✨ቀዳም ሥዑር(የተሻረች ቅዳሜ)

ቀዳም ስዑር ለምለም ቅዳሜ፣ ቅዱስ ቅዳሜ ትባላለች፡፡

    ቀዳም ሥዑር መባሉ ከወትሮው ዕለታት በተለየ ይህችኛዋ ዕለት በጾም ስለምትታሰብ የተሻረች ቅዳሜ እንላታለን፡፡

ለምለም ቅዳሜ መባሏም ካህናቱ የምሥራች አብሳሪ የሆነውን ቄጤማ ይዘው ወደ ምእመናን ቤት ስለሚሔዱ ለምለም ቅዳሜ ትባላለች፡፡

  ቅዱስ ቅዳሜ መባሉም ቅዱስ እግዚአብሔር አምላካችን በጥንተ ተፈጥሮ ሃያ ሁለቱን ስነ ፍጥረታት የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሄዱትን እና በክንፍ የሚበሩትን፣ በባሕር የሚዋኙትንና በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረው በዕለተ ዐርብ ሲሆን ቅዳሜ ዕለት ደግሞ ከሥራው ያረፈበት ዕለት ናት፡፡

   በዘመነ ሐዲስም የማዳን ሥራውን አከናውኖ በከርሰ መቃብር አድሮ በአካለ ነፍስም ሲዖልን በርብሮ ተግዘው የነበሩትን ነፍሳት ያወጣበት ዕለት በመሆኑ ቅዱስ /ልዩ/ ቅዳሜ ተብላ ተሰይማለች፡፡ ዕለቱ ዝርዘር አድርገን ስንመለከተውም ይህች የመጀመሪያው ቅዳሜ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት ናት፤ እግዚአብሔር ሥነ ፍጥረትን ፈጥሮ ስላረፈባት ሰንበት ዐባይ (ታላቋ ሰንበት) ትባላለች (ዘፍ. 1፡3)

   ይህችን ታላቋን ሰንበትም እንዲያከብሯት ሕዝበ እግዚአብሔር የተባሉ እስራኤላውያን ታዘው ነበር፡፡
ዕለተ ቀዳሚት (ሰንበት ዐባይ) በዘመነ ሐዲስም የተለየ የድኅነት ሥራ ተከናውኖባታል፡፡ ጥንት ሥነ ፍጥረትን በመፍጠር ዕረፍት እንደተደረገባት ሁሉ በሐዲስ ኪዳንም አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት የተቀበለው ቸሩ አምላክ በሐዲስ መቃብር አርፎባታል (ማቴ. 27፡61)፡፡

በዚህች ዕለት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሰ መቃብር ዐርፎ የዋለባት ዕለት በመሆኗ በምሥጢር ከሰንበት ዐባይ ጋር ትገናኛለች፡፡
ቀዳም ስዑር (የተሻረች ቅዳሜ) የተሰኘችውም በዓመት አንድ ቀን ስለምትጾም ነው፡፡

   እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታ ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት አንስተው ብርሃነ ትንሣኤውን እስከሚያዩ ድረስ እህል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደርጉት የነበረ መምህራቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ነገረ ሞቱን በማሰብና ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡

   ከቅዱሳን ሐዋርያት ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው ትውፊት መሠረት ቅዱሳን ሐዋርያት በሐዘን፣ በጾምና በጸሎት ዕለቷን እንዳከበሯት ክርስቲኖችም የተቻላቸው ከዓርብ ጀምረው በማክፈል፣ አሊያም ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም የጌታን ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡

ቅዳሜ ጧት ምእመናኑና ካህናቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፡፡

   የጧቱ ጸሎት ሲፈጸም ”ገብረ ሰላመ በመስቀሉ” በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ፣ ሰላምን ፈጠረ፤ የምሥራች እየተባለ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰበው ሁሉ ቄጠማ ይሰጣል፡፡ የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ምእመናኑም እየሰነጠቁ በራሳቸው ያስሩታል፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ላልመጡት ምእመናንም ካህናት በየሰበካቸው ልብሰ ተክህኖ ለብሰው መስቀልና ቃጭል ይዘው ቄጠማውን የምሥራች እያሉ ያድላሉ፡፡

    የዚህ የቄጠማው ታሪክ መነሻው የኖኅ ዘመን ታሪክ ነው፡፡ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሰዎች በማየ አይህ ከጠፉ በኋላ የውኃውን መጉደል እንድትመለከት የተላከች ርግብ የምሥራች ምልክት የሆነ ለምለም ቄጠማ በአፏ ይዛ ተመልሳለች፡፡ በዚህም የውኃው መጉደል፣ የቅጣቱ ዘመን ማለፍ ተረጋግጧል (ዘፍ. 9፡ 1-29)፡፡

    ቄጠማ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደሆነው ሁሉ አሁንም በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ ስትል ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የሆነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፣ በጣታቸው ቀለበት ያደርጉታል፡፡

የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን፣ ከሚያቃጥለው ዋዕየ ሲዖል (የሲዖል ቃጠሎ) ወደ ልምላሜ ገነት፣ ጥንተ ማኅደራቸው መመለሳቸውን በዚህ አኳኋን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡

   ምንጭ :- አትሮንስ ዘተዋህዶ

🏡ቤተሰብ ይሁኑ!
የዩቲዩብ ቻናል፡
http://youtube.com/@EMislene
የቴሌግራም ቻናል፡
https://t.me/EMislene
የፌስቡክ ገጽ፡
https://www.facebook.com/EMislene/