የምስጋና ሕይወት

ደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል


የምስጋና ሕይወት የሚኖር ሰው የተደረገለትን ሥራ እና የተፈጸመለትን መልካም ነገር ሁሉ የማይረሳ ለዚህም ምስጋናውን በደስታ የሚገልጽ አዋቂ ሰው ነው፡፡ለእግዚአብሔር እና ለሰዎች የሚያቀርበው ምስጋና በልቡ ጽላት ላይ ተጽፎ የተቀመጠ በመሆኑ ምስጋና ከአንደበቱ ፈጽሞ ጠፍቶ አያውቅም፡፡ኢየሱስ ክርስቶስ ካነጻቸው ከአስሩ ለምጻሞች መካከል አንዱን ባርኮታል፡፡ከእነርሱ አንዱ እነደተፈወሰ ባየ ጊዜ ‹‹በታላቅ ድምጽ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ›› ኢየሱስም መልሶ ‹‹አሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት ሄዱ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔር ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም››አለ፡፡ሉቃ 17-15-18 ስለዚህ ለተደረገልን ነገር ምስጋና ስታቀርብ እግዚአብሔርን እያከበርህ ለአንተ የሰጠህን ፍቅሩን እና ትሕትናውንም እየገለጽህ መሆንህን ተረዳ፡፡እግዚአብሔር በማንም በኩል አንድ መልካም ነገር ካደረገልህ ከእግዚአብሔር በተጨማሪ ያንን መልካም ነገር እንድትቀበል ምክንያት ለሆነህ ሰውም ምስጋና ስጥ፡፡


ብዙ ሰዎች በየዕለቱ መጀመሪያ እና መጨረሻ ላይ በታላላቅ ክብረ በዓላት ላይ እና በሕይወታቸው በሚያጋጥሟቸው ዋና ዋና ጊዜያት ላይ ብቻ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሰጣሉ፡፡ነገር ግን ‹‹ሁል ጊዜ ስለሁሉ አመስግኑ›› ኤፌ 5-20 ፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ስናቀርብ ጊዜና ወቅት ጠብቀን በተለየ ጊዜ ሳይሆን‹‹ሁልጊዜ›› መሆን አለበት፡፡ምስጋናውም ደግሞ የማይቋረጥ እስከሆነ ድረስ መላ የሕይወት ዘመንን ያጠቃልላል፡፡‹‹ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ››1 ተሰ 5፤16-18 ተብሎ ተገልጧል፡፡


ይህ ትምህርት የምስጋና ጸሎት ጸሎቶችን እንደሚመራ ያስረዳል፡፡የሰርክ እና የነግህ ጸሎቶችን ጨምሮ ሁሉም የቤተክርስትያን ሥርዓቶችና አገልግሎቶች የሚጀምሩት በምስጋና ጸሎት ነው፡፡እግዚአብሔር ሁል ጊዜ በማለዳ በቀትር እና በማታ እናመሰግነዋለን፡፡ በማንኛውም ጊዜ በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነን ስለሁሉም ነገር እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፡፡ስለዚህ እግዚአብሔርን ስለሁሉም ነገር ጭምር ማመስገን ያስፈልጋል፡፡ምክንያቱም ሐዋርያው‹‹እግዚአብሔር ለሚወዱት እንደሀሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን፡፡››ሮሜ 8-28 አንዳለ እግዚአብሔር ያለማቋረጥ በጎ ነገር ያደርግልናል፡፡

ምንጭ – አቡነ ሺኖዳ፥ የምስጋና ሕይወት ገጽ 5

ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት

ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት

እንኳን ለታላቁ ሰማዕት ለሰማይ ጭፍራ ለተባለ ለቅዱስ ሚናስ ቤተ ክርስቲያን መርዩጥ በተባለ አገር ለከበረችበት ለቅዳሴ ቤቱ በዓል (ሰኔ 15) በሰላም አደረሰን።


የቅዱስ ሚናስ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት፦ ከዚህ አስቀድሞ የቅዱስ ሚናስ ሥጋ ተሠውሮ ይኖር ነበር ጌታችንም ሊገልጠው በወደደ ጊዜ ምክንያት አደረገ ይኸውም እንዲህ ነው ቅዱስ ሚናስ ሥጋው ተደፍኖ በሚኖርበት ኮረብታ አቅራቢያ በጎችን የሚያረባ አንድ ሰው በጎቹን እየጠበቀ ይኖር ነበር። ከዚያ እረኛ በጎች ውስጥ ደዌ ያለበት አንዱ በግ በዚያ በኮረብታው አጠገብ ባለ የጒድጓድ ውኃ ተጠምቆ ወዲያውኑ ከደዌው ዳነ እረኛውም አይቶ አደነቀ ሌሎችንም ደዌ ያለባቸውን አመጣ በዚያ ውኃም በታጠቡ ጊዜ ሁሉም ዳኑ።


ከዚህም በኋላ ይህ በቦታው ሁሉ ታወቀ ደዌ ያለባቸውም ሁሉ እየመጡ አፈሩን ከውኃው ጋራ አንድ አድርገው ለውሰው በመቀባት ወዲያውኑ ይድኑ ነበሩ ምክንያቱን ግን አላወቁም። በዚያ ውኃና በአፈሩ በሽተኞችን እንደሚያድን የዚያ በግ ጠባቂ ወሬው በሮሙ ንጉሥ ዘንድ ተሰማ ለንሡም የቊስል ደዌ የታመመች ልጅ ነበረችው ወደ በግ ጠባቂውም ላካት እርሱም በጎቹን እንደ አዳናቸው አዳናት። እርሷም በተፈወሰች ጊዜ ከዚያ ቦታ ፈውስ የሚደረግበትን ምክንያት ታውቅ ዘንድ ወደደች።


ከዚህም በኋላ ቅዱስ ሚናስ በሕልም ተገለጸላትና ” ሥጋዬ በዚህ ቦታ ተደፍኖ ስለሚኖር እነሆ አስቆፍረሽ ታወጪው ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል” አላት። ከእንቅልፍም በነቃች ጊዜ ቅዱስ ሚናስ እንዳዘዛት አደረገች የከበረ ሥጋውንም አወጣች በዚያም ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ሠራችለት ንጉሡም በዚያ ቦታ ከተማ እንዲሠሩ መኳንንቱንና ሹሞቹን አዘዛቸው ታላቅ ከተማም ተሠራች ስሟም መርዩጥ ተባለች።

እግዚአብሔር ከቅዱስ ሚናስ ሥጋ ቊጥር የሌላቸው ድንቆችንና ተአምራትን ገለጠ። ሊቀ ጳጳሳቱም ከኤጲስቆጶሳቱ መጥቶ ቤተ ክርስቲያኒቱን በዛሬዋ ሰኔ 15 ዕለት አከበራት በዚያቺም ቦታ የሚሠሩ የድንቆችና የተአምሮች ወሬ በቦታው ሁሉ ተሰማ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሚናስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ምንጭ፦ የሰኔ15 ስንክሳር።


“ሰላም ለቅዳሴ ቤትከ እንተ ተሐንፀት በመርዩጥ። በትእዛዝ ንጉሥ ሥሉጥ። ሚናስ ዘአንቃሕከ በድነ ሐራውያ እምጸጥ። አስተዋጺኦሙ ዕደው ዘበበ፪ቱ ቂራጥ። መባአ ለከ ዘነሥኡ በሤጥ”። አርከ ሥሉስ(አርኬ) የሰኔ 15።


“ሰላም ለሚናስ ኅሩይ ዘክርስቶስ ሐራይ ጽድቀ ዘአብደረ እምነ ንዋይ፤ አምሳለ ወርኅ ወከመ ፀሓይ ብሩህ”። ትርጉም፦ የክርስቶስ ምርጥ ጭፍራ ከገንዘብ ይልቅ ጽድቅን የመረጠ እንደ ምሳሌው እንደጨረቃ ለደመቀና እንደ ፀሓይም ብሩህ ለኾነ ለሚናስ ሰላምታ ይገባል።

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ።

እግዚአብሔርን መፍራት


ብልህ ሰው መንገዱን ከመነሻው ይጀምራል ይህም እግዚአብሔርን ከመፍራት ነው፡፡ ይህ ፍርሀት ደግሞ በሂደት ወደ እግዚአብሔር ፍቅር ይመራዋል፡፡ አንድ ሰው ኃጢአትን እስካደረገ ወይም የኃጢአት ምኞት በልቡ እስካለ ድረስ በውስጡ ፈሪሀ እግዚአብሔር አይኖርም፡፡ስለዚህ ሰው እግዚአብሔርን ከመፍራት መጀመር ይገባዋል ኃጢአትን የማድረግ ፍላጎት በውስጡ ቢኖር እንኳን ንስሐ ገብቶ ከኃጢአቱ መራቅ አለበት፡፡ብዙ ይፍጨረጨራል ትዕዛዛቱን ለመፈፀም እራሱን እስከማስገደድ ይደርሳል፡፡ጸሎትን፣ቃሉን ማንበብና ማሰላሰልን እንዲሁም ውዳሴን የመሳሰሉትን የፀጋ መንገዶች ይከተላል፡፡


የመንፈሳዊ መንገድ ጀማሪ ገና ከኃጢአት ነፃነትን አልተቀዳጀም ስለዚህ እራሱን ከኃጢአት ያርቃል፡፡ይህን የሚያደርገው የእግዚአብሔር መንፈስ እንዳያሳዝንና እንዳያስቆጣ የቅጣቱም ተካፋይ እንዳይሆን ነው፡፡ትዕዛዙንም በፈጸመ ቁጥር በእነርሱ መደሰት እና መውደድ ይጀምራል፡፡ብዙ ሽልማት እንዳገኘ ሰው ሀሴት ያደርጋል፡፡ መልካም ማድረግን ይወዳል፡፡ ቀምሶ ወደ ወደዳቸው ንፅህና ቅድስናና መንፈሳዊነት የመራውን ትዕዛዝም ያፈቅራል፡፡እግዚአብሔርን በመፍራት ሳንኖር ፍቅሩን ልናገኝ እንችላለን ብለን ማሰብ ፍፁም ስህተት ነው፡፡ፈሪሀ እግዚአብሔር ብቻ ነው ልብን አንጽቶ የመንፈስ ቅዱስ መኖሪያ እንዲሆን ሊያበቃው የሚችለው፡፡መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በልባችን የእግዚአብሔር ፍቅሩ ያፈሳል፡፡በዚህ መንገድ ነው እንግዲህ ሰው ከፈሪሀ እግዚአብሔር ወደ ፍቅሩ መሸጋገር የሚችለው፡፡
ይህ ሽግግር ግን በአንዴ የሚሆን አይደለም፡፡ ከብዙ ትግልና የፀጋ ተግባር በኋላ የሚደርስበትን ሊሆን ይችላል፡፡እንዲህ ባለ ትግልና ጥረት ውስጥ ነው ቁርጠኝነቱንና ልፋቱን ለእግዚአብሔር የሚያረጋግጠው፡፡ እግዚአብሔርም ውሳኔውን ሲያይ ፍቅሩን በልቡ ከማፍሰስም አልፎ ኃጢአት በውስጡ ከፈጠረው ግጭት ያጽናናዋል፡፡ ከመውደቅ ፍርሃትም ያበረታዋል፡፡


ሰው እግዚአብሔርን እወዳለው እያለ ከፍቅሩ በጣም ሊርቅ ይችላል፡፡<<ትዕዛዙን በእርሱ ዘንድ ያለች የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ>> ዮሐ 14-21 ብሎ ይናገራል፡፡ በዚህም መሠረት እግዚአብሔርን እወዳለው እያሉ ትዕዛዙን መተላለፍ የሚቻል አይደለም፡፡ ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ << የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈፅሟል፡፡>> 1ዮሐ 2÷4-5፡፡ ስለዚህ ከሁሉ አሰቀድመን ትዕዛዛቱን ለመጠበቅ የሚገፋፋንን ፈሪሀ እግዚአብሔር ልንይዝ ይገባል፡፡


ኃጢአት የሚያደርግ ማንኛውም ሰው የፍቅርም ሆነ የፍርሀት ደረጃ ላይ አልደረሰም ገና መንፈሳዊውን ጉዞ አልጀመረም፡፡ እግዚአብሔርን ባለመታዘዝ እስከኖረ ድረስ አይወደውም አይፈራውምም ከብርሃን ርቆ ገና በጨለማ ነው ያለው፡፡

✍አቡነ ሺኖዳ እግዚአብሔርን መፍራት ገፅ 82

አንዳንድ ነገሮች ስለ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት

ቅዱስ ላሊበላ ዓሥሩንም ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በጣም በሚያስገርም ሁኔታ በውስጥና በውጭ ያሉት ብዙ ቅርጾች ነገረ ድኅነትን በምሳሌ እንዲወክሉ አድርጎ ነው ያነጻቸው፡፡ የክርስቶስን መከራና በእርሱም የተገኘውን ፍጹም ዘላለማዊ ድኅነት በእያንዳንዱ ቤተ መቅደስ ውስጥ እንዴት አድርጎ በምሳሌ እንዳስቀመጠው እጅግ አስገራሚ ነው፡፡


በላስታ ቅዱስ ላሊበላና አካባቢው የሚገኙ ሌሎች አስደናቂ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፡-

ከአሥሩ የቅዱስ ላሊበላ አስደናቂ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በተጨማሪ የቅዱስ ነአኵቶለአብና የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም አሸተን ማርያም በዋናነት ሕዝበ ክርስቲያኑ የሚጐበኛቸው ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡ በላሊበላና አካባቢው ግን እጅግ ጥንታዊና አስደናቂ የሆኑ በጣም በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ሣርዝና ሚካኤል፣ ብልባላ ቂርቆስ፣ ብልባላ ጊዮርጊስ፣ አርባዕቱ እንስሳ፣ ትርኩዛ ኪዳነምሕረት፣ ገነተ ማርያም፣ ቀንቀኒት ሚካኤል እነዚህ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሲሆኑ እንዲሁም ዋልድቢት ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም፣ አቡነ ዮሴፍ ገዳም፣ ገብረ ክርስቶስ ዋሻ ቤተክርስቲያን፣ ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን፣ ቀደሊት ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ እመኪና መድኃኔዓለምና እመኪና ልደታ፣ ማውሬ እስጢፋኖስ፣ የቅዱስ ገብረ ማርያም ቤተክርስቲያን፣ ማይ ማርያም ቤተክርስቲያን፣ ተከዜ ኪዳነምሕረትና መድኃኔዓለም አንድነት ገዳም ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዳንዶቹ ከ485-536 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በዐፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት የታነጹ ናቸው፡፡ ሌሎቹንና በሰሜን ላስታ ያሉትን ደግሞ እነ ላሊበላና ይምርሃነ ክርስቶስ አንጸዋቸዋል፡፡

ቅዱስ ላሊበላ እኛ ከምናውቃቸው ከድንቅ ሥነ ሕንፃዎቹ ሥራ በተጨማሪ ከሺህ ዓመታት በፊት በሥዕል፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሃይማኖት፣ በኢኮኖሚ፣ በውጭ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙትና በመሳሰሉት ሁሉ እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ቅዱስ ላሊበላ ከሺህ ዓመታት በፊት አዳራሾችን፣ ፎቆችን፣ የውስጥ ለውስጥ መተላለፊያዎችን፣ የእንግዳ መቀበያዎችን፣ የሕፃናት ማሳደጊያዎችን፣ የሕሙማን መፈወሻዎችን፣ የሕንፃ መሳሪያዎችን፣ የትምህርት ማዕከሎችን፣ የመደጎሻ ቦታዎችን ያቋቋመ መሆኑን የብራና ገድሉ እንደሚናገር የደብሩ አባቶች ይገልጣሉ፡፡ ወደፊት ተርጎመው እንሚያቀርቡልን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ቅዱስ ላሊበላ ከዚህ በተጨማሪ የግእዝ ቋንቋን በጽሑፍ አበልፅጎ ያቆየ ባለውለታ ነው፡፡ ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ውጭ ሌሎችንም በርካታ ቤተ መቅደሶች ሠርቷል፤ ከሀገራቸንም አልፎ በሱማሌ ሞቃዲሾ ላይ መቅደሰ ማርያም የተባለች ቤተክርስቲያን ሠርቷል፡፡ ክርስትናን ከግብፅ ምድር ጨርሰው ለማጥፋት ተንባላት በተነሡ ጊዜ ዓባይን ሊያግድባቸው ሲነሣ በብዙ ምልጃና ልመና ስለማራቸው በሀገሪቱ ውስጥ ክርስትና እስካሁን እንዲቆይ የራሱን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ ቅዱስ ላሊበላ ነቢይም ሆኖ፣ ሐዋርያም፣ ጻዲቅም፣ ሰማዕትም ሆኖ ጥበብ መንፈሳዊንና ጥበብ ሥጋዊን ከእግዚአብሔር ተሰጥቶት ንግሥናንና ክህነትን፣ ቅድስናንና ንጽሕናን በሚገባ አስተባብሮ በማያዝ እግዚአብሔርንም ሰውንም በቅንነት ሲያገለግል ኖሮ ሰኔ 12 ቀን 1197 ዓ.ም ከፈጣሪው ታላቅ ቃልኪዳን ተቀብሎ በዝማሬ መላእክት፣ በመዝሙረ ዳዊት ቅድስት ነፍሱ ከሥጋው ተለይታ ሰማያዊ ክብርን ወርሷል፡፡ ክቡር ሥጋውም ራሱ ባነጸው ቤተ ሚካኤል መቅደስ ሥር በክብር ዐርፏል፡፡

መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለቅዱስ ላሊበላ የገባለት ልዩ ቃልኪዳን፡-ወደ ሰማይ ነጥቆ ወስዶት በዙፋኑ ፊት የሰጠው ቃልኪዳን፡- ‹‹ዛሬ በዚህች ቀን ከአንተ ጋር እነሆ ኪዳኔን አጸናሁ፡፡ በጸሎትህ ኃይል ታምኖ በውስጣቸው የሚያመሰግን ትሠራቸው ዘንድ ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የደረሰ ሁሉ አንተን አስቦ ‹አቤቱ ፈጽመህ ይቅር በለኝ› የሚለኝ፣ ‹ይህን የሚያስደንቅ ሥራ በእጁ ስለገለጥክለት ስለ ባሪያህ ስለ ቅዱስ ላሊበላ ብለህ ይቅር በለኝ› እያለ የሚጸልየውን በዚያ ጊዜ እኔ ጸሎቱን እሰማዋለሁ፡፡ ከሕፃንነቱ ጀምሮ የሠራውን ኃጢአት ሁሉ አስተሠርይለታለሁ፤ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ እንደ እንደተወለደባት ቀን የነፃ አደርገዋለሁ፡፡ የዕዳ ደብዳቤውንም በእጅህ ትቀደው ዘንድ ለአንተ እሠጥሃለሁ፤ ዕድሜውንም በምድር ላይ አረዝምለታለሁ፤ ቤቱንና ንብረቱን ሁሉ እባርክለታለሁ፤ በተንኮል የሚከራከረው ቢኖር ድል እንዳይነሣው አሠለጥነዋለሁ፤ እግሮቹ እየተመላለሰ ወደ ቤተክርስቲያን የገሠገሠ ሁሉ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት በኤዶም ገነት ውስጥ እንዲመላለስ አደርገዋለሁ፤ መባዕ የሚያገባ ሁሉ ጥቂትም ቢሆን ብዙም ቢሆን በእጅህ ከምሠራው ከቤተ መቅደሴ የሚያመጣውን መባዕ ሁሉ ቀኝ እጄን ዘርግቼ ከእጁ ፈጽሜ እቀበለዋለሁ፡፡ ከዕጣንም ወገን በየአይነቱ ያገባ ቢኖር እንደሰው ልማድ ሥጋዬን እንደቀባበት እንደ ኒቆዲሞስ ሽቱ እቀበለዋለሁ፣ በቢታንያ እንደቀባችኝ እንደ ማርያም እንተ ዕፍረት ሽቱ መዓዛውን አሸትለታለሁ፤ ስለ ማርያም እንተ ዕፍረት እስከ ዓለም ዳርቻ ሁሉ የመንግሥቴ ወንጌል በተሰበከበት ስሟን ይጠሩ ዘንድ እንዳዘዝኩ ሁሉ ትጉሃን በሚሆኑ በሰማያውያን መላእክት ከተሞች ስሙን ይጠሩት ዘንድ አዛለሁ፡፡ ለመብራት የሚሆን ዘይት ቢያገባ በይቅርታዬ ዘይትነት ራሱን አወዛዋለሁ፡ ሰውነቱ ለዘለዓለሙ አይሻክርም፣ ከፊቱም የብርሃን መብራት አይጠፋም፡፡ ወደ ሠርግ ቤት ከሚገቡ መብራታቸው ካልጠፋባቸው ከልባሞች ደናግል ጋር በመጣሁ ጊዜ በደስታ ይቀበለኛል፡፡››

በኢየሩሳሌም ሳለ ጌታችን የስቅለቱን መከራ በራእይ ካሳየው በኋላ የሰጠው ቃልኪዳን፡- ‹‹ለሌሎቹ ጻድቃን ከዚህ ዓለም በሞት በሚለዩበት ወቅት በፍጹም ልቡናቸው እንደሚገባ ያገለገሉኝን ዋጋቸውን ሰጠኋቸው፣ ለአንተ ግን በሞት የምትለይበት ጊዜ ሳይደርስ በሕይወትህ ሳለህ ኪዳንን ሰጠሁህ፡፡ ማደሪያህ ከጳውሎስና ከጴጥሮስ ጋር ይሆናል፡፡ አቀማመጥህ በቀኜ ነው፣ ደቀ መዛሙርቴን በ12 ወንበር ተቀምጣችሁ በ12ቱ ነገደ እስራኤል ትፈርዳላችሁ እንዳልኳቸው አንተም ወንበርህ ከወንበራቸው አያንስም፤ ብርሃንህ ከብርሃናቸው፣ ክብርህ ከክብራቸው አያንስም፤ ኪዳንህም ከሰጠኋቸው ኪዳን አያንስም፤ ርስትህ ዕድል ፈንታህ ከእነርሱ ጋር ነው፡፡ የሰጠሁህን ቃልኪዳንና ገድልህን የሚያቃልል ሁሉ ዕድል ፈንታው ከአንተ ጋር አይሁን፣ ርስት ጉልቱም ከአንተ ርስት ጉልት አይገኝም፤ የጸናሁልህን ቃልኪዳን የማያምን ያ ሰው እኔን ክርስቶስን እግዚአብሔር አይደለም እሩቅ ብእሲ ነው እንጂ እንደሚለኝ ሰው ይሁን፡፡ መጽሐፍህን ሰምቶ የተቀበለ ሁሉ የመንግሥቴን ወንጌል እንደተቀበለ ይሁን፤ አንተን ያከበረ እኔን እንዳከበረ ይሁን፡፡ ደቀ መዛሙርቴን እናንተን የሰማ እኔን የሰማ ነው፣ እናንተን የካደ እኔን የካደ ነው እንዳልኳቸው አሁንም አንተን የሰማ ቃልኪዳንህንም ያመነ እኔን ጌታህን የሰማ ነው እልሃለሁ፡፡ መከራህንና ቃልኪዳንህን የካደ ሰው ቢኖር እኔ በምድር የተቀበልኩትን መከራ እንደ ካደ ሰው ነው፡፡ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በጸሎትህ ኃይል የታመኑ ሁሉ ማደሪያቸው ከአንተ ጋር ይሁን፤ ለቤተክርስቲያኖችህ አምኃ የሰጠ ቢኖር እንደ ደሜ ፍሳሽ እንደ ሥጋዬ ቁራሽ አድርጌ እቀበለዋለሁ፡፡››

ቤተ መቅደሶቹን ሠርቶ ከጨረሰ በኋላ ጌታችን የሰጠው ቃልኪዳን፡- ቅዱስ ላሊበላ ጌታችን ባሳየውና ባዘዘው መሠረት አብያተ ክርስቲያናቱን አንጾ ከጨረሰ በኋላ በቀኝና በግራው ዓሥር ዓሥር ኪሎ የሚመዝን የዓለት ድንጋይ ተሸክሞ ለ7 ዓመት ሲጾም ሲጸልይ ከኖረ በኋላ ጌታችን ተገልጦለት በፊት የገባለትን ቃልኪዳን በዚህም ጊዜ በድጋሚ አረጋግጦለታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹…ወደ ደጅህ የመጡት ሁሉ አስራት ይሁኑልህ፣ አንተ ከገባህበትም ይግቡ፣ አንተንም ከ12ቱ ሐዋርያት ጋር በፍርድ ቀን 13ኛ አደርግሃለሁ፡፡ ያነጽካቸውን ቤተ መቅደሶች የተሳለመውን ኢየሩሳሌምን እንደተሳለመ አደርግለታለሁ፤ መታሰቢያህን ያደረገውን፣ ገድልህን የጻፈውን ያጻፈውን፣ በዚህ ቦታ ላይ መጥቶ አማልደኝ ያለውን፣ በአማላጅነትህ የተማጸነውን ሁሉ እስከ 15 ትውልድ ምሬልሃለሁ›› ብሎ የመጨረሻውን ቃልኪዳን ሰጥቶታል።

ሰላም ለላሊበላ ሐናጼ መቅደስ በጥበብ
በዕብን ይቡስ እንበለ መሬት ርጡብ
በዘይትአመር ሎቱ ምስፍና ወምግብ
ዝንቱ መዓር ተድላ ነገሥት ወሕዝብ
በእለተ ተወልደ ተዐግተ በንህብ

( በመንፈስ ቅዱስ ጥበብ ከዕንጨት እና ከጭቃ ያይደለ ድንጋዮች እንደ ጭቃ እየተሳቡለት ቤተ መቅደሶቹን ላነጸ ንጉሥ ላሊበላ ሰላምታ ይገባል። ነጋሢነቱን እና ምስፍናውን ይጠይቅለት ዘንድ የነገሥታት እና የምዕመናን ሁሉ ደስታ ይሆን ዘንድ ጻድቅ ላሊበላ በተወለደ ጊዜ በንብ ተከበበ። )

ከቅዱስ ላሊበላ ረድኤት በረከት ይክፈለን!!!

ተዝካረ በዓሉ ለቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት (ሰኔ 12)


ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የሚበር ንሥረ አርያም የሚባል ውዳሴው እንደ ማር የጣፈጠ ንዑድ ክቡር የሆነ
የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል አፎምያን ያዳነበት ዕለት ነው፡፡ ዳግመኛም ይህች ዕለት የባሕራንን የሞት ደብዳቤ ቀዶ ለታላቅ ክብር ያበቃባት ዕለት ናት፡ ዳግመኛም ይህች ዕለት ቅዱስ እለ እስክንድሮስ አንድን ቤተ ጣዖት አፍርሶ ከቦታው ላይ ቤተ ክርስቲያን ሠርቶ ታቦተ ሚካኤልን አግብቶ በዓሉን በደስታ በሐሴት ያሳለፈባት ዕለት ናት፡፡

ሚካኤል ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ሚ-መኑ’ ካ-ከመ’ ኤል- አምላክ ማለት ሲሆን በአንድነት ሲነበብ መኑ ከመ አምላክ (እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው? ማለት ነው፡፡ አንድም ለእግዚአብሔር አሸናፊ ድል አድራጊ የቸርነትና የርህራሄ መገኛ መዝገብ ማለት ነው፡፡

ይህ ታላቅ መልአክ ዮሐንስ ወንጌላዊ በራዕዩ ‹‹በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ›› ብሎ ከተናገረላቸው መላእክት ውስጥ የሚመደብ ሲሆን የሰባቱም ሊቃነ መላእክት አለቃ እንዲሆን እግዚአብሔር መርጦ ሹሞታል፡፡ ይህ ታላቅ መልአክ ያደረጋቸው የሠራቸው እጅግ ብዙ የሆኑ ተአምራት አሉት።

ስለዚህ ስለ ታላቁ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ክብር፤ ጠባቂነትና አማላጅነት ከአባቶቻቸው የተማሩትን በኑሮአቸው ያዩትን አባቶቻችን ጽፈዋል፡፡ ስለ ቅዱስ ሚካኤል ከጻፉት አባቶች መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡

  • ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
  • ኤዎስጣቴዎስ ዘአንጾኪያ
  • ቅዱስ መቃርስ
  • ቅዱስ ያሬድ
  • አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
  • አባ ዲማቴዎስ ሊቀ ጳጳሳት ዘእስክንድርያ ናቸው።

እኛም የአባቶቻችንን አንደበት አንደበታችን አድርገን በኅዳር 12 ክቡር ገናና የሆነ ቅዱስ ሚካኤል ካደረጋቸውና ከሠራቸው ብዙ ተአምራት ውስጥ የተወሰኑትን በመልአኩ ተረዳኢነት እንዲህ ብለን እንናገራለን አንጽፋለን፡፡

ጥንተ ነገሩ እንዲህ ነው፡- ንግስት ክሌዎፓትራ ‹‹ሳተርን› ለሚባለው ጣዖት የሠራችው ቤተ ጣዖት በእስክንድርያ ነበር፡፡ ይህ ቤተ ጣዖት እስከ እስክንድርያው ፓትርያርክ እለ እስክንድሮስ /312 – 326/ ዘመን ድረስ ነበር፡፡ እለ እስክንድሮስ ሊያጠፋው ሲነሣ ሕዝቡ ከልቡ ገና የአምልኮ ጣዖት ስላልጣፋ “18 ፓትርያርኮች ያልነኩትን አንተ ለምን ታፈርስብናለህ?” ብለው ተቃወሙት፡፡ እለ እስክንድሮስም ሕዝቡን መክሮና አስተምሮ የሳተርን በዓል ይውልበት በነበረው ዕለት የቅዱስ ሚካኤልን በዓል እንዲያከብሩ አውጆ
ቤተ ጣዖቱንም በቅዱስ ሚካኤል ስም ሰይሞ ቤተክርስቲያን አደረገው።
ሕዝቡ በየዓመቱ መሥዋዕት እየሠው ተረፈ መሥዋዕቱን እየተመገቡ እየዘፈኑ እያጨበጨቡ ያከብሩ ነበር፡፡ ታላቁ ጻድቅ ንጉሥ ቁስጠንጢኖስ “አብያተ ጣዖታት ይዘጉ አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ” ብሎ ካወጀ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት እለ እስክንድሮስ ቤተ ጣዖቱን አፍርሶ ከቦታው ላይ ቤተ ክርስቲያን ሠርቶ ታቦተ ሚካኤልን አግብቶ በዓሉን በደስታ በሐሴት አሳለፉት፡፡ እለ እስክንድሮስም ሕዝቡን የጣዖቱን በዓል ተው “ይህን የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤልን በዓል አክብሩ” ብሎ በየዓመቱ በዚህ ቀን በዓል እንዲሆን ሥርዓት ሠራላቸው፡፡ ይህንንም የቅዱስ ሚካኤልን በዓል ከሚያከብሩ ምእመናንን አንዱ የባሕራን አባት ነበር፡፡

እርሱም እግዚአብሔርን እጅግ አድርጐ የሚፈራ ወር በገባ በየዐሥራ ሁለቱ ቀን የቅዱስ ሚካኤልን ዝክሩን የሚዘክርና ይልቁንም በኅዳር ዓሥራ ሁለትና በሰኔ ዓሥራ ሁለት ቀን በታላቅ ክብር የሚያከብር አንድ ሰው ነበር። ለዚህ እግዚአብሔርን ለሚፈራ ሰውም ርኅራኄ የሌለው በእርሱም ላይ ጥላቻ ያደረበት አንድ በለጸጋ ጐረቤት ነበረው፡፡ የቅዱስ ሚካኤልን በዓል በሚያከብርበት ጊዜ ሁሉ ይዘብትበት ይሳለቅበት ነበር።
ይህ እግዚአብሔርን ለሚፈራ ሰውዬ በዚህ ዓይነት በጐ ሥራ ብዙ ጊዜ ከኖረ በኋላ ከዚህ ዓለም ድካም ያርፍ ዘንድ የሞቱ ጊዜ ቀረበ። ሚስቱንም ጠርቶ “በጐ ስራ ከመሥራት ለድኃ ከመመጽወት ቸል አትበይየቅዱስ ሚካኤልንም በዓል በየወሩ ከማክበር አትቦዝኝ ይልቁንም በኅዳር ዓሥራ ሁለትና በሰኔ ዓሥራሁለት ቀን ከፍ ባለ ሥነ ሥርዓት እንድታከብሪ አደራ እልሻለው” አላት፡፡ በሚሞትበትም ጊዜ ሚስቱ ፀንሳ ነበር። ይህም ደገኛ ሰው በሰላም ዐረፈና ፍጹም መንግሥተ ሰማያትን ወረሰ።ከዚህም በኋላ ሚስቱ የመውለጃዋ ጊዜ ተቃርቦ ነበርና ምጥ ይዟት በታላቅ ጭንቅ ላይ እንዳለች “አንተ የእግዚአብሔር መልአክ ሆይ በእኔ ላይ ይቅርታን አውርድ ከዝህ ከደረሰብኝም ጭንቅ ይገላግለኝ ዘንድ ስለኔ እግዚአብሔርን ለምንልኝ አንተ ከእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ባለሟልነት ተሰጥቶሃልና” እያለች ለመነች። ይህንንም በምትልበት ጊዜ ያለችበት ቤት በብርሃን ተመላ ከጭንቋም ዳነችና መልኩ በጣምያማረ ልጅ ወለደች። የእግዚአብሔር መልእክተኛ ቅዱስ ሚካኤልም ከሰማይ ወርዶ ያን ሕፃን ባረከውና “ቸርነት ርኅራኄ የሌለውን የዚህን ባለጸጋ ገንዘብና ሀብት እርሻውንም ሁሉ ይህ ሕፃን እንዲወርስ እግዚአብሔር አዟል” አለ። ያን ጊዜ ያ ባለጸጋ በሴትዮዋ ቤት መስኮት አጠገብ ሆኖ ሁኔታውን ሁሉ ይመለከት ነበርና ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ልቡ በታላቅ ኅዘን ተነካ፤ ሕፃኑንም የሚገድልበትን ምክንያት ይፈልግ ጀመር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በቅዱስ ሚካኤል ጸሎት ብላቴናውን ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቀው
ነበር።


ብላቴናውም ዓሥር ዓመት በሆነው ጊዜ እናቱ በጣም ችግር ፀናባት፡፡ በዚህን ጊዜ እምነት የጐደለው ያባለጸጋ “አንቺ ችግረኛ ስለሆንሽ ይላከኝ ያገለግለኝ ዘንድ ልጅሽን ስጭኝና ምግቡንና ልብሱን ምንም ሳላጐድል ተንከባክቤ አኖረዋለው ለአንቺም ሃያ ወቄት ወርቅ እሰጥሻለው” አላት። ይህንንም ባላት ጊዜ ስለ ችግሯ በጣም በመደሰት ልጅዋን ሰጠችውና ሃያውን ወቄት ወርቅ ተቀበለች፡፡ ብላቴናውንም በወሰደ ጊዜ እንግዲህ ሃሳቤ ሁሉ ዛሬ ተፈጸመልኝ እያለ በጣም ደስታ ተሰማው፡፡ ከዚህ በኋላ በልጅ ቁመት ልክ ሳጥን አሠርቶ ሕፃኑን በሣጥኑ ውስጥ አግብቶ በላዩ ላይ ቆለፈበትና ሣጥኑን ወስዶ ከባሕር ጨመረው፤ እንዲሁም የሣጥኑን ቁልፍ መክፈቻ አብሮ ወረወረው። ነገር ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ ያ ሣጥን ሳይሰጥም በባሕሩ ላይ እየተንሳፈፈ ከዚያች አገር ርቃ ወደምትገኝ የባሕር ወደብ ደረሰ።

በባሕሩ አካባቢ በጎቹን አሰማርቶ የሚጠብቅ አንድ ሰው ነበርና ያንን ሣጥን ባየው ጊዜ ከባሕሩ አወጣውና
ወደ ቤቱ ወሰደው። እቤቱም በደረሰ ጊዜ “ይህን ሣጥን በምን እከፍተዋለሁ?” እያለ ሲያወጣ ሲያወርድ
ተመልሶ ወደ ባሕሩ ይሄድ ዘንድ እግዚአብሔር አሳሰበው፤ በሄደም ጊዜ አንድ ዓሣ የሚያጠምድ ሰው አገኘና ዓሣ አጥማጁን “በኔ ስም መረብህን ወደ በሕር ጣልና የተሠገረው ዓሣ ለኔ ይሆናል ዋጋውን ግን እከፍልሃለው” አለው፡፡ ዓሣ አሥጋሪውም እንደ ተነጋገሩት መረብን ከባሕር ቢጥል ታላቅ ዓሣ ተያዘና ለሰውየው ሰጥቶት ዋጋውን ተቀበለ። እሱም ያንን ዓሣ ከቤተሰቦቹ ጋር ጠብሶ ይበላ ዘንድ በችኮላ ወደ ቤቱ ሄደና ያሣውን ሆድ ቢሰነጥቀው የዚያን የሣጥን ቁልፍ መክፈቻ አገኘ፡፡ በዚያን ጊዜ ይህ መክፈቻ የዚህ ሣጥን ቁልፍ መክፈቻ መሆን አለበት ሲል አሰበና ቁልፉን ለመክፈት ቢሞክር ወለል ብሎ ተከፈተ።
በዚህም እየተደነቀ ሳለ ሣጥኑን ቢከፍተው ያ ባለ ፀጋ ሊገድለው ያሰበውን ሕፃን በሣጥኑ ውስጥ አገኘው።
ባየውም ጊዜ እጅግ ተደስቶ በባሕር ውስጥ ስላገኘው ስሙን “ባሕራን” ብሎ ሰየመውና እንደ ልጁ አድርጐ
ይንከባከበው ዘንድ ወሰነ፡፡

