ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ

ቅዱስ ያዕቆብ ቅዱሳን ከሆኑ ወላጆቹ ከቅዱስ አረጋዊ ዮሴፍ(የእመቤታችን ጠባቂ) እና የእመቤታችን አክስት ልጅ ከሆነችው ማርያም የተወለደ እድለኛ ቅዱስ ነው። ምክንያቱም በእመቤታችን እጅ ያደገ የጌታ ወንድም እየተባለ ይጠራ ነበር። አባቶች የጌታ  ወንድም መባሉ ለዚህም ምክንያት ሲያስቀምጡ ለ፴ ዓመታት ከጌታችን ጋር ማደጉ፣ የጌታ የሥጋ አያቱ (ቅድስት ሐና) የእኅት ልጅ በመሆኑ፣ የዮሴፍም የአንድ ቅድመ አያት ልጅ  በመሆኑ በማለት ያስቀምጡታል። የሥጋ  ወንድሞቹ ደግሞ ይሁዳ ፣ ዮሳ እና ሰሎሜ የተባለች እኅት ነበረችው። እናታቸው ማርያም ከሞተች በኋላም ተጎሳቁለው ነበር፤ በተለይ ቅዱስ ያዕቆብ ትንሽ ልጅ ስለነበር ያሳዝን ነበር። እመቤታችን ለአረጋዊ ዮሴፍ ተሰጥታ ከቤተ መቅደስ ወጥታ ወደ አረጋዊ ዮሴፍ ቤት ስትሄድ የአክስቷን ልጆች ሁኔታ አይታ አለቀሰች። በተለይ ያዕቆብን ስታይ ወዲያውኑ ማድጋ ይዛ ወደ ምንጭ ወረደች፤ ውኃውን አምጥታ ሕፃኑን አጠበች። የሰላም፣ የበረከት፣ የምሕረት እናት፤ የአምላክ እናት ገብታለችና የሀዘን ቤት ወደ ደስታ ተቀየረ። ጌታ ከመወለዱ በፊት ለ፱ወር ከ5ቀን እና ከተወለደ በኋላ ለ፪ ዓመታት ያዕቆብን ተንከባከበችው። ከዛ ጌታን ይዛ ተሰዳ ነበር። ከስደት መልስ ደግሞ ለ፳፭ ዓመታት አንድም ቀን እናቱ ትዝ ሳትለው በእንክብካቤ አድጓል። ቅዱስ  ያዕቆብ ጌታችን ሲያስተምር ተከተለው፤ ከሰባ ሁለቱ አርድዕትም ተቆጠረ። ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌልን ተማረ። ከዛም መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ወንጌልን አስተማረ፤ የኢየሩሳሌምም ጳጳስ ሆኖ አገለገለ።
ቅዱስ ያዕቆብ ለመጀመሪያ ጊዜ ከድንግል ማርያምና ከዮሐንስ ጋር ሆኖ  “የጌታን ትንሣኤ ሳላይ እህል አልቀምስም” በማለት ማክፈልን አስጀምሯል። በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት የሐዋርያት ሲኖዶሶችን በሊቀመንበርነት መራ። ከዚህ በኋላ ብዙ ተአምራትን ማድረግ ጀመረ። ብዙ አይሁዳውያንን ወደ ክርስትና መለስ። በመጨረሻው ዘመኑም የአይሁድ አለቆች ወደ  ቤቱ ተሰብስበው “የናዝሪቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ማነው ?የማንስ ልጅ ነዉ?” ሲሉ ጠየቁት። እነሱ የሚፈልጉትን ምላሽ ስላላገኙ በብስጭት ወደ መሬት ወረወሩት፤ እየተፈራረቁ በገድል የተቀጠቀጠን አካሉን ደበደቡት። አንዱ ግን በጭካኔ ከእንጨት በተሠራ ገንዳ የቅዱሱን ራስ ቀጠቀጠው። ሰማዕቱ ቅዱስ ያዕቆብም ወደ ወደደው ክርስቶስ ሐምሌ ፲፰ ቀን ሔደ። ቅዱሱ ሐዋርያ ቤቱን እንደ ቤተመቅደስ አበው ሐዋርያት ይጠቀሙበት ነበር። ቅዱሱ ሐዋርያ የሚያጎድፍ (ጥሉላት ምግብ ) ቀምሶ ፣ ፀጉሩን ተላጭቶ፣ ገላውን ታጥቦ አያውቅም። የያዕቆብ መልእክት የሚለውንም ባለ አምስት ምዕራፍ መጽሐፍ ጽፏል። ጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሙ ለመባል ካበቃው ቅዱሱ በረከትን ያድለን በምልጃው በረከቱ አይለየን ። ምንጭ፡ ስንክሳር ከመስከረም እስከ መጋቢት