
እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በሞሪያም ተራራ ትመሰላለች (ዘፍ 22፡12)፡እግዚአብሔር አበ ብዙኀን አብርሃምን አንድ ልጅህን ሠዋልኝ ባለው ጊዜ የዋሁ ይስሐቅ ሊሠዋበት ያለው የሞርያም ተራራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ በሞሪያም ተራራው ላይ ይስሐቅ ያይደለ በጉ እንደተሰዋ በቤተክርስቲያንም የሩቅ ብዕሲ ደም ሳይሆን መለኮት የተዋሐደው ነፍስ የተለየው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ይፈተታል፡፡ ለዚህም ነው ይህች እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በሞሪያም ተራራ የምትመሰለው፡፡
እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በያዕቆብ ሐውልት ትመሰላለች (ዘፍ 35፡13-15)፡ ቤቴል (ቤት-ኤል) ማለት የእግዚአብሔር ቤት ማለት ነው፡፡ ያቺ ሀውልት እግዚአብሔር ከያዕቆብ ጋር የተነጋገረባት ስፍራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ በቤቴል እግዚአብሔር ለያዕቆብ ተገለፀለት፡፡ በቤተክርስቲያንም አምኖ ለቀረበ እግዚአብሔር በረድኤት ይገለፅለታል፡፡ በቤቴል እግዚአብሔር ያዕቆብን ባርኮታል፡፡ በቤተክርቲያንም ተግቶ የጸለየ እግዚአብሔር በረከትን ያበዛለታል፡፡ በቤቴል እግዚአብሔር የያዕቆብን ስም ለውጦ እስራኤል ብሎታል፡፡ ሰውም ወደ ቤተክርስቲያን ሲመጣ አዲስ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን ተቀብሎ አዲስ ማንነትን (ክርስትናን) ይዞ በአዲስ ስም (በክርስትና ስም) ይጠራል፡፡ እግዚአብሔር በቤቴል ያደረገው ሁሉ ዛሬ በቤተክርስቲያን ለሚደረገው ምሳሌ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በቤተል እግዚአብሔር እስራኤል ለተባለው ያዕቆብ ‹‹ለአብርሃምና ለይስሐቅም የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ፥ ከአንተም በኋላ ለዘርህ ምድሪቱን እሰጣለሁ።›› ሲል የዘላለም ኪዳንን ሰጥቶታል፡፡ ይህ ኪዳን ቤቴል በተባለችው ቤተክርስቲያንም ጸንተው ለኖሩት ለቅዱሳን የተሰጠ ኪዳን ነውና ያቺ እግዚአብሔር ለያዕቆብ የተገለፀባት ስፍራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ መሆኗ በተረዳ ነገር ላይ የተመሠረተ እንጂ በአጋጣሚ የተወሰደ አይደለም፡፡ልክ እንደ ቤቴል ሰውና እግዚአብሔር የሚነጋገሩባት ስፍራ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ በዚያች ስፍራ ያዕቆብ የድንጋይ ሐውልትን መትከሉ ቤተክርስቲያን የተመሠረተችበትን ጽኑዕ መሠረት ያሳያል፡፡ ያዕቆብ በሐውልቱ ላይ ዘይትን አፈሰሰ፡፡ ይህም ዛሬም አዲስ ቤተክርስቲያን እንዴት እንደሚከብር ያሳያል፡፡ በዚያች ቦታ ላይ ያዕቆብ የመጠጥን መስዋዕት እንዳቀረበ በቤተክርስቲያንም አማናዊው የክርስቶስ ደም ለመስዋዕትነት ይቀርባል፡፡ በቤቴል ያዕቆብ የተከላት ሐውልት የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት ስንል እነዚህ ሁሉ ትንታኔዎችን በማስተዋል ነው፡፡
እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በደብረ ሲና ትመሰላለች (ዘፀ 34፡1)፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በደብረ ሲና ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ከጾመና ከጸለየ በኋላ ዐሥርቱ ቃላተ የተጻፈበትን ጽላት /ታቦተ ጽዮን/ ከእግዚአብሔር እጅ ተቀበለ፡፡ በቤተክርስቲያንም ክርስቲያኖች በጾምና በጸሎት ተግተው ሰማያዊ ክብርን (ቃል ኪዳንን) ያገኛሉና ቤተክርስቲያን በደብረ ሲና ተራራ ተመስላለች፡፡ በደብረ ሲና ተራራ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል በቃል ተነጋግሯል፡፡ በቤተክርስቲያንም በጾምና በጸሎት የተጉ አባቶች ከእግዚአብሔር ጋር ይነጋገራሉና ምሳሌነቱ ትክክለኛና ተገቢም ነው፡፡ ሙሴ ከደብረ ሲና ተራራ ሲወርድ ፊቱ እያበራ ነበር፡፡ በቤተክርስቲያን የኖረ ሰው ከዚህ ዓለም ተለይቶ ሲሄድ በመላእክት ታጅቦ እንደዚህ እያበራ ነውና ምሳሌነቱ ጽኑዕ ነው፡፡
ይቆዩን።

