
በዚህ ሳምንት በግብጽ የተካሄደውን ፲፭ኛው (15) ዙር የኦርየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ መግለጫ ተከትሎ የህንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የጉባኤውን ውሳኔ አንድ ነጥብ በመቃወም መግለጫ አውጥታለች፡፡ ይህ ዓይነቱ መግለጫን የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም በ፳፻፲፭ (2015) ዓ.ም. ከተካሄደው ፲፫ (13)ኛው ጉባኤ መጠናቀቅ በኋላ መውጣቷ የሚታወስ ነው፡፡
ለመሆኑ ይህ በአብያተ ክርስቲያናቱ ቅሬታ ያመነጨው የመካከለኛው ምሥራቅ የኦርየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ክፍተት ምንድነው? ለምንስ ነው ቅሬታ የሚነሳበት? የሚለውን በዚህ ሳምንት የቤተክርስቲያን ሳምንታዊ መርሐግብራችን ለመቃኘት እንሞክራለን አብራችሁን ሁኑ፡፡
የሠሜን አፍሪካንና የእስያን ምዕራባዊ ክፍልን የሚያካልለው የመካከለኛው ምስራቅ በአብዛኛው ዐረብኛ ተናጋሪ የሆኑ ኢስላማዊ ሀገራትን የሚይዝ ሲሆን ይህ ዐረብኛ ተናጋሪ ኢስላማዊው ሕዝብ የከባቢውን ማኅበራዊ፣ ምጣኔሀብታዊና ፖለቲካዊ አቅም ይቆጣጠራል፡፡ በመሆኑም በእነዚህ አካባቢ የሚገኙ ክርስቲያኖችም ሆኑ ዐረባዊ ያልሆኑ ሕዝቦች ለልዩ ልዩ ጫናዎች ተጋላጭ መሆናቸውን ታሪክ ይነግረናል፡፡
የሚገርመው ይሄው አካባቢ ዐረባዊ መልኩ እንዲህ ከመስፋፋቱ በፊት ቀደምት የክርስትና መነሻና መስፋፊያ መሆኑ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መዋለ ሥጋዌውን የፈጸመው በዚሁ አካባቢ ባሉ የእስራኤልና የፍልስጤም ግዛቶች ነው፡፡ ሐዋርያትም በርካታ አገለግሎቶች ያከናወኑት በዮርዳኖስ፣ በሶሪያ፣ በግብጽና በመሳሰሉት ሀገራት ነው፡፡ ከ፭ (5)ቱ ታላላቅ መናብርት ውስጥ በዚህ ክልል ውስጥ የማይገኘው የሮም መንበር ብቻ ነበር፡፡ ትልልቆቹ የክርስትና ትምህርት ቤቶች አንጾኪያና እስክንድርያም የተገኙት ከዚሁ ግዛት ነው፡፡
ይህ አካባቢ የቤዛንታይን ክርስቲያናዊ መንግስት በሙስሊሞች መሸነፉን ተከትሎ በተስፋፉት እስላማዊ ስልጣኔዎች ምክንያት ክርስቲያኖች በግዳጅ ለመስለም፣ ለመፈናቀልና ለሞት በመዳረጋቸው በአካባቢው የሚኖሩ የክርስቲያኖች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህል በ፲፱፻፺ (1990)ዎቹ አካባቢ በአካባቢው ካሉ ሕዝቦች ፲፫ (13)በመቶው ክርስቲያኖች የነበሩ ሲሆኑ ነገር ግን ባለፉት መቶ ዓመታት በአርመናውያን፣ ግሪኮችና አሶሪያውያን ክርስቲኖች ላይ የተካሄዱ ጭፍጨፋዎች፣ የኢስላማዊ የሽብር ቡድኖችና አክራሪ ኢስላማዊ መንግስታት መስፋፋትን ተከትሎ የዛሬ ፭(5) ዓመት በ፳፻፲፪ (2012) ዓ.ም. በተደረገ ጥናት የክርስቲያኖች ቁጥር ወደ ፭ (5)በመቶ መውረዱ ተመላክቷል፡፡
ይህንን ተከትሎ በአካባቢው የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የተለያዩ ኅብረቶችና አንድነቶችን በማስፈን በችግሮቻቸው ዙሪያ ለመነጋገርና መፍትሔ ለማስቀመጥ እየሞከሩ ይገኛል። ከእነዚህ መካከል የዛሬ የውይይታችን ማዕከል የሆነው የኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት ዓመታዊ ጉባኤ ነው፡፡ ጉባኤው በብጹአን ወቅዱሳን ፓትሪያሪኮች ከሚደረገው ውይይት በተጨማሪው በተዋረድ የጳጳሳት፣ የካህናትና የነገረ መለኮት ምሁራን የሚገኙበት ቋሚ ኮሚቴዎች እንዳሉበት መግለጫዎቹ ያመላክታሉ፡፡
