
እርሷ በአድማስ ላይ ተቀምጦ እንደሚያበራ እንቁ ናትና ክብሯ ብዙ ነው:: መድኃኒታችን ክርስቶስ በወንጌል እንዳለው “በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትምና “የሰማዕቷ ሕይወት በፊታችን እንደ ብርሃን ተገልጦ ይታያል:: ቅድስት አርሴማ እንደ ልጅ ወላጆቿን በመታዘዝ ደስ ያሰኘች ቡርክት ናት:: ቅድስት አርሴማ “ይሕ ቀረሽ” የማይሏት ውብ ናት:: ቅድስት አርሴማ ድንግል ናት:: ቅድስት አርሴማ ባሕታዊት ጻድቅ ናት:: ቅድስት አርሴማ ኃያል ሰማዕት ናት።
ይህስ እንደምን ነው ቢሉ:- አበው በትውፊት እንደነገሩን ከሆነ ቅዱሱ ጐርጐርዮስ (ዘአርመንያ) የታላቋ ሰማዕት ቅድስት አርሴማ ታላቅ ወንድም ነው:: በዜና ሰማዕታት ተጽፎ እንደሚገኘው በዚያ የመከራ ዘመን ቅዱስ ጐርጐርዮስ (ዘአርመንያ) ሦስት ኃላፊነቶች ነበሩበት:-
1)ቅድስት አርሴማን ጨምሮ ደናግሉን ማጽናት፣
2)ትምህርተ ቤተክርስቲያንን በሚገባ ማጥናት፣
3)የሚመጣውን መከራ ለመቀበል ራሱን ማዘጋጀት። ቅዱሱ ሦስቱንም ኃላፊነቶች በሚገባ በመወጣቱ ከራሱ አልፎ ለሌሎቹ አርአያ መሆን ቻለ:: ያቺን ንጽሕት አርበኛ ቅድስት አርሴማንም አጽንቶ የደናግሉ መሪ አደረጋት:: መከራው በጣም ገፍቶ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ ሆነው ይጸልዩ፣ ይጾሙ ፣ ገዳማዊ ሥራንም ይሠሩ ነበር:: ለዚህም ነው ቅድስት አርሴማና ቅዱስ ጐርጐርዮስ (ዘአርመንያ)ን ጻድቃን የምንላቸው:: በኋላ ግን ማኅደረ ሰይጣን ዲዮቅልጢያኖስ በመልኳ ተማርኮ ቅድስት አርሴማን ካላገባሁ በማለቱ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ድንግሏን አርሴማን ጨምሮ 127 ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ አርማንያ ተሰደደ::
በአርማንያም በአንድ ገዳም ውስጥ ተደብቀው በጾምና በጸሎት ለጥቂት ጊዜ ቆዩ። ነገር ግን ረሃብ ፈጃቸው:: የሚላስ የሚቀመስ ነገር በአካባቢው ባለመኖሩ ቅዱስ ጐርጐርዮስ (ዘአርመንያ) ወደ ከተማ ለመውጣት ተገደደ:: በዚያም በድርጣድስ ቤተመንግስት ውስጥ ባርነት ተቀጠረ:: በሚያገኛት ገንዘብም ወገኖቹን ይረዳ ነበር:: መከራው ግን አለቀቃቸውም:: ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ቅዱሳኑ ወደ አርማንያ መሔዳቸውን ስለ ሰማ ይዞ እንዲልክለት ድርጣድስን ላከው:: ድርጣድስ ግን ቅድስት አርሴማን ባያት ጊዜ ከውበቷ የተነሳ መታገስ ባለመቻሉ “ካላገባሁሽ” አላት:: ድንግሊቱ ግን “እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ፤ አይሆንም” አለችው:: ሊያስፈራራት ሞከረ:: ዐይኗ እያየ ደናግሉን ጨፈጨፋቸው:: አልሳካልህ ቢለው በአደባባይ በግድ ሊያገባት ቢሞክር እጁን ጠምዝዛ በሰው ሁሉ ፊት መሬት ላይ ጣለችው:: እጅግ ስላፈረ አስገረፋት፣ አሰቃያት፣ ዐይኗንም አወጣ:: በመጨረሻም አንገቷን አስቆርጦ ከሰማዕታቱ ጋር ተራራ ላይ ጣላት:: ከነገር ሁሉ በኋላ ድርጣድስና ባለሟሎቹ ለአደን በሔዱበት ርኩስ መንፈስ ወደ አውሬነት (እሪያነት) ቀየራቸው::
የንጉሡ እንስሳ (አውሬ) መሆን በአርማንያ ታላቅ ድንጋጤን አደረገ:: የንጉሡ እኅት ስታለቅስ በራዕይ “ለእመ ኢያዕረግምዎ ለጐርጐርዮስ አልብክሙ ድኂን።” “ጐርጐርዮስን ከተቀበረበት ካላወጣችሁት አትድኑም” አላቸው:: ወዲያውም ቆፍረው አወጡት:: ቅዱሱ እንደወጣ ዕረፍትን አልፈለገም:: ለ15 ዓመታት ቀባሪ አጥቶ የተበተነውን የቅድስት አርሴማንና የሰማዕታቱን
አጽም ሰብስቦ በክብር አኖረው:: ድርጣድስና ባለሟሎቹንም ወደ በርሃ ሔዶ ፈወሳቸው::
የሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ አጽም በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ከሌሎች ሰማዕታት አጽም ጋር ወደ ሃገራችን እንደመጣ አባቶቻችን በትውፊት ነግረውናል:: ለዚህም ይመስላል ቡርክቷ እናታችን ከሌሎች ሃገራት ለይታ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ፍቅር ያላት:: በዋናው ገዳሟ (ወሎ / ኩላማሶ/ስባ/ውስጥ የሚገኘው) ጨምሮ ስሟ በተጠራበት ሁሉ ኃይልን ታደርጋለችና:: ነገር ግን ወንድሞቼና እኅቶቼ በቅድስቷ እናታችን ስም የሚነግዱ ሥጋውያን ሰዎች በዝተዋልና እንጠንቀቅ:: የሰማዕቷ ክብር ብዙ ነውና በሕልም ላይ ብቻ አንታመን:: አባ እንጦንስ እንዳሉት “በሕልሙ የሚታመን ሰው ከንቱ ነውና::”

