ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ

‎ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ በዛግዌ ሥርወ መንግሥት ከነገሡ ፲፩ ነገሥታት አንዱ ሲሆን ከመጨረሻውም ፪ኛ ነው:: እርሱን በ12ኛው መቶ ክ/ዘመን የወለዱት ቅዱሱ ንጉሥ ሐርቤ (ገብረ ማርያም) እና መርኬዛ ናቸው:: ዘመኑ ቅድስና በላስታ ዙሪያ የመላበት በመሆኑ ቅዱስ ሐርቤ ከመመነኑ በፊት ነበር ነአኩቶ ለአብን የወለደው::

    እናቱ መርኬዛ እርሱን ልትወልድ ምጥ ተይዛ ሳለ ጆሮዋ ቅዳሴን ይሰማ ነበር:: ቅዳሴው ሲጀመር የጀመራት ምጥ ድርገት ሲወርዱ (ሥጋ ወደሙ ሲሰጥ) ተፈታላትና ልጇን ተገላገለች:: ሕፃኑን አንስታ ስትታቀፈው ዲያቆኑ ማቁረቡን ፈጽሞ “ነአኩቶ” እያለ ሲዞር ሰማችው::  እዚያው ላይም ‘ነአኩቶ ለአብ’ (አብን እናመስግነው) ስትል ስም አወጣችለት:: ወዲያው ግን አባቱ ቅዱስ ሐርቤ መንግሥቱን ለቅዱስ ላሊበላ ሰጥቶ በረሃ በመግባቱ ቅዱሱ ሕፃን ወደ አጎቱ ላሊበላ ቤተ መንግስት ውስጥ ገባ::

     የቅዱስ ላሊበላ ቤት ደግሞ በቅድስና ያጌጠ ነውና ከእርሱና ከሚስቱ (ቅድስት መስቀል ክብራ) ሕፃኑ ነአኩቶ ለአብ ምናኔና ፍቅረ ክርስቶስን ተማረ:: በዘመኑ ብዙ ሊቃውንት ስለ ነበሩ ቅዱሳት መጻሕፍትን በደንብ አጠና:: ክህነት ተቀብሎ ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግልም ዕድሜው 30 ደረሰ::

    በወቅቱ ቅዱስ ላሊበላና ባለቤቱ መስቀል ክብራ ልጃቸው ይትባረክ እያለ ንግሥናቸውን ለቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አወረሱ:: ቅዱሱ ነአኩቶ ለአብም ምን እንደሚሠራ ሲያስብ አንድ ነገር ተገለጠለት:: ቤተ መንግስቱን እንደሚገባ ካደራጀ በኋላ በቤት ውስጥ አንድ ጉድጓድን በቁመቱ ልክ አስቆፈረ:: በውስጡም በ4 አቅጣጫ ጦሮችን ተከለባቸው:: ድንግል ካህን ነበረና ቀን ቀን ሃገር ሲያስተዳድር፣ ቅዳሴ ሲቀድስ፣ በጾም ይውላል:: ሌሊት ደግሞ ወዳስቆፈረው ቦታ ገብቶ ያለማቁዋረጥ እየጸለየ ይሰግዳል:: ወደ ምድር ሲሰግድ በፊቱ ያለው ጦር ይወጋዋል:: ቀና ሲል ደግሞ የጀርባው ይቀበለዋል:: እንዲህ እያለ የፈጣሪውን ሕማማት ይካፈላል:: በተለይ ዐርብ ዐርብ ሲሆን ደሙ፤ እንባውና ላበቱ ተቀላቅሎ ይፈስ ነበር:: እርሱ መስቀሉን ተሸክሞ ጌታውን ይከተል ዘንድ መርጧልና::

