አባ መከራዊ

ይህ አባት በግብጽ ደቡብ ከምትገኝ ከእስሙናይን ከታላላቆቿ ወገን ነው። ለኒቅዮስ ከተማም ኤጲስቆጶስነት ተሾመ።
የስደትና የመከራ ወራት በሆነ ጊዜም ስሙ ዮፋንስ የሚባል መኰንን ወደዚያች አገር ከንጉሥ ተልኮ መጣ። የክርስቲያን ወገኖችንም ያሠቃይ ዘንድ ጀመረ። የዚህንም የቅዱስ ኤጲስቆጶስ አባ መከራዊን ዜና ሰምቶ ወደርሱ ያመጡት ዘንድ ወታደሮቹን ላከ። እርሱም ወደ መኰንኑ ከመሔዱ በፊት ወደ ቅዱስ መሠዊያው ገባ፤ እጆቹንም ዘርግቶ ጸለየ። ንዋየ ቅዱሳቱንና የመቀደሻውን ልብሶች በመቅደሱ ውስጥ አኖረ።
ከዚያም በኋላ ቤተ ክርስቲያኑን ይጠብቅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ፈጽሞ ማለደ። በላያችሁ የፀሐይ ብርሃን ይወጣ ዘንድ ያልተዋችሁ የጽዮን ልጅ ደጆች ሆይ “ለእግዚአብሔር ቤት ማገልገያ የሆነ ነዋየ ቅድሳቱን ጠብቁ” እያለ ታላቅ ልቅሶ በማልቀስ ጮኸ። ከዚህም በኋላ ከንጉሥ መልክተኞች ጋራ ወጥቶ ሔደ፤ ወደ መኰንኑም ቀረበ። ስለ ስሙና ስለ አገሩ ስም፣ ስለ ሥራውም ጠየቀው። የኒቅዮስ ከተማ ኤጲስቆጶስ እንደሆነም ባወቀ ጊዜ እንዲገርፉትና እንዲያጐሳቁሉት ብርና እርሳስም አቅልጠው በአፉ እንዲጨምሩ አዘዘ።
እግዚአብሔርም የሚያጸናውና የሚያስታግሠው ሆነ። ያለ ጉዳትም በጤንነት መልሶ ያነሣው ነበር። ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ ገዥ ወደ ኄርሜኔዎስ ሰደደው። እርሱም ቅዱስ አባ መከራዊን እንዲአሥሩት አዘዘ። እግዚአብሔርም በእጆቹ ብዙዎች ድንቆች ተአምራትን አደረገ። ከተአምራቱም አንዱ ለአቅፋስ ከተማ ሹም ለሆነ ለዮልዮስ ስሙ አውካሪስጦስ የሚባል እጆቹና እግሮቹ ሽባ የሆነ ልጅ ነበረው። አባ መከራዊም በላዩ ጸለየ፤ ከደዌውም አዳነው። ከዚህ በኋላ በዮልዮስ ቤት ቀድሶ ለአማንያን ቅዱስ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው። ስለ ሥጋውም እንዲዐስብና ገድሉንም እንዲጽፍለት ከዮልዮስ ጋራ ስምምነት አደረገ። መኰንኑ ኄርሜኔዎስም አባ መከራዊ ስለ አደረጋቸው አስደናቂ ተአምራት በሰማ ጊዜ በተለያየ ሥቃይ ያሠቃዩት ዘንድ አዘዘ።
ሕዋሳቱ እስኪቆራረጡ በመንኰራኵሮች ውስጥ አስገብተው አሠቃዩት። ለነጣቂዎች አንበሶችም ጣሉት፣ በባሕርም አሠጠሙት፣ በእሳት ምድጃ ውሰጥም ጨመሩት። ቅዱስ አባ መከራዊ በሥቃዩ ሁሉ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል የሚታገሥና የሚጸና ሆነ። ጌታም ያለ ጉዳት መልሶ በጤንነት ያስነሣው ነበር። የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ቤተ ክርስቲያን የምታገለግል አንዲት ድንግል እኅትም ነበረችው። ሁለት ወንድሞችም ነበሩት፤ የአንደኛው ስም ዮሐንስ የሁለተኛውም ይስሐቅ ይባላል። በእሥር ቤትም ሳለ ወደርሱ መጡ። “አንተ ስለ አባታችን ፈንታ አባት ሆነኽን ነበር፤ እነሆ የሙት ልጆች እንሆን ዘንድ ትተኸን ትሔዳለህ” እያሉ በፊቱ አለቀሱ። እርሱም አጽናንቶ ወደ ቤቶቻቸው አሰናበታቸው። ዮልዮስም “የዚህን ሽማግሌ ሞት በጽሑፍ እዘዝ ከእርሱም ታርፋለህ” ብሎ መኰንኑን መከረው። ቃሉንም ተቀብሎ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ ። በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነትን አክሊል ተቀዳጀ። ዮልዮስም የቅዱስ አባ መከራዊን ሥጋ ወስዶ በከበሩ በወርቅ ልብሶች ገነዘው፣ በደረቱም ላይ የወርቅ መስቀል አደረገ፣ ወደ ሀገሩ ወደ ኒቅዮስም ከአገልጋዮቹ ጋራ ሰደደው። መልካም ነፋስም ሆኖላቸው፤ መርከቢቱ ፈጥና ሔደች። በከተማውም በር አንጻር ደርሳ ቆመች። ቀዛፊዎችም ሊያንቀሳቅሱዋት ፈልገው ነበር ግን አልተቻላቸውም። አብዝተው በደከሙም ጊዜ ሥጋዬ በውስጡ እንዲኖር እግዚአብሔር የፈቀደው ቦታ ይህ ነው የሚል ቃል ከበድኑ ወጣ። ይህንንም ለሀገር ሰዎች ነገሩአቸው፤ የሰሌን ዝንጣፊም እየያዙ ወደርሱ መጡ። በሀገራቸውም ውስጥ እርሱ በመረጣት ቦታ እስከ አኖሩት ድረስ በታላቅ ክብር ተሸክመው ወሰዱት። መላው የሕይወቱ ዘመን አንድ መቶ ሠላሳ አንድ ሆነ። መጻሕፍትን እስከተማረ ድረስ ስምንት ዓመት፣ በዲቁና ሹመት ሃያ አራት ዓመት፣ ከዚያም ቅስና ተሹሞ በቅስና አገልገሎት ሠላሳ ዓመት ኖረ። ከዚያም በኋላ ኤጲስቆጶስ ሁኖ ተሾመ። በዚህም ስልሳ ዘጠኝ ዓመት ኖሮ መልካም ተጋድሎውን ፈጸመ። የሕይወት አክሊልንም ከክብር ባለቤት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ተቀበለ። 
ጸሎቱ፣ በረከቱም  ለዘለዓለም ከእኛ ጋራ ይኑር። አሜን!ምንጭ፡- ስንክሳር ከመስከረም እስከ መጋቢት