ማራናታ: ዳግመ ይመፅዕ በስብሐት

ጥንታዊቷና ብቸኛዋ የክርስቶስ አካሉ የሆነችው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በቅዳሴዋ ላይ ከምታውጀውና ከምትመሠክረው ምስክርነት አንዱ የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምፅዓት ነው። “…ቅዱስ እግዚአብሔር፤ ቅዱስ ኃያል፤ ቅዱስ ህያው ዘኢይመውት። ዘተንሥአ እም ሙታን አመ ሣልሥት ዕለት፤ ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት፤ ወነበረ በየማነ አቡሁ፤ ዳግም ይመፅዕ በስብሐት፤ ተሰአለነ እግዚኦ…።” / “ቅዱስ እግዚአብሔር፤ ቅዱስ ኃያል፣፤ ቅዱስ የማይሞት። በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሳ፤ በምሥጋና ወደ ሰማያት ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ፤ ዳግመኛም በምሥጋና ይመጣል…።” ሠላም ውድ የእግዚአብሔር ምስሌነ ቤተሰቦች! በቤተክርስቲያን ሣምንታዊ ዐምዳችን ከፊታችን የምንቀበለውን የደብረ ዘይት ሳምንት ምክንያት በማድረግ ከክርስቶስ ዳግም ምፅዓት ጋር የተያያዙ ዐሳቦችንና ክስተቶችን እንዳስሳለን አብራችሁን ሁኑ። መጽሐፏን አንብቦና መርምሮ በሕይወት፣ በእውነትና በእውቀት ቤተክርስቲያንን የወደዳት ቅዱስ ያሬድ ትምህርቷን ለየወቅቶቹ በደለደለበት ድጓው የጌታችንን ዳግም መምጣት በእኩለ ፆመ እግዚእ እና በወርሐ ጳጉሜ እንዲታሰብ ሥርዓት ሠርቶልናል። በእነዚህ ወቅቶች አብዝተን እንድናስበው አድርጎናል እንጂ ቤተክርስቲያን የጌታ መምጣት ለቅፅበት እንኳን ዘንግታው አታውቅም።  ራሱ ባስተማራት ጸሎት “መንግሥትህ ትምጣ” እያለች የወርቅ ልብስን ተጎናፅፋ በቀኙ የምትቆምበትን ቀን ትናፍቃለች። ዳግመኛም በአዋጇ “ንዜኑ ሞተከ እግዚኦ፣
ወትንሣኤከ ቅድስት፣
ነአምን ዕርገተከ፣
ወዳግመ ምፅአትከ….።” (“ጌታችን ሆይ ሞትህንና ቅድስት የምትሆን ትንሳሣህን እንናገራለን፤ ዕርገትህንና ዳግም መምጣትህንም እናምናለን” በጸሎተ ሃይማኖቷ ላይም  “…. ዳግመኛም በምሥጋና ይመለሳል፣ በህያዋንና በሙታን ለመፍረድ…… የሙታንን መነሣት ተስፋ እናደርጋለን….” በማለት ነገረ ምፅዐቱ በፍቅር የምትጠብቀው እምነቷና ተስፋዋ መሆኑን ታነሳለች። በእርግጥ የክርስቶስ ዳግም መምጣት ለቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ተጠባቂ ነገር ነው። ምንም እንኳን ይመጣል የሚሉበት ሁኔታና ምክንያት ቢለያይም በዓለም ላይ ያሉ ከሦስት ቢሊዮን በላይ የሆኑ የክርስትና፣ የእስልምና፣ የይኾዋ ምስክሮችና ልዩ ልዩ እምነቶች የክርስቶስን ዳግም መምጣት ይጠባበቃሉ። ይህንን መሠረት በማድረግ በርካቶች በተቀነባበሩ ሤራዎችና ሀሰተኛ ትንቢቶች ክርስቶስ በዚህ ቀን ይመጣል ሲሉ ተደምጠዋል። የክርስቶስ ዳግም ምፅዓት ግምቶችና ሃሳዊ ትንቢቶች መነገር የጀመሩት ክርስቶስ ካረገ ፵ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ነበር። በ፸ ዓ.ም. ከኢየሩሳሌም መጥፋት ጋር ተያይዞ የክርስቶስ ዳግም ምፅዓት መድረሱን ያወጁ ብዙዎች ነበሩ። በ፭፻ ዓ.ም. በተመሳሳይ ክርስቶስ እንደሚመጣ ያስተማሩ ነበሩ። የፍሎሪው (የጣልያን) እያቄም የክርስቶስ ዳግም ምፅዓት በ፲፪፻፷፰ ዓ.ም. እንደሚከናወን ሲተነብይ ጆን ዴ ሪኩታሊድ እስከ ፲፫፻፸ ዓ.ም. ጌታ እንደሚመጣ ተንብዮ ነበር። ኢማኑኤል ስዊዲንበርግ የተሰኘው ሀሰተኛ ነብይ ኢየሱስ በ፲፯፻፶፯ እንደሚመጣ የተነበየ ሲሆን ይህ ትንቢቱ ሲከሽፍበት ጊዜውን አሻሽሎ በ፲፯፻፸ ዓ.ም. የክርስቶስን መምጣት “በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ ይመጣል” ሲል አሻሽሎታል ምንም እንኳን ይሄም ቅዥት ቢሆንበትም። የክርስቶስ መምጣት ዙሪያ የተደረጉ ትንቢቶች ብዙ ቢሆኑም የይሖዋ ምስክሮች አስገራሚ ትንቢት ነው። የቤተ እምነቱ መሥራች ቻርለስ ራስል የክርስቶስ መምጣት በ፲፱፻፲፬ ዓ.ም. እንደሚሆን የተናገረ ሲሆን እርሱም እንደቢጤዎቹ ትንቢቱ ሳይሰምርለት ሲቀር ዝም ከመሰኘት ወይም ሌላ ቀን ከመተንበይ ይልቅ የመጨረሻው ቀን ቅዱሳን ወደ ላይ መነጠቃቸውንና የጌታ ምፅዓት መከናወኑን በ “ካፈርሁ አይመልሰኝ” ትምህርቱ ቀጥሎበት ነበር። የአድቬንቲስት፣ የመጨረሻው ቀን ቅዱሳን የክርስቶስ ቤተክርስቲያን መሥራቾችም የጌታን መምጫ ቀን ቢተነብዩም ከመንፈስ ቅዱስ ያልሆነው ትንቢታቸው አሳፍሮ መልሷቸዋል። በ፳፻፲፪ በማያ ቀመር መሠረት ክርስቶስ እንደሚመጣና ዓለም እንደምትጠፋ የተሰበከው ስብከት ለበርካቶች እውነት የመሰለ ቢሆንም ለሆሊውድ ፊልም መሥሪያ ከመሆን አልተረፈም ነበር። በዘመናችንም በርካቶች በተለይ በፈረንጆቹ ፳፻፳፭ እና ከእዛ በኋላ “ዓለም ትጠፋለች” ብለው በመስበክ የአማኞቻቸውን ንብረት በማሸጥና በመዝረፍ የከበሩ በርካታ ሃሳውያን መሲሆች ተገኝተዋል። የዛሬ ሁለት ዓመት “ክርስቶስ ሊመጣ ነው፤ ወደ ተራራ ወጥተን በፆም እንቀበለው” በሚል ስብከት የምእመናኑን ነብስ የቀጠፈውን አፍሪካዊ ፓስተር ጨምሮ። ቤተክርስቲያን ግን “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። ያን ግን እወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ፣ ቤቱም ሊቈፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።” ማቴ ፳፬÷፵፪-፵፬ በማለት የጌታዋን ቃል በማስተማር “በዚህ ቀን ይመጣል፤ በዚህ አይመጣም” በሚል ትምህርት በመደናበር እንዳይስቱና ሁሌም ተዘጋጅተው እንዲኖሩ ታስተምራለች። እኛ ክርስቲያኖች የዳግም ምፅዓት በነቢይ አስቀድሞ  “እግዚአብሔር ገሃደ ይመፅዕ” (“እግዚአብሔር ግልፅ ሆኖ ይመጣል”) ተብሎ እንደተነገረ በግርማ መለኮት፣ በክበበ ትስብእት ለፃድቃን ሊፈርድላቸው ለኃጥአን ሊፈርድባቸው እንዲሁም ይህን ዓለም አሳልፎ የማያልፈውን ዓለም ሊሰጥ እንደሆነ እናምናለን። በመሆኑም ይህችን ወደፊት ያለች ቀን በየዓመቱ ሰንበተ እግዚኡ – የጌታ ሰንበት እያልን በዓልን እናከብራለን። ስለዚህ ቀን በዓል በኢትዮጵያ በትግራይና በሰሜን ሸዋ ንግሥ የሚካሄድ ሲሆን በጉራጌ አካባቢዎች የሚገኘው ማኀበረሰብም በዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ ፲፱ ላይ ያለውን እራት በማሰብ በደብረ ዘይት ዕለት ድግስ፣  በዚህም ስለክርስቶስ መምጣት ፍስሀ ያደርጋሉ።እኛም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመጣ ጊዜ እንዳያሳፍረን የሕይወት ቃሉን ያሰማን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱን እየተማፀንን ስለነገረ ምፅዓቱ አምልቶ በፃፈው ባለራዕዩ ቅዱስ ዮሐንስ ቃል ጽሑፋችንን እንዘጋለን። ማራናታ! አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና!