
ተወልዶ ባደገባት ሶርያ በመናኝነቱ የሚታወቀው ቅዱስ አትናስዮስ ሕይወቱ በጽሙና የተሞላ ነበር:: በገዳም ገብቶም በዓት ለይቶ ሰውነቱን ለእግዚአብሔር ሲያስገዛት ዘመናት አልፈዋል::በዘመኑ የአንጾኪያ ፓትርያርክ አባ ሚካኤል አርፎ ነበርና ለመንበሯ የሚገባውን ሰው ፍለጋ በየበርሃው ዞሩ:: ነገርግን ከቅዱሱ አትናስዮስ የተሻለ ሰው አላገኙም:: እርሱ መጻሕፍትን ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ለመንጋውም የሚራራ በጐ እረኛ ነውና ይዘውት ወደ ከተማ ሄዱ:: በሃገራቸው ባሕል መሠረት ሊቀጳጳሳት የሚሾመው የሁሉም አህጉረ ስብከት ጳጳሳት ባሉበት ነውና ጠበቁ:: ሁሉ ተገኝቶ በሶርያ የሰልቅ ዻዻስ የነበረው አባ እልመፍርያን ግን ዘገየ:: ለሃምሳ ቀናት ጠብቀው አባ አትናስዮስን ፓትርያርክ ዘአንጾኪያ ብለው ሾመውት ተለያዩ:: በ፶፩ኛው ኛው ቀን አባ እልመፍርያን ሲደርስ በዓለ ሲመቱ መጠናቀቁን ሲነግሩት ተቆጣ:: “እኔ በሌለሁበት የተሾመው አይሠራምና አትናስዮስን “ፓትርያርክ” ብሎ የሚጠራ ሁሉ የተወገዘ ይሁን!” ብሎ ወደ ሰልቅ ተመለሰ:: ቅዱስ አትናስዮስ ይህንን ነገር ሲሰማ ፈጽሞ አዘነ:: ከቀድሞውም አስገድደውት እንጂ እርሱ ሹመቱን ፈልጐ አልመጣም:: ልክ በዘመኑ እንደምንመለከተው ቅዱሱ መልሶ ማውገዝ ይችላል:: ለዚያውም በሥልጣን ይበልጠዋል:: ቅዱሱ ግን ለግል ክብሩ ሲል ቤተክርስቲያንና ምዕመናን ሲከፈሉ ማየትን አልወደደም:: ደቀመዝሙሩን ጠራውና ‘ልጄ! እሺ በለኝ፤ ነፍሴ ትመርቅሃለች:: እኔ ለ1 ዓመት መንገድ ስለምወጣ አንተ በእኔ ፈንታ እዘዝ፤ እሠር፤ ፍታ:! ሕዝቡ ከጠየቁህ “ወደ ገዳም ሔዷል በላቸው” ‘ ብሎት ከመንበረ ጵጵስናው ወጣ:: እጅግ የነተበ የበረሃ ልብሱን ለብሶና በእግሩ ተጉዞ ሰልቅ ውስጥ ደረሰ:: ወደ አባ እልመፍርያን ዘንድ ገብቶም በፊቱ ሰገደ:: “አባቴ! ነዳይ ነኝና አስጠጋኝ?” ብሎ ለመነው:: አባ እልመፍርያንም ከመነኮሳቱ ጋር እንዲኖር ፈቀደለት:: ቅዱስ አትናስዮስ ፓትርያርክ ሲሆን ወገቡን ታጥቆ ያገለግል ገባ:: ውሃ ይቀዳል፣ ዳቦ ይጋግራል ፣ ቤቶችን ይጠርጋል፣ መጸዳጃ ቤቶችን ያጸዳል፣ የመነኮሳቱን እግር ያጥባል:: በዚህ ሁሉ ላበቱ እየተንጠፈጠፈ በሰውነቱ ላይ ይወርድ ነበር:: አባቶች ትጋቱንና ትሕትናውን ሲያዩ ለዲቁና አጩት:: ጳጳሱም ጠርቶ “ዲቁና ልሹምህ!” ቢለው ፓትርያርኩ ቅዱስ አትናስዮስ አለቀሰ:: “ምነው?” ቢለው፣ “አባቴ! በነውር ተይዞብኝ ነው እንጂ ዲቁናስ አለኝ” አለው:: አሁንም ለ7ወራት በዲቁና አገልግሎት ቆይቶ “ቅስና ተሾም!” ቢሉት እንደ ቀደመው እያለቀሰ መለሰላቸው:: ልክ በዓመቱ ግን ለአንዲት ሃገረ ስብከት ጳጳስ ያደርጉት ዘንድ በዕለተ እሑድ ተሰበሰቡ:: ቅዱስ አትናስዮስ እንዲተዉት እያለቀሰ ለመናቸው:: “ለሹመቱ ትገባለህ” ብለው ግድ ሲሉት ግን “ምሥጢር ልንገራችሁ” ብሎ “ፓትርያርኩ አትናስዮስ ይሏችኋል እኮ እኔ ነኝ” አላቸው:: የሰማውን ነገር ማመን ያቃተው አባ እልመፍርያን ደንግጦ በግንባሩ መሬት ላይ ወደቀ:: እየተንከባለለም አለቀሰ:: “ወየው ለእኔ! ጌታዬን አትናስዮስን እንደ አገልጋይ ላዘዝኩ” እያለም ተማለለ:: በአካባቢው የነበሩ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ መነኮሳትና ምእመናንም ከቅዱስ አትናስዮስ የትህትና ሥራ የተነሳ ፈጽመው አደነቁ::
