የልደታ ለማርያም ቅዱስ ትውፊት

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት የተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በዓላት ጋር በተያያዘ ከተለያዩ አካላት በተደጋጋሚ የሚቀርቡ ትችቶችን መሰማት ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል። የዓለማቀፋዊቷ ቤተክርስቲያንን ትውፊት ያጠና ግን በዓላቱ በዘመን የረዘመ፣ በቦታም የሰፋ፣ ነገር ግን እንደ ቦታው ታሪካዊ ሂደት ለውጥን የሚያስተናግድ ተመሳሳይነትን ማግኘቱ የማይቀር ነው። የዚህ ምንጩም ዜና ቅዱሳን ነው።;የቅዱሳንን ዜና ሕይወት መጻፍ በብሉይ ኪዳን የተጀመረ ሲሆን ሊቀ ነብያት ሙሴ በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፉ የቀደሙ ርእሳነ አበውን የነአዳም፣ ኖህ፣ ሄኖክ፣ አብርሃምን ታሪክ ሰንዶልናል።

የቅዱሳን ፣ መሳፍንትና ነገስታትም ዜና ሕይወት በመጽሐፈ መሳፍንት፣ ነገሥትና ዜና መዋዕል በሌሎቹም ክፍላት የተፃፉ ናቸው። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፉም ሉቃስ የሐዋርያትን አገልግሎት ከትቧል። እኒህ ሁሉ ዜና ቅዱሳን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተቱ ሲሆን ሳይገኙ በመዘግየት ያልተካተቱ የሀዋርያት ጽሑፎችና የድህረ ሐዋርያት ዜና ቅዱሳን በተናጥል (ገድላትና ተአምራት) እንዲሁም በስብስብ (ስንክሳር) መልኩ እየተዘገበ ከዚህ ዘመን ተደርሷል። የአንዳንድ ቅዱሳን ዜና በዓለም ሁሉ የሚታወቅ ሲሆን የሌሎች ዜና ገድል ግን በተወሰነ ቦታ ብቻ የሚታወቅ ሆኖ እናገኘዋለን።

እንደ ዓለም ገዝፎ በመታወቅ ደረጃ የቅድስት ድንግል ማርያምን መታወቅና መከበርን የሚያህል የለም። የድንግል ማርያም ነገረ ልደት በሁሉም ጥንታውያን አብያተክርስቲያናት የሚታወቅና የሚከበር በዓል ነው። በነገረ ድኅነታዊ ዋጋቸው በዓለም ሁሉ ከሚከበሩት የሁለት ፍጡራን በዓላትም ዋነኛው የእመቤታችን ልደት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል ተብሎ በጌታችን የተነገረለት የመጥምቁ ዮሐንስ ልደት ነው።

የእመቤታችን ነገረ ልደት የተመዘገበበት ጥንታዊው መጽሐፍ የጌታ ወንድም ተብሎ የተጠራው ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ያዘጋጀው መጽሐፈ ልደት (The book of nativity) ወይም መጽሐፈ ያዕቆብ (Book of James) በግሪኩ ደግሞ ፕሮቶቫንጌልዮን ነው።

መጽሐፉ በኦርቶዶክስና የካቶሊክ አብያተክርስቲያናት በቀኖናቸው ተቀባይነት የሰጡት መጽሐፍ ሲሆን ፲፮ ምዕራፎች ያሉት መጽሐፍ ነው። እንደ ስያሜው አምላክን ስለወለደች ቅድስት ድንግል ማርያምና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የሚያወራ ሲሆን እመቤታችን ዘመዱ እንደመሆኗ ከእርሷና ከቅርብ ዘመዶቿ እየሰማ እንደጻፈው ይታመናል።

በ፪ኛው ክ/ዘ እንደተጠናቀቀ የሚነገርለት ይህ መጽሐፍ እንደ ኦሪገን ያሉ የጥንቷ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት በትምህርታቸው ላይ የጠቀሱት ሲሆን በ፲፭፻፶፪ ወደ ላቲን ተተርጉሟል።
መጽሐፉ ሲጀምር “የኢየሱስ ክርስቶስና የዘለዓለማዊት ድንግል ማርያም የልደት ታሪክ፤ የክርስቶስ ዘመድና ወንድም በሚሆን ዋና ሐዋርያ እንዲሁም የመጀመሪያው የኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች ሊቀጳጳስ በሆነ ታናሹ ያዕቆብ” ብሎ ይዘቱንና ጸሐፊውን ይናገራል።

የመጽሐፉ ታሪክ በሁሉም አቢያተክርስቲያናት የሚታመን ሲሆን ታሪኩ ከመጽሐፉ መታተም ከ፮፻ ዓመት በፊት በተጻፉ ሌሎች ጥራዞች ላይ ሳይቀር መጠቀሱ በዕድሜ ቅድምናና መነሻ ታሪክ እንዳለው ማሳያ ይሆናል።

የቅድስት ድንግል ማርያም የትውልድ ስፍራን በተመለከተ ልዩነቶች ያሉ ሲሆን ናዝሬትና የኢየሩሳሌም መግቢያ ከተሞች “በኔ ነው! በኔ ነው የተወለደችው!” እያሉ ሚፎካሩ ሲሆን ኦርቶዶክሳዊት የተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ግን “ሙሽራዬ ሆይ፥ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፤ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፤ ከአማና ራስ ከሳኔርና ከኤርሞን ራስ፥ ከአንበሶች መኖሪያ ከነብሮችም ተራራ ተመልከች።” መኃልየ. ፬፥፰ የሚለውን የሰለሞንን ቃል መነሻ አድርጋ መወለዷ ከሊባኖስ መሆኑን ታስተምራለች። በሊባኖስም እጅግ ጥንታዊ የሆነ በስሟ የሚጠራ ቤተመቅደስም ይገኛል።

በዓለማችን የሚገኙ የተለያዩ ክርስቲያኖች (ኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣ ምስራቅ ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ አንጋሊካን፣ ሉተራውያን) የእመቤታችን ልደት በተለያዩ ቀናት የሚያከብሩ ሲሆን የምዕራብ አብያተክርስቲያናት ጷግሜ ፫ (September 8), የምሥራቅ አብያተክርስቲያናት (ኦርየንታልና ምስራቅ ኦርቶዶክስ መስከረም ፲ (September 21) እንዲሁም የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የግብፅ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ በግንቦት ፩ ያከብሯታል። የእመቤታችንን ፴፫ በዓላቷን በሚዘረዝረው የተአምረ ማርያም መቅድም ላይም መስከረም ፲ የሚያከብሩ እንዳሉ ይጠቅስና “እኛ ግን..” ብሎ ‘…በተረዳ ነገር አባቶቻችን ሊቃውንት እንዳስተማሩን ልደቷ “ግንቦት ፩ ነው” እንላለን’ ሲል ይመልሳል።

የእመቤታችን የልደት በዓል እስከ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. መግባት ድረስ በብሔራዊ በዓልነት ሲከበር የነበረ ሲሆን እንደ ፊሊፒንስ ባሉ ሀገራት ሥራ የሚያዘጋ ብሔራዊ በዓል ተደርጎ ይከበራል።

ክርስቶስ ተንሥአ እም ሙታን – ክርስቶስ ከሙታን መካከል ተለይቶ ተነሣ!