
የዛሬ ዐሥር ዓመት ነበር ናኤል ጎይቶም ከኢትዮጵያውያንና ከሌሎች ኤርትራውያን ጓደኞቹ ጋር የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ አውሮፓና መካከለኛው ምሥራቅ ለመሻገር በሱዳን በኩል ወደ ሊቢያ ድንበር የገባው፡፡
በወቅቱ የዐሥራ ስድስት ዓመት ታዳጊ የነበረው ናኤልና ባልንጀሮቹ ብዙዎቹ የእነርሱ ታላላቆች እንዳደረጉት ሁሉ የእነርሱም ሕልማቸው ለመለወጥና ለዘመዶቻቸው ለመትረፍ ቢሆንም በቀላሉ ነበር በሊቢያ ምድር በሚንቀሳቀሰው በአይ.ኤስ.አይ. ኤስ. እጅ የወደቁት፡፡
ናኤል ስለዚያች ቀን ሲናገር “ቀኑ የካቲት ሃያ አራት ነበር፡፡ ከኛ ጋር ሶማሊያውያንና ወደ ሰባዘጠኝ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ቁጥራቸው ከ፳ እስከ ፴ የሚጠጋ የአይ.ኤስ. ወታደሮች በደቡባዊው የሊቢያ በረሃ ይዘው ሃይማኖታዊ ጥያቄዎችን ጠየቁን፡፡ ከኛ መሃል ሙስሊም የሆኑትን ለመለየት ነበር፡፡ ክርስቲያኖቹ መስቀልና ቅድሳት ስዕላትን ይዘን ስለነበር ክርስትናችንን መደበቅ አልተቻለንም ነበር፡፡” ይላል።
ሰላም ውድ የቤተክርስቲያን ሳምንታዊ መሰናዶ ተከታታዮች በወርኃ ታኅሣሥ በሊቢያ ስለተሰዉ ግብጻውያን ሰማዕታት ስናነሳ በወርኃ ሚያዚያ ኢትዮጵውያንና ኤርትራውያንን ለማዘከር ቀጠሮ ይዘን ነበር፡፡ ምንም እንኳን በሰሙነ ሕማማትና ሰሙነ ትንሣኤ ዝክሮች ምክንያት የሰማዕታቱ ዜና ምስክርነት የተገለጠበት ሚያዝያ ፲፩ ብናልፈውም ስለሰማዕታቱ እንዘክር ዘንድ ፍቅር ያስገድደናልና ዝክራቸውን በዛሬው ዕለት ማንሳት ጀምረናል፡፡
ከላይ ምስክርነቱን ያነሳነው የያኔው ታዳጊ ናኤል ጎይቶም በ፴ዎቹ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ላይ ስለተፈጸመው ሰማዕትነት የዓይን ምስክር ከሆኑ ጥቂት ግለሰቦች አንዱ ነው፡፡ ይህ ታዳጊ አንገታቸው የታረዱትንም ሆነ በመሳሪያ አፈ-ሙዝ ምስክርነታቸውን የፈጸሙትን ሰማዕታት ከተያዙበት የየካቲት ወር መጨረሻ እስከ ጊዜ እረፍታቸው ድረስ የሆነውን ተመልክቷል፡፡ ያየውንና የሰማውንም በዩናይትድ ኪንግደም ለሚታተመው የኢንተርናሽናል ቢዝነስ ታይም በ፳፻፲፩ ዓ.ም. አካፍሏል፡፡
ናኤል እንደሚለው በቦታው የነበሩ ሶማሊያውያንን ፣ ሙስሊም ኢትዮጵያውያንንና ኤርትራውያንን ሲለቋቸው ክርስቲያኖቹ ግን ወደ አይ.ኤስ. ካምፕ ተወሰዱ፤ ለቀናት ታስረውም ጭምር ነበር፡፡ ወደ ካምፕ የተወሰዱ ክርስቲያኖች ሦስት ምርጫዎች ነበር የተሰጣቸው እምነትን መቀየር ወይም ጀዛ መክፈል ወይም መሞት፡፡ ናኤል ጎይቶምና ሌሎች ጓደኞቻቸው ሃይማኖታቸውን ለመቀየር ሲስማሙ ሰማዕታቱ ግን በሃይማኖታቸው መጽናትን መረጡ፡፡
ስለሞታቸው ቀን ናኤል ጎይቶም ሲናገር ሁለቱም በተለያየ ቦታና ቀን እንደተገደሉ ያነሳና ‘ከዕለታት አንድ ቀን ጥቁር ቱታዎች አመጡና ሃይማኖታችንን አንቀይርም ካሉት ውስጥ ለተወሰኑት እንዲለብሱ ሰጧቸው። ከዛም ይዘዋቸው ሲወጡ ዐስር የምንሆነውን “እኛን ተከተሉን!” አሉን’ ። “ከጀርባቸው ሲተኮስባቸው በዓይናችን ተመለከትን” ብሏል፡፡ “ዐሥራ ዐራት የሚሆኑትንም ብርቱካናማ ቱታ አስለብሰው እንዲከተሏቸው አዘዟቸው። እነሱን ደሞ በፊታችን አረዷቸው” ይለናል፡፡ ይህ የናኤል ምስክርነት ከሌሎች ፫ በተመሳሳይ መንገድ ተርፈው በስደተኛ ማቆያ ከነበሩ ኤርትራውያን ምስክርነት ጋር ይመሳሰላል፡፡
