
፩. ተዋሕዶ የሚለው ቃል የተገኘው በዚህ ጉባኤ ነው።
፪. በአማን ድንግል ወላዲተ አምላክ (የእውነት እመቤታችን ድንግል ማርያም ወላዲተ እግዚአብሔር መሆንኗን)
የጉባኤ ኤፌሶን ቀኖናዎች
፩. “በቤተ ክርስቲያናዊም ሆነ በሥጋዊ ምክንያት ከቅዱስ ሲኖዶስ ልዩነት ያላቸው ሰዎች የጉባኤውን ድንጋጌ ችላ ማለት የለባቸውም (ውሳኔውን ማክበር ይኖርባቸዋል)፡፡ በዚህም ለቅዱስነትዎና ለተወዳጅነትዎ የምናሳውቀው የአንድ ሀገረ ስብከት ርእሰ ኤጲስ ቆጶሳት ለዓለም ዐቀፋዊው ሲኖዶስ ውሳኔ የማይታዘዝ ሆኖ የእምቢተኛነት ጉባኤ ቢሰበስብና ተቃራኒ ውሳኔ ቢያሳልፍ ወይም ከሌሎች ተቃራኒዎች ከሆኑ ውሳኔዎች ጋር ቢስማማ ከአሁን ጀምሮ በጉባኤው ውሳኔ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ተባሮ የተለየ በመሆኑ በሀገረ ስብከቱ ኤጲስ ቆጶሳት ላይ ምንም ውሳኔ ሊያስተላልፍ አይችልም። ቀጥተኛ አስተያየት ያላቸው የሀገረ ስብከቱ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት ከክህነት ደረጃው ያባርሩት ዘንድ ጉባኤው ወክሎአቸዋል፡፡”
፪. የአንዳንድ ሀገረ ስብከቶች ኤጲስ ቆጶሳት ከቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ዘግይተው ወደ እምቢተኛነት ካዘነበሉ ወይም ንስጥሮስ ተወግዞ ከተለየ በኋላ ከመናፍቃን ጋር አንድ ግንባር ለመፍጠር የተስማሙ ከሆነ እንደዚህ ያሉት ሰዎች ከክህነት መዓርጋቸው መሻር አለባቸው ብሎ ጉባኤው ወስኖአል።
፫. ከአስተሳሰባቸው ቀናነት የተነሣ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በንስጥሮስ ወይም በተከታዮቹ አማካኝነት ከክህነታቸው የተሻሩ ከሆኑ ጉባኤው በክህነት ደረጃቸው እንዲቀጥሉ ፈርዶላቸዋል። ዓለም ዐቀፋዊና ኦርቶዶክሳዊ በሆነው በቅዱስ ሲኖዶስ የእምነት ቀኖና ጸንተው ለሚገኙ ካህናት ሁሉ የምናስተላልፈው ትእዛዝ በውግዘት ለተለዩት ኤጲስ ቆጶሳት እንዳይታዘዙ ነው።
፬. ከካህናት መካከል እምቢተኞች ሆነው የንስጥሮስንና የካላስትዮስን የክሕደት ትምህርት በመቀበል ሕዝብም ያንን የክሕደት ትምህርት እንዲቀበል የሚያደርጉ ቢኖሩ ትክክለኛ በሆነው የቅዱስ ሲኖዶስ ፍርድ እንደተለዩ ይቆጠራሉ።
፭. የክህነት ተግባሮችን እንዳያከናውኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ወይም በኤጲስቆጶሳት ለተከለከሉ ሰዎች ንስጥሮስና ተከታዮቹ በግዴለሽነት በክህነት ደረጃ ኅብረት እንዲኖሩ ቢያደርጉአቸው እነዚህን ሰዎች በውግዘት እንዲኖሩ ፈርደንባቸዋል።
፮. በኤፌሶን የተሰበሰበው ቅዱስ ሲኖዶስ ከመዘገበው ውሳኔ ተቃራኒ የሆነ ድርጊትን ለማድረግ የሚፈልጉ ቢኖሩ ኤጲስ ቆጶሳት ወይም ቀሳውስት ከሆነ ከክህነት መዓርጋቸው ይሻሩ፤ ተራ ምዕመን ቢሆን ግን ይለይ፡፡
