አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)

አባታችን አቡነ አቢብ የተወለደው በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ ሮሜ ናት:: ወላጆቹ ቅዱስ አብርሃምና ቅድስት ሐሪክ እጅግ ጽኑ ክርስቲያኖች ነበሩ:: ልጅ ግን አልነበራቸውም:: ዘመነ ሰማዕታት ደርሶ ስደት በሆነ ጊዜ እነርሱም በረሃ ገቡ::
በዚያም ሳሉ በቅዱስ መልአክ ብሥራት ሐሪክ ጸንሳ ብሩሕ የሆነ ልጅ ወለደች:: ቅዱሱ ሕፃን ሲጸነስ ማንም ሳይተክለው የበቀለው ዛፍ ላይ መልአኩ  “ቡላ ገብሩ ለእግዚአብሔር፣ ወቅዱሱ ለአምላከ ያዕቆብ፣ ዘየኀድር ውስተ ጽዮን” የሚል የብርሃን ጽሑፍ ጽፎበት ወላጆቹ ዐይተዋል::

ቅዱሱ ሕፃን ከተወለደ በኋላ ሳይጠመቅ ለ 1 ዓመት ቆየ:: ምክንያቱም ዘመኑ የጭንቅ ነውና ካህናትን እንኳን በዱር በከተማም ማግኘት አይቻልም ነበር:: እመቤታችን ግን ወደ ሮሙ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሰለባስትርዮስ ሒዳ “አጥምቀው!” አለችው:: ወደ በረሐ ወርዶ ሊያጠምቀው ሲልም ሕጻኑ ተነስቶ፣ እጆቹንም ዘርግቶ: “አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውዕቱ መንፈስ ቅዱስ” ብሎ አመስግኖ ተጠመቀ:: ከሰማይም ሕብስትና ጽዋዕ ወርዶላቸው ሊቀ ጳጳሳቱ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው:: የሕፃኑ ወላጆች “ለልጃችን ስም አውጣልን” ቢሉት “ቡላ” ብሎ ሰየመው:: እነርሱም ቅዱሱ ሕፃን ሲጸነስ ማንም ሳይተክለው የበቀለው ዛፍ ላይ መልአኩ  “ቡላ ገብሩ ለእግዚአብሔር፣ ወቅዱሱ ለአምላከ ያዕቆብ፣ ዘየኀድር ውስተ ጽዮን” ተብሎ እንደተጻፈ ምሥጢሩን ያውቁ ነበርና አደነቁ::

 የቅዱሱ ቡላ ወላጆች ለ10 ዓመታት አሳድገዉት ድንገት ኅዳር ፯ ቀን ተከታትለው ዐረፉ:: ሕጻኑን የማሳደግ ኃላፊነት የአካባቢው ሰዎች ሆነ:: ሕጻኑ ቡላ ምንም የ10 ዓመት ሕጻን ቢሆንም ያለ ማቋረጥ ሲጾምና ሲጸልይ ክፉ መኮንን “ለጣዖት ስገዱ!” እያለ መጣ:: በዚህ ጊዜ በሕፃን አንደበቱ አምልኮተ ክርስቶስን ሰበከ:: በዚህ የተበሳጨ መኮንኑ ስቃያትን አዘዘበት:: በጅራፍ ገረፉት፣ በዘንግ ደበደቡት፣ ቆዳውን ገፈፉት፣ በመጋዝ ቆራርጠውም ጣሉት:: ነገር ግን ኃይለ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና 2 ጊዜ ከሞት ተነሳ:: በመጨረሻ ግን ሚያዝያ ፲፰ ቀን ሰማዕት ሆኗል::

ሰማዕትነቱን ከፈጸመ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል በአክሊላት አክብሮ ወስዶ በገነት አኖረው:: ከሰማዕታትም ጋር ደመረው:: በዚያም ቡላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተመልክቶ ተደነቀ:: መንፈሳዊ ቅንዐትን ቀንቷልና “እባክህን ወደ ዓለም መልሰኝና ስለ ፍቅርህ እንደ ገና ልጋደል!” ሲል ጌታንን ለመነ:: ጌታችን ግን “ወዳጄ ቡላ! እንግዲህስ ሰማዕትነቱ ይበቃሃል:: ሱታፌ ጻድቃንን ታገኝ ዘንድ ግን ፈቃዴ ነውና ሒድ!” አለው:: ቅዱስ ሚካኤልም የቅዱስ ቡላን ነፍስ ከሥጋው ጋር አዋሕዶ፣ ልብሰ መነኮሳትንም አልብሶ ግብጽ በረሃ ውስጥ አኖረው።

 አባ ቡላ ወደ በርሃ ከገባ ጀምሮ ዐርብ ዐርብ የጌታን ሕማማት እያሰበ ራሱን ያሰቃይ ገባ:: ራሱን ይገርፋል፣ ፊቱን በጥፊ ይመታል፣ ሥጋውን እየቆረጠ ለአራዊት ይሰጣል፣ ከትልቅ ዛፍ ላይ ተሰቅሎ ወደ ታች ይወረወራል:: በጭንቅላቱ ተተክሎ ለብዙ ጊዜ ጸልዮ ጭንቅላቱ ይፈሳል:: ሌላም ብዙ መከራዎችን የጌታን ሕማማት እያሰበ ይቀበላል:: ስለ ጌታ ፍቅርም ምንም ነገር ሳይቀምስ ለ42 ዓመታት ጾሟል:: ጌታችንም ስለ ክብሩ ዘወትር ይገለጥለት ነበር:: የሚታየውም እንደ ተወለደ፣ እንደ ተጠመቀ፣ እንደ ተሰቀለ፣ እንደ ተነሣ፣ እንዳረገ እየሆነ ነበር:: አንድ ቀንም ጌታችን መጥቶ “ወዳጄ ቡላ! እንዳንተ ስለ እኔ ስም መከራ የተቀበለ ሰው የለም:: አንተም የብዙዎች አባት ነህና ስምህ አቢብ (ሃቢብ) ይሁን!” አለው::አቡነ አቢብ ታላቁ ዕብሎይን ጨምሮ በርካታ ደቀ መዛሙርትን አፈራ:: ከእመቤታችን ጋርም ዕለት ዕለት እየተነጋገረ ዘለቀ:: በተጋድሎ ሕይወቱም ከዐሥር ጊዜ በላይ ሞቶ ተነስቷል:: በዚህች ቀን ሲያርፍ ገዳሙ በመላእክት ተሞላ::

ጌታም ከድንግል እናቱ ጋር መጥቶ “ወዳጄ ቡላ! ስምህን የጠራውን፣ መታሰቢያህን ያደረገውን እምርልሃለሁ:: አቅም ቢያጣ “አምላከ አቢብ ማረኝ” ብሎ 3 ጊዜ በዕለተ ዕረፍትህ የሚለምነኝን: በስምሕ እንኩዋ ቁራሽ የሚበላውን ሁሉ እምርልሃለሁ” ብሎት ነፍሱን በክብር አሳረገ፤ በሰማይም ዕልልታ ተደረገ::