
ከመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በሀገር ፍቅር ቲያትር በኩል ወደ አራት ኪሎ በሚወስደው መንገድ የሚያልፍ ሰው ዓይኑ ከአንድ ጠባብ ነገር፣ ግን ውብ ኪነ ሕንጻን ከሚያሳይ ቤተ ክርስቲያን ጋር መላተሙ አይቀርም፡፡ ሕንጻው የአርመን ሐዋርያዊት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን አርመናዊያኑ ቤተ ክርስቲያኑን በቋንቋቸው “ሶርፕ ኬቩርክ ኤኬጌስቲ” (Սուրբ Քեւորք եկեղեցի) ይሉታል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ማለት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር ግቢ ውስጥ በጉልህ ከሚታየው ቤተ መቅደስ ባሻገር ከቤተ መቅደሱ በስተግራ የሚገኝና በቅርብ ካልሆነ ሳያስተውሉት የሚታለፍ ከነጭ ዕብነ በረድ የተሠራ የመታሰቢያ ሐውልት አለ፤ የአርመናውያን ሰማዕታት መታሰቢያ።
ሰላም ውድ የቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ ዕድምተኞች በዚህኛው የቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ ዓምዳችን በበዓለ ትንሣኤው ሰሙን ምክንያት በወቅቱ መታሠሥ ያልቻልነውን አርመናውያን ኦርቶዶክሳውያን በኢስላማዊው የኦቶማን ቱርክ መንግስት የደረሰባቸው ጭፍጨፋ የዚህ ሳምንት የኃሠሣችን አካል አድርገነዋል፤ ሰናይ ንባብ!
የአርመን አካባቢ በሁለቱ ሐዋርያት ማለትም በበርተለሜዎስና ታዴዎስ ክርስትና የተሰበከባት ሲሆን ከበርካታ የክርስትና የመከራ ዘመናት በኋላም በ፫፻፩ (301)ዓ.ም. ክርስትናን ብሔራዊ ሃይማኖት አድርጋ የተቀበለች የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች፡፡ የአርመን ቤተ ክርስቲያን አሁንም ድረስ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ ፰ (8)መሠረት የሀገሪቱ ብሔራዊ ሃይማት ስትሆን ከሀገሪቱ ጠቅላላ ሕዝብ ውስጥ ዘጠና አምስት በመቶ የሚሆኑት የዚችሁ የአርመን ሐዋርያዊት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ናቸው፡፡ በመሆኑም አርመንና ኦርቶዶክሳዊነት በአንድ ሳንቲም ላይ ያሉ ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ ስለ አርመን ቤተ ክርስቲያን ያለውን ትውውቅ ከዚህ ጋር ገትተን ወደ ርእሰ ጉዳያችን እንግባ።
በምሥራቅ አናቶሊያ ከፍ ያሉት ሜዳዎችና የኖህ መርከብ ያረፈበት አራራት ተራራ ሺህ ዓመታትን ስላስቆጠረው የአርመናውያን ህላዌ ምስክር ነው፡፡ አርሜንያውያን እስከ ፲፱፻፳፫ (1923) ዓ.ም. ድረስ ከ፫ (3)ሺህ ዓመታት በላይ በዚህ አፈር ላይ ተነስተው ኖረዋል። ምንም እንኳን አሁንም ጥቂት የተረፉ ቢኖሩም ታሪካቸው በሚገርም ሁኔታ ተሰርዟል።
አርመናውያን ከእናት ምድራቸው ተሻግረው በአሁኗ የቱርክ መሬት ማለትም በቁስጥንጥንያ (ኢስታቡል)፣ በአንቶሊያና በዙሪያው ባለው ምድር መስፈር የጀመሩት ቱርኮች በግዛቱ ከመስፈራቸውም ሆነ የእስልምና እምነት ከመፈጠሩ በፊት በ፮(6)ኛው ክፍለ ዘመን እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡
ቁስጥንጥንያ የክርስቲያኖች ማዕከል እንደመሆኗና ከአምስቱ ንዑዳን መናብርት አንዱ የሆነው የቁስጥንጥንያው መንበር በዚያ በመገኘቱ በመንበሩ ሥር የነበሩት አርመናውያን ከሌሎች የመንበሩ ሕዝቦች ጋር መልክዓ ምድርና እምነት ተጋርተው ይኖሩ ነበር፡፡ እንደ ቁስጥንጥኒያ መንበርነታቸው በ፬፻፶፩ (451) ዓ.ም. የተካሄደውን የኬልቄዶን ጉባዔ ተቀብለው የነበረ ቢሆንም በ፫ (3) ኛው የዲቪን ጉባኤ የኬልቄዶን ጉባኤን በመቃወም ከቁስጥንጥኒያ መንበር ወጥተው ከእስክንድሪያ መንበር ጋር የእምነት አንድነት ካደረጉ በኋላም የምድሯ አካል መሆናቸው አላበቃም ነበር፡፡
በኦቶማን ግዛት ወቅት፣ የኦቶማን ኢምፓየር በባህል እና ሃይማኖት የተለያዩ ሕዝቦች የተሞሉ ነበር። አርሜንያውያን፣ ምንም እንኳን በእስልምና አገዛዝ ላይ እንደ ሁለተኛ ዜጎች ቢቆጠሩም፣ በንግድና በተለያዩ አገልግሎቶች ውስጥ ተሳትፈው ነበር። ነገር ግን በ፲፱ (19)ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ፣ ኦቶማን የደረሰበት የጦርነት ሽንፈት፣ የኢኮኖሚ ውድቀትና ሃይማኖታዊ ቀውስ ፊቱን በሀገሪቱ ውስጥ ባሉ በአናሳ ክርስቲያኖች ላይ በተለይም በአርመናውያን ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ እንዲያዞር አስገድዶታል፡፡ ይህ የአርሜንያ የሕዝብ ጭፍጨፋ ታሪክ ነው። ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በረሃብ እና በጭፍጨፋ ሞተዋል። ከአንድ እስከ ሁለት መቶ ሺህ ድረስ የሚጠጉ ኦርቶዶክሳውያን በግዳጅ ሰልመዋል፡፡
የኦቶማኑ ገዢ ሱልጣን አብዱል ሃሚድ ፪ (2) ኛ የአርሜንያውያን የእኩልነት ጥያቄ ስለፈራ ከ፲፰፹፯– ፲፰፹፱ (1887 – 1889)ዓ.ም. የሃሚድ ጭፍጨፋዎችን አስከተለ። ከ፫፻ (300) ሺህ በላይ አርሜንያውያን ተገደሉ። የተረፉ አርመናውያን መንደሮች እንደተቃጠሉ፣ አብያተክርስቲያናት እንደጠፉ እና ወንዞች በደም እንደተሞሉ ተናግረዋል።
በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ “ነፃነት፣ እኩልነት፣ ወንድማማችነት” በሚል ቃል የሱልጣኑን ዙፋን የገረሰሱት የቱርክ የወጣቶች ዐብዮት የሱልጣኑን ተግባር የተቃወሙ ቢመስሉም እውነተኛ ግባቸው ከዚህ የከፋውን የኢስላማዊ የቱርክ ብሔርተኝነትን ማፋፋም ነበር። በ፲፱፻፮ (1906) ዓ.ም. ኤንቨር፣ ታላትና ጀማል የተመራው የማኅበረሰብ እና እድገት ኮሚቴ (CUP) ስልጣን ሲይዝ በፓን ቱርኪ ጽንሰ-ዐሳብ ከአናቶሊያ እስከ ማዕከላዊ እስያ ያሉ ቱርኮችን በማንቀሳቀስ “ቱርክ የቱርኮች ብቻ ናት” ሲል ቀደምት የመሬቱን ነዋሪ ክርስቲያኖች ያገለለ ሥርዓት ተከለ፡፡
“በ፲፱፻፯ (1907) ዓ.ም. የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ሲጀመር፣ የወጣቶቹ ፓርቲ በሳሪካሚሽ ጦርነት ላይ በሩስያ ስለተሸነፉ በዚህ አሳብበው አርሜናውያኑን ለመበቀል ዐቀዱ፡፡ በመሆኑም ሚያዚያ ፲፯ ፲፱፻፯ (ሚያዝያ 17, 1907) ዓ.ም.፥ ሌሊት ታላቁን የአርመናውያን ጭፍጨፋ አስጀመሩት፡፡ ዓለም በስፋት ከሚያቃቸው የናዚና የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ በፊት የ፳ (20) ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያው የዘር ጭፍጨፋ ማስጀመሪያ ፊሽካ ፪፻፶ (250) የሚሆኑ ካህናትና ታዋቂ አርመናውያንን በመግደል ተጀመረ፡፡
ከዚያች ሌሊት አንስቶ ለድፍን አንድ ዓመት በቱርክ መንግስት ስር የሚገኙ አርመናውያን ለሞት፣ ለስደትና መፈናቀል፣ ለግዳጅ የሃይማኖት መለወጥ ተዳረጉ፡፡ እልፎች በረሃብ በስደት ምድር ወደቁ፡፡ በሶሪያ በነበሩ የማጎሪያ ካምፖች የጅምላ ግድያ ተፈጸመባቸው፡፡
