ጉባኤ ኒቂያ

ኒቂያ በጥቁር ባሕር ወደብ አካባቢ የምትገኝ ስትሆን የተመሠረተችውም በዲዮናሲስ ነው፡፡አርዮስ የተባለው መናፍቅ በተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ  ተወግዞ የተለየ ሲሆን ለአርዮስ ስልጣነ ክህነት የሰጠው እና ከውግዘቱ የፈታው አክላስ ለመንበረ ማርቆስ ለአንድ ዓመት ከቆየ በኋላ ሞተ፤ እለ እስክድሮስም ተተካ፡፡ ለቤተክርስትያን የተጋደለ ታማኝ አባት ነው፡፡

የእስክንድርያ ቤተክርስቲያን የአርዮስን ዐሳብ ብትታገሰውም እርሱ ግን በድፍረት ዐሳቡን በመግለጽ  የግጥም ጽሑፎችን እያሰራጨ ማዘጋጀት ጀመረ፡፡ ይህ የአርዮስ የግጥም መጽሐፍ “ታሪያ” ይባላል፡፡ ብዙ የዋሃንን ማወናበድ ስለጀመረ መቶ የሚያህሉ የሊቢያ እና የእስክንድርያ ኤጲስ ቆጶሳት ተሰብስበው  አርዮስን አወገዙት፡፡ አርዮስ እለ እስክንድሮስን “የሰባልዮስ የክህደት ትምህርት ያስተምራል” ብሎ ይለፍፍ ጀመር። ዐሳቡን ያልተቀበሉትን ሁሉ “ሰባልዮሳውያን ናቸው” ይል ነበር፡፡ ይህ ውንጀላ በእስክንድርያ ተቀባይነት ስላጣ ወደ ፍልስጤም ምድር ሄደ። ሶርያና ቂሳርያ እየዞረ  በአንጾኪያ ትምህርት ቤት አርዮስ ጓደኞች ስለነበሩት  ለሁሉም “እለ እስክንድሮስ በግፍ አወገዘኝ፤ የሰባልዮስንም ትምህርት እያስተማረ ነው” ብሎ ነገራቸው ፡፡

ከአርዮስ ጓደኞች አንዱ በጣም የሚረቆርለት የኒቆሜዲያ ኤጲስ ቆጶስ የሆነው አውሳብዮስ ከቁስጥንጥንያ ቤተመንግስት ባለ ሙሉ ሥልጣን ነበር፡፡ ወደ ኒቆሜድሮ ገስግሶ እንዲመጣ ጥሪ አደረገለት፤ በአካባቢው የሚገኙ  ኤጲስ ቆጶሳት ሁሉ አርዮስን እንዲደግፉ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ ቁስጥንጥንያ እስክትመሠረት ድረስ የምስራቁ ሮም ክፍል ዋና ከተማ ኒቆሜድሮ ነበረች፡፡ አርዮስም ወደዚህች ከተማ በሔደ ጊዜ አውሳቢዮስ ተቀብሎ ኤጲስ ቆጶሳትን ሰብስቦ ስለ አርዮስ ጉዳይ ጉባኤ አረደገ፡፡ ሲኖዶሱንም የመራው እራሱ አውሳቢዮስ  ነበር፡፡ ሲኖዶሱም አርዮስ መወገዝ እንደሌለበት ከውግዘቱ በመፍታት ወደ አንጾኪያ እንዲመለስ ተደረገ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የእስክንድርያ ቤተክርስትያን አልሰማችም ነበር፡፡ አርዮስ “እለ እስክንድሮስ ሲያወግዘኝ ተፈትቼ መጣሁ” በማት የክህደት ትምህርቱን ማስተማር ጀመረ፡፡ ይህ ሁኔታ እየተባባሰ በመሄዱ በእስክንድርያ ብቻ ሳይሆን በቁስጠንጢኖስ ቤተመንግሥት ስጋት ማሳደሩ አልቀረም፡፡ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስም  ተጨባጭ መፍትሔ እንዲገኝ በማሰብ የእስጳኝ ኤጲስ ቆጶስ ኦስዮስ ወደ እስክንድርያ ላከው። መረጃዎችንም  ሰብስቦ ወደ ቆስጠንጢኖስ ተመለሰ፡፡ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ እንዲደረግ አዋጅ ነገሩ፡፡ ለመጀመሪያው ጉባኤ እንዲደረግ የታሰበው በእንቆራ ነበር፡፡ ባልታወቀ ምክንያት በኒቂያ እንዲሆን ተወስኗል፡፡በዚህ አዋጅ መሠረት  የቤተክርሰቲያን አባቶች ኤጲስ ቆጶሳት እና ሊቃውንት  በኒቂያ ተሰበሰቡ ፡፡ በሲኖዶሱ የተሰበሰቡት  አባቶች በሕይወታቸው ንጽሕና ቅድስና ያላቸው፣ በሃይማኖታቸው  የሐዋርያትን ፈለግ የተከተሉ፣ ስለ ሃይማኖታቸው  በሚመሰክሩበት ጊዜ ተቃዋሚዎች በሚፈጽሙባቸው የግፍ ድርጊት  ዐይናቸው የፈረጠ እጅ እግራቸው የተቆረጡ ነበሩ፡፡ ቁጥራቸውም አትናትዮስ  እንደመሰከረው 318 ናቸው፡፡ 

ሌሎችም የቤተክርሰትያን  ጸሐፊዎች ከፍ እና ዝቅ አድርገው ጽፈዋል፡፡ ሶዞሜን የተባለው የቤተክርሰትያን ታሪክ ጸሐፊ የአርዮስ ደጋፊዎች የግሪክ ፈላስፎች እና አርዮሳውያን በጉባኤው በብዛት ተጠርተው ነበር ኦርቶዶክሳውያን ግን ጥቂት ነበሩ፡፡ ጉባኤውን  በሊቀ መንበርነት እንዲመሩ የተመረጡት 3 ሲሆኑ እነርሱም ሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት የእስክንድርያው እለ እስክንድሮስ  እና የአንጾኪያው  ኤዎስጣቴዎስ  ናቸው። ሦስተኛው  የእስጳኝ ኤጲስ ቆጶስ ኦስዮስ ነው፡፡

ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በጉባኤው ላይ ንግግር አድርጎ “ለቤተክርስትያን እና ለምእመናን አንድነት የመሰላችሁን ታደርጉ ዘንድ ሙሉ ሥልጣን  ሰጥቻችኋለሁ” ብሎ ለዚህም ማረጋገጫ ይሆን ዘንድ የነገሠበትን ዘውዱን ቀለበቱን  አውልቆ ለጉባኤው አስረከበ፡፡ የጉባኤው የመግቢያ ውይይት  ከግንቦት ፳ እስከ ሰኔ ፲፫ ከተደረገ በኋላ ከሰኔ ፲፬ እስከ ነሐሴ ፳፭ ክርክሩ ቀጥሏል ፡፡

ጉባኤው መጀመሪያ የተነጋገረባቸው አንቀጾች

ሀ. አርዮስ ያቀረባቸው ሁሉንም ጥቅሶች መመርምር፣
ለ. ጥበብ የሚለውን ቃል እንዴት እንደተረጎመው ማየት፣
ሐ. ወልድ በባሕርይው ፍጡር ከሆነ በመዳን ምሥጢር ላይ ስለሚደርሰው አደጋ መወያየት፣
መ. የእግዚአብሔር ቃል ለሰው ልጆች ሲል ወዶ ያደረገውን ተዋሕዶ “አርዮስ የባሕርይ ተወራጅነት ቢኖርበት ነው” ስለማለቱ፣
ሠ. ወልድ በባሕርይ ፍጡር ሳለ እንደሌሎች ፍጡራን በገድል በትሩፋት የአምላክነት ክብር አገኘ ስለማለቱ፣ በጉባኤው አርዮስ አቋሙን እንዲያብራራ ተጠይቆ ሲናገር፡ ‹‹ወልድ ባልነበረበት ጊዜ አብ ነበር፤ ወልድን ከምንም ፈጠረና የእግዚአብሔር ልጅ እንዲሆን አደረገው፤ ይህም ማለት አብ ወልድን እንደማንኛውም ፍጡር ፈጥሮታል ማለት ነው፡፡ አብም ወልድን ከፈጠረ በኋላ ስልጣን ሰጥቶት ሁሉን ነገር እንዲፈጥር አደረገው . . .›› በማለት አብራራ፡፡

በዚህ ወቅት እለስንድሮስ ፡ “አምልኮትና ስግደት የሚገባው ለፈጣሪያችን ነው ወይስ ላልፈጠረን?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ አርዮስም “ለፈጠረን›› ሲል መለሰ፡፡ እለእስክንድሮስም፡ ‘ “ፍጡር ነው” ያልኸው ወልድ የፈጠረን ከሆነ፣ ለአብ አምልኮትና ስግደት እንዳቀረብን፣ ለወልድስ ማቅረባችን ምን ያስጠይቃል?’ ሲለው አርዮስ ምላሽ አልነበረውም፡፡ አትናትዮስም፡ “ኢየሱስ የደኅንነቴ ዋስትና ነው፤ ለማዳን የበቃው አምላክ ስለሆነ ነው።” ማለቱ ይታወሳል፡፡

ጉባኤው የወሰነው ውሳኔ
1. አንቀጸ ሃይማኖት (ጸሎተ ሃይማኖት)
2. ሕንፃ መነኮሳት (ለመነኮሳት)
3. ኦርቶዶክስ የሚለው ቃል የተወሰነው የተገኘው በዚህ ጉባኤ ውሳኔ ነው። በአጠቃላይ ይህ የኒቅያ ጉባኤ የተካሄደው በ፫፻፳፭ ዓ.ም. ፫፻፲፰ ተሰብሳቢዎች በተገኙበት “ወልድ ፍጡር”ሲል የሳተውን ቀንደኛ መናፍቅ አርዮስን አውግዘው ለይተዋል፡፡ምንጭ፦  የቤተክርስትያን ታሪክ በዓለም መድረክ