
ንስሐ :- ነስሐ ከሚል የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ሐዘን፣ ፀፀት፣ ቁጭት፣ ቅጣት፣ ቀኖና፣ የኃጢአት ካሣ ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ንስሐ ገባ ሲባልም ዐዘነ፣ ተፀፀተ፣ ተመለሰ፣ ክፉ አመሉን ተወ ማለት ነው፡፡ ንስሐ አንድ ሰው በሠራው ጥፋት፣ ባደረገው ስህተት፣ በፈፀመው ኃጢአት ማዘኑንና መፀፀቱን ዳግመኛም ያንን የመሰለ ኃጢአት ላለማድረግ የሚወስነው ውሣኔ ነው፡፡
እንዴት ንስሐ ይገባል? ፩. ከራስ ጋር መሆን:- ንስሐ መግባት የራስ ፈቃድ ይጠይቃል። የእግዚአብሔር ፈቃድ ሰው ንስሐ እንዲገባ ነው። እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ ሊድኑና እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ እንደሚወዱም ቅዱስ ጳውሎስ በ፩ጢሞ.፪፥፫ ላይ ነግሮናል።
፪. ምክንያትንና ለራስ ይቅርታ ማድረግን ማስወገድ:– በንስሐ ሕይወት ለመኖር የምንሻ ከሆነ ለወደቅንበት ኃጢአት ምክንያት መደርደርና ለራሳችን ይቅርታን ለመስጠት መሞከር የለብንም። ኃጢአትን ከፈፀሙና ከሠሩ በኋላ ለኃጢአት ያበቃ ሌላ ምክንያት ማቅረብና በዚያም አንፃር ለመጽናናት መሞከር በራሱ ኃጢአት ነው። በዚህ ዓይነት ለኃጢአቱ ምክንያት እየደረደረ የሚጽናና ሰው ኃጢአትን እየለመደ ወደ ባሰ አዘቅት ከመውረድ በቀር ንስሐ ለመግባት አይችልም። ምንም ምክንያት ቢደረደር ኃጢአት ምንጊዜም ኃጢአት ነውና ለሠራነው ኃጢአት የተለያዩ ምክንያቶችን በማበጀት ራሳችንን እያጽናናን ነፃ ለመሆን መጣር የለብንም፣
፫. ንስሐ ለመግባት አለመዘግየት (አጋጣሚውን መጠቀም) :- አንዳንድ ሰዎች ንስሐ ለመግባት የገጠማቸውን የተመቻቸ አጋጣሚ ሳይጠቀሙበት በመቅረት ዕድሉ አምልጧቸዋል። እግዚአብሔር ሰው ሁሉ ኃጢአቱን መርምሮ ወደ ንስሐ እንዲመለስ፣ የተቀደሰ ጸጋውን ሊያድለውና በልቡናውም አድሮ ለመሥራት አብዝቶ ይሻል። ሰው በተለያዩ ሁኔታዎችና አጋጣሚዎች ንስሐ ሊገባይችላል። ለምሳሌ:- በመጻሕፍት ፣ በዝማሬ ፣ በበሽታ፣ በአደጋ፣ በሞት ወዘተ. ተመክሮ ንስሐ ሊገባ ይችላል። በእነዚህ አጋጣሚዎች የሚጠቀምባቸው ሰውም አስተዋይ ነው። የጠፋው ልጅ “ተነስቼ ወደ አባቴ ቤት እሄዳለሁ” ሲል እንደተናገረና ከአባቱ እንደታረቀ ወደ ቤቱም እንደ ተመለሰ። ሉቃ. ፲፭፥፲፰ የማያስተውል ሰው ደግሞ ኤሳውን ይመስላል። ኤሳው ብኩርናውንና በረከቱን ሁሉ ከአጣ በኋላ ወደ አባቱ ገብቶ በረከቱን ታናሽ ወንድሙ እንደ ወሰደበት ባወቀ ጊዜ “ታላቅ፣ እጅግም መራራ ጩኸት ጮኸ። ቃሉንም አንሥቶ አለቀሰ።” ዘፍ. ፳፯፥፴፬-፴፰ ፬. ልብን አለማደንደን፣
፭. መሰናክሎችና የኃጢአት ምንጮችን ማስወገድ፣
፮. ለኃጢአት ጊዜ አለመስጠት፣
፯. ጠባይን መመርመር:- ከድብቅ ኃጥያቶች መጠንቀቅ፣
፰. ከሚወዱት ኃጢአት በመሸሽ ደካማ ጎንን ማረም፣
፱, ዘለዓለማዊውን ሕይወትና የሚጠበቅብንን ማሰብ፣
፲. የኃጢአትን ፍቅር ለማስወገድ ፍቅረ እግዚአብሔርን ማጽናት፣ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ወደ ንስሐ በሚወስደው የሕይወት ጎዳና ላይ ማንኛውም ሰው ሊከተላቸው የሚገቡ መርሖዎች ናቸው። ዋቢ መጽሐፍ:- የንስሐ ሕይወት (ቀሲስ እሸቱ ታደሰ ወንድምአገኘሁ)

