
ሊቃውንት ቁመቱንና ቅድስናውን በንጽጽር ሲገልጡ:-
“ሰላም ሰላም ዕብሎ በሕቁ፣
ለዮሐንስ ሐጺር ዘነዊኅ ሒሩተ ጽድቁ” ይላሉ::
“ቁመቱ እጅግ ያጠረ፣ ጽድቁ ግን ከሰማይ የደረሰ
ቅዱስ ዮሐንስን ሰላም ሰላም እንለዋለን” ማለት ነው:: ቅዱሱ የተወለደው በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በምድረ ግብጽ ነው:: ወላጆቹ ምንም በሥጋዊ ሀብት ድሆች ቢሆኑም ባለ መልካም ክርስትና ነበሩና በጎውን ሕይወት አስተምረውታል:: ወደ ምናኔ የገባው ገና በ18 ዓመቱ ሲሆን የታላቁ አባ ባይሞይ ደቀ መዝሙር ሆኖ ተጋድሎንና ትሕርምትን ተምሯል:: ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር በወቅቱ ከነበሩ ቅዱሳን ከቁመቱ ባሻገር በትሕትናው፣ በትእግስቱና በመታዘዙ ይታወቅ ነበር:: አባ ባይሞይ ይጠራውና ያለ ምንም ምክንያት ደብድቦ ያባርረው ነበር:: እርሱ ግን “ምን አጠፋሁ?” ብሎ እንኩዋ ሳይጠይቅ “አባቴ ሆይ! ማረኝ?” እያለ ከእግሩ ሥር ይወድቅ ነበር:: ለብዙ ጊዜ በተመሳሳይ ሲደበድበው እርሱዉ ተደብድቦ እርሱዉ ይቅርታን ሲጠይቅ ኖረ:: አንድ ቀን ግን እንደ ልማዱ ሊገርፈው ሲሔድ 7ቱ ሊቃነ መላእክት ከበውት አይቶ ደንግጦ ተመልሷል:: አባ ባይሞይ ይሕንን ሁሉ የሚያደርገው ጠልቶት ወይ ክፉ ሆኖ አይደለም:: አንድ ሰው የሌላኛውን ግፍ መቀበል ካልቻለ ሰይጣንን ድል አይነሳም የሚል ትምሕርት ስለ ነበረ ነው እንጂ። አንድ ቀን ቅዱስ ዮሐንስ ወደ መምህሩ ቀርቦ “አባቴ ጅብ ካገኘሁ ምን ላድርግ?” ሲል ጠየቀው:: (የአካባቢው አስፈሪ አውሬ ነበር) አባ ባይሞይ ግን “ይዘህልኝ አምጣው” አለው:: ትእዛዝ ነውና ቅዱሱ ወደ በረሃ ወርዶ፣ ጅብ (አውሬ ) አልምዶ ይዞለት መጥቷል::
ሌላ ቀን ደግሞ አባ ባይሞይ ቅዱስ ዮሐንስን ጠራውና ተፈልጦ የወደቀ ደረቅ እንጨት ሠጠው:: “ምን ላድርገው አባ?” አለው:: “ትከለውና እንዲያፈራ አድርገው:: ከዚያ አምጥተህ አብላኝ” ሲል አዘዘው:: ይህ ነገር ከተፈጥሮ ሥርዓት ውጪ መሆኑን እያወቀ ቅዱስ ዮሐንስ “እሺ” ብሎ ወስዶ ተከለው::
ከዚያም ለ2 ዓመታት ሳይታክት ውኃ አጠጣው:: ውኃውን የሚያመጣበት ቦታ ደግሞ 10 ኪሎ ሜትር ያህል ከገዳሙ ይርቅ ነበር:: ቅዱሱ ላቡን እያፈሰሰ አሁንም ማጠጣቱን ቀጠለ:: በ3ኛው ዓመት ግን ለምልሞ አበበ፤ ደግሞም አፈራ:: ካፈራው በኩረ ሎሚም ወስዶ ለመምሕሩ “አባቴ! እንካ ብላ” ብሎ ሰጠው:: አባ ባይሞይ ግን ማመን አልቻለም:: እጅግ አደነቀ፤ አለቀሰም:: ወዲያው ያን ፍሬ ታቅፎ ወስዶ ለገዳሙ መነኮሳት አላቸው: “ንሱ ብሉ፤ በረከትንም አግኙ:: ይህ የዛፍ ሳይሆን የመታዘዝ ፍሬ ነው::” ቅዱስ ዮሐንስ አባ ባይሞይ ቢታመም ለ12 ዓመት አስታሞታል:: መምህሩ ከማረፉ በፊትም መነኮሳቱን ሰብስቦ የቅዱስ ዮሐንስን እጅ አስጨበጣቸው:: “ይህ የያዛችሁት እጅ የሰው ሳይሆን የመልአክ እጅ ነው” ብሏቸው ዐርፏል:: ቅዱስ ዮሐንስም ከዓመታት ቆይታ በኋላ የገዳሙ አበ ምኔት ሆኖ አገልግሏል:: ብዙ ነፍሳትንም ለቅድስና ማርኳል::
በተጨማሪም ገላዋን በመሸጥ በዝሙት ሥራ የምትተዳደር አትናስያ የተባለች በቀደመ ሕይወቷ በገዳማውያኑ ዘንድ ትልቅ ቦታ ይሰጣት የነበራች ብትሆንም በጠላት አሠራር ወድቃ ከዚህ ሕይወት እንዲታደጋት በገዳማውያኑ ተመርጦ አባ ዮሐንስ ሐጺር ወደ መኑፍ ከተማ ሔደ፤ ወደ ቤቷም ደረሰ:: ጠባቂዋን አስፈቅዶ ሲገባ ለረከሰው ድርጊት የመጣ ሰው መስሏት ተዘጋጅታ ነበር:: አባ ዮሐንስ ሐጺር ግን አጋንንትን ያርቅ ዘንድ እየዘመረ ገባ::
“እመኒ ሖርኩ ማዕከለ ጽላሎተ ሞት . . . በሞት ጥላ ሥር እንኩዋ ብሔድ አንተ ከኔ ጋር ነሕና ክፉን አልፈራም” እያለ ቀረባት:: (መዝ. ፳፪)
ፈጠን ብሎ ከጎኗ ተቀምጦ ቅዱሱ ምርር ብሎ አለቀሰ:: አትናስያ ደንግጣ “ምነው?” አለችው:: “የአጋንንት ሠራዊት በራስሽ ላይ ሆነው እየጨፈሩኮ ነው” አላት:: አስከትሎም አጋንንቱን በጸሎቱ ቢያርቅላት በአንዴ ወደ ልቧ ተመለሰች::
ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ሰው የሠራችውን ሁሉ ማመን አቃታት:: ተስፋም ቆረጠች:: ቅዱስ ዮሐንስ ግን “ግዴለሽም፤ ንስሐ ግቢ፤ ፈጣሪ ይምርሻል” ብሎ አሳመናት:: “እሺ አባቴ” ብላ ከቀደመው ዘመን ሥርዓት ያለውን አንዱን ቀሚስ ለብሳ፣ ጫማ ሳትጫማ፣ ሌላ ልብስ ሳትደርብ፣ ምንም ነገር ሳትይዝ ከቤት ወጣች:: ቤቷን አልዘጋችም:: ዘወር ብላ ወደ ኋላም አልተመለከተችም:: ቅዱሱን ተከትላ ጉዞ ወደ በረሃ ሆነ:: ያ በእንክብካቤ የኖረ አካል እሾህና እንቅፋት፣ ብርድና ፀሐይ ጎበኘው:: ሲመሽ እጅግ ደክሟታልና “እረፊ” ብሏት ሊጸልይ ፈቀቅ አለ:: መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜ መላእክት ከሰማይ የብርሃን ዐምድ ዘርግተው አንዲትን ነፍስ በዝማሬ ሲያሳርጉ አየ:: “የማን ነፍስ ትሆን” ብሎ ወደ አትናስያ ሲሔድ መሬት ላይ ዘንበል ብላ ዐርፋ አገኛት:: ቅዱሱም “ጌታ ሆይ! ምነው ለንስሃ እንኩዋ ብታበቃት?” ብሎ አለቀሰ:: ፈጣሪ ከሰማይ ተናገረ: “ገና ከቤቷ ተጸጽታ ስትወጣ ነው ይቅር ያልኩዋትና ደስ ይበላችሁ” አለው:: ይህንን የአምላክ ቃል ሁሉም ገዳማውያን ሰምተው እጅግ ደስ አላቸው:: “ጻድቅ 7 ጊዜ ይወድቃልና፤ 7 