እስቲ አሁን ደግሞ ምስክረነቱን ገታ አድርገን ሚያዚያ ፲፩/፳፻፯ ዓ.ም. የተለቀቀውንና ፴ ደቂቃዎችን የሚፈጀውን ቪዲዮ በዓይነ ልቡናችን እንመልከት፡፡ ግልጽ ማስረጃ እስከመጣላቸው ድረስ /”Until There Came to Them Clear Evidence” በሚል ርእስ የተዘጋጀ ሲሆን በኢራቅና በሶሪያ ያለውን የረጅም ጊዜ የሙስሊምና ክርስቲያን ግንኙነት ያሳይና አምላካችን ኢየሱስን ከቁርአን አንጻር በመመዘን የክርስቲያን ክፍል እንዴት እንደመጣ ያነሳል፡፡
በወቅቱ የቡድኑ መሪ የነበረው አቡበከር አልባግዳዲ የአል ኑሪ መስጂድ ሚንበር ላይ በመውጣት ክርስቲያኖአች “ከሃዲ” መሆናቸውን በማወጅ ወይ ጃዛ መክፈል ወይ መገደል እንዳለባቸው ያውጃል፡፡ ተንቀሳቃሽ ምስሉ በሶሪያ በተለይም ቡድኑ በወቅቱ በተቆጣጠራቸው የአሌፖና የራቃ ከተማ የሚኖሩ ጃዛያ የሚከፍሉ ክርስቲያኖች ቃለመጠይቅ ተደርጎላቸው ደኅንነታቸው እንደተጠበቀ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ተራኪውም ይህ የሆነው ጀዛያ ስለከፈሉና ቡድኑ መሐሪ ስለሆነ እንደሆነ ያነሳል፡፡ አስገራሚው ነገር ግን ምንም እንኳን ደህና ነን ቢሉም ፍርሐታቸው ከፊታቸው ላይ ይነበባል፡፡በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ አይ.ኤስ. ክርስቲያኖችን ሲያሰቃይ እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናትን፣ ሃውልቶችንና የክርስቲያኖችን መካነ መቃብር ሲያፈራርስ ያሳያል፡፡
ለደቂቃዎች እንዲህ ካሳየ በኋላ በጥቁርና ብርቱካናማ ልብስ የተያዙ የሁለት የክርስቲያን ቡድኖችን ያሳያል፡፡ የመጀመሪያው በምሥራቅ ሊቢያ ባርቃ ግዛት የተያዙ በደርዘን የሚቆጠሩ በብርቱካናማ ቱታ የሚታዩ ሲሆን ሁለተኞቹ በደቡብ ሊቢያዋ ፋዛን ግዛት የተያዙ ፲፮ በጥቁር ቱታ ያሉ ወጣቶች ነበሩ፡፡ ምርኮዎቻቸውን እየታዩ ከሥር “የጠላት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የመስቀሉ ተከታዮች” የሚል ጽሑፍ ይታያል፡፡
አንዱ ጥቁር የለበሰ ወታደር መሳሪያውን ወደ ካሜራው በመደቀን “ምስጋና ለአዓማቱ ጌታ ለአላህ ይሁን እንዲሁም ሰላምና በረከት በነብዩ መሐመድ ላይ ይሁን! ለመስቀሉ ሕዝቦች፣ የነብዩ መሐመድ ተከታዮች ወደ ረገጡት አሸዋ ተመልሰን እንነግራችኋለን፤ በእናንተ ሃይማኖት እጅ የፈሰሰው የሙስሊም ደም ርካሽ አይደለም፣ እንደውም ደማቸው ንጹህ ደም ነው፤ ምክንያቱም በቀላቸውን የሚወርስ ሕዝብ ከኋላቸው አላቸው፡፡ በእጃችን እንዲያዋርዳችሁ ለአላህ ቃል ገብተናል፡፡ እስልምናን እስክትቀበሉ በህልማችሁ እንኳን ደኅንነት አይኖራችሁም! “
