
ከጦርነት በፊት ከጠቅላላ ሕዝቧ ዐሥር ከመቶው ክርስቲያን እንደነበረ የሚነገርላት ሶሪያ የዛሬ ዐሥራ ሦስት ዓመት ነበር። በዓረብ የፀደይ ዐብዮት ነበር ወደ እርስ-በእርስ ጦርነት የገባቺው። ከኃምሳ ዓመታት በላይ ሶሪያን የመራው የበሽር አላሳድ ቤተሰብ ለውጥ በሚፈልጉ ተቃዋሚዎች፣ በአይ. ኤስ. አይ. ኤስ. እና መሠል አክራሪ ሙስሊሞች የተከፈተበትን ጦርነት መክቶ ቢቆይም በኅዳር ወር መጨረሻ ሳምንታት የደረሰበትን ምት መቋቋም ባለመቻሉ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንትና ቤተሰቦቻቸው ስልጣንና ሀገራቸውን ጥለው ወደ ሩሲያ ከኮበለሉ አስር ቀናትን ተሻግረዋል። የፕሬዝዳንት በሽር አላሳድን ከሀገር መኮብለል ተከትሎ ሀገሪቱን ኢስላማዊ ተዋጊ ሃይሎች ተቆጣጥረዋታል። በተለይም ሀያት ታህሪር አል-ሻም ዌም (HTS) ተብሎ የሚጠራው የሽብር ቡድን ደማስቆን ጨምሮ ዋና ዋና ከተሞችን የመቆጣጠር እድል አግኝቷል። የአላሳድ ውድቀትን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ደስታቸውን እየገለፁ ይገኛል።
በበሽር አላሳድ ከስልጣን መነሳትና የእስላማዊ ቡድኖች መተካት ከደስታ ይልቅ ስጋት ያረበባቸው ክርስቲያኖች ናቸው። ባለፉት ዐሥራ ሦስት የእርስ በእርስ ጦርነት ዓመታት እኒህ ክርስቲያኖች በልዩነት የጥቃት ሰለባዎች በመሆናቸው ከጦርነቱ በፊት ከነበራቸው የዐሥር በመቶ ሀገራዊ የሥነ ሕዝብ ድርሻ ወደ ሁለት በመቶ ወርደዋል። አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣ ምእመናን በጅምላና በነጠላ ተገድለዋል። ብዙዎች ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል። ይህ ታሪክ ከመፈጠሩ ከሺህ ዘመናት በፊት ግን ሦርያ የክርስቲያኖች መናኸሪያ ነበረች። በአንፆኪያና በደማስቆ ታላላቆቹ ሀዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ አስተምረዋል። ከጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አምስቱ መናብርትና ከሁለቱ ጥንታዊ ትምህርት ቤቶች አንዱ የሚገኙት በሶሪያዋ አንፆኪያ ነበር።
ሶሪያ በኒቂያ ከተሰበሰቡ ሠለስቱ ምዕት የሃያው ሀገር ናት። በዚህች ምድር አግናጢዮስ ምጥው ለአንበሳና ቅዱስ ኤፍሬም በቅለውባታል። ነገር ግን የዐረብ ወረራና በመካከለኛው ክፍለ ዘመን የተነሳው የኦቶማን እንቅስቃሴ ሶሪያውያን ክርስቲያኖች አንፃራዊ የእምነት ነፃነት ወደሚያገኙባቸው ሀገራት እንዲሸሹ አልያም በሀገራቸው ሰማዕትነትን እንዲቀበሉ አስገድዷቸዋል። በዐሥራ ስምንት መቶዎቹ እንኳን በተካሄደ የኦቶማን ጭፍጨፋ ከ፺ ሺህ በላይ ክርስቲያኖች ተገድለዋል።ዛሬ ላይ የተከሰተውን ሁኔታ ተከትሎ የሶሪያ ክርስቲያኖች በከባድ ውጥረት ላይ ናቸው። በተለይ ከአል አሳድ ሽሽት በፊት ክርስቲያኖች በስፋት በሚኖሩባት በአሌፖ የአማፂው ቡድንና ደጋፊዎቻቸው የጥቃት ኢላማ መሆናቸው መጪውን ጊዜ በፍርሃት እንዲመለከቱ አድርጓቸዋል።vከሦርያ ክርስቲያኖች ውስጥ አኀት አብያተ ክርስቲያናት የሚባሉት የሶሪያና የአርመን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት አንድ ሦስተኛውን ይይዛሉ። የተቀሩት በክርስቲያን ምድብ የሚካተቱት የምሥራቅ ኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክ፣ የአሲርያንና የመናፍቃን ቡድኖች ናቸው።