
ምንም እንኳን ቀጥሎ የምናያቸው ቦታዎች የቤተክርስቲያን ምሳሌያት ቢሆኑም አንዳቸውም በሁለንተናቸው ሙሉ ለሙሉ አይመስሏትም ምክንያቱም እርሷ የክርስቶስ አካሉና የሙላቱ ተካፋይ ናትና ፡፡ ኤፌ 1፥23
እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በኖኅ መርከብ ትመሰላለች (ዘፍ 7)
ሊቁ አውግስጢኖስ በማየ አይኅ/በጥፋት ውሃ/ ጊዜ ነፍሳት ከሞተ ሥጋ የዳኑባት ያቺ የኖኅ መርከብ የእውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት ይለናል፡፡ ያቺ የኖኅ መርከብ ሦስት ክፍል ነበራት፡፡ ቤተክርስቲያንም ቅድስት ፣ መቅደስ፣ ቅኔ ማኅሌት የሚባሉ ሦስት ክፍሎች አሏት፡፡ የኖኅ መርከብ በውስጧ የነበሩት ነፍሳት ሁሉ ከጥፋት ውሃ ድነዋል፡፡ ኖኅ መርከብን እንዲሠራ ያዘዘው እግዚአብሔር ነው፡፡ ቤተክርስቲያንንም የመሠረታት ራሱ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ኖኅ ወደ መርከቡ ይገቡ ዘንድ ጥሪ ያስተላለፈው ለሁሉም ነው፡፡ ቤተክርስቲያንም የሰው ልጅ ሁሉ አምኖ ይድን ዘንድ የድኅነት ጥሪዋን ለሁሉም ነው የምታስተላልፈው፡፡ የኖኅ መርከብ ፈቃደኛ ሆኖ ለመጣ ሁሉ (ለእንስሳትም ጭምር) በቅታለች፡፡ ቤተክርስቲያንም አምኖ ለመጣ ሁሉ የሚበቃ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ያላት ናት፡፡ በተጨማሪም የጥፋት ውኃው እየሞላ ሲሄድ የኖኅ መርከብ ከምድር ከፍ ከፍ እያለች ትሄድ ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን የዓለም ፈተና ሲበዛባት በውስጥዋ የሚኖሩት (በፈተና የሚፀኑት) የሚያገኙት ክብር እንደዚሁ ከፍ ከፍ እያለ ይሄዳል፡፡ ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሔር ኖኅን አሰበ፣ የጥፋት ነፋስን አሳለፈ፣ ውኃውም ጎደለ፡፡ በቤተክርስቲያን ላይም የሚመጣውን ፈተና እንደዚሁ እግዚአብሔር ያሳልፋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የኖህ መርከብ ምንም እንኳን የቤተክርስቲያን ምሳሌ ቢሆንም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ወደ ኖኅ መርከብ ተኩላ ገብቶ ሲወጣም ተኩላ ሆኖ ይወጣል:: ወደ ቤተክርስቲያን ግን ተኩላ ሆነው ገብተው በግ ሆነው የወጡ ብዙዎች ናቸው” ብሎአል:: ይህ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ንግግር በሂሳብ ትምህርት የምናገኘውን የፍጹምነት መጠን /Absolute Value/ ያስታውሰናል፡፡ የትኛውም አሉታዊ አኃዝ /Negative intiger በዚህ የፍጹምነት መጠን ││ ውስጥ ሲገባ ወደ አዎንታዊነት አኃዝ /positive intiger እንደሚቀየረውና አወንታዊ አኃዝ ሳይለወጥ እንደሚቀረው በልብ መሻት ወደ ቤተክርስቲያን የሚገባ ኃጥእ ታድሶ ይወጣባታል፡፡
እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በአብርሃም ድንኳን ትመሰላለች (ዘፍ 18፡1)
አብርሃም ሥላሴን በቤቱ በእንግድነት የተቀበለባት ያቺ የአብርሀም ድንኳን (ኀይመተ አብርሃም) የእውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ ሥላሴ በእንግድነት በአብርሀም በቤቱ ድንኳን ስር እንደተገኙ በቤተክርስቲያን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ያድራሉ፡፡ በአብርሃም ድንኳን ውስጥ አብርሃም ምሥጢረ ሥላሴን እንደተማረ በቤተክርስቲያንም ምሥጢረ ሥላሴ ይነገራልና፡፡
በአብርሃም ድንኳን ድሀ ሀብታም፣ ነጭ ጥቁር፣ የተማረ ያልተማረ፣ ኃጥእ ጻድቅ ሳትል እንግዳ እንደተቀበለች ቤተክርስቲያንም ያለ አድሎ ሁሉን በእኩል አይን ትቀበላለች፡፡ በአብርሃም ድንኳን ምግበ ሥጋ ይመገቡባት እንደነበር በቤተክርስቲያንም ሥጋ ወደሙና ቃለ እግዚአብሔር እንመገባለን፡፡ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ቤተክርስቲያን በአብርሀም ድንኳን ትመሰላለች፡፡
በአብርሀም ድንኳን ውስጥ የነበሩት ሁሉ የየራሳቸው ምሳሌ አላቸው፡፡ አብርሀም የካህናት ምሳሌ ነው፡፡ መስዋዕትን ለእግዚአብሔር ሲሰዋ የነበረ ነውና፡፡ በአብርሀም ቤት ይስተናገዱ የነበሩት እንግዶች የክርስቲያኖች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያን በዚች ምድር ላይ ሲኖር እንግዳ ነውና፡፡ ምግበ ነፍስንም (የእግዚአብሔር ቃልንና የክርስቶስን ሥጋና ደም) ወደ ቤተክርስቲያን ቀርቦ ይመገባል፡፡ አብርሀም ቤት ሳይሠራ በድንኳን ውስጥ እድሜውን ሁሉ ኖሯል፡፡ ፍፁማን አገልጋዮችም እንደ አብርሀም ዓለምንና ጣዕሟን ሁሉ ንቀው ቤተክርስቲያንን ተጠግተው ይኖራሉና አብርሀም የእነዚህ አርአያ ነው፡፡ ሥሉስ ቅዱስ በአብርሀም ቤት ተገኝተው ቤቱን በበረከት ሞልተውታል፡፡ ዛሬም እንደዚሁ በእውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ተገኝተው ላመኑትና ለታመኑት ሁሉ ድኅነትን ያድላሉ፡፡
ከዚህ ሌላ ሰይጣን እንግዶች ወደ አብርሃም ድንኳን እንዳይሄዱ ይከለክል እንደነበር በትርጓሜ መጻሕፍት ሊቃውንት አስተምረዋል፡፡ ይህም ምሳሌው ክርስቲያኖች ወደ እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ሲሄዱ የተለያዩ ፈተናዎች እያቀረበ ሊያስቀራቸው እንደሚሞክር የሚያሳይ ነው፡፡ እንግዶች ቢቀሩም ሥሉስ ቅዱስ ተገኝተዋል፡፡ በቤተክርስቲያንም ሰዎች በተለያዩ ፈተናዎች ምክንያን ሳይሄዱ ቢቀሩ እንኳን እግዚአብሔር ሁሌም እንደማይቀር የሚያረጋግጥ ምሳሌ ነው፡፡ …. ይቀጥላል።