ተናጋሪው ይህ ጦርነት በእምነትና በክህደት መሐል የተደረገ መሆኑን ያነሳና ጣዖት አምልኮና ለአላህ መገዛት እስካልተፈጸመ ድረስ ጦርነቱ እንደሚቀጥል ያነሳል፡፡ በመቀጠል በምስሉ ብርቱካናማ የለበሱት ክርስቲያኖች ሲታረዱ ጥቁር የለበሱትም በመደዳ በመሳሪያ ሲገደሉ ያሳያል፡፡ ቪዲዮው በአል ናሽያን ንግግር ይጠናቀቃል፡፡ አል ናሽያን በንግግሩ ክርስቲያኖች እስልምናን ወይም ጀዛያን ካልከፈሉ ከአይ.ኤስ. ሰይፍ እንደማያመልጡ ይናገራል፡፡
ከምስሉ መለቀቅ በኋላ መላው ዓለም በድንጋጤ ተዋጠ። አትዮጵያና ኤርትራ በሀዘን ተሞሉ። ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን ከሰማዕታት መሀል በማየቷ ስትኮራ ስለ ደረሰባቸው መሪር ስቃይ አዘነች፡፡ በየሚዲያው የውግዘትና የሀዘን መግለጫ ተሰጠ፡፡ ስለወቅቱ የሚዲያ ሽፋን ጥናቱን ያካሄደው ስለሺ ሰማኸኝ በወቅቱ “በየሚዲያው የነበሩ ዘገባዎች ሃይማኖታዊ ምስክርነቱን ያቃለሉና በይበልጥ ፖለቲካዊ መልክ የነበራቸው ናቸው።” ይለናል በጥናቱ፡፡ በእርግጥም የጥቃቱ ግብረ መልስ ፖለቲካዊ በመሆኑ ሽብርተኝነትን በሚያወግዙ ሰልፎች እና የስደተኝነትን አስከፊነት በሚያሳዩ መርሐግብራት የተሞላ ነበር፡፡
በ፳፻፯ የተሰበሰበው የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እነዚህን ምስክሮች ሰማዕትነት ያወጀ ቢሆንም ለዚህ ጥንቅር በተመለከትናቸው ዘገባዎችና መረጃዎች መሠረት የሰማዕታቱ ስም በአግባቡ አለመታወቁንና የተደራጀ መረጃ አለመኖሩን ለመመልከት ተችሏል፡፡ በሊቢያ የነበረው የአይ.ኤስ. ይዞታ ከተነጠቀ በኋላ በታኅሣሥ ፲፭/፳፻፲፩ ዓ.ም. የሊቢያ የወንጀል ምርመራ መምሪያ የሰማዕታቱ አጽም መገኘቱን ያረጋገጠ ሲሆን በአዲስ አበባ አፍሪካ ኅብረት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል የሰማዕቱ አጽም ማሳረፊያ የተዘጋጀና ክቡር ስጋቸው ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚመጣ በመንግስትም ሆነ በቤተ ክርስቲያን በኩል የተነገረ ቢሆንም ዜና ገድላቸው በወጉ ሳይያዝና አጽማቸው ወደ ሀገር ሳይገባ እነሆ ዐሥር ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ሰማዕታቱ በእምነታቸው ጸንተው ዓለምን ድል ያደረጉ ቢሆንም በፍርሐት ለጊዜው ክደው የነበሩት ወንድሞቻቸው ስለተቀረው ጊዜያቸው በናኤል አንደበት እንዲህ ይናገራል፡፡ “ስለጉዳዩ ማስተሳሰብ የጀመርሁት አሁን ነው፡፡ ከቀናት በፊት ነገሮች ሁሉ በሕይወት መትረፍ ነበሩ። አሁን ግን ከባባድ ቅዠት አለብኝ፡፡ ሰዎች አንድ በአንድ ሲታረዱና ሲገደሉ አያለሁ።” ሲል ይደመጣል።
በዚያው ዓመት ሚያዚያ ፲፮ በሰጠው ቃል በየወንድሞቻችንን ዜና ሰማዕትነት የዘከርንበት ዓምድ በዚህ ፈጸምን። ድል የማትነሳ የዕምነት ጽናታቸው ከእኛ ጋር ትሁን፡፡ ዝክራቸውና ክብርት ሥጋቸው እንደ ግብጻውያን ወንድሞቻቸው ሲከብር ለማየት አምላከ ቅዱሳን ይርዳን። አሜን!

