
የተፈጥሮን ዑደት ጠብቆ የሚጓዘው የሜዲትራኒያን ባሕር ውኃ በነፋስ እየተገፋ ከሲርጥ የባሕር ዳርቻ አሸዋ ጋር ይላተማል። ከዚህ ትዕይንት የቅፅበታት ማለፍ በኋላ ፳ ጥቁር የለበሱና ፊታቸውን የሸፈኑ ታጣቂዎች ሬንጀር ከለበሰ መሪያቸው ጋር በመሆን በአንድ እጃቸው ቢላ በሌላ እጃቸው በባዶ እግር እንደ በግ በዝምታ የሚነዱ ብርቱካናማ የእስር ቱታ የለበሱ ንጹሐንን አንገት ጨምድደው ሲጓዙ ይታያል።
ለዛሬ የቤተክርስቲያን ሳምንታዊ መርሐግብር የመረጥነው የዛሬ ዐሥር ዓመት በዚሁ ሳምንት የካቲት ፰/፳፻፯ ዓ.ም. በዕለተ ሰንበት ፅንፈኛው አይ.ኤስ.አይ.ኤስ. /ዳዕሽ(ISIS) አል ሃያት በተሰኘ ገፁ “የመስቀሉ ሕዝቦች፣ የጠበኛዋ የግብፅ ቤተክርስቲያን ተከታዮች” በሚል ርእስ ያዘጋጀው የ፭ ደቂቃ ቪዲዮው ወግቢያ ነው።
በሚያቃጥለው የሊቢያ በረሃ በባዶ እግራቸው እንደ በግ የሚነዱት ፳፩ ንጹሐን የቅብጥ ክርስቲያኖች የመታረጃ ቦታቸው ላይ ሲደርሱ በአጋቾቻቸው ተገፍትረው ሲንበረከኩ ይታያል። ሬንጀር ለባሹ መሪያቸው ፈጣሪውን በማመስገን በሚጀምረው ንግግር “ወገኖች ሆይ በአልሻም ተራራ (ሶሪያ) ላይ በዳቢቅ ሜዳ የመስቀሉን ተረት የተሸከሙትን በእስልምናና በሙስሊሞች ጥላቻ የተሞላውን ጭንቅላታቸውን ስንቆርጥ አሳይተናችኋል። ዛሬም በደቡብ ሮም በኢስላም ምድር ሊቢያ ሌላኛውን መልእክት እናስተላልፋለን። ባለ መስቀሎች ሆይ ከእንግዲህ ደኅንነት ለእናንተ ምኞት ብቻ ይሆናል፤ በተለይ ልትፋለሙን ከሞከራችሁ። ጦርነቱ ሸክሙን እስኪያወርድ፣ ኢሳ (ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ የሚመጣ ነብይ አድርገው እንደሚያስቡት ልብ ይሏል) መጥቶ መስቀሉን እየሰበረ፣ እሪያውን እየገደለ፣ ጂዚያን(ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች የሚከፍሉት ታክስ) እስኪሰርዝ ድረስ የሼህ ኦሳማ ቢላደንን አስክሬን የደበቃችሁበት ባሕር ደማችሁን እንቀላቅላለን።” ሲል ይደመጣል።
ከንግግሩ በኋላ በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ “ያ ረብ የሱሃ አል መሲህ” (አቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ) የሚለው የሰማዕታቱ ድምፅ ይሰማል። “ለጣዖታቸው ከነ ሽርክናቸው ይሙቱ” የሚል የዐረብኛ ጽሑፍ በተንቀሳቃሽ ምስሉ ይነበባል።
“ከአላህ ጋር ሮምን እንቆጣጠራለን” የሚለው የመሪያቸው መፈክር ከተሰማ በኋላ አይ.ኤስ.የአይ.ኤስ. ታጣቂዎች ሰማዕታቱን አጋድመው እንደ በግ ሲያርዳቸውና ደማቸው ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር ሲቀላቀል በማሳየት ቪዲዮው ይጠናቀቃል።
