
ነቢይ፣ ሐዋርያ፣ ሰማዕት የሆነው የቅዱስ አጋቦስ በዓል በየካቲት4 ይከበራል። ይህም ቅዱስ፣ ጌታችን ከመረጣቸውና ከመከራው በፊት ይሰብኩ ዘንድ ከላካቸው ከ፸፪ቱ አርድዕት መካከል አንዱ ነው። በጽርሐ ጽዮንም አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከሐዋርያት ጋር ስጦታውን ተቀብሏል። እግዚአብሔር የትንቢት ሃብትን ሰጠው። በዚህ ጸጋውም በዘመነ ሐዋርያት (በቀላውዴዎስ ቄሳር ጊዜ) በዓለም ላይ ከባድ ረሀብ እንደሚመጣ ተናግሮ በርካታ ክርስቲያኖች ከረሃብ እና ሞት የታደገ ቅዱስ ነው። ይህን ጊዜ ያለፉትም ደቀመዛሙርቱ እያንዳንዳቸው እንደችሎታቸው መጠን አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩ ወንድሞች እርዳታ ይልኩ ስለነበር ነው። እንዲሁም የቅዱስ ጳውሎስን መከራ አስቀደሞ በመናገሩ ሐዋርያ ትንቢት ተብሏል። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደተነገረው የጳውሎስን መታጠቂያ አንስቶ ራሱን እግሮቹን አስሮ ” የዚህ መታጠቂያ ባለቤት በኢየሩሳሌም እንዲህ ያሥሩታል” ብሎ ትንቢት ተናገረ ትንቢቱም ተፈጸመች። ከዚህ በኋላ ከሐዋርያት ጋር ሕይወት የሆነውን የወንጌል ትምህርት ሊያስተሞር ወጣ። እያስተማረና ቀና የሆነችውን የእግዚአብሔርን መንገድ እየመራ ብዙ ሀገሮችም ዞረ፤ ብዙ አይሁዳውያንን እና ዮናናውያንን ወደ ክርስትና መለሰ። በዚህ የተነሳ ቅናትን የተሞሉ አይሁዳውያን በኢየሩሳሌም ብቻውን በድንገት ያዙትና ታላቅ ግርፋትን ገረፉት። ከዚህ በኋላ በአንገቱ ገመድ አስገብተው እስከ ከተማ ውጪ ድረስ እየጎተቱት ነፍሱ እስካሳለፈ ድረስ በድንጋይ ወገሩት ብዙ መከራን አደረሱበት። በመጨረሻም በየካቲት ፬ ነፍሱ አረፈች። በዚያን ጊዜ ከሰማይ ብርሃን ወርዶ በሥጋው ላይ እንደ ምሰሶ ተተከለ። አንዲት አይሁዊት ሴትም ልቦናውን ገለጠላትና ይህንን ብርሃን አየቺው። እሷም በውስጧ ሽንገላ፣ ጠብ፣ ቅናት የሌለባት የኦሪትን ሕግ የምትጠብቅ ነበረች። “ይህ ሰው አውነተኛ ነው” አለች። ያን ጊዜ በላይዋ ብርሃን ወረደ፤ እንዲህ እያለች ጮኸች “እኔ በቅዱስ አጋቦስ ፈጣሪ የእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ የማምን ነኝ” ብላ መሰከረች ያን ጊዜም እንደ ቅዱስ አጋቦስ በድንጋይ ወግረዋት ሰማዕት ሆናለች። የቅዱሱ የሰማዕቱ አባታችን በረከታቸው ይደርብን። ምንጭ – ሰንክሳር ከመስከረም እስከ መጋቢት

