
ክሪስቶስ አንስቲ (Χριστός Ανέστη)ክርስቶስ ተነስቷል ለሚለው ቃል የግሪክ አቻ ነው። ቃሉን በኢየሩሳሌም የሚገኙ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ በልዩ ልዩ ቋንቋ ደውላቸውን እየመቱ ለከተማዋ ያውጁታል። ከዚህ አዋጅ በፊት ግን የጌታችን የመድኃኒታችንና የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድስት ሥጋ ያረፈበት መቃብሩ ከሚገኝበት የትንሳኤው ቤተክርስቲያን በመላው ኦርቶዶክሳውያን የሚጠበቅ አንድ ነገር አለ። – የትንሳኤው ቅዱስ እሳት
እንደ ቤተክርስቲያን ታሪክና በ2016ዓ.ም የእድሜ መመርመሪያ መሳሪያ (OSL) በመጠቀም በአቴንስ ዩንቨርስቲ የተሰራው ጥናትም እንደሚያመላክው የትንሳኤው ቤተክርስቲያን በንጉስ ቆስጠንጢኖስ ዘመን የተሰራ ሲሆን በውስጡም የጌታችንን መቃብር ይገኝበታል። ቤተመቅደሱ የተሰራው ከካልሲየም አለት፣ ከእምነ በረድና ከእንጨት ሲሆን በዓመት ሁለት የትንሳኤ በዓላት (የጎርጎርዮሳዊያንና የኦርቶዶክሳዊያን) በዓላት ይከበሩበታል።
በዚህ ቤተክርስቲያን የቅዱሱ እሳት ተአምር የሚጀምረው በኛ ከቀኑ አራት ሰአት ላይ ነው። በኢየሩሳሌም ከተማ ከንቲባ ፅ/ቤትና ና በፓሊስ መምሪያው ትዕዛዝ የእስራኤል ፓሊስ እስከ ቀትር 6 ሰዓት ድረስ 3 ጊዜ ቤተ መቅደሱን በመፈተሽ ምንም አይነት ተቀጣጣይ ነገር ክርስቶስ በተቀበረበት ዋሻም ሆነ በቤተመቅደሱ እንደሌለ ያረጋግጣሉ። ፍተሻቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ሁለት ሙስሊም አባወራዎች ቤተመቅደሱን ቆልፈው በማህተማቸው አትመው ያሽጉታል። በማስከተልም የትንሳኤ ዋዜማ የጸሎት ሥርዓት የሚከናወንበት ሰዓት ሲደርስ በኢየሩሳሌም የግሪክ ሊቀ ጳጳሳት መሪነት የአርመን ሐዋርያዊት ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ፓትሪያርክ፣ የግብፅና የሶሪያ አብያተክርስቲያናት ልዑካንና ከልዩ ልዩ የዓለም ክፍል የተሰባሰቡ ኦርቶዶክሳዊያን ምዕመናን በተገኙበት ሥርዓተ ፀሎቱ ይጀመራል።
የጸሎቱ ሥርዓት እንደተጠናቀቀ የግሪኩ ፓትሪያርክ ልብሰ ፕትርክናቸውን (ካባቸውንና አክሊላቸውን) አውልቀው ምንም ተቀጣጣይ ነገር አለመያዛቸውን በእስራኤል የፀጥታ ሃይሎች ከተፈተሹ በኋላ 20 በ25 ጫማ (1ጫማ = 0.305 ሜትር) ስፋት ወዳለው የክርስቶስ የመቃብር ቦታ (ኤዲኪዩር) ሻማ ይዘው ይገባሉ። በኢየሩሳሌም ቤተመቅደስና በዙሪያው ያሉ መብራቶች ይጠፋሉ። ሁሉም ነገር ፀጥ ብሎ ምዕመናን ቅዱሱን እሳት መጠበቅ ይጀምራሉ። ሊቀ ጳጳሱ በዋሻው ውስጥ ከቆዩ በኋላ ቅዱሱን እሳት ይዘው በመውጣት በመጀመሪያ የአርመኑን ፓትርያርክ ሻማ በመለኮስ እንደየ ክህነታዊ ደረጃቸው ለግብፅና ሦርያ ልዑካን ይሰጣሉ። በመቀጠል እሳቱ ለምዕመናን ሁሉ ይዳረሳል።
የኢየሩሳሌም ከተማም የኢየሱስን ትንሳኤ በሚያውጅ ደውል ይናጣሉ። እሳቱ በአካባቢው ወደሚገኙ አብያተክርስቲያናት ይሰራጫል። ከዛም አልፎ በፈጣን አውሮፕላኖች ወደ ግብፅ፣ አረመን፣ ሩሲያ፣ ሰርቢያና መሰል ሃገራት ይሰራጫል።
