የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን

የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በበዓለ ኀምሳ በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት በሦስት ሺ ምእመናን በሀገረ ኢየሩሳሌም በ፴፬ ዓ.ም. ተመሠረተች:: ከዚያም ሐዋርያት ዓለምን በዕጣ በመከፋፈል ተዘዋውረው አስተማሩ፡፡ አምልኮ ጣዖትን አጠፉ፡፡ ርኩሳን አጋንንትን አሳደዱ፡፡ በመስቀል ዕርፍ አርሰው፣ ንጹሕ ዘር ወንጌልን ዘርተው፣ በደማቸው አተሙ:: በእየሩሳሌም የጀመረችው ቤተክርስቲያን አገልግሎቷ ለዚያች ከተማና በአካባቢው ብቻ የተገደበ ይመስል ነበር። በጽዮን ተራራ ላይ ያለው የላይኛው ክፍል እና በቤተመቅደስም በሰሎሞን መመላለሻ በአንድነት ይኖሩ ነበር። ከሐዋርያት ድንቅ ተአምራትና ከስብከታቸው የተነሣ ብዙ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ተጨመሩ።

የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፡ ቀድሞውን በቁጥር ብዙ ያልሆኑ ክርስቲያኖች በሐዋርያት ይተዳደሩ ነበር። ኋላ ከግሪክ በመጡ ክርስቲያን አይሁዶችና በአረማይክ ተናጋሪ አይሁዶች መካከል አለመግባባት ተከሰተ። ከግሪክ ለመጡ ደቀ መዛሙርት ባልቴቶች ምግብን ሲያካፍሉ ችላ ይሏቸው እንደነበር ስሞታ አቀረቡ። ሐዋርያትም ሲሰሙ ሕዝቡን ጠርተው እንዲህ ያሉ ነገሮችን ይፈጽሙ ዘንድ እንዳልተጠሩ ተናግረው ይልቁን አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ይሥሩ ብለው፣ መሪዎች እንዲሆኗቸው ሰባት ዲያቆናትን ሾሙሏቸው። እኒኽም ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ፣ ፊልጶስ፣ ጵሮኮሮስ፣ ኒቃሮና፣ጢሞና፣ጰርሜናና ተመልሶ ይሁዲ የሆነው ኒቆላዎስ ናቸው። የሐዋ ፮፥፩ ልዩ ሥራቸው ባል ለሞቱባቸው እና ለድሆች እርዳታ መስጠት ነበር። ፡

እስጢፋኖስ ቀዳሜ ሰማዕት፡ ከሰባቱ መካከል መንፈስ ቅዱስ የሞላበት እስጢፋኖስ ትልልቅ ተአምራትንና ድንቅ ሥራን እየሠራ የእግዚአብሔርን ቃል ይናገር ነበር።  ከተመረጠ በኋላ፣ ብዙም ሳይቆይ ትኩረት ሳበ። የነጻ ወጭዎች ከምትባለው ምኩራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያ፥ ከቂልቅያና ከእስያ የሆኑ ሰዎች ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር። በድፍረት በሰበካቸውና ገሰጻቸው በአይሁዶች በድንጋይ ተወግሮ አረፈ፤ ስለዚህም የሰማዕታት መጀመሪያው ሆነ።

ፊልጶስ እና ተልእኮው ፡ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግሮ ካረፈ በኋላ ከኢየሩሳሌም የመጡ ክርስቲያኖች ወደ ሰማርያ ተሰደዱ። ፊልጶስ ከሰባቱ ዲያቆናት አንዱ ለሳምራውያን ወንጌልን ሰብኮ በሰማርያ ቤተ ክርስቲያን አቋቋመ። እንደ እስጢፋኖስ ሁሉ በእጆቹ ታልልቅ ተአምራትን ያደርግ ነበር። ርኩሳን መናፍስትን ካደሩቧቸው ሰዎች እያስወጣ፣ አንካሳና ልምሾዎችን ይፈውስ ነበር ። የእግዚአብሔር መልአክም ፊልጶስን “ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚያወርደው በምድረ በዳ ሂድ” አለው። የሐ. ሥራ ፰፥፳፮  ፊልጶስም ተነሥቶ ሄደ። የኢትዮጵያ ንግሥት የሕንደኬ ጃንደረባ በሀብቷም ሁሉ በጅሮንድ የነበረውን ባኮስን አጥምቆ በኢዮጴ፣ በጋዛ እና በቂሳርያ አዲስ ጉባኤ መሥርቷል።