
“ከሕፃንነትህ ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን አውቀሃል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትን መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሳጽ፣
ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅምሃል።” ፪ኛጢሞ ፫፥፲፰
መጻሕፍትን ምን ያህል ታነባላችሁ? የምታነቡት ለምንድን ነው? የምታነቡትስ ምንድን ነው? እንዴት ባለ የንባብ ስልት? ባታነቡስ ምን የምትሆኑ ይመስላችኋል? ከዚህ የተሻለ በማስተዋል የተደገፈና ተስማሚ መጻሕፍትን ብታነቡስ ሕይወታችሁ ምንን የሚመስል ይመስላችኋል? መጻሕፍትን ማንበብ ለክርስቲያን ግዴታው ነው። ክርስቲያኖች የሚያነቡና ያነበቡትንም የሚያስተውሉ መሆናቸውን ለማወቅ ክርስትናን የኖሩትን ቅዱሳን እንመልከት። ምሳሌ፡ የቅዱሳን ሐዋርያት መልእክታትን ብንመለከት የተጻፉት ሊማሩ፣ ሊጽናኑና ሊያውቁ ለተገባቸው ሰዎች ነው። ቅዱሳን ሰማዕታት አላውያን ነገሥታትን እንደዚህ ተብሎ ተጽፏልና እያሉ ሲረቷቸው እናያለን። ሲናገሩም የቀደሙ አባቶቻችንን እንደምሳሌ ሲጠቅሱ እንመለከታለን። የእመቤታችን ጸሎት ላይም ቢሆን “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች።” የሚለው ጸሎት ሀና በመጽሐፈ ሳሙኤል ምዕራፍ ፪ ላይ ከጸለየችው ጋይ ያለውን መመሳሰል በማየት እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ቅዱሳት መጻሕፍትን አንባቢ እንደነበረች መረዳት እንችላለን። ይሁንና ክርስቲያኖች፡ የተመረጥን፣ አምላካችንን ልንመስል የተገባን ነንና መጻሕፍትን ማንበብ ስላለብን ብለን ግን ያገኘነውን ሁሉ አናነብም። ይህ ማለት መጻሕፍት በብዙህ ዓይነት ሰዎች ሊጻፉ ይችላሉ ። አንድ እግዚአብሔርን የካደ መናፍቅ ክህደቱን ቢጽፍ፣ አንድ ፈላስፋ ቅዱስ እግዚአብሔር በአምሳሉና በአርአያው የፈጠረውን ሰው ከዝንጀሮ እንዴት እንደመጣ ጥናታዊ ጽሑፍ ቢያዘጋጅ፣ ይህንን ማንበብ ለእኛ የተገባ አይደለም። ቅዱሳት መጻሕፍት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንጻፈለት “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” ፪ጢሞ. ፫፡፲፮-፲፯ እንዳለ በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፉ ሁሉ ቅዱሳት መጻሕፍት ይባላሉ። ቅዱሳት መጻሕፍት በዓለማችን ላይ ካሉት ዓለማውያት መጻሕፍት በእጅጉ የሚለዩ የመጻሕፍት ዓይነቶች ሲሆኑ በግብረ መንፈስ ቅዱስ የተጻፉ በመሆናቸው ክብራቸውና ቅድስናቸው ልዩ ነው። እነዚህን መጻሕፍት ማንበብ፣ በመንፈስም በሥጋም የሚያጎለብተን ሲሆን አሁን ካለው ምድራዊ ኑሯችን ባለፈ ለዘለዓለማዊውም ሕይወታችን ስንቅ የሚሆኑ፣ ስናነባቸው የምንቀደስባቸው መጻሕፍት ናቸው።” ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሚነግረን መጻሕፍት እንዲያስተምሩን፣ እንዲገስጹን የተሰጡን ናቸው። አንድ ሰው በአጠገቡ ለሌለ ወዳጁ ደብዳቤ እንደሚጽፍለት ኹሉ፥ እግዚአብሔርም ፣ ሰውን ከመውደዱ የተነሣ ከእርሱ ለራቀው ለሰው ልጅ የላካቸው ደብዳቤዎች ናቸው። ቅዱሳት መጻሕፍት የተሰጡት በኹለት መሠረታዊ ምክንያቶች እንደኾነ ቅዱስ ዮሐንስ ያብራራል፡
የመጀመሪያው: በጊዜ ሒደት አንዳንዶች ከመሠረታዊው ትምህርተ ክርስትና ፈቀቅ እያሉ ስለ ኼዱ ሲሆን
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ: በክርስቲያናዊ ሕይወታቸው ማለትም በምግባራቸው ንጽህናቸውን እያቆሸሹ ስለ ኼዱ (ጥፋታቸው እየበዛ፣ ከሥርዓት እየራቁ ስለመጡ) ነው፡፡
በመኾኑም መጻሕፍት እነዚህ በሃይማኖትም በምግባርም ከእውነት ወደ ሐሰት፣ ከጠባቢቱ ወደ ሰፊዋ መንገድ ፈቀቅ ያሉትን ለመመለስና ሌሎችም ወደዚያ እንዳይሔዱ ለማስታወስ የተሰጡ ናቸው። ሉቃ.፩፡፩-፬ በመሆኑም መጻሕፍትን ማንበብ የሕይወት (የድኅነት) ጉዳይ እንጂ የአማራጭ ጉዳይ እንዳልኾነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመንፈስ ለወለደው ልጁ ለሊቀ ጳጳሱ ለቅዱስ ጢሞቴዎስ መጻሕፍትን ስለ ማንበብ፡ “እስክመጣ ድረስ በማንበብ ተጠንቀቅ፤ በማንበብ ተወስነህ ኑር” ካለው በኋላ ምክንያቱን ሲነግረውም፡ “ይህን ብታደርግ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህ” ብሎታል። ፩ኛ ጢሞ. ፬፡፲፮) በቀጣይ ሳምንትስ ምን አሰቡ?
መልካም ዕለተ ሰንበት!

