
ጊዜ ተስዓቱ ሰዓት
አጽንኖ ርእሱ ኢየሱስ
ወይቤ ተፈጸመ ኩሉ
ለሦስት ሰዓታት በመስቀል ላይ የቆየው ጌታችን የተናገራቸው ሰባት ንግግሮችን ብቻ ነበር። በዙሪያው ሳያቋርጡ የሚጮኹ ሰዎች በተሰበሰቡበት እርሱ ግን እርሱ ሰዊ፣ እርሱ ተሰዊ (መስዋዕት)፣ እርሱ መስዋዕት ተቀባይ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክነቱን በሰባት ወሳኝ ቃላት ብቻ ተናገረ።
ቃላቱ ለብቻቸው በብዙ የሚተነተኑና የሰፉ ቢሆንም የተወሰነ አይተናቸው ወደ ርዕሳችን ተፈጸመ እንመለሳለን።
ኤሎሄ ኤሎሄ ኤልማስ ላማ ሰበቅታኒ ማቴ.27፤46
ዳግማዊው አዳም የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ በአዳም ፈንታ መስዋዕት አቅራቢ ሆኖ የአዳምን ጩኸት ጮኸለት።
አባት ሆይ የሚያደርጉትን አየውቁምና ይቅር በላቸው፤ ሉቃ.23:34
መስዋዕትን የሚያቀርብ ሊቀ ካህን ስለህዝቡ ይቅርታ እንዲለምን እንደ መልከጸዲቅ የዘለዓለም ሊቀ ካህን የሆነ ክርስቶስ ስለ ህዝቡ ሁሉ ሃጢአት ልመናን ያቀርብ ዘንድ ይቅር በላቸው አለ።
አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ፡፡ ሉቃ.23፤46
የአለምን ሃጢአት የሚያስተሰርይ አማናዊ በግዕ እንደሆነ የተመሰከረለት ክርስቶስ መስዋዕትነቱን ሲገልፅ ይህን ተናገረ። አባ ህርያቆስ እንደተናገረው ወየው የሚናገር በግ እንደምን ያለ ነው??
እውነት እውነት እልሃለሁ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ፡፡ ሉቃ.23፤43
በድካሙ ተሳልቀው በሕማሙ በሚቀልዱ መሐል የክርስቶስን አምላክነት የተረዳው በቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ ባለው ጊዜ በመልዕልተ መስቀል ላይ ሆኖ ፈረደለት።
ተጠማሁ፤ ዮሐ.19፤30
ለፊያታዊው በገባለት ቃል አምላክነቱን መግለፅ የወደደ ክርስቶስ ሰውነቱን ይገልፅ ዘንድ ተጠማሁ አለ። በመዝሙረኛው ዳዊት የተነገረ ትንቢቱ ይፈፀም ዘንድ ተጠማው አለ ሀሞትና ከርቤም ቀላቅለው ሰጡት።
እናትህ እነኋት፤ እነሆ ልጅሽ፤ ዮሐ.19፤26-27
በእለተ ሐሙስ ሁሉንም በስምህ ጠብቃቸው ብሎ ለአባቱ አደራ የሰጠው ጌታ በዕለተ አርብም ከመስቀሉ ሥር የተገኘውን ሐዋርያ ዮሐንስን ለእናቱ በአደራ ሰጣት። በበዛ ሃዘን ውስጥ ያለችውን እናቱን ያፅናና ዘንድ በተሰጠው በአንፃረ ዮሐንስ ለምዕመናን ሁሉ ለቤተክርስቲያንም እናት ትሆን ዘንድ ሰጣት።
ተፈጸመ፤ ዮሐ.19፤30
ወደ ጠቅላዩ ቃል እንመለስ። የሕማሙ ምስክር የሆነ ዮሐንስ ተፈፀመ ብሎ ከተናገረ በኋላ ራሱን አዘንብሎ ነፍሱን እንደሰጠ ይነግረናልና ይህቺ በመስቀል የተናገራት የመጨረሻ ቃል ናት።
ለመሆኑ የተፈፀመው ምንድነው?
1. ከእግዚአብሔር አብ የተላከበት ተግባር ተፈፀመ
ምንም እንኳን የክርስቶስ መምጣት የማይነጣጠል የሥላሴ ፈቃድ ቢሆንም ቃል ከልብ እንደሚወጣ እርሱም ከእግዚአብሔር አብ የወጣ ነውና ከእግዚአብሔር አብ ወደ ምድር የመጣበትን ተግባር ስለ መፈፀሙ ተፈጸመ ብሎ ተናገረ። አስቀድሞ በዕለተ ሐሙስም ይህን የመሰለ ቃል ተናግሮ ነበር። “እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ፤” ዮሐ 17፥4
2. ይሰራው ያለው ፅድቅ ሁሉ ተፈጸመ
በባሕረ ዮርዳኖስ ከመንገድ ጠራጊው ዮሐንስ ጋር ሲነጋገር “ አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና (ማቴዎስ 3፥15) እንዳለው በሥጋው ወራት ይፈጽም ዘንድ ያለውን ሁሉንም የፅድቅ ስራ ፈጽሟልና ተፈጸመ አለ።
3. ዘመነ መርገምና ፍዳ ተፈፀመ
የቀደመው የሰው ልጅ በድሏልና በበደሉ የመጣበት እርግማንን አስወግዷልና የአዳም ዘመነ ፍዳ ተፈፀመ
“በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፤ እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል፤” ቆላ 2፥14
4. የሐጢአትና የሞት ገዢነት ተፈፀመ
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?” 1ኛ ቆሮ 15፥55 እያለ ይጠይቃል። ትናንት በብሉይ ኪዳን የነበሩ ሰዎችን ይወጋበት የነበረው ዘመን ተፈጽሟልና ተፈፀመ አለ።
5. የነቢያት ትንቢትና ልዩ ልዩ ምሳሌያት ተፈፀመ
የወልደ እግዚአብሔር ሰው መሆን አስቀድሞውንም በብዙ ምሳሌያትና ህብረ አምሳላት የተነበረ ነበር። ከፅንሰቱ እስከ ስቅለቱ ድረስ በኦሪትና በነብያት የተነገሩት ሁሉ ተፈጽመዋልና ተፈፀመ አለ።
6. በመስቀሉ የሰራው የአስታራቂነት ስራ ተፈጽሟልና ተፈፀመ አለ
ዝንጉዖች ዛሬም ይማልድልናል እንደሚሉት የዘወትር አማላጅነት የሚፈጽም አይደለምና አንድ ጊዜ የማስታረቅ ስራውን ፈጽሟልና ተፈፀመ አለ። ቅዱስ ጳውሎስም ይህን ሲያጠይቅ ” ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥ የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ” ዕብ 9:10-11 ብሎ ተናገረ።
“ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ፦ ተፈጸመ አለ፥ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ።” ዮሐ 19፥30
ኦ ዘጥዕመ ሞተ በሥጋ