ሊቀጳጳሱም አዋቂነቱን አይቶ ቅስና ሊሾመው ወደደ። በእሑድ ቀንም ወደ ቤተክርስቲያን ውስጥ ጠርቶ “መንፈስ ቅዱስ ቅስና ሊሾምህ ጠርቶሃል።” አለው አባ አትናስዮስም ሰምቶ አለቀሰ እንዲተወውም ማለደው። ባልተወውም ጊዜ “አባቴ ይቅር በለኝ፤ እኔ ቄስ ነኝ።” አለ። መነኰሳቱም ሁሉ አደነቁ በእርሱም ደስ አላቸው። አባ እልመፍርያንም አስተዋይነቱን የአንደበቱን ጣዕም የተደራረበ አገልግሎቱንም ተመልክቶ ጳጳስዋ ለሞተባት ለአንዲት ሀጉረስብከት ጵጵስና ሊሾመው ወደደ። ጳጳሳትንና ኤጲስቆጶሳትን ቀሳውስትንና ዲያቆናትንም በእሑድ ቀን ሰበሰበ። አባ አትናትዮስንም አቅርበው እንዲህ አሉት “ለዕገሌ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ልትሆን ዛሬ መንፈስ ቅዱስ ጠርቶሃል” አሉት። እርሱም ሰምቶ አለቀሰ፤ እንዲተዉትም አልቅሶ አማላቸው። እንደማይተዉትም በአወቀ ጊዜ እርሱ የአንጾኪያ ሊቀጳጳሳት አትናስዮስ እንደሆነ ነገራቸው። የአመጣጡንም ምሥጢር ገለጸላቸው። በዚያን ጊዜ አባ አልመፍርያን ደነገጠ። አክሊሉንም ከራሱ ላይ አውልቆ በምድር ላይ ወደ። ለረጅም ጊዜ እንደ ሞተ ሆነ፤ በተነሣም ጊዜ እንዲህ ብሎ ጮኸ፡ “ወንድሞቼ የማደርገውን እስቲ ንገሩኝ! ዛሬ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዳያቃጥለኝ ምድርም አፍዋን ከፍታ እንዳትውጠኝ እፈራለሁና፤ ጌታዬ የአንጾኪያ ሊቀጳጳሳት አትናስዮስ ውኃ እየቀዳ የፈረሶችና የበቅሎዎች ጉድፍ እየጠረገ በቤቴ ውስጥ እንደ ባርያ ሊያገለግል አግባብ ነውን? ወዮልኝ ወዮልኝ።” ጳጳሳቱና የተሰበሰቡት ሁሉ በሰሙ ጊዜ ከእግሩ በታች ወድቀው ሰገዱለት። እጆቹንና እግሮቹንም ሳሙ፤ ሊቀጳጳሱም ያማሩ የክህነት ልብሶችን ያለብሱት ዘንድ መስቀሎችንና አርዌ ብርቱን ያመጡ ዘንድ በመንበር ላይም ያስቀመጡት ዘንድ አዘዘ። ከዚያም በኋላ ጳጳሳቱ ከመንበሩ ጋር ተሸከሙት ሦስት ጊዜ አክዮስ! አክዮስ! አክዮስ! አሉት። ይህም ይገባዋል ማለት ነው። ቤተክርስቲያኑን አዙረው ወደ መቅደስ አስገቡት። ከዚህም በኋላ መቀደሻ ልብስ ለብሶ መሥዋዕቱን አክብሮ ቀድሶ አቈረባቸው፤ እነርሱንም ሀገራቸውንም ባረከ። ለዚያችም ሀገር “ምንኛ መጠን የሌለው ደስታ ሆነ?” ተባለ። በማግሥቱም አባ እልመፍርያን ተነሥቶ በቅሎ አስመጣ፣ ለጉዞ የሚያሻውን ሁሉ አዘጋጀ፣ አባ አትናስዮስንም በበቅሎ አስቀምጦ እርሱ በእግሩ ተከተለው። ጳጳሳቱና ኤጲስ ቆጶሳቱ ሁሉም ከአባ እልመፍርያን ጋር አጅበው ወደ አንጾኪያ ሀገር ወሰዱት። አባት አትናስዮስም አባ እልመፍርያንን “አንተም በበቅሎ ላይ ተቀመጥና በአንድነት እንሒድ!” አለው። አባ እልመፍርያንም “ጌታዬ ለእኔ አይገባኝም! አንተ በእግርህ ወደ ሀገሬ እንደመጣህ እንዲሁ እኔም በእግሬ ወደ ሀገርህ አደርስሃለሁ” አለው ። የአንጾኪያ ሀገር ጳጳሳትም የሊቀጳጳሳት አትናስዮስን መምጣት በሰሙ ጊዜ ከሕዝብ ሁሉ ጋር ሊቀበሉት ወጡ። በታላቅም ክብር ተቀብለው ወደ ሹመቱ መንበር አስገቡት። ለአባ እልመፍርያንም ሁለተኛ ወንበር አድርገው በክብር አስቀመጡት። በዚያችም ቀን ፈጽሞ ደስ አላቸው። ተሰናብተዉትም ወደ ሀገራቸው በፍቅር አንድነት ተመለሱ። ታላቁ እረኛ ቅዱስ አትናስዮስ እነሆ በዚህ መንገድ ቤተክርስቲያንን ለሁለት ከመከፈል ታደጋት:: ቅዱሱ በተጋድሎ ኑሮ በጥቅምት ፱ በሰላም አረፈ።(ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት፣ስንክሳር ዘጥቅምት)

