
ቸርነት፣ ደግነት፣ ምሕረትና ይቅር ባይነት የባሕርይ ገንዘቦቹ የሆኑለት አምላካችን እግዚአብሔር በአምሳሉ የፈጠራቸው የሰው ልጆችን ከመንገዱ በመውጣት በጠላት ወጥመድ ተይዘው እንዳይቀሩ “ወደ እኔ ተመለሱ” እያለ ዘወትር ይጣራል። ይህ ጥሪ የንስሓ ጥሪ ነው። ንስሓ የቃሉ ትርጒም መጸጸት፣ መቆጨት፣ በሠሩት ክፉ ተግባር ማዘን ማለት ነው። (ደስታ ተክለ ወልድ ገጽ ፰፻፸፰) በሌላ በኩል ደግሞ ንስሓ በሙሉ ልብ መመለስንና መለወጥን ያመለክታል። የሰው ልጅ ድካም የሚስማማውን ሥጋ እንደ መልበሱ ይደክማል፣ ይዝላልም። ከእውነት መንገድ፣ ከጽድቅ፣ ከሕይወት፣ ወጥቶ ይስታል። ይሁን እንጂ የሚያስብ አዕምሮና የሚያመዛዝን ኅሊና ያለው ፍጡር እንደመሆኑ የሠራውን ስሕተት አስተውሎ መጸጸቱ የማይቀር ነው። ጸጸቱ የዐሳብ ለውጥ መኖሩን ያመለክታላል። ነገር ግን የዐሳብ ለውጥ ብቻ መፍትሔ አይሆንምና በተግባር መለወጥ አለበት። በዐሳብም በተግባርም መለወጥ ማለት ደግሞ አጠቃላይ የሕይወት ለውጥ መሆኑን ያስገነዝበናል። ንስሓ የሚባለውም ይህ ነው። ማለትም በመጀምሪያ ያለንበትን ሁኔታ ቆም ብለን ማሰብ፤ ያለንበት ሁኔታ ከትክክለኛው የሕይወት መስመር የወጣ እንደሆነ መጸጸትና መቆጨት፤ ቀጥሎም የበደልነውና የተጣላነው ሰው ካለ ይቅርታ መጠየቅና መታረቅ፣ ከሁሉ በላይ ሕጉን በመተላለፍ ያሳዘንነው አምላካችን ይቅር እንዲለን ደጅ መጥናት ንስሓ ይባላል። ከንስሓ በኋላም ወደ ትትክለኛው መንገድ በመመለስ አዲስ ሕይወት መጀመር ይጠበቅብናል። ጠቅለል አድርገን ስንመለከት ንስሓ “እኖር፣ እከብር” ባይ ኅሊና የሚያሳስበንን ሥጋዊ ፍላጎት ተከትለን፣ ስላጠፋነው ጥፋት ስለ በደልነውም በደል ምሕረትና ይቅርታ የምንጠይቅበት ለኃጢአትና ለጥፋት የጋበዘንን ሥጋችንን የምንገሥጽበትና የምንቀጣበት፣ የእግዚአብሔርንም ቸርነት ደጅ የምንጠናበት ሥርዓት ነው። ይህም ማለት አስቀድመን በተከተልነው ክፉ ዐሳብና በፈጸምነው የጥፋት ተግባር የምንቆጭበት፣ የምንጸጸትበት፣ራሳችንን የምንወቅስበት ወደኋላም ተመልሰን የቀደመ ስሕተታችንን ላለመድገም ቃል የምንገባበት ሥርዓት ነው። ለዚህ ደግሞ “ልጆቼ ወደ እኔ ተመለሱ” እያለ ዘወትር የሚጠራንን የአምላካችንን ድምፅ መስማት ይጠበቅብናል። “እንመለስ!“ መልካም ዕለተ ሰንበት
ምንጭ ሐመር መጽሔት የካቲት ፳፻፲፫ ዓ.ም.

