
ንዑድ መምህር ቅዱስ ጳውሎስ “መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም።” 1ቆሮ 2፥15 እንዲል ባህርዩ ለማይመረመር ጌታ አካል የሆነች ቤተክርስቲያን ምሉዕ ባህርይዋን መመርመር ለሰው ልጆች የሚቻል አይደለም። ነገር ግን በቅዱሳት መጻሕፍትና እውነት ላይ ተመሥርተው ሃይማኖታቸው የቀናች 318ቱ ሊቃውንት፡ አዘውትረን በምንጸልየው የሃይማኖት ጸሎት ላይ ስለ ባህርይዋ እንዲህ ይሉናል:-
” ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኲሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት – ሐዋርያት በሰበሰቧት ከሁሉ በላይ በምትሆን በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን” ሃይማኖተ አበው ዘሠለስቱ ምዕት 17:12
በዚህ ከኒቂያ እስከ ቁስጥንጥንያ ባሉ ጉባኤያት የረቀቀው ዓለምአቀፋዊ ጸሎተ ሃይማኖት (Creed) ላይ የቤተክርስቲያን ክብር እንደ መሠረተ እምነት መጠቀሱ ቤተክርስቲያን ምን ያህል በክርስትና እምነት ውስጥ አስፈላጊ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ወደ ርዕሳችን ስንመለስ በዚህ ጸሎተ ሃይማኖት ወይም የእምነት ድንጋጌ አንቀፅ ላይ 4 የቤተክርስቲያንን ባህርያትን እንመለከታለን። አንዲት፣ ቅድስት፣ ዓለም አቀፋዊት፣ ሐዋርያዊት … እስቲ በየተራ እነዚህን ባህርያት እንመልከት
ቅድስት /Holy/
ቤተክርስቲያን ቅድስት ናት ራሷ ቅዱስ ነውና አካሉ ቅድስት ነች። “ዳሩ ግን፦ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።” 1ጴጥ 1:15-16 እንዲል ቅዱስ ጴጥሮስ በእርሱ በክርስቶስ አካልነት ውስጥ ያሉ የቤተክርስቲያን አካላት ሁሉ ከቅድስናው ተካፋይ ናቸውና ቤተክርስቲያን ቅድስት ነች፣ አንድም በጸሎተ ሃይማኖት ትርጓሜ እንደተነሳው ከጉባኤ አይሁድ፣ ከጉባኤ አህዛብ ተመርጣ የተለየች በክርስቶስ ደም የተዋጀች ስለሆነች ቤተክርስቲያን የተመረጠች፣ የተቀደሰች ነች። ሐዋ 20:28
አንዲት /One/
ቤተክርስቲያን በተለያዩ ቦታዎች እንደመገኘቷና በተለያዩ አስተዳደራዊ ክልሎች በመከፋፈሏ አብያተ ክርስቲያናት ተብሎ በብዙ ቁጥር ልትጠራ ብትችልም መነሻዋ እርሱ አንድ እግዚአብሔር እንደሆነ መዳረሻዋም እሱ እንደመሆኑ ልጆቿም በአንድ መንፈስ ቅዱስ እንደመጠመቃቸው የአንዱ ክርስቶስ አካል ናቸውና አንድ ናት። “እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን።” ሮሜ 12፥5 ዳግመኛም “አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤” ኤፌሶን 4፥5
ከሁሉ በላይ የምትሆን /በሁሉ የሞላች (Catholic)
ቤተክርስቲያን የአምላኳ አካል እንደመሆኗ መጠን እርሱ በዓለም የሞላ እንደመሆኑ ሁሉ እርሷም በሁሉ ቦታዎች አለች። በዚህ የለችም የምትባልባት ቦታ የለም እያንዳንዱ አማኝ ቤተክርስቲያን እንደ መሆኑ፣ እያንዳንዱ በእርሱ ስም የተሰበሰቡ በስሙ ያመኑት ሰዎች ስብስብ ቤተክርስቲያን እንደመባሉ እርሷ በዓለሙ ሁሉ የመላች የአንዱ የክርስቶስ መንግስቱ ነች። በሰማይም በምድርም እርሷ አለች።
“እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት።” ኤፌ 1፥23
ሐዋርያዊት (Apostolic)
እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ቅዱስ ፊላታዎስ፣ ቅዱስ አትናቴዎስ ያሉ የቀደሙ አባቶች በመልእክታቸው የቤተክርስቲያን ስም ከመጥራታቸው በፊት ሐዋርያት በሰበሰቧት የምትል ቅፅል በብዛት ይጠቀማሉ። ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት ስንል ማቴዎስ በወንጌሉ የመጨረሻው ምዕራፍ እንደዘገበው ጌታችን ለሐዋርያት ያዘዘውን “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” ማቴ 28:19-20 ቃል መሠረት በማድረግ ነው። በመሆኑም ክርስቶስ እስከ ዓለም ፍፃሜ ድረስ አብሮ የሚሆነው ለሐዋርያዊው ትምህርት ለምትታመን ቤተክርስቲያን ነው። ቅዱስ ጳውሎስም የቤተክርስቲያን እምነት በሐዋርያት ት/ት እንደታነፀ ይናገራል። ኤፌ 2:20 መምህር ጳውሎስ ከዚህም ሻገር ብሎ ወንድሞቹ የሚሆኑትን የመጀመሪያው ጳጳሳት ሐዋርያትን ወክሎ ይሄንን ግዝት ይናገራል:-
“ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።” ገላ 1:8-9
ይቆየን
/እግዚአብሔር ቢወድና ቢፈቅድ በቀጣዩ ሳምንት የቤተክርስቲያን ምሳሌያትን እንዳስሳለን/