ለ20 ዓመታት የኢየሩሳሌም ሊቀጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ዱዶሮስ በፈረንጆቹ 1988 ዓ.ም በነበራቸው ቃለ መጠይቅ በጌታችን መቃብር ዋሻ ለብቻቸው ከገቡ በኋላ ውስጥ ስለሚሆነው ነገር ሲናገሩ በጨለማ ውስጥ መንገድ እየፈለኩ ወደ ውስጥ እገባና ከጌታችን መቃብር ላይ ጸሎት አደርጋለሁ። ብዙ ጊዜ ጸሎቱን እንደጨረስኩ አንዳንዴ ደግሞ ደቂቃዎችን ዘግየት ብሎ ልዩ መልክ ያለው እሳት ይመጣል። እኔም ሻማዬን እለኩስና ወጥቼ በመጀመሪያ ለአርመኑ ፓትርያርክ በመቀጠልም ለምዕመናን ሁሉ አሰራጫለሁ። ብለው ነበር።
ስለዚህ ቅዱስ እሳት የተዘገበ ጥንታዊ ዘገባ የዛሬ 1700 ዓመት በ4ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሲሆን በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ትውፊታዊ መረጃ የእሳቱ መታየትን ወደ 1ኛው ክፍለ ዘመን ይወስደዋል። የኒሳኑ ቅዱስ ጎርጎርዮስና ቅዱስ ዮሐንስ ደማስዮስ በትንሳኤው 1 ዓመት ማለትም በ 34ዓ.ም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታችን መቃብር እሳቱን ማየቱን ፅፈዋል።
ታሪካዊው ማስረጃ ግን በክርስቲያኖች የተዘገበ ብቻ አይደለም በ964 ዓ.ም የሞተው ሙስሊሙ የአረብ የታሪክ ተመራማሪ ኢብን አል ቃስና በ1000ዓ.ም አካባቢ ኢየሩሳሌምን የጎበኘው አል ባይሩኒም በታሪክ ማስታወሻቸው ላይ እውነትነቱን የዘገቡ ሲሆን በቱርክ ኢስላማዊ መንግስት ትመራ የነበረችው ኢየሩሳሌም በከተማዋ ሱልጣን/አሚርና በከተማዋ ኢማም (ዋና የእስልምና የሃይማኖት አባት) ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚከወንና የከተማዋ መስጊዶች መብራት ጭምር ከትንሳኤው ቤተክርስቲያን ቅዱስ እሳት እንደሚለኮስ ፅፈዋል።
የትንሳኤው ቅዱስ እሳት ለየት የሚያረገው ያለ ለኳሽ መብራቱ ብቻ ሳይሆን የእሳቱም ለየት ያለ ተፈጥሮ ነው። አቡነ ዲዶርዮስም ሆነ ብዙዎች እንደሚናገሩት እሳቱ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ያህል አያቃጥልም። በቅዱሱ እሳት ዙሪያ የተቀረፁ ቪዲዮች እንደሚያሳዩት ምዕመናኑ ያለምንም ጉዳት እሳቱን ሲደባበሱ ያሳያል። ነገር ግን ይሄ ለደቂቃዎች ብቻ የሚቆይ ነው ይላሉ የኦርቶዶክስ ሳይንቲስቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ተመራማሪው አባ ገናዲ ዛይድዜ። ራሳቸው በ2016 ዓ.ም የሙቀት መለኪያ (Pyrometer) በመጠቀም ባደረጉት ምርመራ ሊቀ ጳጳሱ እሳቱን ይዘውት ከወጡ ከተወሰነ ቆይታ በኋላ ሲለኩት 42° ሴንቲ ግሬድ (መደበኛ ሙቀት) የነበረ ሲሆን ከ15 ደቂቃዎች በኋላ ግን የእሳቱ የሙቀት መጠን ወደ 350° ሴንቲግሬድ ከፍ ማለቱን ይገልፃሉ።
በሩሲያ ብሔራዊ የኒዩክለር ጥናት ዩንቨርስቲ የማቴሪያል መካኒክስ ረዳት ፕሮፌሰርና የሂሳብና ፊዚክስ ሊቁ ዶ/ር አንድሪው ፎልኮም በ2008 ከመቃብሩ 15 ሜትር ርቀት ላይ የኤሌክትሮ ማግኔቲክ ፍሪኩዌንሲ መለኪያ ማሽን (oscilloscope) በመግጠም ባካሄዱት ጥናት ተዓምሩ በሚከናወንበት ወቅት ላይ ብቻ የተለየ የሙቀት ባህርይ (low temperature plasma) እንደሚታይ ጠቅሰው ምርምሩን ባካሄዱበት ወቅት ኢየሩሳሌም በመደበኛ አየር ንብረቷ ላይ እንደ ነበረችና ልኬቱን የሚያዛባ ምንም አይነት ከባድ ነፋስ እንዳልነበር አረጋግጠዋል።
