
ሰው በብዙ በሚፈልገውም ሆነ በማይፈልገው ምክንያት ከቤቱ ይወጣል። የሚቀበለው ሊፈልግ ይፈልጋል፤ የሚያስተናግደው ይሻል። “የእግዚአብሔር እንግዳ” ብሎ የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ እንዲያሳድሩት ሰዎችን ይለምናል። በዚህ ጊዜ ራሱን እግዚአብሔርን በአካል እንደተቀበሉት ቆጥረው በደስታ የሚያስተናግዱ አሉ። በአንጻሩ ደግሞ ቤቱን ለመሥራት የራሳቸው ብቻ አስተዋጽዖ እንጂ ቤቱ የእግዚአብሔር ስጦታ እንዳልሆነ በመቍጠርና የእግዚአብሔርንም ቸርነት ባለመረዳት “ማንም እንዳይመጣብኝ” የሚሉም አሉ። ሐዋርያው እንግዳ መቀበልን ዕለት ዕለት የሚያዘወትሩትን እያመሰገነ የማይቀበሉትን ደግሞ በረከት እንዳይቀርባቸው እያሳሰበ ያስተምረናል። እንግዳ መቀበል እንደሚገባ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ የእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። እግዚአብሔር አምላክ ለሊቀ ነቢያት ሙሴ የፋሲካን ሕግ በአስረዳበት ትእዛዝ “እንግዳ ሰውም በመካከላችኹ ቢቀመጥ ለእግዚአብሔርም ፋሲካን ሊያደርግ ቢወድ፟ አስቀድሞ ወንድ ዅሉ ይገረዝ፥ ከዚያም ወዲያ ይቅረብ፣ ያድርግም፤ እንደ አገር ልጅም ይኾናል፤ ያልተገረዘ ዅሉ ግን ከርሱ አይብላ።” (ዘፀ.፲፪፥፵፰) በማለት ስለ ፋሲካ ክብር “መገረዝ አለበት” ቢባልም ሊቀበሉት እንደሚገባ ግን ያስረዳናል።
ከዚህም በተጨማሪ እግዚአብሔር አምላካችን “በሀገራችሁ ውስጥ እንግዳ ከእናንተ ጋር ቢቀመጥ ግፍ አታድርጉበት። እናንተ በግብፅ ምድር እንግዶች ነበራችሁና፤ ወደ እናንተ የመጣ እንግዳ እንደ ሀገር ልጅ ይሁንላችሁ፤ እርሱን እንደ ራሳችሁ ውደዱት፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና” (ዘሌ.፲፱፥፴፫-፴፬) ሲል ለሕዝቡ ያስተላለፈውን አምላካዊ ትእዛዝ እናገኛለን። ይህ ሁሉ የሚያስረዳን ከጥንት ጀምሮ እንግዳ መቀበል አምላካዊ ትእዛዝ መሆኑን ነው። እንግዳ ይቀበሉ የነበሩ ሰዎች መላእክትን እንዲሁ እግዚአብሔርን በአንድነት በሦስትነቱ ለመቀበልና ከቤታቸው ለማስተናገድ በቅተዋል። እንግዳ የመቀበል መልካም ልማድ የነበረው ሎጥ መላእክቱን ከቤቱ አስተናግዷል። በቅዱስ መጽሐፍ ‘ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ደረሱ፤ ሎጥም በሰዶም ከተማ በር ተቀምጦ ነበር። ሎጥም ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ተነሣ፤ ፊቱንም ወደ ምድር ደፍቶ ሰገደላቸው፤ አላቸውም “ጌቶች ሆይ ወደ ባሪያችሁ ቤት ገብታችሁ እደሩ፤ እግራችሁንም ታጠቡ፤ ነገም ማልዳችሁ መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ።”
እነርሱም “በዐደባባዩ እናድራለን እንጂ አይሆም” አሉት። እርሱም ግድ አላቸው፤ ወደ እርሱም አቀኑ፤ ወደ ቤቱም ገቡ፤ ቂጣንም አስጋገረላቸው፤ እነርሱም በሉ።’ (ዘፍ.፲፱፥፩- ፫) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም “እንግዳ መቀበልንም አትርሱ፤ በዚህ ምክንያት መላእክትን በእንግድነት ለመቀበል የታደሉ አሉና።” (ዕብ.፲፫፥፩) በማለት የነገረን እንደ ሎጥ ያሉትን እንግዳ ወዳዶች ሊያመስግን ለእኛም ያላቸውን አርአያነት ሊያሳየን ነው። ምንጭ፦ ሐመር መጽሔት መልካም ዕለተ ሰንበት

