ዕረፍቱ ለአቡነ ሀብተማርያም

📚ኅዳር 26

በዚህችም ቀን የተመሰገነና የከበረ ንጹሕም የሆነ የኢትጵያዊ አባታችን የሀብተ ማርያም የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡

የዚህ ቅዱስ አባት የትውልድ ሀገሩ የራውዕይ በምትባል በስተምሥራቅ ባለች ሀገር ውስጥ ነው። በዚያም ስሙ ፍሬ ቡሩክ የሚባል አንድ ሰው ነበር። ይህም ክቡራንና ታላላቅ ከሚባሉት ከዚህች ሀገር ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነው፡፡ እጅግ ሀብታም ነበር፤ ብዙ ንብረትም አለው። በሕጋዊ ጋብቻም ስሟ ዮስቴና የምትባል ብላቴና ድንግልን አገባ፤ ይህችም የተመረጠች በበጎ ሥራ የተሸለመችና ያጌጠች ናት፡፡

ነገር ግን አስቀድመን በዚህ ዓለም ከሕግ ባሏ ጋር በንጹሕ ጋብቻ እግዚአብሔርን በመፍራት ምጽዋትን በመስጠት የዋኅነትን፣ ትሕትናን፣ ፍቅርን፣ ትዕግስትን ገንዘብ አድርጋ በጾም በጸሎት ተወስና እንደኖረች እንነግራችኋለን፡፡

አባታችን አቡነ ሀብተ ማርያምም በባሕር መካከል በመቆም የዳዊትን መዝሙር ሁሉንም ያነባል፤ በባሕር ውስጥም ሰጥሞ ግንባሩ አሸዋ እስኪነካው አምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳል። ከሰንበት ቀኖችም በቀር እህል አይቀምስም ነበር። ከዚህም በኋላ እህልን ትቶ እንደ ዋልያዎች የዱር ቅጠል የሚመገብ ሆነ፡፡

ዓርባ ዓርባ፣ ሰማንያ ሰማንያ ቀን የሚጾምበት ጊዜ አለ። ባሕር ውስጥ በሌሊት ቁሞ በማደር በቀንም አራቱን ወንጌላት ያነባል፤ ሌሎች መጻሕፍትንም በእንዲህ ያለ ሥራ ብዙ ዘመን ኖረ፡፡

ብዙ ተጋድሎንና ድካምንም ባስረዘመ ጊዜ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱም ተገልጦ መጣ። ከእርሱ ጋርም የመላእክት አለቆች የከበሩ ሚካኤልና ገብርኤል የመላእክት ማኅበርም ሁሉ በዙሪያው ሁነው እያመሰገኑት ነበር። “ወዳጄ ሀብተ ማርያም ሰላም ለአንተ ይሁን” አለው፡፡ በዚያንም ጊዜ ከግርማው የተነሣ ወድቆ እንደ በድን ሆነ። ጌታችንም በከበሩ እጆቹ አንሥቶ እፍ አለበትና “ጽና ኃይልህን ላድሳት እንጂ ላጠፋህ አልመጣሁምና። ተጋድሎህና ድካምህ ሁሉ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት እንደተጻፈ በእውነት እነግርሃለሁ፡፡

  እነሆ አኔ በጎ ዋጋህን በዚህ ዓለም በሚመጣውም ዓለም እከፍልሃለሁ፤ የማቴዎስንና የማርቆስን ወንጌል በምታነብ ጊዜ በተራራዎችና በዋሻዎች በፍርኩታ ተሠውረው ወደሚኖሩ እንዳንተ ካሉ ቅዱሳን ጋር ለመገናኘት በላዩ ተቀምጠህ ወደ ምሥራቅ ወደ ምዕራብ ወደ ሰሜንና ደቡብ የምትበርበት የብርሃን ሠረገላ ሰጠሁህ። ሉቃስና ዮሐንስ የጻፉትን ወንጌል ባነበብክ ጊዜ ሥጋዬንና ደሜን በዚያ ትቀበል ዘንድ በላዩ ተቀምጠህ ወደ ኢየሩሳሌም የምትሄድበት የእሳት ሠረገላ ሰጠሁህ” አለው፡፡