ጊዜ ይነሳል::” መላእክት ንጽሕናው ደስ ስለሚያሰኛቸው አብረውት ይውሉ ነበር:: ሲተኛም በተራ በተራ ክንፋቸውን ያለብሱት ነበር:: ምጽዋትን በጣም ስለሚወድ ሰፌድ እየሰፋ ይሸጣል። አንድ ቀን እንደ ልማዱ ወደ ገበያ ወጥቶ ሳለ ተደሞ (ተመስጦ) መጣበት:: ሰማያት ተከፍተው፣ ቅዱሳን ሊቃነ-መላእክት ሚካኤል እና ገብርኤል በግርማ በጌታ ፊት ቆመው ተመለከተ:: “እጹብ፣ እጹብ” እያለ ሲያደንቅ አንድ ገዢ መጥቶ “ባለ እንቅብ ዋጋው ስንት ነው?” ቢለው “እኁየ ሚካኤልኑ የዓቢ ወሚመ ገብርኤል / ከሚካኤልና ከገብርኤል ማን ይበልጣል?” ብሎታል:: ገዢውም ደንግጦ “እብድ መነኩሴ” ብሎት ሔዷል:: ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ ካረፉ ከ900 ዓመታት በኋላ ታላቁ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ቤተ ክርስቲያንን አንጾላቸው ነበርና አጽማቸውን ሊያገኝ ተመኘ:: ወዳጁን ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ጠርቶ “አባ! አጽመ ቅዱሳንን ባቢሎን ወርደህ አምጣልኝ?” አለው:: ቅዱሱ ሐጺር ዮሐንስም በደመና ተጭኖ ባቢሎን ገባ:: በቅዱሳኑ መቃብር ፊትም ሰግዶ አለቀሰ:: ሠለስቱ ደቂቅም “ወዳጃችን! ምን ሆንክ?” አሉት::
ቅዱሱም መልሶ “ወደ ግብጽ እንሒድ:: አባ ቴዎፍሎስ ይፈልጋችኋል” አላቸው:: እነሱም “ለቅዱሱ ቴዎፍሎስ እንዲህ በለው:: እግዚአብሔር ዋጋህን ይክፈልህ:: ግን አጽማችን እስከ ዓለም ፍጻሜ ባቢሎንን አይለቅም:: ለክብርህ ግን እንመጣለን::”
“ለምልክትም ይሆን ዘንድ መብራት ሳታበራ በሌሊት ጠብቀን በለው” ብለው ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ባርከው ሸኙት:: ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርም መጥቶ መልእክቱን አደረሰ:: በዕለተ ቅዳሴ ቤታቸው ቅዱሳን፣ ቴዎፍሎስ ፣ ቄርሎስ ፣ ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርና ሌሎችም ከምእመናን ጋር በጨለማ ሳሉ ቤተ ክርስቲያኑ ቦግ ብሎ በራ:: ከዚህ በኃላ በበርበሮች ምክንያት ከአስቄጥስ ወደ ቁልዝም ተሰዷል:: በዚያም በአባ እንጦንስ በዓት ውስጥ ዐርፏል:: ለ400 ዓመታት በዚያው ቆይቷል::
በ825 ዓ/ም ግን በአባ ዮሐንስ ፓትርያርክ ዘመን ክቡር ሥጋው ወደ ገዳመ አስቄጥስ ተመልሷል:: ቅዱሱ ያረፈው ጥቅምት 20 ቀን ነው። የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ረድኤት በረከት ያሳትፈን።