፯. የሃይማኖትን ቀኖና በሚመለከት፣ ማንም ቢሆን በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ በኒቅያ የተሰበሰቡት ቅዱሳን አባቶች ከወሰኑት እምነት የተለየ ትምህርት መከታተል፣ መጻፍና መድረስ አይገባውም። ወደ አረማዊነት፣ ወደ አይሁዳዊነት፤ ወይም ወደ ሌላ የመናፍቃን ትምህርት ለመመለስ ለሚፈልጉ ሰዎች የእነዚያን እምነት ለማሳወቅ በድፍረት ድርሰት የሚያዘጋጁ ካሉ ኤጲስ ቆጶሳት ቢሆኑ ከኤጲስ ቆጶስነት መዓርጋቸው ካህናት ቢሆኑ ከክህነታቸው ይሻሩ። ምእመናን ቢሆኑ ከኅብረቱ ይለዩ፡፡ ኤጲስ ቆጶሳት፣ ካህናት ወይም ሌሎች ምእመናን ስለ እግዚእብሔር ወልድ ሥጋ መልበስ የንስጥሮስን ትምህርት በመመርኰዝ ቄስ ካሪሲዩስ ያዘጋጀውን የክሕደት ትምህርት የተቀበሉ ወይም ያስተማሩ በዚህ ዓለም-ዐቀፋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ ፍርድ ኤጲስ ቆጶስ ቢሆን ከሹመቱ ተሽሮ በውግዘት ይለይ፤ ካህን ሲሆን ከክህነት ደረጃው ይሻር ተራ ምእመን ቢሆን ከኅብረቱ ይለይ።
፱. በኤጲስ ቆጶስነት ተባባሪአችንና የእግዚአብሔር ወዳጅ የቆጵሮሱ ኤጲስ ቆጶስ አርጌኖስ፣ እንዲሁም አብረውት የመጡት የእግዚአብሔር ወዳጆች ዘይኑንና ኢዩዋግሩስ ከቤተ ክርስቲያን ደንብና ከቅዱሳን ሐዋርያት ቀኖና የተለየ ድርጊት መፈጸሙን ነግረውናል። የአጠቃላዩ ችግር የበለጠ ጉዳት እንዳያመጣ ከፍተኛ እንክብካቤ የሚያስፈልገው ሲሆን ከቆጵሮስ የመጡት ሁላቸውም በቃልና በጽሑፍ እንደገለጹት የአንጾኪያው ኤጲስ ቆጶስ ከአሁን በፊት በቆጵሮስ ጉዳይ ገብቶ የማያውቅ ከሆነ በንጹሓን አባቶች ቀኖና እና ቀድሞ በነበረው ልማድ መሠረት በቅድስት የቆጵሮስ ቤተክርስቲያንና በኃላፊዎችዋ ላይ ምንም ግራ መጋባትና ቅሚያ እንዳይደረግ፣ እነርሱም ኤጲስ ቆጶሳትንና መሪዎቻቸውን ሁሉ በራሳቸው ይሠይሙ ። ይህም ጉዳይ በሌሎች ሀገረ ስብከቶች ሁሉ ይጠበቅ፡፡ ማንኛውም የእግዚአብሔር ወዳጅ የሆነ ኤጲስ ቆጶስ የእርሱ ተከታይ ባልነበረ ወይም እርሱ በተካው ኤጲስ ቆጶስ ሥር ያልነበረውን ሀገረ ስብከት በሥሩ ለማድረግ መሞከር የለበትም፡፡ የሌላውን ሀገረ ስብከት በድፍረት በቅሚያ መልክ በሥልጣኑ ሥር ያደረገ ካለ ያባቶችን ቀኖና ላለመቃወም ይመልስ፡፡ ማንኛውም ሀገረ ስብከት የተቀማውና ከቀድሞ ጀምሮ የነበረው መብቱ ይመለስለት ዘንድ ዓለም-ዐቀፋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል።
ምንጭ፡- የቤተክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ (አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ)