ከባሕራን ሀገር የበግ ጠባቂው አገር የዓሥር ቀን ጐዳና የሚያስኬድ ርቀት ነበረው። ከብዙ ዓመታት በኋላ
ያ ባለ ጸጋ ሰው ለንግድ ከሀገሩ ወጣ፡፡ በጉዞውም ላይ ሳለ ፀሐይ ስትገባ ከዚያ የበግ ጠባቂው ዘንድ ደረሰ።በግ ጠባቂውንም “ወንድሜ ሆይ ባንተ ዘንድ የማድርበት ቢኖር ታሳድረኝ ዘንድ እለምንሃለው፣ ኪራዩንም እከፍልሃለው” ብሎ ጠየቀውና ያ በግ ጠባቂ ወደ ቤቱ አስገባው። ባለጸጋውም ገብቶ ጥቂት ካረፈ በኋላ በግ ጠባቂው ያን ብላቴና ባሕራን ብሎ ሲጠራው በሰማ ጊዜ “ልጅህ ነውን?” ብሎ ጠየቀው። በግ ጠባቂውም “አዎን ይህ አሁን ጐልማሳ ሆኖ የምታየው ወጣት ገና ሕፃን ሆኖ ሳለ በሣጥን ተከቶ ከባሕር ውስጥ
ተጥሎ አግኝቼው ወስጄ አሳድጌዋለሁና ልጄ ነው” አለው። ባለጸጋውም በባሕር ውስጥ የጣለው ሕፃን መሆኑንም ስላወቀ ይህንን ነገር በሰማ ጊዜ ፈጽሞ ደነገጠ፤ ይገድለውም ዘንድ ፈለገ፡፡ በበነጋውም መንገዱን ለመሄድ ሲዘጋጅ ልዩ ልዩ ምክንያት (ሰይጣናዊ ሃሳብ) በመፍጠር በግ ጠባቂውን “ወንድሜ ሆይ አንድ የማስቸግርህ ጉዳይ አለኝ ይኸውም በቤቴ የረሳሁት ነገር ስላለ ዕገሊት ወደ ምትባል ሀገር ሄዶ መልእክት ያደርስልኝ ዘንድ ይህን ብላቴና እንድትሰጠኝ ነው የድካሙንም ዋጋ ሃያ ወቄት ወርቅ እከፍላለሁ” አለው።

ያም በግ ጠባቂ ስለ ወርቁ ስጦታ ደስ በመሰኘት ያን ጐልማሳ ጠርቶ “ልጄ ባሕራን ሆይ ይህ ክቡር ሰው ለሥራ ጉዳይ ወደ ቤቱ ሊልክህ ይፈልጋልና መልእክቱን አድርስለት እግዚአብሔር በሰላም ያግባህ” ሲል ጠየቀው፡፡ ልጁም “እሺ መልካም ነው አባቴ ሆይ ያዘዝከኝን ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁ ነኝ” አለው። ከዚህም በኋላ ያ ባለጸጋ “ይህችን የመልእክት ደብዳቤ ይዞ ወደ አንተ የመጣውን ስሙ ባሕራን የተባለውን
መልእክቷ በደረሰችህ ጊዜ ፈጥነህ ግደለው ገድለህም ሬሣውን ከጉድጓድ ጣለው እኔ በሰላም ተመልሼ እስክመጣ ድረስ ማንም ማን ይህን ምሥጢር አይወቅ” የሚል ጽሑፍ ለሹሙ ጽፎ አዘጋጀ፡፡ እንዲሁም በሹሙና በእርሱ መካከል የሚተዋወቁበትን ማኅተም በደብዳቤው ላይ አትሞ ለባሕራን ሰጠው፡፡ ለመንገዱም የሚሆነው ስንቅ ሰጥቶ ላከው። ባሕራንም መልእክቱን ለማድረስ ዘጠኝ ቀን ተጉዞ የአንድ ቀን ጎዳና ሲቀረው እነሆ ክቡር የሚሆን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በንጉስ ጭፍራ አምሳል በፈረስ ተቀምጦ ወደሱ ደረሰና ወዴት እንደሚሄድ ጠየቀው፡፡ባሕራንም “ከአንድ ባለጸጋ ሰው የተጻፈ ደብዳቤ ይዤ እርሱን ለማድረስ ዕገሊት ወደምትባል አገር እሄዳለሁ” አለው። ንዑድ ክቡር የሚሆን ቅዱስ ሚካኤልም “እስኪ የመልእክቱን ደብዳቤ አሳየኝ?” አለው፡፡ ባሕራንም “ጌታዬ ለማንም አታሳይ ብሎኛል” አለው፡፡ መልአኩም “እሺ ያም ባይሆን እንደተጠቀለለ አሳየኝ” አለው፡፡ ባሕራንም አሳየው፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም በሞቱ ደብዳቤ ላይ እፍ ቢልበት የሞቱን ትእዛዝ አጥፍቶ
የሕይወት ትዕዛዝ ጽፎበታል፡፡ በደብዳቤው ላይ የተጻፈውን የሞት መልእክት ደምስሶ “ከእኔ ከባለጸጋ ዕገሌ የተጻፈ” ይልና “ይህን መልእክት ይዞ ለመጣሰው ዕገሊት የምት ባለዋን ልጄን አጋቡት (ዳሩለት) በዱር የተሰማራውን ከብቴን በቤት ያለውን ሀብቴን በጠቅላላው የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረቴን በሙሉ አውርሼዋለሁና እኔ እስክመጣ ድረስ አትጠብቁ በሄድኩበት ሀገር የምቆይበት ጉዳይ አለኝና፤ በቤቴና በንብረቴ ላይ ሙሉ ሥልጣን ሰጥቼዋለሁና የወደደውን ያደርግ ዘንድ አትከልክሉት ስለዚህም በእኔና በአንተ መካከል የምንተዋወቅበትን ምልክት አድርጌበታለሁ” የሚል ጽሑፍ ጽፎ ሰጠውና “እንግዲህ ወደ ባለጸጋው ቤት ሂድና ይህን መልእክት አድርስ ነገሩ እንዳይገለጽብህ ከእኔ ጋር መገናኘታችንንና የመልእክቱን ጽሑፍ እንደለወጥኩልህ ለማንም አትንገር” ሲል አስጠነቀቀው፡፡ ባሕራንም “እሺ ጌታዬ እንዳዘዝከኝ አደርጋለሁ” ብሎ ጉዞውን ቀጠለና የዚያን የባለፀጋ ቤት እየጠየቀ ከደረሰበት በኋላ ደብዳቤውን ለሹሙ ሰጠው።

ያም ሹም ደብዳቤውን ተቀብሎ ሲያነብ የታተመበት ማኅተም ዕውነተኛ መሆኑን ከአረጋገጠ በኋላ እግዚአብሔር እንዳዘዘው በቤተ ክርስቲያን ደንብ የባለጸጋውን ልጅ በተክሊል አጋባው፣ የሠርጉንም በዓል እስከ ዐርባ ቀን ድረስ በታላቅ ደስታ አከበሩ። ከሠርጉም በዓል ፍጻሜ በኋላ ያ ባለጸጋ ሰው ከሄደበት አገር ወደ ሀገሩ ተመልሶ ገባና በቤቱ አካባቢ ሲደርስ የደስታና የዘፈን ድምፅ ስለሰማ “ይህ የምሰማው ድምፅ ምንድነው?” ሲል ጠየቀ፡፡ ሰዎቹም “ባሕራን የተባለ ጐበዝ ካንተ ዘንድ ልጄን ዳሩለት የሚል ትእዛዝ አምጥቶ ልጅህን አግብቶ በሠርጉ ምክንያት ይዘፍናሉ ይደሰታሉ እነሆ እየበሉና እየጠጡ በቀንና በሌሊት እየዘፈኑ ሲደሰቱ ዐርባ ቀን ሆኗቸዋል በመልእክትህም እንዳዘዝከው ገንዘብህን የወንድና የሴት ባሮችህን በጠቅላላው የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረትህን ሁሉ በሙሉ አስረክበውታል” አሉት። ያም ባለጸጋ ያህን ቃል በሰማ ጊዜ ከድንጋጤው የተነሳ በታላቅ ቃል በመጮኽ ከመሬት ላይ ተከስክሶ ሞተና ነፍሱን አጋንንት ተረክበው ወደ ሲኦል
አወረዷት። ከዚህም በኋላ ባሕራን የተባለ ያ ጐልማሳ የቅዱስ ሚካኤልን በዓል በየወሩ እያከበረ ዝክሩን እየዘከረ ይኖር ጀመር። በዚያን ጊዜ በጉዞ ላይ ሳለ ተገልጾለት የሞቱን መልእክት ወደ ሕይወት የለወጠለት ቅዱስ ሚካኤል እንደሆነም አወቀ ተረዳ።

ንዑድ ክቡር የሚሆን የመላእክት ሁሉ አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ያደረገው ተአምር ሊቆጥሩት የማይቻል ብዙ ስለሆነ በኛም ላይ ኃይለ ረድኤቱ አድሮብን ይኑር እስከ ዘላለሙ ድረስ አሜን።