አሁን ላይ የሰማዕታቱ መታሰቢያ የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በታነጸበት በዘመኑ የበረሃዋ ሲዖል ዳር ዛር የተፈጸመው ድርጊት እጅግ የሚያሰቅቅ እንደነበር በወቅቱ የዓይን እማኝ የነበሩ የኩርድ ነጋዴዎች ያስታውሳሉ። ጉድጓዶች በአስክሬን የተሞሉ ነበሩ ኤፍራጠስም በሞቱ ሕፃናት ተሞልታ ነበር፡፡
የአንድ ዓመቱ ጭፍጨፋ አሰቃቂ ቢሆንም ግድያው፣ አፈናው፣ ማፈናቀሉና የግዳጅ እምነት ማስለወጡ አስከ አንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያና የቱርክ ሪፐብሊክ ምሥረታ ድረስ ለ፰ (60)ዓመታት የቀጠለ ነበር፡፡ ከጭፍጨፋው በፊት በቱርክ እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ አርመናውያን ኦርቶዶክሳውያን የነበሩ ሲሆን ከጦርነቱ በኋላ ግን ሃይማኖታቸውን ከቀየሩ እስከ ሁለት መቶ ሺህ እስከሚደርሱ አርመናውያን በቀር ክርስቲያኖቹ በጣት የሚቆጠሩ ሆነው ነበር፡፡
በዚህ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን አርመናውያን በተገደሉበት ጭፍጨፋ ከአርመናውያን ባሻገር የግሪክ ኦርቶዶሳውያንና አሶሪያውያን ሲገደሉ በቱርክ ይኖሩ የነበሩ አዘርባኖችና ኩርዶች አለመነካታቸው ጭፍጨፋው ሃይማኖታዊ መልኩ ትልቅ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
የአርመን ሃዋርያዊት ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የዛሬ ዐሥር ዓመት የአርመን ሰማዕታት መታሰቢያ መቶኛ ዓመት በተከበረበት ዕለት ለነዚህ ኦርቶዶክስ አርመናውያን ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያን ጨምሮ የአኃት አብያተ ክርስቲያናት ቅዱሳን ፓትሪያርኮችና ልዑካን በተገኙበት “ሰማዕታተ እምነት – አቃቢያነ ሃይማኖት በደም” ስትል የጅምላ ቅድስናን ሰጥታቸዋለች፡፡ ቱርኮችና አዘርባጃኖች “የዘር ጭፍጨፋ አይደለም፤ ጦርነት እንጂ” ብለው በሚከራከሩትና የሰሜንና ደቡብ አሜሪካ፣ አውሮፓና ሩሲያን ጨምሮ ወደ ፴ (30) ሃገራት የዘር ጭፍጨፋ መሆኑን በተቀበሉት በዚህ እልቂት ምክንያት አርመናውያን በየቦታው እንዲበተኑ ምክንያት ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያም፣ በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና የወቅቱ ንጉሥ ወላጅ አልባ የሆኑ ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ አርመናውያን በምድሯ አስጠልላ ከመከራ ሰውራቸዋለች፡፡ ዛሬ ላይ “በአርመን ከሚገኘው አርመናዊ በሰው ሃገር ያሉት ይበልጣሉ” አስኪባል በየሀገሩ የተበታተኑት አርመናውያን በየሀገራቸው ያንን አሰቃቂ ጭፍጨፋና የቅዱሳን ሰማዕታቱን አይበገሬነት በማሰብ ይዘክሩታል፡፡
ጠፍተዋል የተባሉት አርመናውያን ሰማዕታት በየአንዳንዱ አርመናዊ ልብና በቤተክርስተያን ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡ አጥፍተናቸዋል ያሉት ነገስታት ግን እንደ ፈርዖንና እንደ ናቡከደነጾር እንደ ዲዮቅሊጢያኖስና መክስሚያኖስ በታሪክ ፊት ተነስተው በክፉ ብቻ እየታሰቡ ይኖራሉ፡፡ ሊያጠፏት ያሰቧት ቤተ ክርስቲያን ግን ከትናንት ሳትጎድል ዛሬን ትኖራለች፤ ነገም የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ይቻለው ዘንድ ማንም የለምና በክርሰቶስ ደም እንደታተመች በሰማዕታቷ ደም እንደ ተዋበች ትቀጥላለች፡፡
የሰማዕታቱ ድል የማትነሳ የእምነት በረከት ለኛም ትድረሰን፡፡ እግዚአብሔር አካሉን ቤተክርስቲያንና ልጆቿን ይጠብቅ፡፡
ይቆየን!