፳ው ግብፃውያን እና ፩ የጋና ተወላጅ ከእናት ሀገራቸው ወደ ሊብያ የተሰደዱት ኑሮን ለማሸነፍና የተሻለ ቀንን ለማየት ነበር። በሊቢያ በረሃ በግብርናና በልዩ ልዩ ሥራዎች የተሰማሩ ከፊሉም ድንበር የሚያቋርጡ ነበሩ። ይህ ታዲያ እስከ ተያዙባት የታኅሣሥ ፳፻፯ ዓ.ም. ምሽት ድረስ ነው። ከዛች ምሽት በኋላ ሁሉም አንድ ናቸው። ሰማዕታት። ከተንቀሳቃሽ ምስሉ በኋላ ከሌሎች ስደተኞችና በቁጥጥር ስር ከዋሉ የአይ.ኤስ.አይ.ኤስ. አባላት የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት መጀመሪያ ላይ የተያዙት ፯ ብቻ ሲሆኑ ቀጥለው ፲፫ቱ ተቀላቅለዋቸዋል። የመሞታቸው ምክንያት በተንቀሳቃሽ ምስሉ በግልፅ እንደሚታየው አምላካቸውን ላለመካድ በመምረጣቸው ነበር። ይህ የ፳ው የዕምነት ፅናት የሳበውና ከምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጋና ሰማዕት ሚቲው አያርጋ “እኔም ክርስቲያን ነኝ፤ እንደ እነሱ ነኝ” በማለት ተቀላቀላቸው። አጋቾቻቸው ኢየሱስን እንዲክድ በጠየቁት ሰዓትም “አምላካቸው አምላኬ ነው” የሚል ምስክርነትን ሰጠ።
የሰማዕታቱን የመጨረሻ የምድር ቆይታ የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስሉ የብዙኃንን ልብ የሰበረ ቢሆንም ልባቸውን በክርስቶስ ፍቅር ለሞሉ ኦርቶዶክሳውያን የሚያነቧቸውን ዜና ሰማዕታት እውነትነት ያረጋገጡበትና አንገታቸውን ቀና ያደረጉበት ነበር። “The 21” (21ዱ) የተሰኘውን የሰማዕታቱን ዜና መዋል የሚያትት መጽሐፍ የፃፈው ጀርመናዊው ማርቲን ሞስባህ “ብዙዎች የጥቃት ሰለባዎች ብለው ይገልጿቸዋል፤ እነርሱ ግን እንዲህ አይደሉም። ሰለባ ያለፈቃዱ ጥቃት የደረሰበት ነው፤ እነርሱ ግን በፈቃዳቸው ሰማዕትነት የመረጡ ናቸው” ሲል በኩራት ያነሳቸዋል።
የግብፅ ቤተክርስቲያንም ይህንን ለዓለም የተነገረ ዜናቸውን በመመልከት ሰማዕትነታቸውን አውጃዋለች። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም ከግብፅ አቢያተክርስቲያናት ጋር ባለ ነባር አንድነት በተመሳሳይ መልኩ በሚያዚያ ከተሰው ፴ ልጆቿ ጋር ታስባቸዋለች። የሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያንም ከባለፈው ዓመት ጀምራ ስማቸውን በመዝገበ ሰማዕታት ውስጥ አካታዋለች።
መካነ ሰማዕታት ሲርጥ በጥቅምት ፳፻፱ ዓ.ም. ከአክራሪዎች ነፃ በሆነች ሰዓት ነበር የሰማዕታቱ ክብርት ሥጋ መገኘቱን የአካባቢው ባለሥልጣናት ያሳወቁት። ይህን ተከትሎ ከሰማዕታቱ ቤተሰቦች በተሰበሰበ ዘረመል (DNA) አማካኝነት የ፳ው ሰማዕታት ክቡር ሥጋ በግብፅ ሚኒያ ግዛት አል አውር በስማቸው በታነፀው የሰማዕታተ አሚን ቤተክርስቲያን (The church of Martyrs of Faith) በክብር አርፏል። በሐምሌ ፳፻፲፩ ዓ.ም. የግብፅ ቤተክርስቲያን ባቀረበችው ይፋዊ ጥያቄ መሠረት በ፳፻፲፫ ዓ.ም. የ፳፩ኛው ጋናዊ ሰማዕት ክቡር ሥጋ ፳ውን ወንድሞቹን ተቀላቀለ። በዕለቱ የተገኙ የ፳ው ሰማዕታት ቤተሰቦች የጋናዊውን ሰማዕት አፅም መምጣት ተመልክቶ “ደስታችን ሙሉ ሆነ” ሲሉ ተደምጠዋል።