መጋቢት ፪ / ፲፱፻፺ (2/1990)ዓ.ም. በግብጽ ዋዲ አል ናጥሩን የአባ ቢሾይ ገዳም የመጀመሪያውን ጉባኤ ያካሄደው የመካከለኛው ምሥራቅ የኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ መንበራቸው በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ የሶሪያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የኪልቂያ ካቶሊኮስ የሚያጠቃልል ሲሆን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ካልተከሰቱ በስተቀር በየዓመቱ ይካሄዳል፡፡ ጉባኤው አብያተ ክርስቲያናቱ በመካከለኛው ምርራቅ እንደመገኘታቸው በአካባቢውና በኦርየንታል ኦርቶዶክስ ዙሪያ ባሉ የጋራ ጉዳዮች ላይ በተለይም በኢኮሚዩኒካል አንድነቶች (በአብያተ ክርስቲያናት ኅበረት)፣ በነገረ መለኮት ውይይት፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ ጉዳዮችና በአብያተ ክርስቲያናቱ ግላዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደርጋል፡፡
በ፲፱፻፺፩ (1991) ዓ.ም. በሶሪያ የተካሄደው ሁለተኛው ጉባኤ መግለጫ እንደሚያመላክተው ጉባኤው ከመካከለኛው ምሥራቅ አልፎ ሌሎች የኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናትን በማካተት የዛሬ ፷ (60) ዓመት በ፲፱፻፶፰ (1958)ዓ.ም. የተካሄደው የአዲስ አበባ ጉባኤ ተከታይ የመሆን ፍላጎት እንዳለው ቢያሳውቅም ባለፉት 27 ዓመታት ምንም ዓይነት ለውጥ አላሳየም፡፡ ስለ ጉባኤው ቀደም ሲል አምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በዘመነ ፕትርክናቸው በወቅቱ የነበሩትን የሦስቱንም አብያተ ክርስቲያናት ፓትርያርኮች የጠየቁ ሲሆን በወቅቱ የመለሱላቸው መልሶች አንደኛው ጉዳዩ የሚመለከተው መንበረ ፓትርያኮቻቸው እና ዋና ማዕከላቸው በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የግብጽ እስክንድርያ፣ የሶርያ አንፆኪያ እና የአርመን ቂልቅያ መንበሮችን መሆኑን እንዲሁም የምክክሩ ዓላማም በወቅቱ በመካከለኛው መሥራቅ የነበረውን የአክራሪዎች እንቅስቃሴ በተመለከተ፣ በተጨማሪም ሦስቱ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ሌሎቹን ለማግለል ሳይሆን የመካከለኛው ምሥራቅ ችግር ከሌሎቹ ስለሚለይ ያንን የተመለከተ ጉባኤ መሆኑን ገልጸው እንደነበረ የተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል ዘገባ ያመላክታል፡፡
ጉባኤው ዘንድሮ እና በ፳፻፲፭ (2015) ዓ.ም. በተካሄዱ ውይይቶች ላይ ከሦስቱ አብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ ባሻገር የኢትዮጵያንና የህንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትን ጉዳይ በተመለከተ ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ በአብያተ ክርስቲያናቱ ዘንድ ጥያቄ አምጥቷል፡፡ በዴር ሱልጣን ገዳምና በህንድ የያዕቆባዊት የሦሪያ ቤተክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደረገው ጉባኤው ጉዳዩ ከግብጽና ሦሪያ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ስለሚነካካ መነሳቱ የሚያስከፋ ባይሆንም በአንድ ወገን በቀረበ መረጃ መሠረት አቋም መያዙ ነበር ተቃውሞ እንዲገጥመው ያደረገው፡፡ እስቲ ሁለቱን ጉዳዮች እንመልከታቸው፡፡
