
ከ፭ መቶ ዓመታት በፊት አንድ አይሁዳዊ ወጣት ከስፔን ምርኮ ሸሽቶ ወደ ትውልድ ሀገሩ እስራኤል ይመለሳል ። ወደ መንደሩም በደረሰ ጊዜ አይሁድ ከገጠማቸው መከራ ይድኑ ዘንድ የሚድራሽ ረቢ(መምህር) የሆነው ይስሐቅ ሉርያ የአይሁድ ጉባኤን ሰብስቦ እየጸለየ ነበር ያገኘው ። ይህ ከምርኮ ያመለጠው ወጣትም በመካከለቸው ገብቶ እያለቀሰ ፈጣሪውን
” ጌታዬ ሆይ! ምንም የማውቀው ጸሎት የለኝም። የዕብራይስጥ ፊደላትን ብቻ እንጂ፤ ቋንቋውንም ቢሆን አላውቀውም፤ እባክህ ጌታ ሆይ እነዚህን ፊደላት ወስደህ ፥ አንተ የምትወደውን ፣ ለአንተ የሚገባውን ፣ ላንተ የሚሆነውን እጅግ ውብ ጸሎት አድርገህ አዘጋጀው” እያለ ከልቡ ያዝን ጀመር። ቀኑን ሙሉም የዕብራይስጥ አሌፋትን እየደጋገመ ሲጠራ ዋለ ። በዚያን ምሽት አይሁድ ከገጠማቸው ፈተና የዳኑት በዚህ ምስኪን ፣ ት።ሑትና የተሰበረ ልብ የነበረው ወጣት ጸሎት እንጂ ፥ በይስሐቅ ሉርያ፣ በደቀ መዛሙርቱና በአይሁድ ጉባኤ ጸሎት እንዳልነበር መምህሩ ይስሐቅ ሉርያ በራዕይ ተገለጠለት ። ረቢውም የትሑት ሰው ጸሎት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ተረዳ ። ሥጦታን ለወዳጁ ሊሰጥ ያሰበ ሰው ወዳጁ ምን እንደሚያስደስተው አስቀድሞ እንዲመረምር ፣ እንዲጠይቅ ፥ በፈጣሪው ዘንድ የተወደደ ሥጦታ የሚያቀርብም ሰው አምላኩን ምን ሊያስደስተው እንደሚችል አስቀድሞ ማወቅ ይኖርበታል። ስጦታን የሚቀበል ሰው የሚወደውን ስጦታ ገዝተው ሲሰጡትም እንዲወድ ፥ እግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ሲያቀርቡለት ይወዳል ።
“እግዚአብሔርን የሚያስደስተው ሥጦታ ምን ይሆን?” ብለን ብንጠይቅ ልበ አምላክ የተባለ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ አምላኩን “መሥዋዕትን ብትወድድስ በሰጠሁህ ነበር፤ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ደስ አያሰኝህም። የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበርውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።” በማለት እግዚአብሔር ከጸሎታችን በላይ ጸሎታችንን ያቀረብንበት በንስሐ የተሰበረ ልባችንን ፣ በትሕትና የተገነባ ሕይወታችንን እንደሚወድ ይነግረናል። ከቃየን ይልቅ የአቤልን መሥዋዕት፣ ከፈሪሳዊው ይልቅ የቀራጩን ጸሎት እግዚአብሔር የተቀበለው ሥጦታቸውን ሳይሆን ስጦታቸውን ያቀረቡበትን ልበ ትሕትናቸውን ስለተመለከተ ነው ። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ኦሪት ዘፍጥረትን በተረጎመበት ድርሳን “እግዚአብሔር የአቤልን የበግ መሥዋዕቱን የተመለከተው ከተቀባዩ ከእግዚአብሔር አንጻር ሲታይ መሥዋዕቱ በምንም መልኩ ከነውርና ነቀፋ ንጹሕ ስለነበር ሳይሆን ከመስዋዕቱ አቅራቢ በንጹሕ ልብ የቀረበ ስለ ነበር ነው።” በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ አሥራ ስምንት ላይ የሚገኘውን የቀራጩንና ፈሪሳዊ ታሪክ አንስቶ ባስተማረበት ድርሳንም የፈሪሳዊው ልመና ለምን ተቀባይነት እንዳላገኘ ሲገልጽ “ፈሪሳዊው ስለ ቀራጩ የተናገረው እውነት ቢሆንም ነገር ግን በጸሎቱ የራሱን ኃጢአት ከማሰብና ከማሳሰብ ይልቅ ወንድሙን እያማ ስለነበረ ወደ ቤቱ የተመለሰው የጾምን ዋጋ ሳያገኝ ባዶውን ነበር ” በማለት የትዕቢተኛ ሰው ጸሎት እንደሆነ ይነግረናል። የእኛስ ጸሎት?? በዲ/ን ዘአማኑኤል ገዛኸኝ

