ተፈጥሮ እንኳን አያስተምራችሁም: 1ቆሮ 11:15

ተፈጥሮ እንኳን አያስተምራችሁም: 1ቆሮ 11:15

ነገረ ድኅነታዊውን የዓለምን ታሪክ ለሁለት እንክፈል ካልን የምንከፍለው በሁለት ነው። የመጀመሪያው ዓለም አስቀድሞ የተፈጠረበት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ዓለም የታደሰበትና እንደገና የተወለደበት ዘመን ነው።

ዓለም የተፈጠረው በስድስት ቀናት ሲሆን ይሄም እግዚአብሔር ዓለምን ለማዳን የጠበቃቸው የስድስት ሺህ አመታት (5500 ዘመን) ምሳሌ መሆናቸውን ቤተክርስቲያን ታስተምራለች። በእነዚህ ስድስት ቀናት የተፈጠሩ ፍጥረታት የነገረ ድኅነት ማሳያ መሆናቸውን በወፍ በረር ለመመልከት እንሞክራለን።

እሑድ

የብሉይ ኪዳን መፅሐፍ የሚጀምረው በሥነ ፍጥረት ትረካ ነው። መጽሐፉ የሥነ ፍጥረት ትረካውን ለመጀመር የሚጠቀማት ዓረፍተ ነገር “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ” የምትል ናት። ይህች ዓረፍተ ነገር የእግዚአብሔርን አምላክነት፣ ከሃሊነትና ፈጣሪነት የምታውጅ አዋጅ ናት። የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ሊቀ ነብያት ሙሴ መጽሐፉን በጻፈበት ቋንቋ ልዩ ምሥጢር እንዳለው ይነግሩናል እንመልከተው:-
בְּרֵאשִׁית בָּרָא אֱלֹהִים אֵת הַשָּׁמַיִם וְאֵת הָאָרֶץ‎ 
(ቤሬሺት ባራ ኤሎሂም ኤት ሃሽማይም ቬት ሃ’ርትዝ)

እንደ ሊቁ ጠርጡለስ ያሉ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በመጀመሪያ የሚለው ቃል ከጊዜ ገላጭነቱ ባሻገር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የፍጥረት መጀመሪያ ብሎ የጠራውን መነሻ በማድረግ መጀመሪያ የሚለው ቃል የኢየሱስ ክርስቶስ ስሙ ነው ይላሉ። በዮሐንስ ወንጌል ላይም ሥጋን የተዋሐደ ቃል እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ሲያጠይቅ በመጀመሪያም ቃል ነበረ ብሎ የቃል (የክርስቶስ)ን መጀመሪያነት ይናገራል። “ባራ/ፈጠረ” የሚለውም ቃል በእብራይስጥ ለእግዚአብሔር ብቻ የሚነገር አምላካዊ የመፍጠር ችሎታን የሚናገር ቃል ነው።

የዕብራይስጡ ኤሎሒም የሚለው ቃል ደግሞ በሐዲስ ኪዳን በገሃድ ስለተነገረው ስለ ምሥጢረ ሥላሴ ይናገራል ምክንያቱም ኤሎሂም የኤል (አምላክ) ብዙ ቁጥር አመልካች / Plural/ ሲሆን ፈጠረ የተባለበት ቃል ባራ ግን ነጠላ ቁጥር /singular/ መሆኑ የእግዚአብሔርን ልዩ ሦስትነት አመልካች ነው። ለአያያዥነት የምትገባው “ኤት” ከፊደል አፃፃፏ ባሻገር ባላት የዕብራይስጥ ሥዕላዊ መግለጫ ደግሞ እጅግ ድንቅ ምስልን ይሰጠናል። ኤት የአሌፍና የታው ፊደላት ድምር ሲሆን አሌፍ በሥዕላዊ መግለጫ የበሬ አንገት አይነት ምልክት ሲኖረው ታው ደግሞ የመስቀል ምልክት አለው። ይሄም የኢየሱስ ክርስቶስን በመስቀል የመሰዋት ምስጢር የያዘ ነው። በቃሉ ላይ ያሉት አሌፍና ታው የዕብራይስጥ የመጀመሪያና የመጨረሻ ቃላት መሆናቸው ደግሞ አልፋና ኦሜጋ (ራዕ 21:6) ያለውን ያመላክታል።

እንግዲህ በአንዱ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ነገረ ሥላሴና ነገረ ክርስቶስ በዚህ መልክ በምሳሌያት ተጠቅሶ ይገኛል።

ሰኞ
በዕለተ ሰኞ የተሰራው ታላቅ ሥራ ከአራቱ ባህርያተ ሥጋ አንዱ የሆነውን ውሃን መከፈል ነበር። የውሃ መከፈልን ቅዱስ ባስሊዮስ በሰማይ የሚያመሰግኑና በምድር የሚራዱ የመላእክትን ሕብረት ይወክላሉ ሲል ምሳሌነቱን የሁለቱን አብያተ ክርስቲያናት (ከአይሁድና ከአህዛብ የመጡ ክርስቲያኖች) እንዲሁም በሰማይና በምድር የሚገኙ የቅድስት ቤተክርስቲያን አካላትም ይተረጎማል።

ማክሰኞ

የማክሰኞ ሥነ ፍጥረት ውስጥ በጉልህ የምናየው የምድር ማብቀል ዘወትር ማክሰኞ የምንደግመውን ውዳሴ ማርያም ያስታውሰናል። በውዳሴ ማርያሙ አፈ በረከት ቅዱስ ኤፍሬም ንፅህት ድንግል የሆነች እመቤታችንን ዘር ያልተዘራባት እርሻ አንቺ ነሽ የሕይወት ፍሬ ካንቺ ወጣ ይላታል። ብሉይ ኪዳን በኢሳያስ ትንቢትና (ኢሳ 7:14) በሉቃስ ወንጌል ላይም (ሉቃ 1:34-35) ተፅፎ እንደምናነበው ክርስቶስ የተወለደው ህቱም ድንግል ከሆነች ከእመቤታችን ማርያም ያለወንድ ዘር ነው። የመጀመሪያዋ ምድር ያለ ገበሬ በእግዚአብሔር ፈቃድ እንዳበቀለች ሁሉ እመቤታችንም በእግዚአብሔር ፈቃድ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኝታለች።

ረቡዕ

በዚህ ቀን ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ተፈጠሩ። ፀሐይ የፀሐየ ጽድቅ የክርስቶስ ምሳሌ ናት እርሱ በባህሪው ብሩህ የሆነ ነው ( ዮሐ 8:12) ጨረቃና  ከዋክብት ከፀሐይ የሚካፈሉ ሲሆን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እናንተ የክርስቶስ ተካፋዮች ናችሁ (ዕብ 3:14) እንዲል የቀደመ እምነታቸውን ጠብቀው የሚገኙ ሁሉ እነርሱም በጸጋ የዓለም ብርሃን ይሆናሉና (ማቴ 5:14) ጨረቃና ከዋክብት የቅዱሳን ምሳሌ ናቸው። ይሄውም በመስቀል በተከፈለ ዋጋ የተገኘ ክብር ነው።

ሐሙስ

ሰው ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግስት አይወርስም የሚለው ነገረ ድኅነታዊ ጥሪ ለኒቆዲሞስና ለብዙ ሰማዕያን እንግዳ ነገር ነው። ዮሐ 3:1-10 ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ግን በዕለተ ሐሙስ ነፍሳትን (እንስሳትን፣ አራዊትን፣ አዕዋፋትን) ያስገኘችውን ውሃ እንድንመለከት ይነግረናል። በውሃው ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ ሰፎ ነበር የሚለውን አብነት አድርጎ ዶሮ እንቁላሎቿን ሸፍና በሙቀት እንደምተፈለፍል ሁሉ ይህችም የቀደመችው ውሃ ሕያዋንን አስገኝታለች። የቀደመችው ውሃ በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅነትን ለምታስገኘው ውሃ ምሳሌ ናት። የቀደመችው ፍጥረታዊ ውሃ የሚባሉና የሚያስፈሩ እንስሳትን አስገኝታለች ዳግማዊቷ የድኅነት ውሃ ግን በእረኛቸው ክርስቶስ ፊት የሚሰበሰቡ በጎች ምዕመናን ታስገኛለች።

አርብ

በክርስቶስ ደም  የሰው ልጅ ዳግም የተወለደባት ዕለተ አርብ ጥላ በሆነችው ቀዳሚቷ አርብ የሰው ልጅ ተፈጠረ። የተፈጠረው በእግዚአብሔር መልክ ነው። የእግዚአብሔር መልክ ከሚተረጎምባቸው ትርጓሜዎች ብዙ ናቸው ከእነርሱም አንዱ በዮሐ 1:18፣ቆላ 1:15 ላይ በተጠቀሰው መነሻ ያ መልክ ከአዳም የልጅ ልጅ ተወልዶ የሰውን መልክ ገንዘብ የሚያደርገው የክርስቶስ መልክ መሆኑን ነው።

ቅዱስ አትናቴዎስ ነገረ ሥጋዌን በገለፀበት ድርሳን እንዳለው የአዳም ከሥጋና ከነፍስ መሰራትም የክርስቶስ የሥጋና የመለኮት ፍጹም ተዋሕዶ ማሳያ ነው። ፍፁም ተቃራኒዎቹ ስጋና ነፍስ ያለመቀላቀል፣ ያለመጠፋፋት አንድ እንደሆኑ በክርስቶስም መለኮትና ሥጋ ከሁለት አካልና ባህሪ ያለመከፈል አንድ እንደሆኑ ማሳያ ነው።

ይቆየን