
ቤተክርስቲያን የሰማያዊያንና የምድራውያን ኅብረት ናት።
የዓለማችን እጅግ ጥንታዊና አካታች ኅብረት ቤተክርስቲያን ናት። ከሰማያዊያን መላእክት ጀምሮ እስከ ዕለት አማኝ ድረስ በአሚነ ሥላሴ ሥር ያሉትን ሁሉ ታጠቃልላለች። በመሆኑም በእያንዳንዱ ምድራዊ ኅጥእ መመለስ በሰማይ መላእክት ዘንድ ደስታ ይደረጋል። /ሉቃ 15:7, ሉቃ 15:10/ በዚህ አለም በፀናች በቀናች ሃይማኖት ውስጥ ሆነው ያንቀላፉትም ቢሆኑ በእርሱ እንደማመናቸው ቢሞቱ እንኳን ሕያው ናቸውና (ዮሐ 11:25) የሞት ኃይል ከቤተክርስቲያን ኅብረት አይነጥላቸውም። እንደውም እንደደመና በዙሪያችን ከበውን ምሳሌነታቸውን ያሳዩናል ይማልዱልናልም። (ዕብ 12:1፣ ራዕ 6:10)
የቤተክርስቲያን አንድነት የሚመነጨው ትንሳኤና ሕይወት በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ግንድነት ላይ ነው። በስሙ የሚያምኑ ሁሉ ቅርንጫፎቹ ናቸው። ፍሬ ማፍራትን እንቢ ካላሉ በስተቀር የትኛውም ኃይል ከግንዱ ክርስቶስ ሊያላቅቃቸው አይችልም። (ዮሐ 15:1-5) በዕለተ ሐሙስ ጸሎቱ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክርስቲያኖች አንድነት የዘለዓለማዊው የቅድስት ሥላሴ አንድነት (የፈቃድ፣ የሀሳብ፣ የስልጣን) መልክ መሆኑን ይነግረናል:- “..ከዚህም በኋላ በዓለም አይደለሁም፥ እነርሱም በዓለም ናቸው፥ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ። ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው።.…እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል።…” ዮሐ 17:11-23 ። ለዛም ነው ፈቃዳቸውን ለእግዚአብሔር በማስገዛት በሐዋርያት ሥራ እንደምናነበው በስሙ ያመኑ ሁሉ በአንድ ልብ ነበሩ የተባለው። ሐዋ 1:14፣ 2:1፣ 4:24፣ 5:12፣ 15:26። ያም ልብ የክርስቶስ ልብ ነው። 1ቆሮ 2:16።
ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተች ናት። ቤተክርስቲያን የተመሰረተችው በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነትን በሚገልፅ መሠረተ እምነት ላይ ነው። ለዚህም ነው ክርስቶስ፡ ጴጥሮስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ ብሎ ሲመሰክር አንተ አለት (በግሪኩ Πέτρος – ጴጥሮስ) ትባላለህ ካለው በኋላ ምስክርነቱን በሴት አንቀጽ በዚህችም አለት (በግሪኩ πέτρα – ጴጥራ ) ቤተክርስቲያኔን እመሰርታለሁ ብሎ ተናግሯል ። የመመስረቻው አለት ጴጥሮስን ከሰየመበት አለት ተለይቶ በሴት አንቀጽ መነገሩ ሐዋርያው በተናገራት የእግዚአብሔር ቃል እንጂ በራሱ በሐዋርያው ላይ የተመሠረተች አለመሆኑን ይነግረናል (ማቴ 16: 15-18)። ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር ቃል ተመስርታለች ስንል ምን ማለታችን ነው የሚል ካለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይለናል “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤” ኤፌሶን 2፥20 በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የሚናገሩ የነቢያትና የሐዋርያት፡ የመጻሕፍትም ሆነ የትውፊት ትምህርቶች የቤተክርስቲያን መሠረቶች ናቸው።
ራሷ ክርስቶስ ነው እሷም አካሉ ናት። የቤተክርስቲያንና የክርስቶስ ግንኙነት በዘመናት ውስጥ ለአይን ጥቅሻ እንኳን የተቋረጠ አይደለም። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ “እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” ማቴዎስ 28፥20 ብሎ እንደተናገረው ለቅፅበት እንኳን እርሱ ቤተክርስቲያንን ሊተዋት አይችልም። ከክርስቶስ የተለየች ቤተክርስቲያን ትሞታለች ምክንያቱም ክርስቶስ የቤተክርስቲያን ራሷ እርሷም አካሉ ናትና። አንዳንዶች ክርስቶስ የቤተክርስቲያን ራስ ነው ስንል ምሳሌ (Metaphor) አድርገው ይወስዱታል ነገር ግን እውነታው ይህ አይደለም። ብርሃነ አለም ጳውሎስ በኤፌሶን የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ስለ ክርስቶስ ሕማም ከተናገረ በኋላ “ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው።” ኤፌሶን 1፥22 ብሎ ራስነቱ የምሳሌ ሳይሆን የእውነት መሆኑን ያስረዳናል። ለአካሉ ራስ እንደመሆኑ መጠን በቤተክርስቲያን ላይ የሚደርስን ነገር ሁሉ በእርሱ ላይ እንደደረሰ ይቆጥረዋል። ይህንን ቅዱስ ጳውሎስ በቀደመ ዘመኑ አስተውሎታል። ከክርስቶስ እርገት በኋላ ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ሲፋጠን የነበረው ሳውል (በቀድሞ ስሙ) በታላቅ ብርሃን ውስጥ የገጠመው አምላካዊ ወቀሳ “ለምን ቤተክርስቲያንን ታሳድዳለህ” ሳይሆን “ለምን ታሳድደኛለህ” የሚል ነበር ምክንያቱም የቀድሞው ሳውል ያሳደደው ክርስቶስ ራሱ የሆነላትን ቤተክርስቲያንን ነውና። (ሐዋ 9:1-6) ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ራስነትን በፍፁም ልቧ የምትቀበለው በመሆኑ የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን የፖፕ የበላይነት (ራስነት) ትቃወማለች። ቤተክርስቲያን አካባቢያዊ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት (የኢትዮጵያ፣ የህንድ፣ የግብፅ፣ የሶሪያ፣ የአርመን፣ የኤርትራ ፓትሪያርክ) እንጂ ሁሉ አቀፍ ምድራዊ ራስ/አባት የላትም ምክንያቱም አለማቀፋዊ አባቷ፣ ሊቀካህኗና ራሷ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና።
ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ሙሽራናት። ቤተክርስቲያንን የሚያመለክቱ ቃላት የሚገለፁት በሴት ፆታ ነው። ይሄም በክርስቶስ አባትነትና ሙሽራነት ትይዩ ያለችው ቤተክርስቲያን የምዕመናን እናትና ሙሽራ ስለሆነች ነው። ሙሽራው ክርስቶስ ከእርሷ ጋር ነውና ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ሙሽራ ናት /ዮሐ 3:29/ በመሆኑም ሙሽራ ለሙሽሪት ባለው ፍቅር መጠን ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ተወዳለች እርሱም ነፍስን አሳልፎ እስከመስጠት ያለ ነው። (2ቆሮ 11፣ ኤፌ 5) የቤተክርስቲያን ሙሽርነት አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን በኋላም በሐዲስ ኪዳን የተገለጠ መለኮታዊ ሀሳብ ነው። ባለ ራዕዩ ዮሐንስም በዮሐንስ ራዕይ ለታረደው በግ ሙሽራ ትሆን ዘንድ አዲሲቷ ኢየሩሳሌም እንደወረደችና ይህችም የቅዱሳን ህብረት መሆኗን ይናገራል። (ራዕ 19-21)
ቤተክርስቲያን የምሥጢራት መፈፀሚያ ናት። ክርስትና ከሌሎች ሃይማኖቶች የሚለየውና አማናዊነቱ የሚገለጠው በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ጸጋ በሚገኝባቸው የጥምቀት፣ የሜሮን፣ የቁርባን፣ የንስሐ፣ የክህነት፣ የተክሊልና የቀንዲል ምሥጢራት ነው። እነዚህ ምሥጢራት አንድን ሰው አስቀድሞ ክርስቲያን በማድረግ በቤተክርስቲያን በኩል ከክርስቶስ ጋር አንድ ያደርጉታል። ይኸውም መንግስቱን መውረስ ነው። ነገር ግን ከእነዚህ ምሥጢራት አንዳቸውም በነጠላ ቁጥር ሊፈፀሙ አይችሉም። የግድ የአማንያንን ኅብረት ይጠይቃሉ በመሆኑም በአካለ ሥጋም ሆነ በአካለ ነፍስ ያሉ ምዕመናን ሊገኙ ይገባል። ከዛም ባሻገር ምሥጢራቱን የሚመራው አካል በክርስቶስ ለቤተክርስቲያን በተሰጠ ስልጣነ ክህነት ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ የተሾመ መሆን ይኖርበታል። ለዛም ነው ሐዋርያት መሰባሰብን ቁልፍ አድርገው የሚያስተምሩት (ሐዋ 15:6፣ 1ቆሮ 11) የመሰባሰቡ አስፈላጊነት “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።” ማቴ 18፥20 የሚለው የማይሻር አምላካዊ ቃል ነው በመሆኑም ምሥጢራቱን የሚፈጽሙ ሁሉ በመሰባሰብ የሚታየውን አገልግሎት አማናዊ ያደርገው ዘንድ በመሐላቸው ያለውን ክርስቶስ ይጠይቁታል።
ይቆየን