     ከተጋድሎው ጎን ለጐጎ ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አብያተ ክርስቲያናትንም ያንጽ ነበር:: በተለይ በ፲፪፻፲፩ ዓ.ም.  አካባቢ ያነጻት አሸተን ማርያም ልዩ ናት:: እርሷን ካነጸ በኋላ ከቤተ መንግሥቱ በደመና ሠረገላ ተጭኖ እየሔደ ያጥናት፣ ይቀድስባትም ነበር:: ታዲያ አንድ ቀን አጥኖ ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ብዙ ቅዱሳን መቅደሱን ከበው ተመለከተ:: እርሱም “ወገኖቼ! ከወዴት መወጣችሁ?” ቢላቸው “መዐዛ እጣንህን አሽተን መጣን” ሲሉ መለሱለት:: በዚህ ምክንያትም እስከ ዛሬ ድረስ “አሽተን (አሸተን) ማርያም” ስትባል ትኖራለች::

     ዛሬ ታቦቱ ያለበት ገዳሙም በእርሱ የታነጸ ሲሆን እጅግ ተአምረኛ ቦታ ነው:: ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ የነገሠው በ፴ ዓመቱ ነው:: ለ፵ ዓመታት በእንዲህ ያለ ቅድስና ኑሮ ፸ ዓመት ሞላው:: በዚህ ጊዜም ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ሰላምታንም ሰጠው::

     “ወዳጄ ነአኩቶ ለአብ! አንተ ስለ እኔ ፍቅር ለ፵ ዓመታት መከራን ተቀብለሃልና ሞት አያገኝህም፤ ክፍልህ ከነ ኤልያስ ጋር ነውና:: የሚያከብርህን አከብረዋለሁ:: ደጅህን የሳመውን፣ ይህ ቢያቅተው በሩቁ ሆኖ በአድናቆት የተመኘህን፣ መታሰቢያህን ያደረገውን ሁሉ እምርልሃለሁ” አለው:: ቀጥሎም “ይህች ቤት አንተ ስትደማ እንደኖርክባት እርሷም እስከ ምጽዓት ድረስ ለመታሰቢያህ ስትደማ ትኑር” አለው:: እነሆ ዛሬም ድረስ ከመቅደሱ ጸበል ይንጠበጠባል:: ለዚህም ደግሞ እኛ ኃጥአን ምስክሮች ነን:: ሳይገባን የቅዱሱን ደጅ ተመልክተናልና::

     ቅዱስ ነአኩቶ ለአብም የዚህን ዓለም ተጋድሎውን ፈጽሞ ወደ ብሔረ ሕያዋን መላእክት ወስደዉታል:: የተሰወረበትን ዕለት ስንክሳር ኅዳር ፩ ሲያደርገው አንዳንድ መዛግብት ደግሞ በ፫ ነው ይላሉ:: በዙፋኑም ላይ የአጎቱ የላሊበላ ልጅ አፄ ይትባረክ ተተክቷል።

ይህ ቅዱስ ንጉሥ ሆኖ ሳለ ገዳማዊ ሕይወትን በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ያሳየ ንጹሕና ድንግል  ጻድቅ ነው። የጦር መሪ ሳለ በእጁ ደም ያልፈሰሰ ፍቅር ማለት ለእርሱ ክርስቶስ ብቻ የሆነ ነበር። የሃገር መሪ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት እንደመሆኑ እጅግ ጊዜው የተጣበበ ቢሆንም  ለክርስትናው ጊዜ ያጣ ሰው አልነበረም::

እኛ ቤተ ክርስቲያንን “በሐኪ” ለማለት (ለመሳለም) እንኳ ‘ጊዜ የለኝም’ ስንል እርሱ ግን አብያተ ክርስቲያናትን ይፈለፍል፣ ያንጽ፣ በክህነቱ ያገለግል፣ በማዕጠንት ያጥን፣ ለረጅም ሰዓትም ይጸልይና በቀኝና በግራ  ጦር እየተከለ ይሰግድ ነበር። ታድያ ይህ ቅዱስ ለእኛ እንደምን ያለ ተሞክሮ በጎ አርአያ ነው?

አምላከ ቅዱሳን በጻድቁ ንጉሥ ጸሎት ይማረን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!