፈትልኮ ወጣ . . .ሄደ.. ገሰገሰ ወደ ኋላ ነጎደ . . . ለካስ የዓለም ሁካታ ሲከንፍ ከጀርባየ ተከትሎኛል . . . አቤት . . የድምፁ መረበሽ ቀጠለ ጫጫታው “የጭንቅ ደራሿ ማሠሪያ ነው አምስት ዐሥር ያላቹህን …..የፈጥኖ ደራሹ … ጣሪያው እያፈሰሰ ነው። ዐሥር ሺህ ብር ትኬቱን ለበረከት . . ወንድማችን እገሌ …በኩላሊት በሽታ ….ወደ ውጭ ሀገር ሂዶ እንዲታከም. . . ጧፍ በአንድ ብር በአንድ ብር: ልዩ ሎተሪ በጊዮርጊስ ቀን የሚወጣ፣ ትሪ፣ ሳሃን፣ ብረት ድስትም፣ አለ ወ ዘ ተ ወ ዘ ተ” ውይ …ሲያደክም ተደበላለቀብኝ የትኛውን ትቼ የተኛውን እንደምሰማ ግራ ግብት አለኝ ነፍሴን . . . እረሳኋት. . . . ተውኳት ጭራሽ ተሰናበትኳት . . . በድንገት ስልኬን አወጣሁ፤ ሰዓቴንም በፍጥነት ተመለከትኩ፤ ሰዓቱ ሂዷል ራሴን ስለነፍሴ ሳይሆን ሰለ ሰዓቱ መሄድ ሲጨነቅ አገኘሁት …ይሄኔ ታዴያ ራሴን ታዘብኩት በመንፈስ ሳይሆን በሥጋ እንደነበርኩ ታወቀኝ፡፡


የሥርዓተ ቅዳሴውን መጠናቀቅ ሳይሆን የሰዓቴን ጉዳይ አስቀድሜ ቅዱሱን ደጀ ሰላም በድፍረት ረጋግጨ በምእመናንና በቅዱሳን መላእክት ላይ ተረማምጀ ስከንፍና ስክለፈለፍ ወጣሁ . . . ከውስጥ ጆሮየን መስጦ ሲጠራኝ ወደ ነበረው ጎትቶ ወደ አስወጣኝ ሁካታ በፍጥነት ተቀላቀልኩ …. የሥጋ ስሜቴን በመንፈሳዊ ገበያ ሸመትኩ …. ይህ ሁሉ ሁኖ ግን ነፍሴ አላረፈችምና ሰላም አላገኘሁም . . .እንደገና ተጨነኩ እንደገና ውጥረትና መረበሽ . . . ነፍሴ ታርፍ ዘንድ እድሉን የዕለት ቀለቧን የዘመናት ምግቧን ቃለ እግዚአብሔርን ታገኝ ዘንድ አለፈቀድኩላትምና ዕረፍት አላገኘችም ።


መለስ ብየ የአባ ሞገስን ተመስጦ አስተዋልኩ። ዕድሜ ልካቸውን በአገልግሎት ተጠምደው ኑረው አሁን ደግሞ የጸሎት ጊዜ ሲያገኙ ራሳቸውን እንደ ፍጹም ኃጢአተኛ ቆጥረው ማረኝ ማረኝ ይላሉ። እኔ ግን በአግባቡ ቅዳሴ ለማስቀደስ እንኳን አልበቃሁም። የአባ ሞገስን ጽናት እንደሳቸው ለመሆን ባልችልም ወደ እርሳቸው ሕይወት የሚወስደኝን መንገድ የሚዘጉብኝን ምክንያቶች እያሰብኩ እንዲህ ማለት ጀመርሁ። ደግሜ ደጋግሜ እጠይቃለሁ ዕረፍት ታገኝ ዘንድ ነፍሴን የት ልውሰዳት ፤ የነፍሴ ማረፊያ የልቤን ሰላም ሳዝን መጽናኛየን “ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ” (ማቴ. ፳፩፥፲፫) የተባለላትን እናቴን ቅድስት ቤተ ክርስትያንን የመሸጫ የመለወጫ የሌባና የቀማኛ ዋሻ ልታደርጉ በዙሪያዋ የከበባችሁ መንፈስ አልባ ሥጋ ለባሶች ከሰማያዊነቴ አርማና ምስከር ከቅድስት ቤተ ክርስትያን ትርቁ ዘንድ እለምናችኋለሁ።


አጥንትን የሚያለመልመውን ልቡናን የሚመስጠውን ሰማያዊውን የቅዱስ ያሬድን ጥዑም ዜማ አፍናችሁ የምሕረቱን ዐውድ በገንዘብ ጉዳይና ጨረታ የከፈታችሁ የሥጋ ጠበቆች ከነፍሴ መሸሸጊያ ከማረፊያ ወደቤ ወግዱልኝ፡፡ “እስመ ቅንዓተ ቤትከ በልዓኒ ትዕይርቶሙ ለእለ ይትኤየሩከ ወድቀ ላዕሌየ የቤትህ ቅናት በለታኛለችና የሚሰድቡህም ስድብ በላየ ወድቋል” (መዝ. ፷፰፥፱) እንዲል መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት አቤቱ የቤትህ ቅናት አቃጥሎኛል ነፍሴን ታሳርፋት ዘንድ ጅራፍ አንስተህ ሻጭና ለዋጮችን ከቤተ ክርስቲያን፣ ማደሪያህ ከሆነው ቤተ መቅደስ ከተባለው እኔነቴ ደግሞ ከንቱ ዓለማዊ ሐሳብን አርቀህልኝ ትንሣኤ ልቡናን አድለህኝ ምክንያተኝነቴንና ሰበበኝነቴን አሸቀንጥሬ ጥዬ የነፍሴን ዕረፍት አፋጥን ዘንድ ጣቶችን ወደ ሌሎች መቀሰር ብቻ ሳይሆን ወደ ራሴም ተመልክቼ በመንፈስ እበረታ ዘንድ እርዳኝ፡፡ የነፍስ ዕረፍት ከልቡና ከሐሳብ ይጀምራልና ልቡናየን በምሕረት ከወደቀበት ታነሣልኝ ዘንድ እለምንሃልሁ አዎ ያኔ ነፍሴ ማረፊዋን ታገኛለች ፡፡(ከሐመር መጽሔት የተወሰደ)