የአርዮስ አሟሟት እና መንፈቀ አርዮሳውያን በቤተክርስቲያን ላይ ያደረጉት ዘመቻ

የኒቂያ ጉባኤ ከተፈጸመ በኋላ ቆስጠንጢኖስ አርዮስን በቦታ ወስኖ ባጋዘው በሁለት ዓመቱ የቆስጠንጢኖስ እኅት በአርዮስ እና በአውሳብዮስ ደጋፊዎች ተለምና አርዮስ ከውግዘቱ እንዲፈታ ቆስጠንጢኖስን ለመነችው፡፡ ቆስጠንጢኖስም ወደ ቤተክርስቲያን እንዲመለስለት አዘዘ፡፡

የአርዮስ መመለስ በቤተክርስቲያን ላይ ችግር አላመጣም፡፡ ዋናው ችግር በቤተክርስቲያን ሲኖዶስ የተወሰነው ውሳኔ በንጉሡ አለመከበሩ ነው፡፡ ይህም ድፍረት ቤተክርስቲያንን እና የቁስንጥንያ ቤተመንግሥትን አጋጭቷል፡፡ አርዮስና ደጋፊዎቹ የኒቂያ ጉባኤ ያስተላለፈውን ውሳኔ በግልጥ ሊቃወሙ ባይችሉም ወደ ቤተመንግሥቱ ጠጋ ብለው በጉባኤው ተስማሚነት የነበራቸውን ሰዎች ስም በማጥፋት ከንጉሡ ማጣላትና ማሳደድ ጀመሩ፡፡

ለምሳሌ ጉባኤውን በሊቀመንበርነት የመራው ኤዎስጣቴዎስ በ፫፻፴ ዓ.ም. የአንጾኪያው መንበር በንጉሡ በቆስጠንጢኖስ ትዕዛዝ እንዲለቅ ተደረገ፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የቆስጠንጢኖስ እናት ዕሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም ስትሔድ በአንጾኪያ አልፋ ነበርና “መንግሥታዊ  አቀባበል አላደረገላትም”፡፡ በማለት አርዮሳውያን ነገር ሰርተው ነው ፡፡ ብዙዎች ኦርቶዶክሳውያን በውስጥ ለውስጥ አድማ ይህን የመሠለ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ብዙ ግፍ ከተፈጸመባቸው ኦርቶዶክሳውያን አባቶች አንዱ አንጋፋው ቅዱስ አትናቴዎስ ነው፡፡ አትናቴዎስና ቆስጠንጢኖስ ሆድና ጀርባ ሲሆኑ አትናቴዎስን ለመክሰስ ለወንጀለኞች ቀላል ነበር፡፡

አርዮሳውያን  አትናቴዎስን በኃጢአት ከሰሱት።
  ፩. በነፍሰ ገዳይነት፣
  ፪. በድብድብ ወንጀል፣
  ፫. በንጉሡ ላይ ለመጡ ሽፍቶች ስንቅና ትጥቅ አቀብሏል፣
  ፬. በዝሙት አግኝተነዋል፡፡


በማለት ከሰሱት፤ ጉዳዩ በጉባኤ እንዲታይ  ተደረገ፡፡ጉባኤው ተጀምሮ የአትናቴዎስ ክሶች እየተነበቡ የእምነት ክህደት ቃል ይስጥ ተባለ፡፡
ቅዱስ አትናቴዎስ የተከሰሰባቸውን ክሶች እንዳላደረገ በማስረጃ  አስደግፎ ተናገረ፡፡ ሁሉም ውሸት እንደሆነ ተናገረ፡፡ ከሳሾቹም አፈሩ፤ ንጉሡ ግን በግል ቂም ተነሳስቶ ወደ ትሬቬሬ አስጋዘው፡፡ በመጨረሻም ቅዱስ አትናቴዎስ ለ፵፯ ዓመታት በፓትርያሪክነት፣ ለ፲፬ ዓመታት በስደት አሳልፎ በ፸፭ ዓመቱ ግንቦት ፯ ቀን በ፫፸፬ ዓ.ም. ዐረፈ።

ምንጭ፦ የቤተክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ.