
❖ ቅዱስ መርቆሬዎስ በግእዝ ልሳን በእንግልጣር Mercurius በጽርዕ Ἅγιος Μερκούριος, በቅብጥ Ⲫⲓⲗⲟⲡⲁⲧⲏⲣ Ⲙⲉⲣⲕⲟⲩⲣⲓⲟⲥ; በሲርያክ: ܡܳܪܩܘ̇ܪܝܘ̇ܣ; ተብሎ ይጠራል። የተወለደው በምሥራቅ ታሕታይ እስያ በቀጶዶቅያ በአኹኗ ቱርከሰ በ224 ዓ.ም. ሲኾን ወላጆቹ ክርስቲያኖች ሲኾኑ ስሙን ፒሉፓዴር Philopater ብለውታል ትርጓሜውም በግሪክኛ “የአብ ወዳጅ” ማለት ነው። በመንፈሳዊ ትምህርት አጠንክረው አሳድገውታል።
❖ በ17 ዓመቱ የሮማን ሰራዊት ተቀላቀለ “ወተውህቦ ኀይል ዐቢይ ለቅዱስ መርቆሬዎስ ወተሰምዐ ዜናሁ በኲሉ ወተለዐለ እምሰብአ ቤተ መንግሥት” ይላል። ታላቅ የድል አድራጊነት ኀይል እንደ ዳዊት ተሰጥቶት ዜናው በኹሉ ቦታ ሲሰማ ከቤተ መንግሥት ሰዎችን ይልቅ ከፍ ከፍ ብሏል፤ በዚኽ ምክንያት ከ249-251 የሮማ መሪ በነበረው ንጉሥ በዳኬዎስ ዘንድ በ17 ዓመቱ ባለሟልነት አግኝቷል፡፡
❖ ከዚያም በሮም ላይ የበርበር ሰዎች ተነሥተው የዳኬዎስን መንግሥት ሊወጉት መጡ፤ እጅግ ብዙዎችም ነበሩና ንጉሡ እጅግ ፈራ፤ ቅዱስ መርቆሬዎስ ግን በክርስቶስ ላይ ያለው እምነት የጸና ነበርና ንጉሡን “እግዚአብሔር ያጠፋቸው ዘንድ አለውና አትፍራ” አለው፡፡
❖ “ወእምዝ ርእዮ ቅዱስ መርቆሬዎስ ለመልአከ እግዚአብሔር በውስተ ቀትል ወሰይፍ በሊኅ ውስተ እዴሁ” ይላል፤ የእግዚአብሔር መልአክ በውጊያው ውስጥ የተሳለ የሚያበራ ሰይፍ በእጁ ይዞ ተገልጦለት ሰይፉን በመስጠት “ጠላቶችኽን ድል ባደረግኽ ጊዜ ፈጣሪኽ እግዚአብሔርን ዐስበው” ብሎ ሰጥቶታል፤ አንዱ ራሱ ለውጊያ የያዘው ሰይፍ ኹለተኛም ከመልአኩ የተቀበለው ሰይፍ ነበርና በዚኽ ምክንያት “አበ አስይፍት” (የሰይፎች አባት፤ Abu-Seifein) በዐረብኛ Abu-Sayfain, Abu-Sifin ወይም أبو سيفين, በቅብጥ ⲁⲃⲩⲥⲉⲫⲁⲓⲛ ሲኾን በኹሉም ፍቺው ተመሳሳይ ነው።
❖ ከዚኽ በኋላ ንጉሡ ዳኬዎስ ለጣዖታት ዕጣን ሊያቀርብና በዓልን ሊያደርግ ወደዶ በዓልን ባደረገ ጊዜ ቅዱስ መርቆሬዎስ ግን ከርሱ ጋር አልወጣም፤ በዚኽ ምክንያት ንጉሡ አስጠርቶት “ለአማልክት ዕጣን ለማሳረግ ከእኔ ጋር ያልወጣኽ የእኔንስ ፍቅር ለምን ተውኽ?” ብሎ ጠየቀው፤ በዚኽ ጊዜ ቅዱስ መርቆሬዎስ በንጉሡ ፊት ትጥቁንና ልብሱን ወርውሮ “እኔ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን አልክደውም ለረከሱ ጣዖታትም አልሰግድም” በማለት መለሰለት፡፡
❖ ንጉሡም እጅግ ተቈጥቶ ርጥብ በኾኑ የሽመል በትሮችና እንዲደበደብና ከላም ቆዳ በተሠራ ጅራፍ እንዲገረፍ አዘዘ፡፡ ይህንን ሁሉ በክርስቶስ ስም ተቀበለ።
❖ ከመሬት ከፍ ከፍ ያሉ ሁለት ምሰሶ ላይ እንዲታሰር አደረጉት። በችንካር ቸንክረው ገላውን በስል ምላጮች ቆራርጠውታል። ከዚያም ወደ እስር ቤት ቢከቱትም በወኅኒ ቤት ሳለ ቅዱስ ሚካኤል ተገልጾ ሰውነቱን በዳሰሰው ጊዜ ተፈውሷል።
❖ ቅዱስ መርቆሬዎስ ካለው ተወዳጅነት የተነሣ ሰዎች እንዳይነሡበት በመፍራት የቀጶዶቅያና የእስያ ክፍል ወደ ኾነች ወደ ቂሳርያ በብረት ማሠሪያ ታሥሮ እንዲላክ አድርጎ በዚያም ብዙዎች ሥቃያትን አደረሱበት።
❖ ከዚያም አንገቱ እንዲቆረጥ ሲወሰን እጆቹን ወደ ላይ ዘርግቶ መጸለይ ጀመረ። አምላካችን ክርስቶስ መላእክትን አስከትሎ በታላቅ ግርማ ተገለጸለትና “የተወደድክ ልጄ መርቆሬዎስ ወደ ዘላለማዊ ዕረፍትህ ከቅዱሳን ጋር ና፤ ጸሎትህ መልካም መዐዛ እንዳለው ዕጣን ወደ እኔ ዐረገ፤ የአንተን ስም በያዘ ቤተ ክርስቲያን ሁሉ ተአምር ይደረጋል፤ በአንተ ምልጃ የሚማጸኑኝን እጠብቃቸዋለሁ፤ የአንተን ዜና ገድል የሚጽፉትን የሚያነቡትን ስማቸውን በሕይወት መጽሐፍ እጽፈዋለሁ” ብሎ ቃል ኪዳንን ገባለት።
❖ ከዚህ በኋላ ጌታችን ቅዱስ መርቆሬዎስን ባረከው፤ ያን ጊዜ በጣም ተደሰተና አንገቱን እንዲቆርጡ የታዘዙት ጋር በፍጥነት ሄዶ ከንጉሡ የታዘዙትን ፈጥነው እንዲፈጽሙ ለመናቸው። ተንበርክኮ “ጌታ ሆይ ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” ብሎ ጸለየላቸው። ከዚያም በተወለደ በ25 ዓመቱ በኅዳር 25 ቀን በ250 ዓ.ም. ራሱን በተሳለ ሰይፍ ቈርጠውት በክርስቶስ ስም የሰማዕትነትን የክብር አክሊል ተቀዳጀ፤ የሰማዕታት ዘመን ካለፈም በኋላ በመላው ዓለም አብያተ ክርስቲያናት ታንጸውለታልና፡፡
❖ ቅዱስ መርቆሬዎስ በፈጣን ተራዳኢነቱ የሚታወቅ ሲኾን ከሓዲው ዑልያኖስ ታላላቆች ሊቃውንት የነበሩትን ቅዱስ ባስልዮስንና ቅዱስ ጎርጎርዮስን ሊገድላቸው በመጣ ጊዜ በቅዱስ መርቆሬዎስ ሥዕል ፊት ቆመው ቢማፀኑ ቅዱስ ጴጥሮስ ሐናንያና ሰጲራን በሞት እንደቀጣ፤ ቅዱስ ጳውሎስ የበርያሱስን ዐይን እንዳጨለመ፤ ዳዊት ጎልያድን በእግዚአብሔር ስም እንደጣለው ቅዱስ መርቆሬዎስም በተራዳኢነቱ እንደ ጎልያድ የታበየውን ክርስቶስን የካደው ከ361 – 363 ድረስ የመራውን ዑልያኖስን (Julian the Apostate) በረቀቀ ጦር ወግቶታል።
❖ በደብረ ምጥማቅ እመቤታችን ትገለጥ በነበረ ጊዜ ከቅዱስ ጊዮርጊስና ከቅዱስ ቴዎድሮስ በመቀጠል ይመጣ የነበረው ቅዱስ መርቆሬዎስ ነበር።
❖ ኢትዮጵያዊዉ ሊቅ አርከ ሥሉስም የቅዱስ መርቆሬዎስን ተጋድሎ በማዘከር፡-
“ሰላም ለከ መርቆሬዎስ ዘሮም
መስተጽዕነ ፈረስ ጸሊም
አመ አንደዱ ታሕቴከ ውሉደ መርገም
እምቅሡፍ አባልከ እንተ ውኅዘ ደም
አርአያ ዝናም ብዙኅ አጥፍኦ ለፍሕም”
(በጥቊር ፈረስ ላይ የተቀመጥኽ የሮም ሰው ለኾንኸው ለመርቆሬዎስ ሰላምታ ይገባኻል፤ የመርገም ልጆች ከሥርኽ እሳትን ባነደዱ ጊዜ ከተገረፈው ሰውነትኽ በብዙ ዝናብ አምሳል የፈሰሰው ደም ፍሙን አጠፋው) እያለ መስክሮለታል፡፡
❖ ሊቁም በአድናቆት በመሆን፦
“ሮማዊ ግሩም
በመንፈስ ቅዱስ ሕቱም
መዐዛ ቅዳሴከ ጥዑም ከመ ጽጌ ገዳም
ነዓ ነዓ ማዕከሌነ ቁም
በበዓልከ ትባርከነ ዮም”
(ግሩም ሮማዊ በመንፈስ ቅዱስ የታተምክ፤ እንደ ምድረበዳ አበባ የምስጋናህ መዐዛ የጣፈጠ መርቆሬዎስ በበዓልህ ዛሬ ትባርከን ዘንድ ና ና በመካከላችንም ቁም) ይለዋል።
❖ ሊቁ አባ ጊዮርጊስም በተአምኆ ቅዱሳን መጽሐፉ ላይ፦
“ሰላም ለመርቆሬዎስ ሰማዕት ንጹሕ ድንግል
ፈጻሜ ቃለ ወንጌል”፡፡
(የወንጌል ቃል የፈጸመ ለኾነ ለንጹሕ ድንግል ሰማዕት መርቆሬዎስ ሰላምታ ይገባል) በማለት አወድሶታል፨
[የቅዱስ መርቆሬዎስ በረከት ይደርብን፤ እናንተም በአስተያየት መስጫው ላይ በረከቱ እንዲያድርባችሁ ቅዱስ መርቆሬዎስን አወድሱት]
✍ ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ

