
ወርኀ የካቲት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቅዱሳን ፓትርያሪኮች አገልግሎት ላይ ልዩ ትዝታን ከሰነዱ ወሮች መካከል አንዱ ነው። በያዝነው ወር በ፳፬ኛው ቀን ከተከበረው ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዓለ ሲመትና በማግስቱ ታስቦ ከዋለው ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቀርዮስ ዜና-ዕረፍተ ተጨማሪ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት ደርግ በግፍ ከመንበራቸው የተነሱትም በዚህ የየካቲት ወር ፱ኛው ቀን ላይ ነበር። ይህ ዕለት አቡነ ቴዎፍሎስን ከመንበረ ፕትርክና ከማውረዱ በተጨማሪ የያኔው ጳጳስና በኋላም ፭ኛው ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከሌሎች ጳጳሳት ጋር ለእስር የተዳረጉበት ነው። በዛሬው ቤተክርስቲያን ሳምንታዊ ከእነዚህ ሁሉ የየካቲት መዋዕሎች መካከል በዕለተ ሰኞ የተከበረውን ፲፪ኛ ዓመት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን የ፲፪ ዓመታት ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዳስሳለን። በዓለ ሲመት ክህነታዊት በሆነችው ቤተክርስቲያን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ቀን ነው። ለልጆቿ መንፈሳዊ አገልግሎትን ይሰጡ ዘንድ በሐዋርያዊ ቅብብሎሽ የተጠበቀውን የእረኝነት አገልግሎት የሚያስቀጥሉ አበውን የምታገኝበት ስለሆነ ቤተክርስቲያን በዓሉን በልዩ ሁኔታ ታከብረዋለች። የሚሾሙበት ዕለትም በዕለተ ሰንበተ ክርስቲያን እንዲሆን በፍትህ መንፈሳዊ መደንገጓ በዓለ ሲመት ምን ያህል ታላቅ መሆኑን ያሳያል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ እንደሚያመላክተው ረጅሙን ዘመኗን በግብፅ ቤተክርስቲያን ሥር እንደሚገኝ አኅጉረ ስብከት ከእስክንድርያ በሚመጡ ሊቃነ ጳጳሳት ስትተደዳር ቆይታለች። ኢትዮጵያዊያን አባቶችና ነገሥታት ቋንቋና ባህላቸው የሚገባቸው ኢትዮጵያዊ ሊቃነ ጳጳሳትን ለማሾም ብዙ ደክመዋል። ከዘመነ ዛጉዌ ጀምሮ ከግብፅ መንግሥትና እስክንድርያ ቤተክርስቲያን ጋር የተደረጉ ተደጋጋሚ ውይይቶች ፍሬ አፍርቶ በ፲፱፻፵ ዓ.ም. የራሷ ተወላጅ ሊቃነ ጳጳሳት፣ በ፲፱፻፶፩ዓ.ም. ደግሞ የራሷን መንበረ ፓትርያርክ ለመመሥረት ችላለች። እንግዲህ ዛሬ ዜና መዋዕላቸውን የምናነሳቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከቅዱሳን ፓትርያርኮች አቡነ ባስልዮስ፣ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ አቡነ መርቆርዮስና አቡነ ጳውሎስ ቀጥሎ ፮ኛው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የመንበረ ማርቆስ ወራሴ፣ የአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃኗ የአክሱም ሊቀጳጳስና በተክለሃይማኖት መንበር ዕጨጌ ናቸው። በ፲፱፻፴፬ ዓ.ም. በትግራይ አጋመ አውራጃ የተወለዱት የቀድሞው ተክለ ማርያም አሥራት ከወቅቱ የአስመራው ሊቀጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ ድቁናን ከብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ደግሞ የቁምስና ማዕረግ ተቀብለዋል።
ቅዱስነታቸው ለአገልግሎትና ትምህርት ወደ የተለያዩ አድባራትና ገዳማት የተዘዋወሩ ሲሆን በአዲስ አበባ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት አቡነ ቀሲስና ምክትል ፀሐፊ በመሆን አገልግለዋል። ተኻራሚውና መናኒው ፓትርያርክ አቡነ ተክለሃይማኖት በጥር ፱፫ በ፲፱፻፸፰ ዓ.ም. ባካሄዱት ሲመተ ጵጵስና መምህር ተክለ ማርያም አሥራትን ብፁዕ አቡነ ማትያስ ብለው የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ አድርገው ሾመዋቸዋል። ቅዱስነታቸው በኢየሩሳሌም፣ በሰሜን አሜሪካ በተለይም በዩናይትድ ስቴት ከፍተኛ አባታዊ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። በተለይም በ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. የተከሰተው የሲኖዶስ መከፈል በምዕመናንና በአገልጋዮች ዘንድ ሥር እንዳይሰድ የማቀራረብ ሚናን ይጫወቱ ስለነበር ከሁለቱም ሲኖዶስ ውጪ እንዳሉ ገለልተኛ ሊቀጳጳስ ተብለው እስከመቆጠር ደርሰው ነበር። በ፳፱፬ ዓ.ም. ነሐሴ የተሰማውን የ፭ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ዜና ዕረፍት ተከትሎ በተካሄደ ምርጫ ፮ኛ ሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን መንበረ ፕትርክና የተረከቡት አቡነ ማትያስ ላለፉት ፲፪ ዓመታት የመንጋው እረኛ በመሆን አገልግለዋል። የቅዱስ ፓትርያርኩ ዘመነ ፕትርክና በመከራ የተፈተነ ነበር። ገና በተሾሙ ቅርብ ዓመታት ኢትዮጵያዊያንን ስደተኞች መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በተለይም በአይ.ኤስ.አይ.ኤስ. የታረዱ ፴ ኦርቶዶክሳዊያን ዘመነ ፕትርክናቸውን የሚፈትን ነበር። ከዚህ ባሻገር ከ፳፻፰ ዓ.ም. ጀምሮ በመላው ሃገሪቱ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች መበራከትና ትኩረቱን ኦርቶዶክሳውያንና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ ማድረጉ ሌላኛው ፈታኝ ጉዳይ ነበር።ሁሉም ክልሎች ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ኢትዮጵያ በሰላም ሰባኪዋ ቤተክርስቲያንና በልጆቿ ደም ታጥባለች። ማንነትን መሠረት ካደረጉ ጥቃቶች መለስ ስንል በሃገሪቱ የሰሜኑ ክፍል የተጀመረውና ቀስ በቀስ ወደ ተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተዛመተው በመንግስትና ታጣቂ ኃይሎች መካከል የተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነትም ለዘመናቸው መራር መልክን የሰጠ ክስተት ነው።
ቅዱስነታቸው በመልእክቶቻቸው ደጋግመው የሚያነሷቸው የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት፣ ፆታዊ ጥቃት፣ የሰብዓዊ መብቶች መሸራረፍ፣ ኢሰብአዊ ጨካኝ ድርጊቶችና ረሃብም ሌሎች ዘርፎች ናቸው። የኮሮና ወረርሺኝ ያመጣው ችግር ሳይረሳ። በውስጣዊ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥም እየጠፋ የመጣው ፈሪሃ እግዚአብሔር፣ የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ጎጠኝነት ዘመናቸውን የፈተነ ተግባር ነበር። ራሳቸውን የጎጃም ሃይማኖት ብለው የሚጠሩት የቅባት ሰዎች በጎቃ ኪዳነምሕረት ከመሠረቱት መንበር ጀምሮ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ የማያቃቸውና ራሳቸውን መንበረ ጴጥሮስ፣ መንበረ ሰላማ፣ መንበረ ሃርቤ እያሉ የሚጠሩ የጎጥ ሲኖዶሶች የተፈለፈሉትም በቅዱስነታቸው ዘመነ ፕትርክና ነው። በእኒህ ሁሉ ችግሮች ቢታጀብም ዘመናቸው ዛሬም እግዚአብሔር ከቤተክርስቲያን ጋር እንዳለ በሚያሳዩ በርካታ ጠብቆቶች የተከበቡ መሆናቸው የሚዘነጋ አይደለም። ከምንም በላይ በልዩነት ለዘመናት ተከፋፍለው የነበሩ ብፁዓን አበው ወደ አንድነት መጥተው ቅዱስነታቸው ከአራተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ጋር በአንድነት ቤተክርስቲያንን ለመምራት መታደላቸው እጅጉን የሚከበር ታላቅ ስኬት ነው። ከዚህ ባሻገር ቤተክርስቲያን የቴሌቪዥን ጣቢያ እንዲኖራት ማስቻል፣ በደርግ ዘመን የተወረሱ በርካታ ንብረቶቿን ማስመለስ፣ የቤተክርስቲያንን በዓለም ደረጃ ያላትን ተደራሽነት መጨመር፣ በዐረብ ሀገራት የቤተክርስቲያን ይዞታ ማግኘት፣ የሃገረስብከቶችን ቁጥር ከነበረበት ከፍ እንዲል ማድረግ፣ ቃለ-ዓዋዲን ማሻሻል፣ ከአኀት አብያተክርስቲያናት ጋር የነበረን ግንኙነት በተለይም ከኤርትራ ቤተክርስቲያን ጋር የነበረንን ግንኙነት ማደስ፣ ከምሥራቅ ኦርቶዶክስና ከካቶሊክ አብያተክርስቲያናት ጋር የሚደረጉ የነገረ መለኮት ውይይቶችን እንደገና ለማስጀመር የሚደረገውን ጥረት መደገፍና የመሳሰሉ ስኬቶችን ዘመነ ፕትርክናቸው አስገኝቶልናል። ሰላም ከቅዱስነታቸው አንደበት የማትጠፋ ቃል መሆኗን ከሚሰጧቸው ቃለ መጠይቆች፣ የበዓላትና የቅዱስ ሲኖዶስ መልእክቶቻቸው መረዳት ይቻላል። ምንም እንኳን ሰሚ ለማግኘት መታደላቸውን ማረጋገጥ ቢከብድም ከዓለም መንግስታት ጀምሮ በኢትዮጵያ ያሉ የፌደራልና የክልል መንግስታት፣ ታጣቂ ኃይሎች፣ ምሁራንና የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ምእመናንና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሰላም ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ ሳያነሱ አያልፉም። በዘንድሮው በዓለ ሲመታቸውም ላይ አፅንዖት የሰጡት ስለሰላም አስፈላጊነት ነበር። የቅዱስነታቸው የሰላም ጥሪ ፍሬ ያፈራ ይሆን? ይሄ ሁላችንም ራሳችንን የምንጠይቅበትና በቀጣይ ዘመናቶቻቸው የሚመለስ ጥያቄ ነው። የዛሬውን ቤተክርስቲያን ሳምንታዊ አምዳችንን የምንቋጨው ለቅዱስነታቸው ረጅምና ያማረ የአገልግሎት ዘመን በመመኘት ነው። የቅዱሳን አባቶቻችን ድል የማትነሳ ሃይማኖታቸው ከእኛ ጋር ትሁን። አሜን!