ብዙዎችን እንዲያስቆጣና ተስፋ እንዲያስቆርጥ የተዘጋጀው ተንቀሳቃሽ ምስል በተቃራኒው አማንያኑን በፅናት የሚያጀግንና ከበቀል ይልቅ ፍቅርና ይቅርታን ያሳየ ነበር። የግብፅ ቤተክርስቲያን የእንግሊዝኛ የምሕዋጸ-ርሑቅ(Television) ጣቢያ የሆነው ሲ.ዋይ.ሲ. ምሕዋጽ ከሰማዕታቱ ቤተሰብ ጋር ባደረገው ቆይታ የሳሚህ ሳላህ ባለቤት መርየም እንዲህ ትላለች “እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። በፍፁም አላዝንም። ክርስትናዬን አውቀዋለሁ። ባሌ በሰማዕትነት እንጂ በአደጋ አልሞተም። ከተጋባን ጀምሮ ስለ እግዚአብሔርና ስለሁሉም ነገር ይነግረኝ ነበር። ስለሱም እግዚአብሔርን እወደዋለሁ። በክርስትናችን እንኮራለን እንደ ክርስቲያን የሆነው ነገር አኩርቶናል። ጌታችን ክርስቶስ ስለኛ ተሰቅሏል፣ ደሙን አፍሷል ተገርፏል። እኛ ይህን ማድረግ ይከብደናል? ትንሽ የደም ጠብታ ስለሱ ያቅተናል? በፍፁም! ይህንን ማድረግም መቋቋምም እንችላለን። . . . እንደነሱ መሞትን እንመኛለን። ይህ ሞት አይደለም ሰማዕትነት ነው። ሳይገባኝ(“ባ” ጠብቆ ይነበብ) የሰማዕት ሚስት ሆኛለሁ። እግዚአብሔር ማንንም አይተውም። ጥቁር ለብሰን በቤታችን ብንቀመጥም ይህ የመጨረሻው አይደለም። በእነሱ እንኮራለን።”
የሰማዕቱ ናሲፍ ኢዛት ሚስት ደግሞ እንዲህ ትላለች “ለሱ (ለባሏ) መንገር የምፈልገው ‘ምን ያህል ዕድለኛ ነህ?…ልጃችን ስታድግ ትኮራብሃለች። አባቷ ሰማዕት እንደሆነ ትናገራለች። ኢዛት እኔም እኮራብሃለው የትም ስሄድ የሰማዕቱ ሚስት እንደሆንኩ እናገራለሁ” ስለ ገዳዮቹ ስትጠየቅ “በኢየሱስ እንደሚያምኑ አምናለሁ ስለሰሩት ኃጢያት እንደሚፀፀቱ አምናለሁ። ይቅር ብያቸዋለሁ አልጠላቸውም።”
የሰማዕቱ ታድሮስ ሚስትም “እሱ የእኔ ትልቁ ሰማዕት ነው፤ በሰማይ ስለእኛ እንዲጸልይ እጠይቀዋለሁ። እነሱንም እግዚአብሔር ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲመልሳቸው እጠይቃለሁ” ኢብስታም ኖሺይምም እንደሌሎቹ ሴቶች ባሏ እግዚአብሔር ወዳዘጋጀለት ወደ ተሻለው ቦታ እንደሄደና በዚህም እግዚአብሔርን እንደምታመሰግንና በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ባሏን እንዲያስባት እንደምትጠይቀው ከተናገረች በኋላ “እነሱ (ገዳዮቹ) ልባችንን በጥልቅ ጎድተውታል ግን እግዚአብሔር ይቅር ይበላቸው።…ባሌ በሰማዕትነቱ ወቅት ደስተኛ ነበ፤ እርሱ ክርስቶስንና ድንግል ማርያምን ሲያያቸው ነበር። በፊቱ ገነት ተከፍታ ነበር። ለምንም ግድ አልነበረውም ሁሌም ፈገግ ብሎ ነበር። መስቀሉን ስላልበጠሰና ስላልተሸነፈ እንኮራበታለን። እግዚአብሔርንም እናመሰግናለን እርሱ እኔንና የሰማዕቱን ልጆች ይጠብቃል።” ትላለች።
እንደ ቅብጣውያኑ ሁሉ በወርሃ ሚያዝያ በክርስቶስ ስላለች እምነታቸው ምስክር የሆኑትን ኢትዮጵያዊያንን ዜና ገድል በወቅታቸው ለመዘከር እንዲያበቃን እየተመኘን የዚህ ሳምንቱን ቤተክርስቲያን ሳምንታዊ በዚህ ቋጨን። የማርቲን ሞስባህ ሃያ አንዱ (the 21)፣ CYC tv ከሰማዕታቱ ቤተሰብ ጋር ያደረገው ቆይታ፣ አል አረቢያ ስለ ሰማዕታቱ ግድያ የዐይን ምስክር ምስክርነት ጥንቅርና የቮይስ ኦፍ ማርቲር፣ቫቲካን ኒውስና የሪዎተርስ ዘገባዎችን በምንጭነት ተጠቅመናል፡፡