በ፳፻፲፭ (2015) ዓ.ም. በተካሄደው ጉባኤ በግብጽ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን በኩል የቀረበውን በዴር ሱልጣን የይገባኛል አቤቱታ ምክንያት በማድረግ ፫ቱ ቅዱሳን ፓትሪያሪኮች በ፳፻፲፭ (2015) ዓ.ም. በዕለተ ትንሣኤ ዋዜማ ኢትዮጵያን መነኮሳት የሃገራቸውን ሰንደቅ አዓማ በርስት ምድር ዴር ሱልጣን መትከላቸውን “ትንኮሳ” ብለው የገለጹት ሲሆን ዴር ሱልጣን የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ ይዞታ እንደመሆኑ መሰል ትንኮሳዎችን እንደሚቃወሙ ገልጸዋል፡፡ የሶሪያና የአርመን ኦርቶዶክሳውያን አባቶች ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን በኩል ያለውን ብቻ በመስማት፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ሳያማክሩና በርካታ ሕጋዊ፣ ታሪካዊና ትውፊታዊ ማስረጃ ያለውን የኢትዮጵያ ቤ/ክ የባለቤትነት መብት ወደ ጎን በመተው ያስተላለፉት ውሳኔ ኢፍትሐዊ መሆኑን በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በውጭ ግንኙነት መምሪያዋ በኩል መግለጫ ሰጥታበት ነበር፡፡
ሰሞኑ ደግሞ የኒቂያ መቶኛ ዓመት መታሰቢያ በተደረገበት ፲፭ኛው (15)ጉባኤ ደግሞ የሶሪያ ቤተ ክርስቲያን ዘንድሮ በመጋቢት ፳፻፲፯ (2017) ዓ.ም. ያዋቀረቺው ዓለምአቀፋዊ የሶሪያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ብጹዕ ማር ባስሊዮስ ዮሴፍን በህንድ የሶሪያ ኦርቶዶከስ ቤተ ክርስቲያን ካቶሊኮስ አድርጎ በመሾም በአንድ ሀገር ውስጥ ከማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲን ጋር ትይዩ ቤተ ክርስቲያናዊ መዋቅር መመሥረቷን በማድነቅ ከሶሪያ ቤተክርስቲያን መዋቅር ውጪ ካሉ ተገንጣይ ቡድኖች ጋር የምሥጢርና የነገረ ሃይማኖት አንድነት እንዳይፈጸም የተወሰነውን ውሳኔ ጉባኤው መቀበሉ የህንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን አስቆጥቷል። መግለጫው የማላንካራ ቤተ ክርስቲያንን “ተገንጣይ” ማለቱ የህንድ ቤተ ክርስቲያን ያላትን መንፈሳዊ ስልጣንና አንድነት “የናደ ነው” ብላዋለች፡፡
በ፲፭ኛው (15) ጉባኤ መግለጫ የአርመኑ የኪልቂያ ፓትርያርክ አቡነ አራም ቀዳማዊና የግብጹ ፓትሪያርክ አቡነ ታዎድሮስ ከሶሪያው ፓትሪያርክ አቡነ ኢግናጥዮስ ኤፍሬም ሁለተኛ ጋር በመሆን ሁለቱን የህንድ ካቶሊኮሶች ወደ እስክንድርያ አምጥቶ ለማደራደርና ለማስማማት ፈቃደኛ መሆናቸውን ቢጠቅሱም የህንድ ማላንካራ ቤተ ክርስቲያን “የአርመን ኦርቶዶክስ የቅድስቲቱ ኢታችማንዴዝ እናት መንበር፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ባልተገኙበት የተካሄደ ጉባኤ ይህንን የመወሰን መብት የለውም” ስትል ጥያቄውን ውድቅ አድርጋለች፡፡
በህንድ ከፈረንጆቹ ፲፱፻፸፬ (1974)ዓ.ም. ጀምሮ ሁለት የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት (በብጹዕ ወቅዱስ ባስሊዮስ ማርቶማ ማቴዎስ ፫ኛ የሚመራ የማላንካራ ሶሪያዊት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና በሶሪያ የአንጾኪያና የመላው ምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መንበር ሥር ያለው የህንድ የሶሪያ ቤተክርስቲያን) ሲኖሩ በመካከላቸው ከፍተኛ የሕጋዊነትና የባለቤትነት ክርክሮችና ግጭቶችን እያስተናገዱ ይገኛሉ፡፡ ጉዳያቸውን የተመለከተው የህንድ ፍርድ ቤት ከዚህ በፊት አብያተ ክርስቲያናቱን ቆጥሮ እስከማካፈል ድረስ ደርሶ እንደነበር አይዘነጋም። በቅርቡም የማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተነሳውን ጥያቄ ተመልክቶ ሕጋዊ መብቷን ማረጋገጡ በመግለጫው ላይ ተመላክቷል፡፡ በቅርቡ የሶሪያ ቤተ ክርስቲያን አዲስ ካቶሊኮስ ለሕንድ መሾሟ ውጥረቱን እንዳያሰፋው ሲሰጋ ነበር፡፡
እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን አባቶች መልካሙን መንገድና ዐሳብ እንዲያሳያቸው እየጸለይን ቤተ ክርሰቲያን አንድነቷ የተጠበቀ ሰላማዊት የክርስቶስ ማኅደር እንድትሆን በመመኘት የዛሬውን በዚህ አበቃን፡፡