ከብዙ ዘመናትና ከብዙ ተጋድሎ በኋላ የሚሞትበት ጊዜ ሲደርስ ለሞቱ ምክንያት የሚሆን ቸነፈር ያዘው። ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱ መጥቶ “ወዳጄ ሀብተ ማርያም ሰላም ለአንተ ይሁን፤ ዛሬ ግን የመጣሁት ከድካም ወደ ዕረፍት ልወስድህ ነው። እነሆ ሰባት አክሊላትን አዘጋጅቼልሃለሁና፤ አንዱ ስለ ድንግልናህ፣ ሁለተኛው ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉን ትተህ በመውጣትህ፣ ሦስተኛው ፍጹም ስለሆነው ምንኵስናህ፣ አራተኛው አራቱን ወንጌሎች አዘውትረህ የምታነብ በመሆንህ፣ አምስተኛው ስለ እኔ ፍቅር መራብና መጠማትን ስለታገሥህ፣ ስድስተኛው በልብህ ቂምና በቀልን ባለማሳደርህ፣ ሰባተኛውም ስለ ንጹሕ ክህነትህና ስለምታሳርገው ያማረ የተወደደ ዕጣንህና መሥዋዕትህ ሰጠሁህ። እነዚህ ሰባቱ አክሊላትም ለእያንዳንዳቸው ዐሥራ አምስት ዐሥራ አምስት ኅብር አላቸው።

መታሰቢያህን ካደረጉና በጸሎትህ ከተማጸኑ ጋር የምትገባበትን ቤት በውስጧ አምስት መቶ የወርቅ ዐምዶች የተተከሉባትን ሰጠሁህ። ደግሞ የእሳት መስቀልን የወርቅ ጫማን የብርሃን ልብስን ሥውር የሆነ መናን እሰጥሃለሁ” አለው፡፡

  መድኃኒታችንም ይህን ቃል ኪዳን ሲሰጠው በየነገዳቸውና በየሥርዓታቸው ዘጠና ዘጠኝ የመላእክት ሠራዊት መጥተው “ወዳጃችን ሰላም ለአንተ ይሁን! ዛሬስ ከፀሐይ ሰባት እጅ ወደምታበራ ሀገራችን በዝማሬና በማኅሌት አክብረን ልንወስድህ መጣን” አሉት፡፡ አባታችን  ሀብተ ማርያምም “በሰማያት ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ሰላም ሆነ፤ የሰው ነጻነቱ ሊሰጠው” አለ፡፡

ይህንንም በተናገረ ጊዜ ጌታችን በሦስትነቱ ተገልጦ ታየውና “የመጥምቁ ዮሐንስን ሀገር ተጠጋግታ ያለች ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ ሀገርን እሰጥህ ዘንድ በራሴ ማልኩልህ” አለው፡፡

“መታሰቢያህን የሚያደርገውን፣ በስምህ ለቤተክርስቲያን መባዕ የሚሰጠውን፣ ስምህን የጠራውን ወደዚህች ሀገር አገባዋለሁ፤ ዓራቱን ወንጌሎችም እያነበብክ ስለኖርክ የየአንዲቱን ቃል ፍሬዋን እንደ አንድ ሺህ አደረግሁልህ፤ ይኸውም ከአንተ በኋላ ለሚመጡ ልጆች መጽሐፈ ገድልህን ለሚያነቡና በእምነት ለሚሰሙ የገድልህ መጽሐፍ በተነበበበት ውኃ ለሚረጩ ለሚነከሩበት ይህን ቃልኪዳን ሰጥቼሃለሁ፡፡

ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን አፉን ሦስት ጊዜ ሳመው በዚያንም ጊዜ ከፍቅሩ ጣዕም ብዛት የተነሣ ነፍሱ ከሥጋዋ ተለየች፤ ጌታችንም ተቀብሎ አቅፎ ከእርሱ ጋር አሳረጋት፡፡ በመላእክት ጉባኤም ብዙ ምስጋና ተደረገ፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በዚህ ጻድቅ ጸሎት ይማረን፤ በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር፤ 

ኢንኅድግ ማኅበረነ እግዚአብሔር ምስሌነ።