ቸርነት

ሐዋርያው ስለ ጌታ ሲናገር‹‹ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሓ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግስቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን;›› ሮሜ 2-4 ይላል፡፡ይህ ታዲያ የሚገልጸውም እኛን ለሚታገስ የእግዚአብሔር ትዕግስት እና ወደ ንስሓ ስለሚመራን መልካምነቱ ነው፡፡ቸርነት የእግዚአብሔር ባህርይ እንዲሁም ከሰው ልጅ ጋር ባለው ግንኙነት ልዩ መገለጫው ነው፡፡በተጨማሪም ሐዋርያቱ የሚታወቁትበት በዚህ ነው፡፡

ቸርነት ከጭካኔ ከሁከት እና ከትዕቢት የጸዳ የየዋህነት፤የርህራሄ፤የደስታና የትህትና ሕይወት ፍሬ ነው፡፡ቸርነት ቅዱስ ጳውሎስ እነደገለጸው ረጋ ያለ ሰውን የሚያመለክት የእርጋታ መንፈስ ነው፡፡በሚያሳዝን ሁኔታ አንዳንድ ሰዎች መንፈሳዊ ሕይወት ጾምና ጸሎት ብቻ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ በሌሎች ላይ በንዴት የሚፈጽሟቸውን ክፉ ድርጊቶች ከግምት ውስጥ አያስገቡም፡፡ይህ የመንፈስ ፍሬ የሌለው ሰው በእርግጥም መንፈሳዊ ሰው አይደለም፡፡በመንፈስ እየተመራ አይጓዝምና፡፡ስለዚህ በትህትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግስትም እርስ በእርሳችሁ በፍቅር ታገሱ፡፡ኤፌ 4-22 ገላ5-22፡ ቸርነት በጠፋው ልጅ ታሪክ ውስጥ አባት ለጠፋው ልጅ እና ለታላቅ መንድሙ ርህራሄ ባሳየበት መንገድ በግልጽ ታይቷል፡፡

የጠፋው ልጅ ከአባቱ ገንዘብ የሚያደርሰውን ክፍል ለመጠየቅ ወደ አባቱ ሄደ አባቱ ግን በሕይወት እያለሁ የእኔን የአባቱን ገንዘብ እንዴት ለመውረስ ይፈልጋል በማለት አልገሰጸውም፡፡በተቃራኒው በትሕትና እና በቸርነት ሀብቱን በማካፈል ለልጁ ድርሻውን ሰጠው፡፡ልጁም በከንቱ ሕይወት እና በአባካኝ ኑሮ ከአባቱ ገንዘብ የደረሰውን ካጠፋ በኋላ ችግረኛ እና ረሀብተኛ ሆነ ጥፋቱ በማመንም ወደ አባቱ ቤት ተመለሰ፡፡አባቱም በደስታ ተቀበለው፡፡ልጁ ከአባቱ መንገድ ቢያፈነግጥም ከመጸጸቱና ይቅርታ ከመጠየቁ በፊት በደስታ ሮጦም በጉልበቱ በመውደቅ ሳመው፡፡በልጁ መመለስ በመደሰት የተሸለ ልብስ አለበሰው ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ሰጠው፡፡የሰባ ፍሪዳም አምጥቶ አረደለት፡፡እንዴት ቸር ነበር! አባቱ ከቸርነቱ የተነሳ ልጁ የልብ መሰበር ወይም ኃፍረት እንዲሰማው አላደረገም፡፡

ታላቁ ልጅ አባቱ ወንድሙን በደስታ በመቀበሉ ምክንያት በወንድሙ መመለስ ወደ ቤት ለመግባት ከነእርሱ ጋር ለመደሰት ፍቃደኛ ባለመሆን አባቱን ባማረረውና በተቆጣ ጊዜ እንኳን አልተናደደም፡፡ስግብግብና ኢሚዛናዊ በመሆኑ ምክንያት እርሱን በመተቸት በተናገራቸው ጠንካራ ቃላት አባቱ አልተበሳጨም፡፡‹‹እነሆ ይህን ያህል ዓመት እንደባሪያ ተገዝቼልሃለው ከትዕዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም ለእኔም ከወዳጆቼ ጋር ደስ እንዳለኝ አንድ ጠቦት ስንኳ አልሰጠኸኝም ነገር ግን ገንዘብህን ከጋለሞቶች ጋር በልቶ ይህ ልጅህ በመጣ ጊዜ የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት፡፡›› አለው፡፡ሉቃ 15-29-30

በእነዚህ ቃላት ከመናደድ ይልቅ በትሕትና ‹‹ልጅ ሆይ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ ለእኔም የሆነም ሁሉ የአንተ ነው ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበር ህያው ስለሆነ ጠፍቶም ነበር ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን ፍስሐ እንድናደርግ ይገባልና አለው፡፡ሉቃ 15-31-32 ታለቁ ልጁ አባቱን እና ወንድሙን በመቃወም ለተናገረው ትችት አባቱ አልወቀሰውም እንዲሁም አልገሰጸውም ይልቁንም በቸርነት‹‹ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው…ደስ እንዲለን ፍስሐም እናድናደርግ ይገባል›› ሲል አዎንታዊ መልስ መለሰለት፡፡

የመንፈስ ፍሬዎች አቡነ ሺኖዳ
ገጽ 61

አቡነ ያዕቆብ ዘሥሩግ

      ሀገሩ ሶርያ ሲሆን አባቱ ሊቀ ካህናት ነበር። በኤጲስ ቆጶስነት የተሾመባት አገር በጤግሮስና በኤፍራጥስ መካከል በምትገኝ ሥሩግ በምትባል አገር ስለሆነ ያዕቆብ ዘሥሩግ ተባለ። በ 3 ዓመቱ እናቱ ቤተ መቅደስ ስትወስደው መልአክ እጁን ይዞ በሊቀ ጳጳሱ እጅ እንዲቆርብ አድርጎታል። በዚህም ጊዜ ምሥጢራት ሁሉ ተገልጠውለታል።ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ገና በ ህጻንነቱ  ሦስት ነገሮችን እንደሚፈራ ተናግሯል።  “ነፍሴ ከሥጋዬ ተለይታ ስትወጣ ፡ከጌታችን ጋር ስትገናኝና መጨረሻውን ፍርድ ስሰማ እነዚህን ሦስት ነገሮች በእጅጉ እፈራለሁ” ብሏል።

      በ 12 ዓመቱ ብሉይንና ሐዲስን አጠናቆ ተምሮ ጨርሷል። ጸጋውን ዐውቀው 5ቱ ታዋቂ ሊቃነ ጳጳሳት መጥተው እጅ ነስተውት አዲስ ድርሰት ድረስልን ቢሉት እርሱም በፍጹም ትሕትና “በእናንተ ፊት እንኳን አዲስ ድርሰት ልደርስ ቀርቶ የተደረሰውንም መናገር አልችልም” ብሏቸዋል።

ቅዱስ ያዕቆብ ከዚህ በኋላ ወደ ገዳም ገብቶ ትሕርምተ አበውን : ዕጸበ ገዳምን : ሕይወተ ቅዱሳንን በተግባር ተምሯል:: በድንግልናው ጸንቶ : ጾምና ጸሎትን እያዘወተረ ኑሯል:: በፈቃደ እግዚአብሔር የሥሩግ (በኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች መካከል የምትገኝ የሶርያ ግዛት ናት) ኤዺስ ቆዾስ ሆኖ ተሹሟል::

በዘመኑም:-
1.የ451ን የኬልቄዶን ጉባኤ አውግዟል::
2.ብዙ መናፍቃንን ተከራክሮ ምላሽ አሳጥቷል::
3.በወንጌል አገልግሎት መልካም እረኝነቱን አሳይቷል::
4.ዛሬ የምንገለገልበትን መጽሐፈ ቅዳሴውን ጨምሮ በርካታ መንፈሳዊ ድርሰቶችን ደርሷል::

ንጽሕናውና ቅድስናው እንደ መላእክት ነው የተባለለት ያዕቆብ ዘሥሩግ ጻድቅም ሐዋርያም ደራሲም ተከራካሪ መምህርም ነው።

በሦርያ ቋንቋ በመቶዎች የሚቆጠሩ በግጥም መልክ የተዘጋጁ ድርሳናትን ፣በመጻፍ “ዕንዝራ መንፈስ ቅዱስ “ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።በስሙ የሚታወቅ ቅዳሴም ደርሷል። በሀገራችን በቅዱሳን መላእክት በዓላትና በነገረ ምጽአት መታሰቢያ ዕለት ቅዳሴው ይቀደሳል።ስለ ነገረ ድኅነት በስፋት አስተምሯል።ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በግጥም መልክ የተዘጋጀ ድርሰት ደርሷል።

ቅዲስ ያዕቆብ ዘሥሩግ የመለኮትና ትስብእትናን ፍጹም ተዋሕዶ በማስተማሩ “የተዋሕዶ ጠበቃ “ተብሏል።የንስጥሮስንና የኬልቄዶናውንን የምንታዌ ትምህርት ይቃወማል።

    ዕረፍቱም ሰኔ 7 ቀን ነው። ከአባታችን ከአቡነ ያዕቆብ ዘሥሩግ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎቱም ይማረን!።

ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን

ራስን መግዛት


በመንፈስ የሚኖር ሁሉ የመንፈሳዊ ሕይወት ፍሬ የሆነው ራስን መግዛት ይኖረዋል፡፡

ራስን መግዛት የሥጋ ስሜቶች፤ የአንደበትን፤ የአእምሮን፤ የልብን ሙያ፤የእጅ …..ንጽሕና እና እነዚህን ሁሉ መቆጣጠር ያጠቃልላል፡፡


የአንደበት ንጽሕና ማለት መጥፎ እና ከንቱ ቃልን ማስወገድ ማለት ነው፡፡ስለዚህ ጌታ ‹‹ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፡፡›› ማቴ 12-36 ብሏል፡፡ እነዲህ ዓይነቱንም ቃል የሚያረክስ ብሎ ይቆጥረዋል፡፡‹‹ሰውን የሚያረክስ ወደ አፍ የሚገባ አይደለም ከአፍ የሚወጣ ግን ሰውን የሚያረክስ ይህ ነው፡፡››ማቴ 15-11 ብሏልና፡፡በእርግጥ ንጹሕ ሰው በምንም ቃል አይረክስም፡፡


ንጹሕ አንደበት የስድብ ወይም የፌዝ ቃል አያሰማም ንጹሕ ሰው ሌሎችን ያከብራል ማንንም በጎጂ ቃል ወይም የንቀት በሆነ በሚያዋርድ ወይም በፌዝ ቃል አይጎዳም፡፡ንጹሕ አንደበት ትሁት ሰው አክባሪ ከመናገሩ በፊትም እያንዳንዱን ቃል የሚመዝን የተከበረ አንደበት በመሆኑ ምክንያት የማንንም ስም አያጠፋም ወይም አያስደነግጥም፡፤ከዚህ በተጨማሪ ተፈጥሮ በመሆኑ ንጹሕ ቃል ይጠቀማል እንጂ ለመናገር ምንም ዓይነት ጥረት አይፈልግም፡፡


የልብና የአእምሮ ንጽሕና ደግሞ የእያንዳንዱ ውጪያዊ ንጽሕና መሠረት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና፡፡››ምሳ 4-23 ይላል፡፡ የልብ ንጽሕና የስሜቶችን የደስታዎችን እና የድርጊቶችን እንዲሁም የዕቅዶችን ሀሳቦችን እና የፍላጎቶችን ንጽሕና ያጠቃልላል፡፡ከአንድ ምንጭ እርሱም ከልብ ንጽሕና የአእምሮ ንጽሕና የአንደበት ንጽሕና እና የስሜቶች ንጽሕና ይወጣል፡፡ስለዚህ አእምሮ ንጹሕ ባልሆነ መንገድ ሲባክን ካገኘኸው ፈጥነህ ተቃወመው ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ከመሸጋገሩ በፊት አቁመው፡፡ አእምሮ ራሱን በአንደበት በስሜቶች ወይም በድርጊት አማካኝነት ይገለጻልና፡፡


የልብ እና የአእምሮ ንጽሕና ከውስጠ ኅሊና ጋርም ደግሞ የተያያዘ ነው፡፡ ውስጠ ኅሊና የሚሠራው በውስጡ በተከማቹ አስተሳሰቦች ምስሎች ምኞቶች እና ስሜቶች አማካኝነት ነው፡፡እነዚህ ሁሉ ንጽሕና አልባ ከሆኑ ህልሞች እና አስተሳሰቦች ቅርጽ ይገለጣል፡፡ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው የልቡን እና የእእምሮውን ንጽሕና በመንፈሳዊ ሥራዎች እና የአንደበት ስሜቶች እና የአካል ንጽሕና ምንጭ ሊሆኑ በሚችሉ በመንፈሳዊ ሥራዎች እና መልካም ነገርን ንጽሕናን በመውደድ ለመሙላት የበረታ ይሁን፡፡

አቡነ ሺኖዳ 
                                             የመንፈስ ፍሬዎች ገጽ 120    

ጾመ ሐዋርያት


ሐዋርያት ወንጌለ መንግሥት እንዲስፋፋና በሕዝብም ሆነ በአሕዛብ ዘንድ አገልግሎታቸው የሠመረ እንዲሆን መንፈስ ቅዱስን በተቀበሉ በበዓለ ሃምሳ ማግሥት ጾም ጀመሩ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ በሰጣቸው ሥልጣን ድውያንን መፈወስና አጋንንትን ማውጣት እንዲሁም የተለያዩ ገቢረ ተአምራትን ይፈጽሙ ዘንድ ጸሎትና ጾም ያስፈልጋቸው ነበርና፡፡ በማቴዎስ ወንጌል እንደተጻፈው ጌታችን ጋኔን ያለበትን ልጅ ካዳነው በኋላ ሐዋርያቱ ስለምን እነርሱ ጋኔን ከሰው ማውጣት እንዳልቻሉ በጠየቁት ጊዜ እንዲህ ሲል መልሶላቸዋል፤ ‹‹…ይህ ዓይነቱ ግን ያለጾምና ጸሎት አይወጣም፡፡›› (ማቴ.፲፯፥፳፩)

ሐዋርያት ጌታችን ኢየሱስ ገቢረ ተአምራትን ሲፈጽም፣ ሲጾምና ሲጸልይ አብረውት ሆነው አይጾሙም ነበር፤ በዚያን ጊዜም የሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙርት ወደ እርሱ ቀርበው ‹‹እኛና ፈሪሳውያን ብዙ እንጾማለን፤ ደቀ መዛሙርትህስ ለምን አይጾሙም›› ብለው ጌታችንን ጠየቁት፡፡ ጌታችንም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ ‹‹የሙሽራው ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ አይችሉም፤ ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፤ ያንጊዜም ይጾማሉ፡፡ (ማቴ.፱፥፲፬-፲፭)


ሙሽራ የተባለውም ጌታችን ኢየሱስ በምድር ላይ ነገረ ድኅነትን ፈጽሞ እስኪያርግና መንፈስ ቅዱስ ሚዜዎቻቹም በተባሉት ሐዋርያት ላይ እስኪያድር ድረስ አልጾሙም፤ ከዚህ በኋላ ግን ጾማቸውን እንደሚጀምሩ ጌታችን አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ ያለ ጾምና ያለ ጸሎት አገልግሎት ሊሰምር አይችልም፤ ጠላታችን ዲያብሎስንም ማሸነፍ አይቻለንም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ላይ ‹‹መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው?›› ብሎ እንደተናገረው ሐዋርያት በዓለም ዙሪያ በ፸፪ ቋንቋ ማስተማር የቻሉትና ተልእኮአቸው የሠመረላቸው አስቀድመው በመጸለያቸውና መጾማቸው ነው፡፡


ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹እነዚህም ፍጻሜያቸው ለጥፋት የሆነ፥ ሆዳቸውን የሚያመልኩ፥ ክብራቸው ውርደት የሆነባቸው፥ ምድራዊውንም የሚያስቡ ናቸው›› በማለት እንደተናገረው ለከርሣቸው የሚኖሩ ክብራቸውን ያጡ ሰዎች በርካቶች ናቸው፤ ሰው እግዚኢብሔር አምላኩን የሚተወው ራሱን ለሥጋ ምግቦች አዘጋጅቶ ለሆዱ ብቻ ሲኖር ነው፡፡ ለጾም ያደሉ ቅዱሳን ግን ፊታቸው የሚያበራ፣ በጥላቸው ድውይ የፈወሱ፣ ሙት ያነሡ፣ በመቅደሱ ገብተው ከእናታቸው ማኅፀን ጀምሮ ሽባ የሆኑትን ሰዎች በመፈወስ ያዳኑ ናቸው፤ (ፊል.፫፥፲፱)


ሐዋርያት በጾምና በጸሎታቸው ወንጌለ መንግሥት እንዲፋጠን ከአምላካቸው እግዚአብሔር የተሰጣቸውን መመሪያ ይዘው ተጉዘዋል፡፡ እኛም በጾምና በጸሎት ተግተን ጌታችን ኢየሱስ በመሠረተልን የድኅነት መንገድ ተጉዘን ወደ እግዚአብሔር ክብር ራሳችንን በንስሓ መለወጥ እንችላለን፡፡


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም በየዓመቱ የሐዋርያትን ጾም በማወጅ ሕዝበ ክርስቲያን እንዲጾሙ ታደርጋለች፤ በዚህ ዓመትም ጾሙ ከግንቦት 28 ቀን እስከ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በመሆኑ ሁላችን ልንጾመው ይገባል፡፡


ነፍስን የሚያለመልምና በቅድስና ሕይወት የሚያኖር፣ በወንዝ ዳር እንደተተከለችና ሁል ጊዜ ፍሬዋን እንደምትሰጥ ዛፍ ነፍሳችን እንድታፈራ የሚያደርግ ጾም በመሆኑ ሁላችን ልንጾም ይገባል፡፡

ዕርገት

ዕርገተ ክርስቶስ


‹‹በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፡፡›› መዝ 67(68)፡33፡፡‹‹ አምላክ በእልልታ፣ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ፡፡ ዘምሩ፣ ለአምላካችን ዘምሩ ፤ ዘምሩ ፣ ለንጉሣችን ዘምሩ፡፡ እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና ፤ በማስተዋል ዘምሩ፡፡ እግዚአብሔር በአሕዛብ ላይ ነገሠ ፤ እግዚአብሔር በቅድስናው ዙፋን ይቀመጣል፡፡ ›› መዝ 47፡5-8፡፡


‹‹ እነሆም አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ፡፡ እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው፡፡ ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ፡፡ እነርሱም ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፣ ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ፡፡ ›› ሉቃ 23፡50-53፡፡


‹‹ ዕርገት ›› የሚለው ቃል ዐረገ ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ‹‹ ከፍ ከፍ አለ ፣ ወደ ሰማይ ወጣ ›› ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን ላይ ‹‹ በስምሽ በመለመን በመማጸን የሰው ልጆችን ጸሎት ያሳርጋሉ ›› እንዲል፡፡ እንዲሁም በእሁድ ውዳሴ ማርያም ላይ ‹‹ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያሳረገ›› እንዳለ፡፡