የመንግስት ግልበጣው ሲካሄድ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ህንድ የነበሩት የሶሪያ (ያዕቆባዊት) ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ሞራን ሞር አግናጢዮስ ኤፍሬም ፪ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን አቋርጠው ከወገኖቻቸው ጋር የሚመጣውን ለመጋፈጥ ወደ ሶሪያ ተመልሰዋል። ቅዱስነታቸው ወደ ሶሪያ መንበራቸው ከተመለሱ በኋላ በሶሪያ መንበረ ፓትርያርክና በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ሀገረ ስብከቶች ሊቃነ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳትና አገልጋዮች ጋር የተወያዩ ሲሆን ከሀገሪቱ ጊዜያዊ አስተዳዳሪዎች ጋር በመገናኘትም ክርስቲያኖች የሀገሪቱ ጠቃሚ አካል እንደመሆናቸው ደኅንነታቸው እንደሚጠበቅ ከመንግስት ቃል እንደተገባላቸው ከውይይቶቻቸው በኋላ በመንበረ ፓትርያሪካቸው በኩል በወጣው መግለጫ አንስተዋል።
ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አዕምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና ዐሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል። ፊል ፬÷፮-፯ በሚል ርእስ ባወጡት መግለጫ ምእመናንና አገልጋዮች ከመቼውም ይልቅ በፆምና በጸሎት እንዲሁም የሀገሪቱን ሁኔታ በንቃት በመከታተል እንዲያሳልፉ፣ መንግስት የአናሳዎችን መብት እንዲያስጠብቅ፣ ፓሊሶችና የጦር ኃይሎች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ በውጭ ያሉ ሀገረስብከቶች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ጠይቀዋል። ፓትርያሪኩ “የሰላምና የተስፋ ምንጭ የሆነውን የጌታችን የልደት በዓል ከፊት እየጠበቅን ሰላምና ብልፅግናን ለሀገራችን እንዲያመጣልን እንመኛለን” ብለዋል። ብፁዕ አቡነ ሞር ቡትሮስ (ጴጥሮስ) ቀሲስም ሶሪያውያን ክርስቲያኖች እውነታውን በመረዳት፣ በንቃትና በእምነት ሆነው እንዲጋፈጡ ምእመናንን እያበረታቱ ይገኛሉ።የሦርያ ክርስቲያኖች ከአል አሳድ መነሳት በኋላ የመንግስትን ቃል አምነው ያሳለፍነው እሑድ ቤተ መቅደሶቻቸውን ቢከፍቱም አክራሪዎችን ማመን የሚያስከፍለውን ዋጋ ያውቃሉና ዛሬም በስጋት ልብ ውስጥ ሆነው ወደ ቤተ ክርስቲያን ያመራሉ።በአርመን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሶሪያ አሌፖ ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማጋር አሽካሪን “ፍጹም የሚባል ደኅንነት የለም፤ ነገር ግን እንደ ክርስቲያን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን። እንደ ዐሳቡ ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንደሆነ እናምናለን። ብለዋል።እግዚአብሔር በምድረ ሶሪያ መረጋጋትን ለቤተክርስቲያን ደግሞ ሰላምና ፍፁም አንድነትን እንዲሰጣት እንድንጸልይ እያሳሰብን የዛሬን በዚህ አሳረግን።

