
ባህረ ሀሳብ የግእዝ ቃል ሲሆን ከሁለት ቃላት የተወሰደ ነው። ባህር ማለት ዘመን፤ሀሳብ ማለት ደግሞ ቁጥር ማለት ነው። ባህረ ሀሳብ ማለት የዘመን አቆጣጠር ነው። ባህረ ሀሳብን “የጻፈው ማን ነው?” ቢሉ የመንበረ እስክንድርያ ፲፪ኛ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ድሜጥሮስ ነው። ይህ ቅዱስ አባት ቤተክርስቲያን በዘመነ ሐዲስ የምትመራበትን የአጽዋማትና የበዓላትን ቀመር ባህረ ሀሳብን የሠራ ነው።
ድሜጥሮስ ማለት መስታወት ማለት ነው፡፡ ድሜጥሮስ ምንም እንኳን የቤተክርስቲያን ትምህርት ባይኖረው ሕገ እግዚአብሔርን አክብሮ የሚኖር ስለነበር በዚህ ቅድስናው ምክንያት መልአከ እግዚአብሔር ለ፲፩ኛው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ዩልያኖስ ተገልጦ በነገረው መሰረት ድሜጥሮስ ፲፪ኛው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ሆኖ በመንበረ ማርቆስ ተሾሟል፡፡
ኢትዮጵያ የራሷ የዘመን አቆጣጠር እንዲኖራት ያደርገችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ናት።ይህ ባህረ ሀሳብ ያለፉትን ዓመታት፣ አሁን ያሉበትን፣ወደፊት እስከ ምጽአት የሚመጡትን አጽዋማት እና በዓላት ለማወቅ ይረዳል።
ቅዱስ ድሜጥሮስ (ከ፻፹ – ፪፻፳፪ ዓ.ም.) በመንበረ እስክንድርያ ላይ ቆይቷል፡፡ ይህም ቅዱስ አባት ቤተክርስቲያን በዘመነ ሐዲስ የምትመራበትን የአጽዋማትና የበዓላትን ቀመር ባህረ ሀሳብን የሠራ ነው፡፡ በተጨማሪም በዘመኑ ብዙ ድርሰቶችን መጽሐፎችን ጽፏል፡፡
በዚህ የዘመን አቆጣጠር ውስጥ የዘመነ ብሉይና የዘመነ ሐዲስ ድምር በጠቅላላው ዓመተ ዓለም ይባላል፡፡
አዕዋድ:
አዕዋድ የሚለው ቃል ኦደ ከሚል ግስ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ዞረ ማለት ነው፡፡ አዕዋድ ማለት ደግሞ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ዞሮ የሚመጣ ማለት ነው፡፡ አዕዋድያት የሚባሉት ሰባት ናቸው፡፡ እነርሱም
ዓውደ ዕለት፡- ከሰኞ እስከ እሑድ ያሉ ቀናት ሲሆኑ እነዚህ ቀናት በየሳምንቱ ተመላልሰው የሚመጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ሳምንታት እየተመላለሱ ወራትን ያዋቅራሉ፡፡
ዓውደ ወርኀ፡-ይህ በሠላሳ ቀን በየወሩ እየተመላለሰ ዓውደ ዓመትን ይሰራል፡፡
ዓውደ ዓመት፡- በፀሐይ ፫፻፷፭ ቀናት በጨረቃ ፫፻፶፬ ቀን ነው።
ዓውደ አበቅቴ (ንኡስ ቀመር)፡- ዐሥራ ዘጠኝ ሲሆን በየ፲፱ ዓመቱ ዞሮ የሚመጣ ነው፡፡ ፀሐይና ጨረቃ ተራክቦ የሚያደርጉበት ወቅት ነው፡፡
ዓውደ ፀሐይ፡- ሃያ ስምንት ዓመት ሲሆን በየ፳፰ ዓመቱ ተመላልሶ የሚመጣ ነው፡፡
ዓውደ ማኅተም (ማዕከላዊ ቀመር)፡- ሰባ ስድስት ዓመት ነው፡፡ በ፸፮ ዓመት አንድ ጊዜ አበቅቴው እና ወንጌላዊው ይገናኙበታል፡፡
ዓውደ ዐበይ ቀመር (ዐቢይ ቀመር)፡- አምስት መቶ ሠላሳ ሁለት ዓመት ነው፡፡ ዕለት፣ ወንጌላዊ እና አበቅቴ ይገናኙበታል፡፡
በዚህም መሠረት የ2017 ዓ.ም. አጽዋማት መቼ እንደሚውሉ እንግለፅ:-
# ጾመ ነነዌ : የካቲት ፫
# ዐቢይ ጾም: የካቲት ፲፯
# ደብረ ዘይት ፦መጋቢት ፲፬
# ሆሳዕና ፦ሚያዝያ ፭
# ስቅለት ፦ሚያዚያ ፲
# ትንሣኤ ፦ሚያዝያ ፲፪
# ርክበ ካህናት ፦ግንቦት ፮
# ዕርገት ፦ግንቦት ፳፩
# ጰራቅሊጦስ ፦ሰኔ ፩
# ጾመ ሐዋርያት ፦ሰኔ ፪
# ጾመ ድኅነት ፦ሰኔ ፬
http://youtube.com/@EMislene