በተጨማሪም በራእይ 8፡4 ላይ ‹‹የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር በመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ›› በማለት ዐረገ የሚለውን ቃል በአማርኛ ‹‹ወጣ›› በማለት ይገልጸዋል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ሞቶ ድኅነትን ከፈፀመ በኋላ በሦስተኛው ቀን የሞትን መውጊያ ሰብሮ ተነሣ፡፡ ከዚህ በኋላ በሞቱ ቀቢጸ ተስፋ ይዟቸው የነበረውን ሐዋርያትና አርድዕትን በተደጋጋሚ ትንሣኤዉን በመግለጥ ያጽናናቸው ነበር፡፡ ጌታችን ከሞት ከተነሣ ከኋላ ለአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ኪዳንንና ትምሕርተ ሕቡዓትን በዝርዝር አስተምሯቸዋል፡፡


መድኃኔዓለም ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ ጀምሮ እስከ 40 ቀን ድረስ ሐዋርያትን ፣ አርድዕትን በጠቅላላው 120ውን ቤተሰብ ሲያጽናና ቆይቶ ለቅዱስ ጴጥሮስ የፕርትክና (ታላቅ አባት የመሆን) ሥልጣንን ከሰጠው በኋላ 120ውን ቤተሰብ ወደ ደብረ ዘይት ይዞአቸው ወጣ፡፡ በዚያም ሳሉ ‹‹ኃይልን እስክትለብሱ ድርስ በኢየሩሳሌም ጸንታችሁ ቆዩ›› የሚለውን ታላቁን የዕርገት መልእክት አስተላልፎ ከምድር ከፍ አለ፡፡

በመላእክት ምስጋና ‹‹በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ›› እንዲል ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ከዐይናቸዉም ተሰወረ፣ ሐዋርያትም ወደላይ አንጋጠው አንገታቸውን አቅንተው ይመለከቱ ነበር፡፡ ሐዋ 1፡2፡፡ በዚህ ጊዜ ሁለቱ ብርሃናውያን መላእክት እንዲህ ሲሉ ተናገሯቸው ‹‹የገሊላ ሰዎች ሆይ! ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ለምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁ እንዲሁ ይመጣል፡፡››


ይህ ታላቅ የተስፋ ቃል የመላእክት ንግግር ከቅዱስ ዳዊት ትንቢት ጋር የተዛመደ ሲሆን የጌታችን ምጽአት በምሥራቅ በኩል እንደሚፈጸም ያሳያል፡፡ ሁለቱ መላእክት በንግግራቸው በዚህ ሲሄድ እንዳያችሁት በግርማ ደግሞ በዚህ ይመጣል ብለው ነበር፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ ለእግዚአብሔር ዘምሩ ›› መዝ 67(68)፡33 በማለት ይናገራል፡፡ በመሆኑም ጌታችን ያረገው በምሥራቅ ነው ፤ ደግሞ ለፍርድ የሚመጣው በምሥራቅ ነው ማለት ነው፡፡


የጌታችን ዕርገት ምሳሌ እና ትንቢት አለው፡፡ ምሳሌው እንደምን ነው ቢሉ የቅዱስ ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀን አድሮ በሦስተኛው ቀን መውጣቱ ለትንሣኤው ምሳሌ እንደሆነ ሁሉ እንዲሁ የቅዱስ ኤልያስ ዕርገትም ለጌታችን ዕርገት ምሳሌ ነው፡፡ ልዩነቱ ግን ቅዱስ ኤልያስ በመላእክት እርዳታ በፈቃደ እግዚአብሔር ያረገ ሲሆን ጌታችን ግን በፈቃዱ በራሱ ኃይል ዐርጓል፡፡


ትንቢቱም ቅዱስ ዳዊት ‹‹ ወደ ሰማይ ላረገው ለእግዚአብሔር ዘምሩ ›› መዝ 67(68)፡33 ብሎ የተናገረው ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹ወደ ላይ ዐረግህ ምርኮን ማረክህ ስጦታንም ለሰዎች ሰጠህ›› (መዝ 67፡18) የሚል እናገኛለን፡፡ በመጨረሻም የጌታችን ታላቁ የዕርገት መልእክት ‹‹ኃይልን እስክታገኙ በኢየሩሳሌም ጽኑ›› የሚለው ታላቅ መልእክት ነው፡፡
ጌታችን በኢሩሳሌም እንደተወለደ እንዳደገ እንዳስተማረ እንደተሰቀለ በቤተ ክርስቲያንም በቤተልሔም ሥጋው ደሙ የሚዘጋጅባት ቃሉ የሚነገርባት በቤተ መቅደስ ሥጋው የሚቆረስበት ደሙ የሚፈስባት ቦታ ናትና ኢየረሳሌም የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ ስለሆነም ቅዱስን የእግዚአብሔር መንፈስ እንዲሁም ጸጋ ለማግኘት በቤተ ክርስቲያን መጽናት እንደሚገባ በአጭር ዐረፍተ ነገር ያስተማረው ታላቅ በዓል ነው፡፡


የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገቱን ከትንሣኤው አከታትሎ ወዲያውኑ አላደረገም ፣ ምክንያቱም ፈጽመው ክፋትን የተመሉ አይሁድና በኋላም የሚነሣ የረከሱ መናፍቃን ዕርገቱ ምትሐት ናት ብለው እንዳያስቡ ነው፡፡ ጌታችንም በረቀቀ ጥበቡ የደቀ መዛሙርቱን ተሸብሮ የነበረ ልቡናቸውን እያጽናና መነሣቱንም እያስረዳቸው ከትንሣኤው በኋላ አርባ ቀን ኖረ፡፡


ይህ የዕርገት በዓል ከጌታችን ዓበይት (ታላላቅ) በዓላት መካከል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጌታችንን የዕርገት በዓል ሁለት ጊዜ ታከብራለች፡፡ ይኸውም በመጀመሪያ ጌታችን ያረገበትን ጥንተ በዓሉን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የቀመር በዓል ነው፡፡


ዓመታዊ በዓላት ዓዋድያት (Movable Feasts) እና ዓዋድያት ያልሆኑ (Immovable Feasts) ተብለው በሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ፡፡ ዓዋድያት (Movable Feasts) የሚባሉት በቅዱስ ዲሜጥሮስ ቀመር መሠረት መባጃ ሐመርን ተከትለው ወደፊት ወደኋላ በመመላለስ በየዓመቱ በተለያየ ቀንና ወር የሚውሉት ናቸው፡፡ እነዚህም እንደ ስቅለት፣ ሕመማት፣ ትንሣኤ፣ ደብረ ዘይት ፣ ሆሣዕና ፣ ዕርገትና ጰራቅሊጦስ የመሳሰሉት ናቸው፡፡


ዋድያት ያልሆኑ (Immovable Feasts) የሚባሉት ደግሞ ሁልጊዜም በወር ውስጥ በሚገኝ በታወቀ ቀን ብቻ በቋሚነት የሚውሉት ናቸው፡፡ እነዚህም እንደ ፅንሰት (ትስብእት) ፣ ልደት ፣ ጥምቀት ፣ ደብረ ታቦር ፣ ቃና ዘገሊላ ፣ ዘመን መለወጫ ፣ መስቀል ፣ 33ቱ የእመቤታችን በዓላት ፣ የመላእክት ፣ የሰማዕታትና የቅዱሳን በዓላት ናቸው፡፡

የጌታችን ዓበይትና ንዑሳት በዓላት፡- ለመጀመሪያ ጊዜ የጌታችንን በዓላት ማክበር የጀመሩት የከበሩ ሐዋርያት ናቸው፡፡ ሠለስቱ ምእት ደግሞ ከ325 ዓ.ም ጀምረው በዓላቱ በቀኖና በሕግ እንዲከበሩ አዘዋል፡፡ ለዚኽም በፍትሐ ነገሥቱ ላይ የተጻፈውን በማስረጃነት ማየት እንችላለን፡፡ ‹‹እግዚአብሔር የጠመመውን እያቀናላቸው፣ የጎደለውን እየሞላላቸው የጌታን በዓላት ማክበር እንዲገባ 318 ሊቃውንት በጉባኤ ኒቅያ በእግዚአብሔር አጋዥነት የጌታችንን በዓላት ያከብሩ ዘንድ፣ ተአምራቱን ይገልጹ ዘንድ፣ ምስጋናውንም ይናገሩ ዘንድ አዘዙ ተናገሩ›› እንዲል፡፡ (ፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ፣ ገጽ 260)


የጌታችን ዓበይት በዓላት ዘጠኝ ናቸው፡፡ እነዚህም፡- ፅንሰት (ትስብእት)፣ ልደት፣ ጥምቀት፣ ደብረ ታቦር፣ ሆሣዕና፣ ስቅለት፣ ትንሣኤ፣ ዕርገትና ጰራቅሊጦስ ናቸው፡፡
የጌታችን ንዑሳት በዓላት የሚባሉትም ዘጠኝ ሲሆኑ እነርሱም ስብከት ፣ ብርሃን ፣ ኖላዊ ፣ በዓለ ጌና ፣ ግዝረት፣ ልደተ ስምዖን ፣ ቃና ዘገሊላ ፣ ደብረ ዘይትና መስቀል ናቸው፡፡

የጌታችን የከበረ የዕረገቱ ረድኤት በረከት ይደርብን!
በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ላረገ አምላካችን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና ይሁን ከቸር አባቱ ከአብ ሕይወት ከሆነ ከመንፈስ ቅዱስም ጋራ ለዘለዓለሙ አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።