የቤተክርስቲያኑ ዜና መዋዕሎች ደግሞ አንዳች የተለየ ታሪክን ዘግበዋል በፈረንጆቹ 1579 የነበሩት የቱርክ መሪዎች ሊቀ ጳጳሱን ሶፎንያስ 4ኛና ምዕመናኑን ቤተመቅደስ እንዳይገቡና በዓሉን እንዳያከብሩ አገዷቸው። የታገዱት ካህናትና ምዕመናንም ከመቅደሱ በር በስተግራ በቆሙት ሊቀ ጳጳሳቸው ከውጭ ሆነው ሥርዓተ ጸሎቱን አድርሰው እንደጨረሱ ቅዱሱ እሳቱ የቤተክርስቲያኑን ግድግዳ ሰንጥቆ በመውጣቱ ሊቀ ጳጳሱም እሳቱን መለኮስና ለሁሉም ማጋራታቸው ተዘግቧል። እሳቱ የሰነጠቀውም ቦታ አሁንም ድረስ ይታያል።
በስንጥቃቱ ዙሪያ ያጠናው ሩሲያዊው ሳይንቲስት ኢቭጋኒ ሚካኤሎቪችም ይህ ስንጥቃት በአንዳች ሃይል የተፈጠረ እንጂ ሰው ሰራሽ ሊሆን አይችልም ምክንያቱም በ16ኛው ክፍለ ዘመን የሳይንስ እውቀት እንዲህ አይነት ስንጥቃት መፍጠር የማይታሰብ መሆኑን ያትታል።
በተአምር በማያምኑ ወይም በሚጠራጠሩ ወገኖች ተአምሩን እንደ አንድ ማጭበርበር ወይም ማታለል (fraud/trick) የሚወስዱት ሲሆን ማጭበርበሩ ተፈጽሟል ሲሉ ሁለት መላምቶችን ያስቀምጣሉ አንደኛው ቤተመቅደሱ ውስጥ የተቀመጠ ወይም ሊቀ ጳጳሱ ይዘውት የሚገቡት ተቀጣጣይ ነገር ይኖራል የሚል ሲሆን ይህ መላምት ውድቅ የሚያደርገው ከሥርዓቱ በፊት በሊቀጳጳሱም ላይ ሆነ በቤተመቅደሱ ላይ ጥብቅ ፍተሻና ቁጥጥር መደረጉ ነው። ቁጥጥሩ የሚደረገው በቤተክርስቲያኗ ሳይሆን በመንግስት አካላት መሆኑና ፍተሻውን የሚያካሂዱት የክርስቶስን ትንሳኤ የሚክዱት የአይሁድና የእስልምና እምነት ተከታዮች መሆኑ ደግሞ ፍተሻው ምን ያህል ጠንካራ መሆኑን አመላካች ነው።
ሌሎች ተጠራጣሪዎች ደግሞ በራሱ የሚነደው ነጭ ድኝ (White phosphorus) ይጠቀማሉ ባይ ናቸው የነዚህ ክርክርም ቢሆን ሚዛን የማይደፋ ሆኖ ይገኛል። በመጀመሪያ በፍተሻ ወቅት መያዙ አይቀርም ግን አለፈ እንኳን ቢባል እንደዚህ አይነት እሳት መፍጠር አይችልም።
የካምብሪጅ ዩንቨርስቲው ኤሌክትሪካል ኢንጅነር ዶ/ር ራሚ ሞርጋን እንደሚናገረው የነጭ ድኝ እሳት የተቀመጠበትን ነገር እያቃጠለ የሚነድ ሲሆን ቅዱሱ እሳት ግን ነገሮችን የማቃጠል አቅሙ ደካማ ነው ይላል። ሌላው ነገር ደግሞ ነጭ ድኝ ከባቢ አየር ላይ ካለው ኦክስጅን ጋር ሲዋሃድ ፎስፈረስ ኦክሳይድ (phosphorus oxide) የተባለ መርዛማ ጋዝ ስለሚፈጥር እሳቱ መርዛማ ይሆን ነበር። ነገር ግን እስካሁን ድረስ አንድም ታሪካዊ ሰነድ፣ አንድም ተጓዥም ሆነ የከተማዋ አስተዳደር በእሳቱ የተመረዙ (የተቃጠሉ) ሰዎች መኖራቸውን ሪፖርተር አድርገው አያውቁም ይላል።
የአቴንስ ዩንቨርስቲ የፍራክቸራል መካኒክ ምሁሩ ጆርጅ ፓፓዶብሎስ “በሳይንሳዊ አነጋገር እሳቱ ከየት እንደሚመጣ አይታወቅም” ይላል።
ፅሁፋችንን ለዚህ ዝግጅት በዋቢነት በተጠቀምነበት የሲዋይሲ የግብፅ ቤተክርስቲያን ቴሌቪዥን ዶክመንተሪ አዘጋጅ ዶ/ር ሃኒ አሽማላ ሃሳብ እናጠናቅ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 20 ላይ እንደተጠቀሰው ቶማስ የክርስቶስን ትንሳኤ በተጠራጠረ ወቅት ክርስቶስ ናና ሰውነቴን አረጋግጥ ብሎት ነበር ዛሬም በትንሳኤው ህያው ምስክር በቅዱሱ እሳት ዙሪያ የሚጠራጠር ቢኖር መጥቶ እንዲያይ እንጋብዘዋለን።
ክርስቶስ ተንስአ እም ሙታን – ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነስቷል።

